Ethiopia Zare's weekly news digest, week 53rd, 2012 Ethiopian calendar

ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃምሳ ሦስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም. - መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም.) እንኳን ለ2013 አዲስ ዓመት አደረሰን! አዲሱ ዓመት የሰላም የእድገትና የብልጽግና ይሆን ዘንድ እንመኛለን! ያሳለፍነው ሳምንት የ2012 ዓ.ም. የመጨረሻ ቀናት የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ያረፉበት ነው። በእነዚህ ያሳለፍናቸው ሰባት ቀናት በኢትዮጵያ ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል አዲሱን ዓመት አስታክኮ የአዲስ አበባን ገጽታ በተለየ መልኩ የቀየረው የሸገር ፓርክ ምርቃት በወታደራዊ ትርዒት ታጅቦ በይፋ መመረቁ አንዱ ነው።

ሕገወጥ ነው የተባለው የትግራይ ክልል ምርጫ የተካሔደበት፤ ውጤቱም እንደተጠበቀው የሕወሓት አሸናፊነት የተነገረበት ሲሆን፤ 98.2 በመቶ ሕወሓት ድምፅ አገኘ ተብሏል። በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢቢሲ የሰጡት ቃለ ምልልስ ብዙዎች የተመለከቱት የተለያዩ አስተያየት የተሰጠበት ጉዳይ ሲሆን፣ በዚህ ቃለ ምልልስ የትግራይን ምርጫ የጨረቃ ምርጫ ብለዋል። ለውጡ ድጋፉ እየቀነሰ ነው ለሚለው ጥያቄ በፍጹም የሚል ምላሽ የሰጡበትን ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የባልደራስ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ አካልን የማውጣት ማመልከቻ ያስገባበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ እርሳቸውና ሌሎች የባልደራስ አባላት በሽብር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ዜናዎች በተመለከተ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለአዲሱ ዓመት በማስመልከት ያደረጉት ንግግር ብዥታን የፈጠረ ኾኗል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሕወሓት ከውጭ መንግሥታት ጋር ለመገናኘት የሚያደርገው ሙከራ ሕገወጥ ተብሏል። ከትግራይ ክልል ምርጫ ማብቃት በኋላ በፌዴራል ፓርላማ አባል የኾኑ በክልሉም ፓርላማ ተመርጠዋል መባሉ አስደማሚ ኾኗል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዲሱን ዓመት አስታኮ 551 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ ለቅቋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ከጸጥታ ሥጋት ጋር ተያይዞ ለዘመን መለወጫ ርችት አይተኮስ ብሎ ማሳሰቢያ መስጠቱም ከሳምንቱ ወሬዎች የሚጠቀስ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚታወቁት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መሾማቸው ዜናም ትኩረት ከሳቡት ውስጥ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በቅርቡ ተፈጥሮ በነበረ ኹከት ለኦርቶዶክስ ጉዳት ለደረሰባቸው ምእመናን 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጋለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ማስተላለፉተ መልእክት “ባገኘናቸው ድሎች ረክተን አንቀርም” ብለዋል።

ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መካከል ኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ለውጥ ኩባንያ ለመሸጥ ወደ መጨረሻ ምዕራፍ መደረሱ የተገለጸበት ሳምንት ነው። በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የተቀናበረውን ሳምንታዊ አንኳር ዜናዎች እነኾ!

