ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

የቀድሞ የኢትዮጵያ የአየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄነራል አበበ ተ/ኃይማኖት “ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን የመጠቀም ህጋዊ መብቷን ያጣችው በፓርቲው (ኢህአዲግ) ውስጥ በነበረው ድንቁርና እና ትዕቢት ነው” ማለታቸውን በመጥቀስ፣ ጋዜጠኖች ለጠየቋቸው ጥያቄ አቶ መለስ ዜናዊ ሲመልሱ፦

 

“አሠብን ያጣነው በድንቁርና ከሆነ የዓለም አቀፍ ሕግ የሰው ሀገር ወደብን የባለቤትነት መብት ይሰጣል ማለት ነው። እሱን አላወቅነው እንደሆነ ድንቁርናችን ያሳዝነናል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ የሕግ ሙያተኞች የሚባሉት እንደ አጋጣሚ ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ተቀጥረው የሚሠሩት ናቸው። በዩኒቨርሲቲ መምህራን ሆነው የሚያገለግሉት፣ በውጭም የዓለም አቀፍ ሕግ ሲቀረፅ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት እነዚሁ የመንግሥት ሙያተኞች ናቸው። እነዚህ ሙያተኞች እንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግ የለም፤ እንኳን የሕግ ባለሙያ ቀርቶ መሐይምም ቢሆን ይህንን ሊገነዘብ ይገባል። ብለው ይነግሩናል። እኔ የሕግ ሊቅ አይደለሁም፤ የሕግ ሙያተኞች የሚሉኝን ግን መነሻ አደርጋለሁ። ለመምረጥ የምሞክረውም ትክክለኛ የሕግ ባለሙያ መሆኑን ብቻ ነው።” ነበር ያሉት።

 

የሕግ ባላሞያ እንዳልሆኑ፣ ግን ያማከሯቸው የሕግ ባላሞያዎች “ማንም ሀገርን በሌላ ሀገር ወደብ ላይ የባለቤትነት መብት የሚሠጥ፣ የዓለም አቀፍ ሕግ የለም፣ ሊኖርም አይችልም” እንዳሏቸው አቶ መለስ ተናግረዋል።

 

ሲያጠቃልሉም “አሰብ የኢትዮጵያ ወደብ ሆና የማገልገሏ ጉዳይ እንዲያበቃ ያደረገው የ30 ዓመት ትግል ነው። የሕግ ፕሮፌሠር፣ ትዕቢተኛና ደንቆሮው ሳይሆነ የ30 ዓመቱ ትግል ለዓሰብ ጉዳይ መልስ ሰጥቷል። ያ ጦርነት ባለቀበት መልኩ አለቀ” በማለት ለኢትዮጵያ ጥቅም ደንታ እንደሌላቸው፣ ለህዝቡ ንቀት እንዳላቸውና “ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ያጣችው በሰላሳ አመቱ ጦርነት ተሸንፋ እንደሆነ ከመናገር ወደኋላ አላሉም።

 

አቶ መለስ የሕግ ሞያተኛ አለመሆናቸው ትክክል ነው

በዚች አቶ መለስ በሰጡት አጭር መልስ አሥራ አንድ ጊዜ “ሕግ” የሚለውን ቃል እናገኛለን። ስለ ዓለም አቀፍ ሕግ፣ ስለ ሕግ ሙያተኖች ብዙ ይናገራሉ። አዲስ ነገር ያየነው የሕግ ባለሞያ አለመሆናቸውን አቶ መለስ መናገራቸው ነበር። እዚህ ላይ አቶ መለስ በርግጥ እውነት ተናግረዋል። የሕግ ባለሞያ አለመሆናቸውን ማወቃቸውም በራሱ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው እንላለን።

 

የሕግ ባለሞያ አለመሆናቸውን አቶ መለስ ቢቀበሉም፣ የሕግ ባለሞያዎች የሚሏቸውን መነሻ እንደሚያደርጉ፣ የሕግ ሞያተኞች የሚመክሯቸውን እንደሚሰሙ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም። ይህም የሚያሳየው እውነት በተናገሩ በሴኮንዶች ዘለው ወደ ውሸት መግባታቸውን ነው።

 

