Ethiopia Zare's weekly news digest, week 41th, 2012 Ethiopian calendar

ከሰኔ 8 - 14 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አርባ አንደኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከሰኔ 8 - 14 ቀን 2012 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት መሪ አጀንዳ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በተያዩ አቅጣጫዎች የተዘገቡ ዜናዎች ናቸው። በኢትዮጵያ በግብጽና በሱዳን መካከል እየተደረገ የነበረው ውይይት በውጤት ባይቋጭም ውይይቱን አስመለክቶ በየዕለቱ የተሰጡ መረጃዎች ያዝ ለቀቅ ያሉ ኾነው ከቆዩ በኋላ ግብጽ ውይይቱን ችላ ብላ ደግሞ ወደተባበሩት መንግሥታት አቤት ያለችበት ኾኗል። ከኢትዮጵያ አንፃር ድርድሩ ውጤት አመጣ አላመጣ፤ እኔ በያዝኩት ዕቅድ መሠረት በቀጣዩ ወር የውኃ ሙሌት ሥራዬን አከናውናለሁ ብላ ቁርጥ ያለ ምላሽ ሰጥታለች።

ሳምንቱን በተለየ እንዲታይ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ በተከታታይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ወክለው በድርድር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችና ሌሎችም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን የሚመለከት አስተያየቶቻቸውን ሲሰጡም ነበር።

እንዲህ ካሉ አስተያየቶች ጐን ለጐን የቀድሞው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዓለማየሁ ተገኑ፤ በህዳሴ ግድብ እንቅስቃሴና ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር ላይ የነበረውን ችግር በግልጽ ያስቀመጡበት ቃለምልልስ ግን ለየት ባለሁኔታ እንዲታይ አድርጐታል። የቀደመው አሠራር ግድፈቶች እንደነበሩበት ሁሉ ያመለከቱት አቶ ዓለማየሁ በተለይ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ሲፈጥሩ ነበር ያሉትን ጫና ሁሉ የጠቀሱበት ነበር። በጥቅሉ ሳምንቱ ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ መረጃዎች የበረከቱበት ነበር ማለት ይቻላል።

ከህዳሴ ግድብ ወጣ ብሎ በኢትዮጵያ አስጊነቱ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ቫይረስ በዚህም ሳምንት ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተነገረበት ሳምንት ነው። ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ በአንድ ቀን 339 ሰዎች መያዛቸው የተነገረውም በዚህ ሳምንት ሲሆን፣ አጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ4 ሺሕ በላይ መድረሱ የታወቀው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ሌላው የሳምንቱ ዐበይት አጀንዳ ኾኖ መነጋገሪያ የኾነው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የአገር ሽማግለዎች የብልጽግና ፓርቲንና ሕወሓትን ለማግባባትና በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለመፍታት ወደ መቀሌ የማምራታቸው ጉዳይ ነው። በመቀሌው ቆይታቸው ከሕወሓት አመራሮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ከመቀሌ እንደተመለሱም ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር ተነጋግረዋል። ምን እንዳስገኙም መግለጫ የሰጡት በዚሁ ሳምንት ነበር።

የትግራይ ክልል የራሴን ምርጫ አደርጋለሁ በማለት በምክር ቤት ደረጃ ማስወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ የሕወሓት አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ አሁንም ምርጫን ከማድረግ የሚያግደን የለም ብለው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ትግራይን የመገንጠል ዓላማ አለኝ ያለው አዲስ ፓርቲ፤ ጠቅላላ ጉባዔውን በማድረግ ፍላጐቴ ከኢትዮጵያ መገንጠል ነው ብሎ ማሳወቁ የተሰማው በዚሁ ሳምንት ነበር።

በርቅቡ ሕዝበ ውሳኔ በማድረግ በተገኘው ውጤት 10ኛዋ የአገሪቱ ክልል ለመኾን የቻለው የሲዳማ ዞን፤ በዚህ ሳምንት ክልል የመኾን ርክክብ መፈጸም ተችሏል።

ከሳምንቱ ሌሎች ተጠቃሽ ዜናዎች ደግሞ አቶ ዮሐንስ ቧያለው አልቀበል ብለው የነበረውን የመለስ አካዳሚ የፕሬዝዳንትነት ሹመት፤ የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኾነው ሲያገለግሉ ለቆዩት አቶ አወሉ አብዲ እንዲሰጥ መደረጉ፤ በኢትዮጵያ የፀሐይ ግርዶሽ መታየቱና የመሳሰሉት ዜናዎች ይገኙበታል። ከቢዝነስና ኢኮኖሚ አንፃር ደግሞ ሜድሮክ አዲስ መዋቅርና ሹመት መስጠቱ ነው። እንዲህ ባሉት የሳምንቱ ዜናዎች ላይ ኢትዮጵያ ዛሬ እንደሚከተለው አጠናቅራቸዋለች። መልካም ንባብ!

