20210302 adwa

Ethiopia Zare's weekly news digest, week 49th, 2012 Ethiopian calendar

ከነኀሴ 4 - 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አርባ ዘጠነኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከነኀሴ 4 - 10 ቀን 2012 ዓ.ም.) ባሳለፍነው ሳምንት ዐበይት ጉዳዮች ውስጥ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በቀን ወደ ባለ አራት ዲጅት መድረሱ መዘገብ የጀመረበት መኾኑ ነው። ከሰሞኑ በቀን ከ22 ሺሕ በላይ ምርመራ መደረግ የተጀመረው በዚህ ሳምንት ነው። ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ሊጠቀስ የሚችለው ሌላ መረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ብዙ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግለጿል።

ፖለቲካዊ ነክ ዜናዎች ውስጥ ትግራይ ክልል ለመካሔድ የታሰበው ምርጫ ዘግይቶ ቀን የተቆረጠለት በዚህ ሳምንት ነው። የኦነግ ተከፋፍሏል የሚባለው ዜና የዚህ ሳምንት ዜና ኾኖ ቀጥሎ፤ የድርጅቱ ሊቀመንበር በጊዜያዊነት ታግደዋል የተባለው በዚሁ ባጠናቀቅነው ሳምንት ነው። በወላይታ ዞን የተቀሰቀሰው ቀውስ አሁን ጋብ በማለቱ፤ መከላከያ ሠራዊቱ ከዞኑ ወጥቷል። የታሰሩትም የዞኑ አመራሮች ተፈትተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ነውጥን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ ኮምሽን መግለጫ በዚህ ሳምንት አውጥቷል። ዓረና ሕወሓት እየፈጸመው ያለው በደል በምክትል ሊቀመንበሩ በኩል ማብራሪያ የሰጠበትም ሳምንት ነው።

ከሳምንቱ አንኳር ወሬዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ በረራውን እንደሚያሳድግ ማሳወቁ አንዱ ነው። የሳምንቱ አነጋጋሪ የነበረው ሌላው ዜና፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል መባሉና ምላሻቸው ነበር። እነዚህና ሌሎች አንኳር ሳምንታዊ ዜናዎች እንደሚከተለው በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ተጠናክረው ቀርበዋል። መልካም ንባብ!

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኮሮና የተያዙ ሰዎች ብዙ ናቸው

በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መስፋፋት ጋር ተያይዞም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ባደረጉት የውይይት መድረክ ላይ አንድ ጣል ያደረጉት መረጃ ነበር። ተቋማት ምርመራ ማድረግ አለባቸው የሚለውን ጭብጥ ይዘው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እንዲመረመሩ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

ይህ አገላለጻቸው ግን በጽሕፈት ቤታቸው ብዙ የሚባሉ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ስለመኾኑ የጠቆሙበት ነው የሚል አመለካከትን አሳድሯል። ስለጉዳዩ “የቴስት ካፓሲቲ ስላሳደግን ፎከስ ማድረግ ያለብን (ቴስት ማድረግ ላይ ነው)፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሙሉ ያለ ሠራተኛ ትናንትና ከትናንትና ወዲያ ቴስት ተደርገዋል። እናም እዚህም ያገኘነው ቀላል ቁጥር አይደለም። ሰፋ ያለ ቁጥር ተገኝቷል” በማለት ነበር የገለጹት። (ኢዛ)

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና ኮቪድ 19

ከሰሞኑ አነጋጋሪ ከነበሩ ዜናዎች ውስጥ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል የሚል ወሬ መሰማቱ ነው። የወሬው መነሻ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጠባቂ በኮሮና ቫይረስ ከመያዙ ጋር ተያይዞ የተሠራጨ ነው። በእርግጥም አቶ ኃይለማርያም ከጠባቂያቸው በቫይረሱ መያዝ ጋር ተያይዞ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው ኾኗል።

ከምርመራው ውጤት በኋላ አቶ ኃይለማርያም በቲውተር ገጻቸው፤ ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸውን ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል። የግል ጠባቂያቸው ግን በቫይረሱ ስለመያዙም አሳውቀዋል። እኔ ግን ነፃ ነኝ በማለት መነጋገሪያ ለነበረው ጉዳይ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

በመጨረሻም የትግራይ ክልል ምርጫ ቀን ተቆረጠለት

ከሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጪ መኾኑ እየተጠቀሰ ያለው የትግራይ ክልል ምርጫ ይካሔድበታል የተባለውን ቀን የክልሉ ምክር ቤት ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነው። ከክልሉ ምክር ቤት የወጣው መረጃ እንዳመለከተው ምርጫው ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ይካሔዳል።

