Ethiopia Zare's weekly news digest, week 3rd, 2013 Ethiopian calendar

ከመስከረም 18 - 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሦስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከመስከረም 18 - 24 ቀን 2013 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ አገራዊና አነጋጋሪ የሚባሉ ክንውኖችን ያስተናገደ ነበር። ዐበይት እና ትኩረት ካገኙ ዜናዎች ውስጥ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የሚያካሔዱ መኾኑን ተከትሎ በተለይ ከትግራይ እየተሰማ ያለው ተቃውሞ ተጠቃሽ ነው።

ዘገባውን በዩቲዩብ ለመመልከትና ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ!

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በትግራይ ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣሱ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች መኖራቸውን የጠቆሙትም በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። የኢሬቻ በዓልን ተንተርሶ አደጋ ለመጣል የተደራጁ ቡድኖች መኖራቸውን በማረጋገጥ መንግሥት ጥብቅ የጸጥታ ጥበቃ እያካሔድኩ ነው ማለቱም ከሳምንቱ ዜናዎች የሚጠቀሱ ናቸው። በሕወሓትና በኦነግ ሸኔ አደራጅነት በኢሬቻ በዓል ላይ ሽብር ለመፍጠር ሲዘጋጁ ነበሩ የተባሉ ከ500 በላይ ግለሰቦች ተይዘዋል። የፌዴራል ፖሊስ የመስቀል አደባባይ ትዕይንትም ከሰሞኑ ትኩረት የሳበ ዜና ነበር።

እስከ ዛሬ ከሚቀርብ የክልል ጥያቄዎች በተለየ በደቡብ ክልል ያሉ አምስት ዞኖችና አንድ ወረዳ ተጣምረው ክልል ለመኾን ስለመወሰናቸውም ተሰምቷል። ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚከፈተው የሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባ ላይ የሕወሓት የምክር ቤት አባላት ካልተገኙ ምን ሊኾን ይችላል የሚለውም ጉዳይ የተለያየ አስተያየት ሲሰጥበት የሰነበተ ጉዳይ ነው።

በወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው የምርጫ ቦርድ አንድ የቦርድ አባል ያልተስማማኹበት ጉዳይ አለ ብለው መልቀቂያ ማስገባታቸው በአነጋጋሪነቱ የሚጠቀስ ዜና ነው።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የተሰማው የታወቁ ምሁርና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ዜና እረፍት የመገናኛ ብዙኀንን ይዞ ሰንብቷል።

ከፍርድ ቤት ውሎ አቶ ልደቱ አያሌው ደግሞ ዋስትና እንዲሰጣቸው የተከራከሩ ሲሆን፤ የእነአቶ እስክንድር ነጋ የዋስትና ጥያቆ ውድቅ ኾኗል። እነአቶ ጃዋር መሐመድ ጉዳያቸውን ለመመልከት ለኅዳር 18 ቀጠሮ ተሰጥቷል። በአርቲስት ሐጫሉ ግድያ የተጠረጠሩ ግለሰቦችም ክስ የተመሠረተባቸው በዚሁ ሳምንት ነው።

የምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሔድ ከሚያስፈልጉኝ ግብዓቶች 90 በመቶው እጄ ላይ አለ ማለቱና በትግራይ ክልል ምርጫው እንደሚካሔድ ያሳወቀው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ቢዝነስ ነክ ከኾኑ ዜናዎች፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮቪድ 19ን በመቋቋም ከ122 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱ የተገለጸበት ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ከተሰሙ የቢዝነስ ዜናዎች ውስጥ የብር ለውጡን ተከትሎ ባንኮች ያልጠበቁት የተቀማጭ ገንዘብ እያገኙ ሲሆን፤ በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ደንበኞች ማፍራት ስለመቻላቸው እየተናገሩ መኾኑ የሚጠቀሱ ናቸው። በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የብር ኖት ተቀይሯል።

እንዲህ ባሉ ሳምንታዊ ክንውኖችና በሌሎች የሳምንቱን ክዋኔዎችን በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የተጠናከሩትን እንሚከተለው ይቀርባል። መልካም ንባብ!