የሸገር ፓርክ ምረቃ

ከሰሞናዊ አገራዊ ጉዳዮች በመልካም ዜናነቱ የሚጠቀሰው የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ በይፋ መመረቅ ነው። በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሸገር ፓርክ አበርክቶ ኢትዮጵያውያን አልፎም አፍሪካውያን የሚኮሩባት አዲስ አበባ እንዲህ ዐይነት ፓርክ ማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል። በአዲስ አበባ የተገነቡት ፓርኮች የአገሪቱን እና የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት በዘለለ በትብብር ከሠራን ምን ዐይነት ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ሕያው ምስክር ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ አያይዘውም በንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የፓርኩን ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ሥራውን ከሥር ከሥር በመከታተል እና አመራር በመስጠት፤ ፓርኩ ለኢትዮጵያውያን የአዲስ አበባ የአዲስ ዓመት ስጣታ እንዲኾን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቻይና መንግሥት ድጋፍ የሚከናወነው እና የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የኾነው ይህ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ መስከረም 20 ቀን 2012 ጠቅላይ ማኒስትሩ በተገኙበት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፤ የወዳጅነት አደባባይ የሚል ስያሜ የተሰጠው ፓርኩ ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለው 42 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ነው።

በፕሮጀክቱ አምስት ግዙፍ ማዕከላት ያካተተ ሲሆን፣ የስብሰባ፣ የጥበብ ማቅረቢያ ስፍራ፣ የሕፃናት መዝናኛ ማዕከል እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከላት አካትቶ የተገነባ ሲሆ፤ን የአዲስ አበባ ገጽታን በእጅጉ የቀየረ ኾኖ ታይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የተመረቀው ይህ ፓርክ፤ የምረቃ ሥርዓቱ ወታደራዊ ትርዒትን አካትቶ የተከናወነ ነበር። ይህም ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች እንዲሰጥበት አድርጓል። ፓርኩ እንዲህ ባለ ወታደራዊ ትርዒት ታጅቦ መመረቅ አለበት ወይ? የሚል ጥያቄ ያነሱ ያሉ ሲሆን፤ አጋጣሚውን መጠቀሙ ተገቢ ነው የሚል አስተያየቶችንም አጠንክረው ሐሳብ የሰጡ ነበሩ። ፕሮጀክቱ ግን ጀምሮ መጨረስ የሚቻል መኾኑን ያሳየ ስለመኾኑ ግን ሁሉም የሚስማማበት ፕሮጀክት ስለመኾኑ ታምኗል። (ኢዛ)

አወዛጋቢው የእነዶክተር ደብረጽዮን ውክልና

ከሰሞኑ አነጋጋሪ ከነበሩ ዜናዎች ውስጥ የትግራይ ክልል ምርጫና ውጤቱ ተጠቃሽ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ይበልጥ አነጋጋሪ የኾነው በክልሉ በተደረገው ምርጫ በፌዴራል ፓርላማ ውስጥ አባል የኾኑት ዶ/ር ደብረጽዮንና ሌሎች የሕወሓት ባለሥልጣናት በሰሞኑ ምርጫ ለክልል ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረው የገቡ በመኾኑ፤ ከዚህ በኋላ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ኾኗል።

በዚህ ጉዳይ ሰሞኑን ከተንሸራሸሩት መረጃዎች ውስጥ ፓርላማ ውስጥ ከተወከሉት 33 የትግራይ ተወካዮች መካከል ዶ/ር ደብረጽዮን፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ እና አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ያትታል። አያይዘውም አሁን ደግሞ በወያኔው ምርጫ ምክንያት እነዚህ ሰዎች የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት ኾነዋልና። ከዚህ በኋላ እነዚህ ሰዎች የሁለቱም ምክር ቤት አባላት ይኾናሉን? እንዲህ ዐይነቱ ሁኔታ ከዚህ በኋላ እንዴት እና በምን ዐይነት መንገድ ይስተናገዳል? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ኾኗል። ሁለቱም ምክር ቤቶች ላይ ይኖራሉ ወይስ አንዱን ይመርጣሉ?