እስከዚህ ሳምንት አጋማሽ ድረስ ምርጫው ይካሔዳል ይባል እንጂ፤ የምርጫ ቀኑ ሳይቆረጥ ቀርቶ ነበር። ይህም ምርጫው አይካሔድም የሚል እምነት አሳድሮ የነበረ ሲሆን፤ በተለይ ምርጫን በዚህ አጭር ጊዜ ማካሔድ የይስሙላ መኾኑም ሲጠቀስ ቆይቷል። አሁንም ግን በብዙዎች እምነት ክልሉ ምርጫውን ካካሔደ፤ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ልዩነት በማስፋት በአገሪቱ ፖለቲካ ሒደት ውስጥም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። (ኢዛ)

የኦነግ ጉዳይ አሁንም እንቆቅልሽ ኾኖ ቀጥሏል

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ረዥም ዕድሜ ያለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በተደጋጋሚ አመራሮቹ በመከፋፈል እና አሸናፊ ኾኖ የወጣው እየቀጠለ ዛሬ ደርሷል።

በመጨረሻ ላይ ግን በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ እርሳቸውን በመሪነት ይዞ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን እንደገና የመከፋፈል አደጋ ገጥሞታል መባል ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህ አደባባይ የወጣ ጉዳይ እየሰፋ መጥቶ፤ በዚህ ሳምንት ደግሞ በአቶ ዳውድ የሚመራው ቡድን የድርጅቱን ስድስት ከፍተኛ አመራሮች ማገዱን ማሳወቁ፤ ኦነግ እየተከፋፈለ ነው የሚለውን እምነት ያጐላ ሲሆን፤ ጉዳዩን የበለጠ እንቆቅልሽ ያደረገው ደግሞ፤ ታግደዋል የተባሉት አመራሮች “አጋጅና ታጋጅ ብሎ ነገር የለም” በማለት ምላሽ መስጠታቸው ነው።

እንዲህ ያሉ ምልልሶች ለምን ተፈጠሩ? የሚለው ጥያቄ ይኼ ነው የሚባል የተረጋገጠ ምላሽ ሳያገኝ በሁለት ቀናት ልዩነት ደግሞ፤ ሌላው የኦነግ የከፍተኛ አመራሮች ቡድን፤ “አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኦነግ ሊቀመንበርነታቸው ለጊዜው ታግደዋል” ብሎ ብቅ አለ። እንዲህ ያሉት ምልልሶችና መግለጫዎች የወጡት በዚህ ሳምንት ቢኾንም፤ በቀደመውም ሳምንትም ቢሆን የኦነግ አመራር እርስ በርስ መናበብ የተሳናቸው ስለመኾኑ አመላካች ድርጊቶች የተፈጸሙበት እንደነበር ይታወሳል።

ምክትል ሊቀመንበሩንና ሌሎች አመራሮችን የያዘው ቡድን ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ፤ አቶ ዳውድ ይህን መግለጫ እንደማያውቁ መናገራቸው ችግሩ ቀደም ብሎ የነበረ መኾኑን የሚጠቁም ነበር። አቶ ዳውድ አያይዘውም በቀደመው ሳምንት ስለተሰጠው መግለጫ ምንም እንደማያውቁ መግለጻቸውና ምክትላቸውንም ጠይቀው ስለመግለጫው እንደማያውቁ ነግረዋቸው እንደነበር፤ ኾኖም ኦነግ ሰጠ በተባለው መግለጫ ላይ ምክትላቸው ተገኝተው መግለጫውን ሰጥተዋል በማለት አቶ ዳውድ መናገራቸው ኦነግ ቤት ውስጥ ያለውን ልዩነት ያሳየ ነው ተብሏል። ለዚህ ነው ሰሞናዊው የኦነግ ጉዳይ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ኾኖ ቀጥሏል እየተባለ ያለው። (ኢዛ)

የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች

በዚህ ሳምንት ብዙ አነጋጋሪ ከነበሩ ዜናዎች ውስጥ በወላይታ ዞን የክልል ጥያቄን ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ ነው። በዚህ ቀውስ የአገር መከላከያ ጣልቃ ገብቷል። የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ለዚህ ምክንያት ናቸው የተባሉ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በእስር እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ፤ በቀናት ልዩነት ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ እንዲለቀቁ ተወስኗል። የመከላከያ ኃይሉም ዞኑን ለቅቆ ወጥቷል። ሕዝቡም ሠራዊቱን በሰላም ሸኝቷል።

አሁን በአንፃራዊ ዞኑ የተረጋጋ ነበር የተባለ ሲሆን፤ ያለመረጋጋቱ በነበረበት ወቅት የጸጥታ ኃይሉ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል የሚል አስተያየት ቢሰነዘርም፤ የዞኑ ነዋሪዎች ሠራዊቱን በሰላም መሸኘቱ ታውቋል። (ኢዛ)