ጠንካራ የጸጥታ ጥበቃ የተካሔደበት ሳምንት

ከጸጥታ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በተከታታይ የተሰሙ ዜናዎች የሳምንቱን ዐቢይ ጉዳይ ነበር። በተለይ የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት አደጋ ለመጣል የተደራጁ ቡድኖች ስለመኖራቸው መንግሥት አስታውቆ፤ ባካሔደው አሰሳ በበዓሉ ላይ ኹከት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ500 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አውሏል። የጦር መሣሪያዎችንም ይዟል።

እነዚህ በዓሉን አስታከው ኹከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉት ግለሰቦች፤ በሕወሓትና በኦነግ ሸኔ ፊት አውራሪነት የተፈጸመመ ስለመኾኑ መንግሥት በይፋ አስታውቋል። ሽብር ለመፍጠር ሲደረግ ነበር የተባለውን ዝግጅት ለመቀልበስ መንግሥት ጥብቅ የጸጥታ ጥበቃ በማካሔዱ፤ የጸጥታ ችግር ሳይከሰት በዓሉ በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል። የአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ የተካሔደው የኢሬቻ በዓል በሰላም ስለመጠናቀቁም አስታውቋል። (ኢዛ)

ሕወሓት ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም በማለት እየቀሰቀሰ ይገኛል

ሕወሓት ከመስከረም 25 በኋላ ሕጋዊ መንግሥት የለም በማለት በተከታታይ በተለያዩ ባለሥልጣናቱ በኩል ሲናገር ሰንብቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚያካሔዱት የጋራ ስብሰባና የ2013 በጀት ዓመት ሥራ መጀመራቸውን ይፋ የሚያደርጉበት ስብሰባ ሕገወጥ ነው በሚል አስታውቋል።

ሕወሓት በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከመስከረም 25 በኋላ ሕጋዊ መንግሥት ስለሌለ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም እስከማለት ደርሷል። ለዓለም አቀፍ መንግሥቱም ደብዳቤ መላኩ ተደምጧል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይፋዊ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ከመስከረም 25 በኋላ ሕጋዊ መንግሥት የለም በማለት ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል ሜዳ ነው እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኃላፊዋ ወይዘሮ ፍረወይኒ ገብረእግዚአብሔር አክለው እንዳመለከቱት ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም ስንል፤ የዐቢይ ቡድን ወዲያውኑ ይወገዳል ማለት አለመኾኑንና ተንገዳግዶ እስኪወድቅ ሕገወጥ ተግባራቱን ይዞ ሊቀጥል ይችላል በማለት ስለመግለጻቸው ተሰምቷል።

የፌዴራል መንግሥቱ ግን ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም የሚሉ አካላትን በጥብቅ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። በዚህ ሳምንትም የፌዴራል ፖሊስ የመከላከያና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት የያዘውን ጠንካራ አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል። (ኢዛ)

በሁለት ሳምንት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀይሯል
- 580 ሺሕ አዲስ የሒሳብ ደብተር ተከፍቷል

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው የብር ምንዛሪ ለውጡ መካሔድ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በአጠቃላይ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ባንክ ገቢ መደረጉን አስታውቋል።

ባለፉት አሥራ አራት ቀናት ብቻ 580 ሺሕ ዜጐች አዲስ የሒሣብ አካውንት ሲከፍቱ፤ ከባንክ ውጭ የነበረም 14 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ መግባቱን አመልክቷል።

ባንኩ ጨምሮ እንደገለጸው 67 ቢሊዮን ብር አዲሱን የብር ኖት በመላ አገሪቱ ባሉ 99.9 በመቶ በሚኾኑ ቅርንጫፎች ማሠራጨቱንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገልጿል። (ኢዛ)

ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሔድ ዝግጁ መኾኑን አስታወቀ
- በትግራይ ምርጫው ይደረጋል ብሏል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ እንዲካሔድ ከወሰነ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቀጥታ ወደ ሥራ መግባቱንና ዝግጅቱን በተመለከተ ይፋዊ መረጃዎች መስጠት የጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ለምርጫ ከሚያስፈልጉት ግብዓቶች ዘጠና በመቶ የሚኾነው በእጁ ያለና ይህንንም ለጋዜጦች መረጃ ከመስጠት ባለፈ የተዘጋጁትን የምርጫ ቁሳቁሶችና የሕትመት ውጤቶች ለጋዜጠኞች አስጐብኝቷል። የቦርዱ አመራሮች እንደገለጹትም ምርጫው በሁሉም ክልሎች እንደሚካሔድና በትግራይ ክልልም እንደሚካሔድ አሳውቆ፤ በክልሉ ለሚካሔደው ምርጫ የተዘጋጁትን የሕትመት ውጤቶች አሳይቷል። (ኢዛ)