የህዳሴ ግድብና የቀድሞ ተግዳሮቶች ሲገለጥ

ከግብጽ ጋር ፍጥጫ የተገባበት የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ሳምንቱን በሙሉ በሁሉም የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የተለያዩ ዘገባዎች የተስተናገዱበት ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት የውኃና በተያያዥ መስኮች የተሰማሩ ምሁራን፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እና ሌሎችም በተለያየ መንገድ ምልከታቸውን የገለጹበት ነበር።

ለየት ባለመልኩ ግን የቀድሞ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር እና የህዳሴ ግድብ የቦርድ አባልነት የሚያገለግሉት፤ አሁን ደግሞ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመኾን እያገለገሉ ያሉት አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ፤ ሰሞኑን ከዘመን ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ተጠቃሽ ነው። ብዙዎች የተነጋገሩበትና መረጃውንም በሰፊው የተቀባበሉት ነበር ማለት ይቻላል።

በተለይ የህዳሴ ግድብ መጓተትና አንዳንድ ወገኖቹ “አሁን ያለው የለውጥ ኃይል ግድቡን ሸጦታል” በሚለው የተጣመመ አስተያየት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡበት ነው። “የህዳሴ ግድቡን ሸጣችሁታል” በሚለው ጥያቄ ላይ ለማን ይሸጣል? ሻጭም ገዥም የለም የሚሉት ዓለማየሁ ተገኑ፤ ግድብ መረከብ አይደለም አንስተህ ለሌላ አገር የሚሸጥ አለመኾኑን በመግለጽ ጉዳዩ ከለውጡ በፊት በነበረው አመራር ላይ ስለመኾኑ ያመላከቱበትን ምላሽ ሰጥተዋል። ግድቡን ለመሸጥ የሚደረግ ድርድር ያለው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ስለመኾኑና በዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ የዶክተር ዐቢይ አቋም የፀና እንደነበረ ገልጸው፤ አቶ ኃይለማርያምም ኾነ አቶ መለስ የነበራቸው አቋም የፀና ነው፤ የሚዋዥቅ ያለመኾኑን ያመላከቱበት ነበር።

“ባለፈው ጊዜ ዶክተር ዐቢይ ሩሲያ መጥቶ ነበር። ከግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋርም ኾነ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ሲወያይ ነበርኩ። ከአልሲሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዶክተር ዐቢይ “ግድቡን በሚመለከት አሁን የቀረው ጉዳይ የቴክኒክ ስለኾነ እኛው እንጨርሰው፤ የትም አንውሰደው” ብለው ነግረዋቸው ተስማምተው ነበር።” በሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አልሲሲ በወቅቱ ለዶክተር ዐቢይ ያነሱላቸው ሐሳብ፤ “ፓርላማ ላይ ግድቡን በሚመለከት እዋጋለሁ ብለሃል” ብለው ጠይቀውት ነበር የሚሉን አቶ ዓለማየሁ፤ ዶክተር ዐቢይ በምላሻቸው “ፕሮጀክቴን ከአደጋ እከላከላለሁ ማለት ምን ነውር አለው? ደግሞም ወታደር ነኝ፤ ፕሮጀክቱ ላይ አደጋ የሚያደርስን አካል መከላከል አለብኝ፤ ምን ስሕተት አለው ብለህ ነው” ብለው መልሰውላቸው እንደነበርና ዶክተር ዐቢይ በግድቡ ላይ የፀና አቋም ያላቸው መኾኑን አስረድተዋል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ቀደም ብሎ በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ይመራ የነበረው ቦርድ ፈጸመ ያሉትን ተግባርም በዚህ ቃለምልልሳቸው ላይ አስታውሰዋል። የህዳሴ ፕሮጀክቱን የመብራት ኃይል ቦርድ አካል አይገመግመውም ነበር ያሉት አቶ ዓለማየሁ፤ በዚህ ጉዳይ በየጊዜው ለቦርዱ ጥያቄ ያቀርቡ እንደነበር፤ ትልቁ ችግር ቦርዱም ገምግሞ ወደ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግምገማ ሪፖርቱን የማይልክ የነበረ መኾኑን ነው። “እኛ ግን ሪፖርቶችን ከመብራት ኃይል እየወሰድን ጉድለቶቹን እንናገር ነበር” ይላሉ።