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሰሞነኛ አንደበት

ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሳምንት በተለያዩ ክንውኖች ላይ ነበሩ። በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ኮንፈረንስ መዝጊያ ፕሮግራም ላይ ነበሩ። ወደ አፋር በመሔድ በአዋሽ ወንዝ ሙላት በተፈጠረ ጐርፍ ድጋፍ ለመስጠት አሳይታም ሔደዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ሕንፃ እድሳትን ጐብኝተዋል።

በተገኙበት ቦታ ሁሉ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በተለይ ግን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችና መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ሰፊና በርካታ አገራዊ ጉዳዮችን ያነሱበት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሳታፊዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስና ማብራሪያ አዳዲስ መረጃዎችን ያካፈሉበት ነው። በመድረኩ ከጠቀሱዋቸው አንዳንድ መረጃዎች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቅሳሉ። (ኢዛ)

መስከረም ላይ በኢትዮጵያ የኮቪድ መመርመሪያ ኪት ይመረታል

ኢትዮጵያ ከአንድ ወር በኋላ የኮቪድ መመርመሪያ ኪት ማምረት እንደምትጀምር መግለጻቸው አንዱ ነው። በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ባይሰጡም፤ አሁን ከውጭ በእርዳታና በግዥ የሚገባውን የመመርመሪያ ኪት መስከረም ወር ላይ እዚሁ ማምረት የሚጀመር ስለመኾኑ አረጋግጠዋል። ይህም የኾነበት ዋና ምክንያት የመመርመር አቅምን ለመጨመር ስለመኾኑም አመላክተዋል። (ኢዛ)

አንድ ቢሊዮን ችግኝ ለጐረቤት አገሮች ይሰጣል

በዘንድሮው የክረምት ወቅት አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘው መርኀ ግብር ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ስለመጠናቀቁ የገለጹት ዶክተር ዐቢይ፤ ከሲቪክ ማኅበራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ይህንኑ ገልጸው፤ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙ ገልጸዋል።

የቀጣዩን ዓመት ለየት የሚያደርገው ግን ከስድስት ቢሊዮኑ ችግኝ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ችግኝ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተከል ያለመኾኑን ገልጸዋል። አንድ ቢሊዮን የሚኾነውን ችግኝ ለጐረቤት አገሮች በመስጠት፤ እነርሱም የዚህ ተቋዳሽ እንዲኾኑ ማድረግ ነው ብለዋል። (ኢዛ)

የሰብአዊ መብት ኮምሽኑ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ችግር የተከሰተባቸው አካባቢዎች በተመለከተ መግለጫ ያወጣው በዚህ ሳምንት ነበር።

የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተከሰተው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ ላይ ፈጣን ምርመራ ማድረግ መጀመሩን አስታውቆ የነበረው ኮሚሽኑ፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም ከ40 በላይ ችግሩ ተከስቶባቸዋል በተባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ የምርመራ ቡድኖችን አሰማርቶ ምርመራ አድርጓል። ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ምስክሮችን እና የመንግሥት አካላትን በማነጋገር መረጃ ለማሰባሰብ እና አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ጥረት ማድረጉን በዚሁ መግለጫው ላይ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በምርመራው ወቅት የታዩና በአፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሥጋቶችን ለሚመለከታቸው አከላት ሁሉ በይፋ በማሳወቅ፤ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ጥረት አድርጓል። አሁንም የጥቃት ሥጋት ያለባቸው ነዋሪዎችን በተመለከተ፣ ሰብአዊ እርዳታ፣ ድጋፍ እና የተፈናቀሉ ተጎጂዎችን ሁኔታ እና የእስረኞች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል። አሁንም የጥቃት ሥጋት ያለባቸው ነዋሪዎች በተመለከተ የምርመራ ቡድኖች በተጓዙባቸው በአብዛኛው አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት የተሻለ መረጋጋት ያለ መኾኑን በመግለጫው ገልጿል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር መጨመር

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚበርባቸው የአገር ውስጥ መዳረሻዎቹን የበረራ ቁጥር መጨመሩን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማደግ ላይ ያለውን የደንበኞች የጉዞ ፍላጎት ለማሟላት፤ በአገር ውስጥ መዳረሻዎቹ የሚሰጠውን ሳምንታዊ መደበኛ የበረራ አገልግሎት በማሳደግ፤ ሲያደርግ የነበረውን የበረራ ቁጥር መጨመሩን አስታወቀ።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ በተለይ ለፋና እንደገለጹት፤ “እስካሁን ስናደርገው እንደቆየነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት የመከላከያ እርምጃዎችን በጥብቅ ዲሲፕሊን በአየር ማረፊያም ኾነ በበረራ ወቅት ተግባር ላይ በማዋል የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት እየተከላከልን የደንበኞቻችንን እና የሠራተኞቻችንን ደኅንነት በመጠበቅ አገልግሎታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል። (ኢዛ)