የፌዴራል መንግሥቱ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በነበረበት እንዲቀጥል ወስኗል። አሁን በወያኔ ምርጫ ውጤት መሠረት ደግሞ ይህ ምክር ቤት አዳዲስ አባላት ባሉት አዲስ ምክር ቤት ይተካል ማለት ነው። ያ ማለት ከኾነ ደግሞ የትግራይ ክልል ሁለት ምክር ቤቶች ይኖሩታል ማለት ነው። መንግሥት የሚያውቀው ምክር ቤትና መንግሥት የማያውቀው ምክር ቤት። እንግዲህ ትግራይን በተመለከተ ክልሉን ወክሎ አዋጅ የሚያወጣው፣ የሚያጸቅደውና የሚወስነው ይህ አዲሱ የወያኔ ምክር ቤት እንደኾነ ግልጽ ነው።

በዚህም መሠረት በጀትንና እና መሰል የምክር ቤቱ ውሳኔዎች በመንግሥት በኩል ተቀባይነት የሌላቸው ይኾናሉ። ይህ እንደሚኾን የታወቀው ደግሞ መንግሥት የወያኔን ምርጫ ሕገወጥ ነው ካለበት ቀን ጀምሮ ነው።

መንግሥት በዚህ ሕገወጥ ምክር ቤት ለተወሰኑ ውሳኔዎች ማስፈጸሚያ የሚኾን የበጀትም ኾነ የበጀት ድጎማ ጥያቄዎችን የማይቀበልና የሚከለክል ከኾነ ደግሞ፤ ወያኔም በክልሉ የሚሰበሰበውን ግብር ለፌዴራል መንግሥቱ ገቢ ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም። ያው ለክልሉ ያውለዋል ማለት ነው። (ኢዛ)

የዶክተር ደብረጽዮን የአዲስ ዓመት ንግግርና አንደምታው

የትግራይ ክልል ምርጫ ተካሒዶ ተጠናቋል ከተባለ በኋላ፤ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ያደረጉት ንግግር “የትግራይ ሕዝብ ምርጫ የሚወሰነው የትግራይ ክልል መንግሥት ሕወሓት ወይም ሌሎች ፓርቲዎች አይደሉም። የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት የትግራይ ሕዝብ ነው። ዳኛው ይግባኝ ሰሚው የመጨረሻ ፍርድ ሰጪው የትግራይ ሕዝብ ብቻ ነው” በማለትም አክለዋል።

በዚሁ ለአዲስ ዓመት ጭምር ባስተላለፉት መልእክት የተገባደደው 2012 ዓ.ም. የአማራና የትግራይ ሕዝብ ለማጋጨት የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፤ የመሬት አስመላሽ፣ ነፃ አውጪ ኮሚቴዎችና ሌሎች የተፈለፈሉ በማሰማራት ትሕነግ የምትባል ፍጡር እስካለች ድረስ የአማራ ሕይወት ከምስቅልቅል አይወጣም የሚልም አክለዋል። ዶ/ር ደብረጽዮን በዚሁ መልእክታቸው አማራን በተመለከተ ከተናገሩት ውስጥ፤ “ለትግራይ ክልል አቅራቢያ ያሉት የአማራ ሕዝቦች እንደሚያውቁት በክልሉ አመራር የሚታገዙ ታጣቂዎች ትናንት ታሪካዊ ምርጫችን ለማደናቀፍ ያዙን ልቀቁን እያሉ የነበሩ ቢኾንም፤ በትግራይ ሕዝብና የጸጥታ ኃይሉ ፊት መቆም የማይችሉ መኾኑ ለምስክር መቅረብ ይችላሉ” የሚል ነበር።

በመልእክታቸው ማጠቃለያ ላይም፤ “በትግራይ ሕዝብ ላይ ከውጭ ኃይሎችም እየተባበራችሁ ሁሉም ዐይነት ግፍ እየፈጸማችሁ የምትገኙ የድሮና አዳዲስ አኀዳውያንና ሌሎች ተስፈኞች እና ተላላኪዎች፤ ከተላላኪዎች በታች የኾናችሁ ሁሉ ማሳወቅ የምንፈልገው የትግራይ ሕዝብ የማያከብር ጨው ለራሱ ብሎ ይጣፍጥ ነው” በማለት አወዛጋቢ ንግግራቸውን መቋጫ አድርገዋል። (ኢዛ)