“በዚሁ ሁኔታ ውስጥ የምናገኘውን መረጃ ይዘን እንደ ዘርፍ መግለጫ በምንሰጥበት ወቅት “ምን አግብቷችሁ ነው መግለጫ የምትሰጡት” በማለት በቦርድ ሰብሳቢው በኩል ቁጣ ይደርስብን ነበር” በማለት በወቅቱ የነበረባቸውን ችግር ተናግረዋል።

ቦርድ ሰብሳቢው (ዶ/ር ደብረጽዮን) ለግድቡ እኔ ብቻ ነኝ ቢሉም፤ በዚህ ረገድ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሽፋን በመኾን እንዳለፉት፤ በዚህ ሁኔታም ፕሮጀክቱ ከሕዝብ ፕሮጀክትነቱ ወርዶ የአንድ ግለሰብ ፕሮጀክት እስከመኾን ደርሶ እንደነበር አቶ ዓለማየሁ በዝርዝር ተናግረዋል። ይህም በመኾኑ የግድቡን ግንባታ ለውድቀት ከመዳረጉ ባለፈ፤ በአገራችን ታሪክ የሚያሳዝን ድርጊት ኾኖ እንዳለፈም ሳይገልጹ አላለፉም።

“የህዳሴ ግድቡ ሥራና ውሳኔዎች ወደ አንድ ሰው ፕሮጀክት ኾነ የሚለው ስያሜ በሚገባ ይገልጸዋል” ብለዋል። ይህም ሁኔታ ነው ግድቡን ለውድቀት የዳረገ ነው ብለው ያምናሉ።

“በወቅቱ የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር ደብረጽዮን ነው። አባላት ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደበበ የሚባል፣ ወርቅነህ ገበየሁም አንድ ወቅት ነበር፤ ከንግድ ባንክ ተወካይ፣ ረዘም ያለ ጊዜ ስለኾነ እነዚህን ብቻ አስታውሳለሁ።” የሚሉት ዓለማየሁ፤ እነዚህን አባላት ፕሮጀክቱን ይገመግሙ ነበር ወይ ተብለው ሲጠየቁ፤ እንደማይገመግሙ ይናገሩ እንደነበር በመግለጽ፤ ለግድቡ ሥራ መራዘምና ገጥሞት በነበረው ችግር ዋነኛ ምክንያት እንዲህ ያለው ሁኔታ ነው የሚል ምልከታቸውን በቃለ ምልልሱ ላይ አስረድተዋል።

አቶ ዓለማየሁ በቀድሞው ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደብረጽዮን አድራጊ ፈጣሪነት ከፍተኛ ኪሣራ ስለመድረሱም አስታውሰው። በህዳሴው ግድብ ላይ የነበረውን ወቅታዊ ሁኔታ ሲገለጽ ምን አገባችሁ በማለት ቁጣ ይደርስባቸው እንደነበር መግለጻቸው ከሰሞኑ ብዙ ትኩረት ያገኘ ዜና ኾኗል።

የህዳሴ ግድቡ ከለውጡ በኋላ ያለውን አካሔድ በተመለከተም በተለይ ከለውጡ በኋላ ጥራቱን ጠብቆ በሚፈለገው ሁኔታ እየተጓዘ ነው፤ ውኃ ለመሙላት ደርሷል። በፕሮጀክቱ ግንባታ በዚህ መልኩ የተጓዘበት ጊዜ እንዳልነበረው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከለውጡ በኋላ የተሠራው ሥራ እጅግ እመርታ የታየበት መኾኑን የሚያመለክተውን ንግግራቸውን የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል።

“በሁለት ዓመታት ውስጥ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ማምጣት በራሱ ጊዜ ይፈልጋል። እንደ ሜቴክ አምጥተህ የምትሠጠው ሥራ አይደለም። አሁን እኮ ለውጡ እየታየ ነው። ዘገየ የሚለው ሐሳብ ለተራ የፖለቲካ ጥቅም ፍለጋ ካልኾነ በስተቀር ሚዛን የሚደፋ ትችት አይደለም።” በማለትም በዚሁ ጉዳይ ላይ የሰጡትን ምላሽ አስፍተው ገልጸዋል።