አቶ መለስ እርሳቸው ብቻ እንደሚያወቁና እርሳቸው ብቻ ትክክል እንደሆኑ የሚያስቡ መሆናቸውና በድርጅታቸው ውስጥ ሁሉ ሳይቀር እርሳቸውን ለመናገር የሚደፍር ሰው እንደሌላ በታወቀበት ሁኔታ “እኔ የሕግ አማካሪዎች የሚሉትን እሰማለሁ” ማለታቸው ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

 

የአሰብን ጉዳይ ሲወስኑ የራሳቸው ድብቅ ውሳኔን የሕግ ሽፋን ሰጥተውት፣ ሆን ብለው ለማጭበርበር ሙከራ አደረጉ እንጂ የሕግ አማካሪዎችን ያማከሩበት ሁኔታ በጭራሽ አልነበረም። አማከርኳቸው ያሏቸው ሞያተኞች ምናልባት የሻዕቢያው አፈቀላጤ የነበሩት ዶ/ር በረከት ገብረስላሴ ወይንም የመንግሥቱ ኃይለማሪያም የሕግ አማካሪ የነበሩትና እንደ እስስት የሚለዋውጡትን ዶ/ር ፋሲል ናሆምን ከሆነ እርሱ ሌላ ነገር ነው።

 

እንኳን ሕግን ሊያከብሩና ትክክለኛ የሆነ የሕግ ምክር ሊሰሙ ቀርቶ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ለሕግ ከበሬታ እንደሌላቸውና ሕግን እንደሚረግጡ የተረጋገጠላቸው ሰው ናቸው። ብዙ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። እንደ ምሳሌ የብርቱካን ሚደቅሳን ጉዳይ እናንሳ።

 

ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኖች፣ ሃርድቶክ ለተባለው የቢቢሲ ፕሮግራም አቶ መለስ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊ እንደሆነ ነው ደጋግመው የተናገሩት። መስረት ያደረጉበት የሕግ አንቀጽ የይቅርታ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395፣ አንቀጽ 16 ንኡስ አንቀጽ ሁለትን ነበር።

 

“የይቅርታ ውሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የይቅርታ ውሳኔ በማጭበርብር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ውሳኔው ዋጋ አይኖረውም” ይላል አንቀጹ።1

 

ከዚህ በመነሳት ነው እንግዲህ አቶ መለስ ዜናዊ “ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አጭበርብራ ነው ይቅርታ የጠየቀችው” የሚል አሳፋሪ ክስ ያቀረቡባት። የሀገሪቷን ሕገ መንግሥት እንዲሁም የይቅርታ አሰጣት አዋጅ አንቀጾችን በሙሉ ከግምት ውስጥ ላስገባ የሕግ ሰው ቀርቶ፣ ማንበብና መጻፍ ለሚችል የስምንተኛ ክፍል ተማሪ፣ ይህ የአቶ መለስ የሕግ አተረጓጎም ስህተትና የተዛባ መሆኑ ያጣዋል ብለን አናስብም።

 

አቶ መለስ እንዳደረጉት፣ ይህንኑ አንቀጽ በነጠላ እንኳን ብንመለከተው፣ ይቅርታ የሚሰረዘው ይቅርታ የተሰጠው ሰው ሲያጭበረብር ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ አልጠየኩም አላለችም። አላጭበረበረችም። ምናልባት ዘኢኮኖሚስትን ብቻ ስለሚያነቡ አላነበቡት ይሆናል እንጂ፣ ወ/ት ብርቱካን ታሪካዊ በሆነው ቃሌ በተሰኘው ጽሁፏ “በሀገር ሽምግልና ወግ መሰረት ይቅርታ እንደጠየቀች በግልጽ አስቀምጣለች። አልካደችም። አልዋሸችም። ማንንም አላታለለችም። አቶ መለስ ከየት አምጥተውት “የተሰጣትን ካደች” እንዳሉ ቢመልሱልን ጥሩ ነበር። ታዲያ በርግጥ አጭበርባሪውና አታላዩ እራሳቸው መሆናቸውን ይህ አያሳይምን?