የፌዴራል ፖሊስ ትዕይንት በመስቀል አደባባይ

በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በመስቀል አደባባይ የታየው የፌዴራል ፖሊስ ትርዒት ተጠቃሽ የሳምንቱ ዜና ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የተካሔደው የፌዴራል በፖሊስ ትርዒት ፖሊስ ያለውን አቅም ያሳየበት ነበር።

በዚህ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደጉት የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽነር አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም በሚል የሚያቀነቅኑ አካላት እንዲቆጠቡና ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ፖሊስ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መኾኑ ነው።

የፌዴራል ፖሊስ በሁሉም ረገድ እንዲጠናከር ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲሠራ ነበር በማለት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ለውጡ በትክክል እየተተገበረ መኾኑን ተናግረዋል። ትዕይንቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገር ወዳድ ሕዝብ አክባሪና ራሱን ለአገሩና ለሕዝቡ አሳልፎ የሚሰጥ የፌዴራል ሠራዊት ለመገንባት ሲደረግ የነበረው ጥረት ማሳኪያ የኾነ ትርዒት ነውም ብለዋል። (ኢዛ)

የምክር ቤቱ የሕወሓት ተወካዮች ዕጣ ፈንታ
- ተጠባቂው የምክር ቤቶቹ ውሳኔና ሕወሓት

አነጋጋሪ እንደሚኾን በብዙዎች ዘንድ ይጠበቃል ተብሎ የሚታመነውና ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚካሔደው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በሕወሓት ላይ ምን ሊወሰን ይችላል የሚለው ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ከትግራይ ክልል የተወከሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መገኘት አለመገኘታቸው ያልለየ ቢኾንም፤ ሕወሓት ተወካዮቹን እንደማይልክ፣ ስብሰባውም ሕገወጥ ነው የሚል ማስተላለፍ ከጀመረ ሰነባብቷል። በሰኞው ስብሰባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትግራይ ክልልን ወክለው ወንበር ያላቸው አባላት በስብሰባው ባይሳተፉ፤ በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ ኾኗል።

የጉዳዩን አነጋጋሪነት የሚያጐላው በክልሉ የተወከሉት አባላት ስብሰባውን ሕገወጥ ነው ብለው ከቀሩ የምክር ቤት አባልነታቸው የሚያበቃ ሲሆን፤ ከምክር ቤት አባልነታቸው ያገኙ የነበረው ገቢና በአባልነታቸው የተሰጣቸውን የመኖሪያ ቤት እስከማጣት ይደርሳሉ የሚለው አስተያየት እየተሰማ ነው።

ይህም ውሳኔ በተለያየ መንገድ ሊገለጽ የሚችል መኾኑን የገለጹት አፈ ጉባዔ፤ ከውሳኔዎች መካከል በክልሉ ሕገወጥ ምርጫ በመካሔዱ ምርጫ እስኪካሔድ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚለው አንዱ ነው። ከዚህም ሌላ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ያለውን ሁኔታ ወደ ሕጋዊ መስመር ለማምጣት የፌዴራል የጸጥታ ኃይል እንዲገባ ሊወሰን ይችላል የሚል ውሳኔ ሊወሰን እንደሚችል የሚጠቁም ነው። (ኢዛ)

ኮቪድ 19 ያላንበረከከው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 122.4 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል

ከሳምንቱ ዐበይት የቢዝነስ ዜናዎች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2012 በጀት ከ122.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ መገለጹ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበጀት ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ አቅዶ የነበረው 149.7 ቢሊዮን ብር እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ አፈጻጸሙ ግን 82 በመቶ ኾኖ 122.14 ቢሊዮን ገቢ ሊያገኝ እንደቻለ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታን አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል።