እስከ ዛሬ በነበረው የሦስቱ አገራት ድርድር ላይ በሰጡት ተጨማሪ ሐሳብ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም የተለሳለሰ ነገር ያለመኖሩን፤ ነገር ግን ግብጾች ለውይይት እና ድርድር ሲመጡ የተለያዩ ውሸቶችን ይዘው የሚመጡ መኾኑን በመጠቀስ፤ አገር ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን በተለይ በሚገባ መጠቀም ይፈልጋሉ። ከዚህ አኳያ እኛ አንድ ኾነን ጥቅማችንን አሳልፈን ላለመስጠት መሥራት አለብን ብለዋል። ነገር ግን በተቃራኒው የአገርን ጥቅም አሳልፎ መስጠት በታሪክ ይቅር የማያስብል ስሕተት በመኾኑ ማስተዋል እንደሚገባም ሳይጠቅሱ አላለፉም። (ኢዛ)

የግብጽ የሚዲያ ምክር ቤት እንቆቅልሽ የኾነው እርምጃ

ከሰሞኑ ከወደ ግብጽ የተሰማው ሌላ ዜና ደግሞ የግብጽ የመገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት የአገሪቱ የሚዲያ አውታሮች ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ስለ ኮሮና ቫይረስ፣ በሊቢያ እና በሲና በረሃ ከታጣቂዎች ጋር ስላለው ግጭት እንዳይዘግቡ እገዳ መጣሉን የሚገልጽ ነው።

ምክር ቤቱ የሚዲያዎች በአገሪቱ ባለሥልጣናት የሚወጡ መግለጫዎችን ብቻ እንዲጠቀሙ ከማስጠንቀቂያው ጋር አስታውቋቸዋል። ስለ ህዳሴው ግድብም ኾነ ክልከላ በተጣለባቸው ጉዳዮች ላይ ማወያየትም ኾነ ዘገባ መሥራት እንደማይችሉ ምክር ቤቱ አስታውቆ፤ ይህን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይም እርምጃ ይወሰዳል ብሏል።

የሕትመት ሚዲያዎችም ክልከላ በተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ የሚያሳትሙትን ዘገባ ከማሳተማቸው በፊት ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማስገምገም እና ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው የምክር ቤቱ መግለጫ ያመለክታል ተብሏል። ይህ እርምጃ ለምን? የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም ምላሽ ያገኘ አልኾነም። (ኢዛ)

የአቶ ጌታቸው ረዳ ምርጫ እናደርጋለን ትርክትና ምርጫ ቦርድ

ሕወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሔድ በክልሉ ምክር ቤት ጭምር ያስወሰነ ሲሆን፤ ይህ አቋሙ ግን አሁንም ተቃውሞ እየገጠመው ነው። ይሁንና የሕወሓት አመራሮች ምርጫ እናደርጋለን የሚለውን ዘመቻቸውን ቀጥለዋል። በዚህም ሳምንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሰጡት አስተያየት በአነጋጋሪነቱ የሚጠቀስ ነው። “አሁንም ደጋግመን ማውራት ያለብን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ የማስፈፀሚያ መሣሪያ እንጂ፤ የመምረጥ መብትን የሚሰጥ ተቋም አይደለም” በማለት፤ በሕገ መንግሥቱ ለምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ሥልጣን የሚገፋ ሐሳባቸውን አንፀባርቀዋል። ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫ ለማካሔድ ከለከሉ ወዘተ … ተረት ተረት፣ የሚወራው የሌለ ለጉዳዩ ቴክኒካዊና ቢሮክራሲያዊ ትርጉም ለመስጠት ካልኾነ በስተቀር፤ የመምረጥና የመመረጥ በገሃድ ያለ መብት ስለመኾኑም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

በዚሁ ሰሞነኛ ንግግራቸው አክለው ያስቀመጡት ሐሳባቸው፤ “የትግራይ ወጣት ከፍታ፣ ተስፋና ፍላጎት ባሟላ መልኩ ምርጫውን ካላደረግን በስተቀር፤ በነገራችን ላይ እንደ ዶ/ር ዐቢይ ዐይነት ሰዎች ጋር በምትገባው እልህ የምትወስዳቸው ውሳኔዎች ብቻቸውን አገር አጥፊ ነው የሚኾኑት” የሚልም አክለዋል። ለዚህም ምክንያቴ ነው ብለው የገለጹት፤ አካሔዱ ሕዝብን አደጋ ላይ ስለሚጥል ነው ይላሉ።

“ስለዚህ ትግራይ ውስጥ የምታደርገውን ምርጫ በሁሉም መልኩ የትግራይን ሕዝብን (Aspiration) ያሟላና የሁሉም ፖለቲካዊ ኃይሎች ተሳትፎ ያረጋገጠ፤ በዛ ላይ ተመሥርቶ ደግሞ ትግራይ ጠንካራ የሕዝቧን ፍላጎት ሊጠብቅ የሚችል መንግሥት ይዛ መቀጠል የምትችል መኾን መቻል አለበት” በማለት የፓርቲያቸውን አቋም የሚያንፀባርቅ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