 

ለዚህም ነው በርካታ የኢህአዲግ ደጋፊዎች ሳይቀሩ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ለማሰር አቶ መለስ የሚሰጡትን የሕግ መከራከሪያ ለመቀበል ሲከብዳቸው የታዘብነው። አፍቃሪ ኢህአዲግ ፓልቶክ ክፍልን የሚመሩት አባ መላ፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን መታሰር አጥብቀው ሲቃወሙ “ሕግ እንደሌጦ እየተተረጎመ” ሲሉ ነበር በሕግ ስም የሚደረገውን ስህተት የነቀፉት። ጌታቸው መኳንንት የተባሉ ሌላ አፍቃሪ ኢህአዲግ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ “በሀገር ሽምግልና መሰረት ነው ይቅርታ የጠየኩት” ማለቷ ትክክለኛ ነው ሲሉም መታሰሯን ተቃውሟል።2

 

ፕሮፌሠር ዶናልድ ሌቪን የብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ሕጋዊነት እንዳልታያቸው በመጠቆም፣ የርሷን ጉዳይ የሕግ አዋቂዎችን ያቀፈ ኮሚሽን ተቋቁሞ እንዲያጠናውና እስከዚያም በሰብዓዊነት፣ ጉዳይዋን በኮሚሽኑ እስኪወሰን ድረስ፣ ብርቱካን እንድትፈታ ጥሪ ማቅረባቸውም ያታወሳል። እኝህ ሰው በጉዳዩ ላይ እነ ካድሬ ሽመለስ ከማል ሳይሆን፣ በሕግ የታወቁ፣ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች ጉዳዩን ይመልከቱት ነበር ያሉት።3

 

አቶ መለስ ግን ከዚህ በፊትም በአሰቡ ጉዳይ ላይ ሰውን አልሰሙም ነበር፤ አሁንም እየሰሙ አይደለም። እኝህ ሰው ለሕግ ከበሬታ የሌላቸው፣ ለራሳቸው እንዲጠቅም አድርገው የሕግ አንቀጾችን የሚያጣምሙ፣ ከሕግ በላይ የሆኑ ሰው በመሆናቸው አሁንም ብርቱካን ሚደቅሳን በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ።

 

ሕግ በሀገሪቷ ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ ጉልበተኛው ደካማውን እንዳይጨፈልቅ ዋስተና የሚሰጥ፣ በዜጎች መካከል እኩልነትን የሚያስፈን መሆን ነበረበት። ነገር ግን አቶ መለስ ዜናዊ በሚመሯት ኢትዮጵያ ሕግ ብሎ ነገር የለም።

 

የአሰብና የኤርትራ ጉዳይ

በመጀመሪያ ደረጃ ኤርትራ ነፃ እስከትወጣ ድረስ፣ መላው የኤርትራ ግዛት የኢትዮጵያ ነበር። ስለዚህ በዓለም አቀፉ ሕግ መሰረት ኢትዮጵያ የባህር ወደቦች ነበሯት። ሻዕቢያ በኮንፌዴረሽን ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመሆን ጥያቄ አቅርቦ እንደነበረ ጦቢያ የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበ ሲወራ ሰምቼ ነበር። አቶ መለስ ግን በችኮላ ለኤርትራ የመጀመሪያ እውቅና ሰጡ።

 

የሻዕቢያ የኮንፌደሬሽንን ጥያቄ አቶ መለስ ተቀብለው፣ ከኤርትራውያን ወገኖቻችን ጋር ያለው መቀራረብ እንዲዳብር አድርገው ቢሆን ኖሮ፣ ይሄን ጊዜ አሰብ ብቻ ሳይሆን ኤርትራም በሙሉ የኢትዮጵያ አካል ትሆን ነበር። አቶ መለስ እንዳሉት የሰላሳ አመቱ ጦርነት ሳይሆን ኢትዮጵያን ባህር አልባ ያደረገው፤ የርሳቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ፖሊሲ ነው ።

 

በሁለተኛ ደረጃም ኤርትራም እንኳን ለብቻዋ ብትሆን፣ ታሪካዊ ስምምነቶችንና ሰነዶችን በማቅረብ አሰብ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ መከራከሪያዎችን ማቅረብ ይቻል ነበር። በዓለም አቀፍ ሕግ ሞያተኛ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማሪያም፣ የሕግ ሞያተኛ የሆኑት ጄኔራል አበበ ተክለኃይማኖት እንዲሁም በርካታ ምሁራን በስፋት እንደጻፉት፣ አሰብ የኢትዮጵያ እንድትሆን ማድረግ ይቻል ነበር። ነገር ግን አቶ መለስ ዜናዊ ይህን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል። ኢትዮጵያ ባህር አልባ የሆነችውም በሰላሳ አመቱ ጦርነት ሳይሆን በርሳቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ፖሊሲ ነው።