በኮቪድ 19 ሳቢያ የዓለም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ክፉኛ በተመቱበት ወቅት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች በተለየ ከፍተኛ የሚባል ገቢ ማግኘት የቻለ መኾኑም ተጠቅሷል። (ኢዛ)

የብር ኖት ለውጡ ለባንኮች ሲሳይ ኾኗል
- በየዕለቱ አዳዲስ ደንበኞች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያስገቡ ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት የብር ኖት ለውጡን ካስጀመረ ሁለት ሳምንታት በላይ የተሻገረ ሲሆን፤ በእነዚህ ሁለት ሳምንታት ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውን እያሳደጉ መኾኑን እየገለጹ ነው። ከሌላው ጊዜ በተለየ አዳዲስ አካውንት የሚከፍቱ ሰዎች መበራከታቸውንም እያሳወቁ ይገኛሉ።

ባሳለፍነው ሳምንት በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ባንኮች ከሰጡት መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው፤ የብር ለውጡን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ መሠረት፤ ገንዘብ ለመለወጥ ወደ ባንክ የሚመጡ ደንበኞች አካውንት መክፈት የሚጠበቅባቸው በመኾኑ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ደንበኞች ማፍራት ችለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በዚህ ጉዳይ መግለጫ ከሰጡት ባንኮች መከከል አንዱ የኾነው ዳሽን ባንክ፤ በ15 ቀን ብቻ ከ25 ሺሕ በላይ አዳዲስ ደንበኞች አካውንት መክፈታቸውንና ከእነዚህ ደንበኞችም ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ነው። አዋሽ ባንክና አቢሲኒያ ባንኮችም በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ደንበኞች እያፈሩ መኾኑን ገልጸዋል።

ከአቢሲኒያ ባንክ የተገኘው መረጃ ደግሞ፤ ከብር ለውጡ መጀመር ወዲህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ከ20 - 25 በመቶ እድገት እያሳየ መኾኑን ገልጿል። ሌሎች ባንኮችም በተመሳሳይ የብር ለውጡ የተቀማጭ ገንዘባቸውን እያሳደገ መኾኑን እያስታወቁ ነው። (ኢዛ)

ሐሰተኛ የነባሩና የአዲሱ ብር ኖቶች እየተያዙ ነው

ባንኮች አዲሱን የብር ኖት በሁሉም ቅርንጫፎች እያደረሱ ሲሆን፣ በዚህ የብር ኖት የቅያሪ ሥራቸው ይኼ ነው የሚባል ችግር ያልገጠማቸው ቢኾንም፤ መጠነኛ ቁጥር ያላቸው ሐሰተኛ የነባሩና የአዲሱ የብር ኖቶችን እያገኙ ስለመኾኑ እያመለከቱ ነው።

ከሰሞኑ በዚህ ጉዳይ መግለጫ የሰጠው ዳሸን ባንክ፤ በአንድ ቅርንጫፉ ሐሰተኛ የብር ኖት ይዞ የቀረበ ሰው መያዙን ገልጾ፤ አልፎ አልፎም ሐሰተኛ ነባሩን የብር ኖት ያጋጠመ መኾኑን ገልጾ፤ ይህ እንደተገኘ ግን ለፖሊስ ማመልከቱን አስታውቋል። ባንኮች ሐሰተኛ የብር ኖቶችን በጥብቅ እየተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በተለይ አዲሱ የብር ኖት በሐሰተኛ መንገድ የማይሠራ በመኾኑ በቀላሉ ሊያዝ እንደሚችልም እየጠቆሙ ነው።

ከዚሁ ሐሰተኛ የብር ኖት ጋር ተያይዞ የመቶና የሁለት መቶ አዲሱ የብር ኖቶችን ይዘው ወደ ባንክ ቀርበው ነበሩ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች፤ በባሕር ዳር ተይዘው ፍርድ ቤት ቀርበው ተፈርዶባቸዋል። ገንዘቡን ያገኙት ከእውቅናቸው ውጭ በመኾኑ ግለሰቦቹ ላይ የአንድ ወር እስራት ተፈርዷል። (ኢዛ)