ግብጽ ደግሞ ወደ ተመድ

የህዳሴ ግድብ ጉዳይ እንዲሁም የሦስቱ አገራት ድርድርና ከዚሁ ጋር የሚያያዙ ሰሞናዊ ዘገባዎች በተለያየ መልኩ አንኳር አንኳር የሚባሉ የዜና ማዕዘን የነበራቸው ናቸው። ከዚህ ውስጥ ግብጽ እንደ አዲስ ለቀናት እየተደረገ የነበረውን የሦስትዮሽ ድርድር እያካሔደች እንደገና ነገሩን በድጋሜ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት መውሰዷን ማስታወቋ አንዱ ነው።

እንደገና ባስገባችው አቤቱታ ከዚህ ቀደም አቅርባው ለነበረው አቤቱታ፤ ያለ ሦስቱ አገራት ስምምነት ኢትዮጵያ በተናጥላዊ ውሳኔ ግድቡን ውኃ መሙላት ሳትጀምር የጸጥታው ምክር ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃለች። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሳሜህ ሽኩሪ በኩል ለተባበሩት መንግሥታት ምክር ቤት የላከችው ደብዳቤ፤ ግብጽ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ለመውሰዷ ምክንያት ያደረገችው፤ እየተካሔደ የሚገኘው የውኃ ሚኒስትሮች የሦስትዮሽ ውይይት አዎንታዊ ውጤት ስለማያመጣ ነው የሚል ነው። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በተናጥል ውኃ መያዝ እንዳትችል የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያስቆምላት በድጋሜ ያቀረባቸው አቤቱታ ለተመድ (የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) የደረሰው በዚህ ሳምንት ነው።

ግብጽ ከአንድ ወር በፊት ለጸጥታው ምክር ቤት ተመሳሳይ ደብዳቤ ማስገባቷ የሚታወስ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ለግብጽ አቅርበው ለነበረው አቤቱታ ለጸጥታው ምክር ቤት በሰጠችው ምላሽ፤ በራሴ ተፈጥሯዊ ወንዝ የማንንም ፈቃድ አልጠይቅም፣ ውኃውን መጠቀሜንም እቀጥላለሁ የሚል ጠንከር ያለ አቋሟን አስታውቃበታለች። ግብጽ ጉዳዩን በሦስትዮሽ ድርድር እንድትፈታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሳደሩን ተከትሎ ወደ ድርድሩ ተመልሳ የገባች ቢሆንም፤ የተጀመረው የሦስቱ አገራት የውኃ ሚኒስትሮች ውይይት ሳይጠናቀቅ ግብጽ በድጋሚ ድርድሩን ማቋረጧን ማስታወቋ፤ ተጀምሮ የነበረውን ድርድር አስተጓጉሏል።

በሌላ በኩል የግብጽን አካሔድ በእጅጉ የኮነነው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌቱን እንዳታደርግ የሚያግዳት ስምምነትም ኾነ ሕግ የለም በማለት ያስታወቀና ኢትዮጵያ በቀጣዩ ሐምሌ ወር ውኃውን እየሞላች በቀሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሔዷን እንደምትቀጥል ገልጿል።

በዚህ መሠረት በመጀመሪያው ዓመት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይሞላል፤ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ በአጠቃላይ 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይደርሳል። እንዲህ እንዲህ እያለች ኢትዮጵያ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃውን እንደምትሞላም በይፋ አስታውቃለች።

በሰሞኑ ድርድር በድርቅ ወቅት የውኃ አጠቃቀም ምን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ ነው። በዚህ ረገድ ስለውኃ ሙሌቱ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ውኃ መሙላት አትችልም የሚል ይዘት ያላቸው መረጃዎችን ግብጽም ኾነ አሜሪካ ማወጣታቸው፤ የውይይቱን ይዘት የማይወክሉ እና የተሳሳቱ መኾናቸው በሰሞናዊ ድርድሩ ላይ የኢትዮጵያን አቋም የሚያንፀባርቀው ሐተታ ያመለክታል። (ኢዛ)