ቦሌ ላይ የተያዘው 23 ሺሕ ግራም ወርቅ

በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ 23 ሺሕ ግራም ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል መያዙ ሌላው ተጠቃሽ ሳምንታዊ ዜና ነው። 46 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው ይህ ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል የተያዘው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ነው።

23 ሺሕ ግራም ወርቁን በሕገወጥ መንገድ ሊያስወጣ ሲል የተያዘው ናይጄሪያ ዜግነት ባለው ግለሰብ ነው። ግለሰቡ ወርቆቹን በሕገወጥ መንገድ ወደ ዱባይ ይዞ ለመሔድ ሲሞክር ነው በቁጥጥር ሥር ስለመዋሉ የሚያመለክተው መረጃ የጠቆመው። ይህን ሕገወጥ ተግባር በቁጥጥር ሥር ላዋሉ የቦሌ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አመራሮች፣ ሠራተኞኛ የጸጥታ አካላት፤ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ምስጋናቸውን ማድረሳቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር ገልጿል። (ኢዛ)

ሕወሓትና ዓረና

በሕወሓት የሚመራው የትግራይ መንግሥት እንደ ዓረና ባሉ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ የሚያደርገው ማዋከብና አፈና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ዓረና ትግራይ በዚህ ሳምንት ሰፋ ያለ መግለጫ ሰጥቷል።

የዓረና ትግራይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋይ ሰሞኑን እንደገለጹት፤ ሕወሓት በቅርቡ ብቻውን ለማካሔድ ላሰበው ሕገወጥ ምርጫ መሳካት ሲል፤ እንደ ዓረና ባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና በደል በከፍተኛ መጠን ስለመጨመሩ አትተዋል።

በተለይም በቅርቡ ስምንት የዓረና አመራሮችን በማሰርና በማንገላታት ለሌላው መማሪያና መቀጣጫ አድርገዋቸዋል። ሕጉ በ24 ሰዓታት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቢያስገድድም፤ ከአምስት እስከ 15 ቀናት በየእስር ቤቱ በማጎር ቶሎ ፍትሕ እንዳያገኙ በማድረግ ጉዳት እንዳደረሱ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለምልልስ ገልጸዋል።

“አባሎቻችን በሕዝብ ፊት ግለሂስ አድርገው ፓርቲውን ለቀው እንዲወጡ፤ አልያም ደግሞ ትግራይ ለባንዳ ቦታ የሌላት በመኾኑ፤ ክልሉን ለቃችሁ ሒዱ ይባላሉ” በማለትም ተናግረዋል። ከእስራትና ከእንግልቱ በተጨማሪ አባላቶቹ በአከራዮቻቸው ከቤታቸው እንዲባረሩ፤ አለፍ ሲልም ከትዳር አጋሮቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲለያዩ በማድረግ፤ ቤተሰብ እስከመበተን የሚደርስ የዘቀጠ አሠራር እየተከተለ መኾኑን ምክትል ሊቀመንበሩ በዚሁ ቃለምልልሳቸው አመልክተዋል። (ኢዛ)

የሮማ ካቶሊካዊት በህዳሴ ግድብ ላይ

የህዳሴ ግድብን የተመለከቱ መረጃዎች በዚህም ሳምንት መነጋገሪያ መኾኑ አልቀረም። ለየት የሚለው ህዳሴን የተመለከተው የዚህ ሳምንት መረጃ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የገቡበትን ውዝግብ በውይይት እንዲፈቱ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ ጥሪ ማቅረባቸው ነው። በግድቡ የገቡበት ውዝግብ ወደ ግጭት ሊመራቸው እንደማይገባ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሳያሳስቡ አላለፉም።

“ዘላለማዊው ወንዝ የሕይወት ምንጭ መኾኑን እንዲቀጥል በድርደሩ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች በንግግር መንገድ እንዲቀጥሉ እጋብዛለሁ” ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ፤ “ዓባይ የሚያተባብር እንጂ የሚከፋፍል፤ ወዳጅነት፣ ብልጽግና እና ወንድማማችነትን የሚያለመልም እንጂ የጠላትነት፣ የአለመግባባት እና የግጭት ሊሆን አይገባም” ብለዋል።

በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሦስቱ አገሮች ንግግር፤ በሱዳን ጥያቄ ለጊዜው የተቋረጠ መኾኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሔድ የታቀደው ድርድር በሱዳን ጥያቄ ለአንድ ሳምንት መራዘሙን ኢትዮጵያ አስታውቃለች። የኢትዮጵያ የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዳለው፤ ድርድሩ ሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ይካሔዳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!