የጨረቃው ምርጫና ጠቅላይ ሚኒስትሩ

ባሳለፍነው ሳምንት ብዙዎች የተመለከቱትና የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡበት ጉዳይ ቢኖር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከኢቢሲ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነበር። በዚህ ቃለ ምልልስ ማግስት በሚካሔደው የትግራይ ክልል ምርጫ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ ተጠቃሽ ነው። “ምርጫውን እንደ ጨረቃ ቤት ነው የምመለከተው፤ እዛ ያለው ኃይል ጭንቅላቱ ደርቋል። ኪሱ ሲደርቅ ይጠፋል። እኛ የትግራይ ሕዝብን በልማት እንደግፋለን እንጂ ጦር አናዘምትበትም” በማለት የመንግሥታቸውን ሐሳብ አንጸባርቀዋል።

“የጨረቃ ቤት ካርታ እንደሌለው ሁሉ ይኼም ምርጫ ሕጋዊ ያልኾነ፤ ምርጫ ቦርድ የማያውቀው ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አገራዊ ምርጫ ሲካሔድ፤ እዛ ያለው ቡድን ካልተሳተፈ ፓርላማ መቀመጫ አይኖረውም። ለዚህ ብለን ጦርነት አንከፍትም። ለትግራይ ሕዝብ ኮሮናን እንዲከላከል አፍ መሸፈኛን እንሰጣለን፣ ውኃን እናስገባለን፣ እድገትን እናመጣለን እንጂ፤ የኾኑ ቡድኖችን ለመዋጋት ጦርነት አንከፍትም። እዛ ያለው ኃይል ጭንቀላቱ ደርቋል። ኪሱ ሲደርቅ ይጠፋል። በድሮ በሞተ ሐሳብ የሚንቀሳቀስ ነው” በማለት የሕወሓትን አመራሮች ወርፈዋል።

በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ፤ የለውጡ መንግሥት እንደ ጅማሬው አይደለም ድጋፉ ቀንሷል? ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሲመልሱ “ፌስ ቡክን አይተኽ ድጋፍና ተቃውሞን የምትለካ ከኾነ ጥሩ መለኪያ አይኾንኽም። መንግሥታችን ሰፊ ድጋፍ አለው። አሜሪካ በቴክኖሎጂ ካልኾነ ማሳካት የማትችለውን ሕዝባችንን በአጭር ጊዜ አምስት ቢልዮን ችግኝ ሐምሌ ወር ሳያልቅ ተክሏልል፤ ሊያውም በኮሮና ወቅት። ለህዳሴ ግድብ የሚያዋጣው ገንዘብ ድጋፍ ጨምሯል። ሸገርን ለማስዋብ በተሰናዳ የእራት ገበታ ላይ በአንድ ጀንበር ሁለት ቢልዮን ብር ባለሀብቱ ለግሷል። ይሄ ሁሉ ሰፊ ድጋፍ እንዳለን ያሳያል በማለት፤ አሁንም ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸዋል የሚሉ አስተያየቶች እዚህም እዚያ ይነሳሉ። ከሰሞኑ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የቃለ ምልልስ ቆይታ የነበረው የኢቢሲው ጋዜጠኛም ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል እንዱ ይኸው ነው። (ኢዛ)

“ባገኘነው ድሎች ረክተን አንቀርም” ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

የአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት የተላለፈው የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ በተመረቀበት ወቅት ነው። በዚሁ መልእክታቸው እስካሁን ባገኘናቸው ድሎች ረክተን አንቀርም ገና ወደ ልዕልና እንመጥቃለን ነው ነበር ያሉት።