በትግራይ የሚንቀሳቀሰው አዲሱ ፓርቲ ትግራይን እንገንጥል ይላል

ከሰሞኑ ከወደ ትግራይ የተሰማው ዜና፤ ለትግራይ ነፃነት እንደሚታገል በማስተወቅ መግለጫ የሰጠው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ጉዳይ ነው። ፓርቲው ትግራይን ነፃ ማድረግ ይፈልጋል። “የኢትዮጵያ የትግራይ ብሔራዊ ሕልውናና የተጋሩ ብሔራዊ ማንነት የምትቀበል አይደለችም” የሚል አቋም እንዳለው ገልጿል።

የትግራይ ነፃነት ፓርቲ የመጀመሪያው ነው በተባለው ጠቅላላ ጉባዔው አመራሮቹን የመረጠበት ጭምር ሲሆን፤ “የትግራይ ብሔራዊ ሕልውናና ብሔራዊ ማንነት በተሟላ መልኩ እውን መኾን የሚችለው፤ ትግራይ አገር ስትኾን ነው” የሚለውንም አቋሙን በትግራይ አክሱም ሆቴል አደረገ በተባለው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አስታውቋል።

ፓርቲው ትግራይ ክልልን በሰላማዊ ትግል ከኢትዮጵያ ለመነጠልና ሉዓላዊት አገር ለማድረግ እንደሚታገል የገለጸ ሲሆን፤ በትግራይ ይካሔዳል በተባለው ክልላዊ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ ነውም ተብሏል። (ኢዛ)

የሲዳማ 10ኛው ክልል የመኾን ርክክብና የወላይታ ዞን ተቃውሞ

ከጥቂት ወራት በፊት በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ የሲዳማ ዞን ራሱን የቻለ ክልል እንዲኾን የሚያስችል ድምፅ ተሰጥቶ ክልል የመኾን ጥያቄው መልስ አግኝቷል። በሕዝበ ውሳኔው መሠረት በክልል ደረጃ ለመዋቀር መፈፀም ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቷል የሚል ትችትና አስተያየት ቢሰጥበትም፤ በዚህ ሳምንት ግን ከዚሁ ጋር የተያያዘ አንድ ዐቢይ ክንውን ተፈጽማል። ይህም የሲዳማ ዞን አስረኛው የኢትዮጵያ ክልል ኾኖ በይፋ የሥልጣን ርክክብ መደረጉ ነው።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ባካሔደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ይህ ርክክብ የተፈፀመ ሲሆን፤ ሲዳማ ክልል ኾኖ መደራጀቱን የሚገልጽ ርክክብ ተካሒዷል። በዚህ ሥርዓት ላይ የደቡብ ክልል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሔለን ደበበ ለቀድሞው የሲዳማ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሰለሞን ላሌ የሥልጣን ማስረከቢያ ደብዳቤው በማስረከብ፤ ሲዳማ አስረኛው ክልል ለመባል በቅቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የወላይታ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ላቀረበው ጥያቄ ተገቢው ምላሽ ሊሰጠው አልቻለም ያሉ 38 የወላይታ ተወካዮች በሲዳማ አስረኛ ክልል መኾንዋን ከሚያመለክተው የምክር ቤቱ ስበሰባ ላይ አልተገኙም። ይህንንም አቋማቸውን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ከመካሔዱ በፊት ያሳወቁ መኾናቸው አይዘነጋም። (ኢዛ)

ብልጽግናና ሕወሓትን ለማሸማገል ወደ መቀሌ ከዚያም አዲስ አበባ

ከሳምንቱ ዐበይት ዜናዎች መካከል በትግራይ ክልልና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እና እርቅ ለማውረድ በማለት 43 አባላት ያሉት የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ወደ መቀሌ መጓዛቸው ነው። የሃይማኖት አባቶቹና ሽማግሌዎች በመቀሌ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና ሌሎች የሕወሓትና የክልሉ ባለሥልጣን አነጋግረዋል።

ሽምግልናው ምን ይመስል ነበር የሚለው መግለጫ ከሸምጋዮቹ በኩል ምንም ሳይባል በጉዳዩ ላይ ብዙ ተብሎም ነበር። በተለይ ሕወሓት ሰጠ የተባለው መግለጫም ነገሩን ያምታታ ቢሆንም፤ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የነበረውን ሁኔታ በኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት አመራሮች መግለጫ ተሰጥቶበታል።

የመማክርቱ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ፤ መማክርቱ ከዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር በመኾን የሚታዩ ችግሮችን በባህልና ወጋችን መሠረት ለመፍታት የጋራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረ መኾኑን ገልጸው፤ ወደ ትግራይ የተደረሰው ሰሞናዊ ጉዞም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