 

በባድመ ጦርነት ጊዜ የተፈጠረውን ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ያን ያህል ብዙ ሺህ ወገኖቻችን፣ ከሁለቱም ወገን ያለቁበት ጦርነት፣ መኖር ያልነበረበት ጦርነት ነው። ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነበር። ለዚህም አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በታሪክ የሚጠየቁበት ይሆናል።

 

ጦርነቱ ከተጀመረና የኢትዮጵያ ጦር ሸንበቆን፣ ባሬንቱን፣ ተሰነይን፣ አፋበትን፣ ፆረናን … በጥቂት ቀናት ተቆጣጠሮ፣ መንደፈራና አዲቋላ ሊደርስ፣ አስመራንም ሊቆጣጠር ትንሽ ነበር የቀረው። መቶ በመቶ ድልን በሻዕቢያ ላይ ተጎናጽፎ ነበር ማለት ይቻላል።

 

ነገር ግን አቶ መለስ ዜናዊ ጦሩ እንዲመለስ ወሰኑ። የተገኘውን ድል ቀለበሱት። ፀረ-ኢትዮጵያ የአልጀርስ ስምምነት ፈረሙ። መጀምሪያውኑ ጦርነቱን አለማድረግ ነበር። መጀመሪያውኑ ወገኖቻችን አለመማገድ ነበር።። ነገር ግን ጦርነቱ ሊያልቅ ጥቂት ሲቀረው፣ የተገኘውን ድል መልሰው ለሻዕቢያ አስረከቡ።

 

እንግዲህ ይሄ እየታወቀ ነው አቶ መለስ ዜናዊ አይናችውን በጨው አጥበው፣ ኢትዮጵያ ባህር አልባ የሆነቸው በሰላሳ ዓመቱ ጦርነት ተሸንፋ ነው የሚሉን። አይደለም። ኢትዮጵያ ሀገራችን ባህር አላባ የሆነቸው አቶ መለስ ዜናዊ በሚያራምዱት ፀረ-ኢትዮጵያ ፖሊሲ ነው።

 

እዚህ ላይ የአቶ መለስ ዜናዊን ውሸትና ክህደት ለማሳየት የተደረገ ሙከራ እንጂ በአሰብና በኤርትራ ጉዳይ ላይ አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ ተብሎ የተዘጋጀ ጽሑፍ አይደለም ይህ ጽሑፍ።

 

በአሁኑ ጊዜ በኤርትራውያን ወገኖቻችንና በተቀሩት ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል እየተደረገ ያለ ጠቃሚ ውይይት አለ። ይህ ውይይትና መቀራረብ በጣም የሚደገፍ ነው። የተከበሩ ፕሮፌሠር ተስፋጽዪን እንዲሁም የተከበሩ ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ እያደረጉት ያለው ጥረት በእጅጉ fየሚደነቅና በሁላችንም ሊደገፍ የሚገባው ጥረት ነው። በግድ ወይንም በጦርነት ሳይሆን በፍቅር፣በሠላም ሁለታችንንም በሚያስማማ፣ የሁለታችንም ክብርና ጥቅም ባልነካ መንገድ፣ አብረን የምንኖርበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይቻላል። ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ እንዳሉት፣ ኤርትራውያን ከተመቻቸው በፌዴሬሽን፣ ካልተመቻቸውም ደግሞ ፕሮፌሠር ተስፋጽዮን እንዳሉት በኮንፈዴሬሽን እንደገና አብረን መሆን የምንችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንችላለን። በንግግር በውይይት በፍቅር የማይፈታ ነገር የለም።

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለእውነት ያደረ፣ እውነትን የሚናገር እግዚአብሔር የሚፈራ መሪ ይስጣት!


ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) fመጋቢት 8 ቀን 2002 ዓ.ም.

1 http://peacewithkinijit.tripod.com/pardon_proclamation.pdf

2 http://aigaforum.com/articles/A_Call_for_Release_Birtukan.htm

3 http://aigaforum.com/articles/DLevine_Looking_Ahead.htm

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