እንደ ምድር ስበት የሚስቡን ችግሮቻችንን አልፈን ልክ እንደ መንኮራኩር፣ ለዚህ በተዘጋጁ እና በቆረጡ መጣቂዎች እና ባዘጋጀነው የ10 ዓመት ፍኖተ ብልጽግና መንኮራኩርነት ሕብረ ብሔራዊነት በተሰኘ ማምጠቂያ ስፍራ ብልጽግና ወደተባለ ደርሰንበት ወደማናውቀው የመንፈስ፣ የቁስ እና የኢኮኖሚ ከፍታ እንመጥቃለን በማለት፤ 2012 ብዙ ኀዘንና ደስታ የተፈራረቀበት ቢኾንም በዛው ልክ ኢትዮጵያ ጨለማ የማይበግራት የብርሃን አገር፣ የብርቱ ሕዝብ የጽኑ ዜጋ አገር መኾኗ የታየበት እንደነበር ጠቅሰዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት እንደ ስኬት ካነሱዋቸው ውስጥ የህዳሴ ግድብ የመጀመያ ዙር የውኃ ሙሌትን በስኬት ማጠናቀቋን፤ እንዲሁም የመጀመሪያ ሳተላይት ማምጠቋን በምሳሌነት አመልክተዋል። (ኢዛ)

የሕወሓት ከውጭ አገራት ጋር ለመገናኘት የሚያደርገው ሙከራ ሕገወጥ ተባለ

ሕወሓት ከውጭ አገራት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ስለመኾኑ መነገር ከጀመረ ቆይቷል። በቅርቡም በሳውዲ ዐረቢያ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆችን በተመለከተ ለሳውዲ መንግሥት ጻፈ የተባለው ደብዳቤ ይገለጻል። እንዲህ ያለውን እንቅስቃሴና ሌሎች ይፋ ያልተደረጉ ተመሳሳይ ድርጊቶችን በመመልከት፤ ምሁራን ይህ የክልሉ ድርጊት ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በዚህ ጉዳይ አስተያየት የሰጡ ምሁራን እንደገለጹትም “ድርጊት ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መኾኑንና ከዚህ አካል ጋር የሚተባበር ማንኛውም አካል የወንጀሉ ተባባሪ መኾኑን ለዓለም አገራት ማሳወቅ ይገባል” ብለዋል።

ሕወሓት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በመጣስ ያደረገው ምርጫ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መኾኑ እየታወቀ፤ የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን በመውሰድ ከውጭ አገራት እያደረገ ያለው ግንኙነት በዓለም አቀፍ ሕግም ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። በመኾኑም የዓለም አገራት ከሕወሓት የሚደረግላቸውን ማንኛውንም ጥሪ መቀበል እንደማይገባቸውና ይህን ካደረጉም የኢ-ሕገ መንግሥታዊ ተግባር ተባባሪ እንደኾኑ ማሳወቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ምሁራን አክለው እንደገለጹትም የትግራይ ክልል መንግሥት ሰሞኑን ያደረገው ምርጫም ኾነ ከተለያዩ አገራት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች በግልጽ የሚጥስ መኾኑን ጭምር ነው። (ኢዛ)

551 የፌዴራል ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀቁ

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የ2013 ዓ.ም. አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በፌዴራል፣ በክልልና በመከላከያ ወታደራዊ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ 551 የፌዴራል ታራሚዎች በተለያዩ መስፈርቶች መነሻነት ይቅርታ ማድረጉን ያስታወቀው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ይቅርታ የተደረገው የፌዴራል ይቅርታ ቦርድ በተለያዩ ጊዜያት የፌዴራል ታራሚዎችን የይቅርታ ጥያቄ በመመርመር እና ለኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት በማቅረብ እንደኾነም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አሳውቋል።

ይቅርታው አንድ ታራሚ የተፈረደበትን ቅጣት ከመጨረሱ በፊት በፈጸመው ወንጀል መጸጸቱ፣ መታረሙ እና መልካም ዜጋ መኾኑ ከተረገገጠ፤ ቅጣቱን ሳይጨርስ ከማረሚያ እንዲወጣ የሚሰጥ ውሳኔ መኾኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ማለት ይቅርታ መንግሥት የሕዝብን የመንግሥትን እና የታራሚውን ጥቅም ያስከብራል ብሎ ሲያምን የሚሰጠው ችሮታ እንጂ፤ እንደ መብት የሚጠየቅ አለመኾኑንም ይኸው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አመልክቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!