መማክርቱ በመጀመሪያው ዙር በሕወሓትና ብልጽግና ፓርቲ መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለመመለከት ይዘት በነበረው ዕቅድ መሠረት ወደ ትግራይ ክልል በመሔድ ከሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር እንደመከረ የመማክርቱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ ገልጸዋል። በመቀሌ በተደረገው ምክክርም የሰላምና አንድነት ጉዳይ የውዴታ ግዴታ በመኾኑ፤ ሁሉም በኃላፊነት ሊቆምለት የሚገባ ጉዳይ ነው በሚለው መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

ከሌላ በኩል ግን የሕወሓት አመራሮች በርካታ ጥያቄዎች እንዳላቸውና ያንንም ለመማክርቱ ያቀረቡ ስለመኾኑም በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተጠቅሷል። ሕወሓት በጋራ ተገናኝቶ ለመነጋገር ግን ዝግጁ መኾናቸውን እንደነገሯቸው የገለጹት መማክርቱ፤ በአዲስ አበባም ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር በመገናኘት እንደተነጋገሩ ሳያመለክቱ አላለፉም። ከብልጽግና ጋር በነበረው ውይይት በሕወሓት በኩል የተነሱ ጥያቄዎች ያቀረቡ መኾናቸውን፤ እንዲሁም በሰላምና አንድነት ጉዳይ እንዲሁም ተገናኝቶ መነጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ከስምምነት መድረስ እንደተቻለ አመልክተዋል። በመማክርቱ መግለጫ ላይ ጐልቶ የታየው ሐሳብ ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ ባደረጉት ጥረት መገንዘብ የቻሉት።

በሁለቱ አካላት መካከል ቀርቦ ያለመነጋገር እንጂ ቢነጋገሩ በልዩነት ውስጥ ተስማምቶ በጋራ መቀጠል የሚቻልበት እድል ያለ መኾኑን ነው።

የመማክርቱ ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ፓስተር ዳንኤል ገብረሥላሴ አሁን ኢትዮጵያን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የውስጥ አንድነት ወሳኝ በመኾኑ፤ እስከ መጨረሻው ድረስ ይህን በጎ ዓላማ ለማድረስ ጥረታቸውን የሚቀጥሉ መኾኑን ገልጸዋል።

ከመማክርቱ ከተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ ሁለቱን ወገኖች አገናኝቶ ለማወያየት ዕቅድ መኖሩን ነው። ቀጣዩ ሥራም ይህ እንደሚኾንና ሁለቱም ወገኖች የሚወያዩበት ሐሳቦች ተመልክቶ በአንድ ላይ ለውይይት እንደሚጠራና ወደ መፍትሔ መምጣት እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ አመልክተዋል። ምክክሩ በሕወሓትና በብልጽግና ፓርቲዎች ብቻ የሚያበቃ አይደለም ያለው መማክርቱ፤ በቀጣይ በኦሮሚያና ሌሎች አካባቢዎችም ባሉ ልዩነቶች ላይ ምክክር እንዲደረግ፤ ከዚያም ወደ መግባባት እንዲመጣ ሥራውን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በዚህ የሽምግልና ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ የሰነበቱ ሲሆን፤ በተለይ አቶ ታዬ ደንደአ ያሰፈሩት አስተያየት በተለየ የሚታይ ኾኗል። የአገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው አባቶች ችግሮችን በእርቅ ለመፍታት ማሰባቸው እንደሚያስመሰግን በመጥቀስ፤ አስተያየታቸውን የጀመሩት አቶ ታዬ ደግሞ፤ እርቀ ሰላም የብልጽግና አንዱ መርኅ መኾኑንም አስታውሰዋል። አያይዘውም “ከወያኔ ጋር የሚደረግ ሽምግልና ግን በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። ወያኔ በአፉ እርቅ እያለ በእጁ ተንኮል ይሸርባል” ብለው። ለዚህም አባባላቸው በ2000 ዓ.ም. ዋዜማ ከቅንጅት ጋር የነበረው ታሪኩ ይህን እንደሚያሳይ አመልክተዋል። “ስለዚህ ቅድመ ሁኔታ ያስፈልጋል። ወያኔ እርቅ ከፈለገ የደበቃቸውም ዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ለፌዴራሉ መንግሥት ያስረክባል” ብለዋል።

“በምርጫ ስም የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ለመናድ የሚያደርገውን መፍጨርጨር ያቆማል። ላለፉት 27 ዓመታት ዘርፎ ውጭ አገር ያከማቸውን የአገር ሀብት ቆጥሮ ይመልሳል። ይህ ከመኾኑ በፊት ስለሽምግልና ማውራት ግን የኢትዮጵያዊያንን ቁስል ማመርቀዝ ይኾናል።” ያሉት አቶ ታዬ፤ የአስተያየታቸውን የቋጩት፤ “ብልጽግና እስከ አሁን ጉዳዩን እንደማያውቅ በአክብሮት ይገልጻል! እኛ ብልጽግናዎች ነን! በመደመር መንገድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እንጓዛለን!” በማለት ነበር። (ኢዛ)

አቶ ዮሐንስ ቧያለው እንቢ ባሉት ቦታ አቶ አወሉ ተሾሙ

ከጥቂት ወራት በፊት የመለስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት በመኾን እንዲያገለግሉ ተሹመው የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው፤ ሹመቱን አልቀበልም በማለት እስካሁን ክፍት በኾነው ቦታ ላይ ያልተጠበቀ ነው የተባለ ሹመት ተሰጥቷል። በሳምንቱ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ወሬዎች መካከል አንዱ ነበርም ማለት ይቻላል።

አቶ ዮሐንስ በዚህ ቦታ ላይ አልሠራም ብለው በይፋ ባሳወቁበት በዚህ ቦታ ላይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት አድርገው የሰየሙት ደግሞ በአሁኑ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ኾነው ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ አወሉ አብዲን ነው።

በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ሹመት እንደኾነ ያመላከተው ደግሞ፤ አቶ አወሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ኾነው በተሰየሙ በአጭር ጊዜ ወደ መለስ አካዳሚ በሚኒስትርነት ማዕረግ መዛወራቸው ነው።

አቶ ዮሐንስ በወቅቱ ኃላፊነታቸውን ለመቀበል ያልፈለጉት ከአካዳሚው መጠሪያ ስያሜ ጋር ተያይዞ እንደነበር አይዘነጋም። (ኢዛ)

ሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በአዲስ አመራርና መዋቅር ሥራ ጀመረ

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ የጐላ ድርሻ ያለውና 27 የሚደርሱ ኩባንያዎችን በማንቀሳቀስ የሚታወቀው ሜድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በአዲስ መዋቅርና የኃላፊነት ምደባ መምጣቱን ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነው።

በቅርቡ ከ25 ዓመታት በላይ ቴክኖሎጂ ግሩፑን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ የቆዩት ዶክተር አረጋ ይርዳው በሼሕ መሐመድ አላሙዲን ደብዳቤ ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ፤ አዲሱ የግሩፑ መዋቅር ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው አዳዲስ ሹመቶችንም ያካተተ መኾኑ ታውቋል።

በመረጃው መሠረት እስካሁን የነበረው መዋቅር ፈርሶ ከዚህ ሳምንት ጀምር በአዲሱ መዋቅሩ መሠረት ይጀምራል።

በአዲሱ ምደባና መዋቅር መሠረት ቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች ቁጥር ወደ 32 አድጐ እነዚህን ኩባንያዎች በአንድ ሥራ አስፈፃሚ ሥር ከማድረግ በአራት ከፍሎ ለአራቱም ዘርፎች የየራሳቸው ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

በዚህም መሠረት በአራት የተከፋፈሉትን ዘርፎች በዋና ሥራ አስፈፃሚነት እንዲመሩ በሼሕ አላሙዲን የተሾሙት አቶ አብነት ገብረመስቀል፣ አቶ ደረጀ የእየሱስወርቅ፣ አቶ ኃይሌ አሰግዴና አቶ ጀማል ማሕመድ ናቸው።

በእነዚህ ሥራ አስፈጻሚዎች ሥር ያሉ የተለዩ ዘርፎች የየራሳቸው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኖሯቸው የሚሠሩ ይኾናል ተብሏል። ይህ የምዋቅር ማስተካከያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲጠና የነበረ እንደኾነ ተገልጿል።

የቴክኖሎጂ ግሩፑን ከምሥረታው ጀምሮ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ የቆዩት ዶክተር አረጋ ይርዳው የሥራ መልቀቂያ በማስገባታቸውና ይህንንም ሼሕ መሐመድ በመቀበላቸው፤ ዶ/ር አረጋን ማሰናበታቸው የሚታወስ ነው።

ከቴክኖሎጂ ግሩፑ ከወጡ በኋላም ዶክተር አረጋ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ሥር የነበረውን ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በፕሬዝዳንትነት እየመሩ እንዲቀጥሉ ተደርጓል። ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትነት 80 በመቶ የሼሕ መሐመድ አላሙዲን፤ 20 በመቶ የዶ/ር አረጋ ይርዳው ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!