የምርጫ ቦርድ አባሉ መልቀቂያ አስገቡ
- የማልስማማበት ጉዳይ ስላለ ነው ብለዋል

ከሳምንቱ አነጋጋሪ ዜናዎች ውስጥ አንዱ፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባል የኾኑት ዶክተር ጌታሁን ካሣ የማልስማማባቸው ጉዳዮች ስላሉ በማለት ከቦርዱ ለመልቀቅ መወሰቸውን ማሳወቃቸው ነው።

ዶክተር ጌታሁን ከቦርዱ ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ ከደረሱ በኋላ ይህንኑ የመልቀቂያ ጥያቆያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

የማይስማሙባቸው ጉዳዮች ስላሉ ከቦርዱ ለመልቀቅ ስለመወሰናቸው እንጂ ለመልቀቅ ያበቃቸውን ዝርዝር መረጃ ያልሰጡት ዶክተር ጌታሁን፤ ለመልቀቂያቸው ጥያቄ ተቀባይነት ካገኙ በኋላ ምክንያታቸውን ሊያሳውቁ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል። ስለምክንያታቸው እየተሰራጩ ካሉ ወሬዎች ውስጥ ምርጫ ቦርድ የኢሕአዴግን መፍረስ መፍቀድ የለበትም፤ የኢሕአዴግ መፍረስ አገር ያፈርሳል ብለው ተከራክረው እንደኾነ ተደምጧል።

መልቀቂያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት፤ ሹመቱን ያጸደቀው ምክር ቤቱ በመኾኑ ነው። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን ጨምሮ አባላቱ አምስት መኾናቸው ይታወቃል። (ኢዛ)

አምስት ዞኖች እና አንድ ወረዳ ክልል ለመኾን ወሰኑ

ባሳለፍነው ሳምንት ለየት ባለ ክዋኔው የሚታይ ዜና ኾኖ የሚጠቀሰው በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ አምስት ዞኖች እና አንድ ወረዳ በጋራ ባካሔዱት ስብሰባ ከደቡብ ክልል ወጥተው ራሱን የቻለ ክልል ለመመሥረት ውሳኔ ማሳለፋቸው ነው።

እስካሁን እየቀረቡ ካሉ የክልል እንሁን ጥያቄ ወጣ ባለ መልኩ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት አምስቱ ዞኖች ቤንች ሻካ ዞን፣ ከፋ ዞን፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ሸካ ዞንና ዳውሮ ዞን ናቸው። ከእነዚህ ዞኖች ጋር በኩታ ገጠሙ የኮንታ ልዩ ዞንም ተጨማሪ በመኾን ከደቡብ ክልል ወጥተው የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሚል ራሱን የቻለ ክልል ለመፍጠር በጋራ ባካሔዱት ስብሰባ መወሰናቸው የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ከእነዚህ ዞኖች ውስጥ እንዳንዶቹ በተናጠል ክልል የመኾን ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፤ አሁን ግን በጋራ ክልል ወደ መመሥረት ስምምነት ገብተዋል። (ኢዛ)

የእነ አቶ እስክንድር የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ኾኗል
- ፍርዱ ይፋጠንልን ሲሉ ጠይቀዋል

ከሳምንቱ የፍርድ ቤት ውሎዎች ውስጥ እነ አቶ እስክንድር ነጋ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ መኾኑ አንዱ ነው። እነ አቶ እስክንድር የተመሠረተባቸው ክስ ዋስትና የማያስከለክል በመኾኑ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁ ቢኾንም ጉዳዩን የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጐታል።

እነ አቶ እስክንድር በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ካቀረቡት መቃወሚያቸው ባሻገር፤ የምርጫውን እድል እንዳያጡ ፍርድ ቤቱ ፍርዱን ሳያጓትት በአጭር ጊዜ ያጠናቅልን በማለት ጥያቄ ያቀረቡበት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ከዚህ አቤቱታ አንጻር የተፋጠነ ዳኝነትና ፍትሕ የመስጠት የሕግም የሞራልም ግዴታ አለብን ማለቱ ተዘግቧል። (ኢዛ)

የአቶ ልደቱና የዓቃቤ ሕግ ክርክር

ከአንድ ሳምንት በፊት የተሰጣቸው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ የተደረገባቸው አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ዳግም ጠይቀዋል። ጉዳዩን ለተመለከተው የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ በሰጠው የመከራከሪያ ምላሽ፤ የጸና ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ክስ የተመሠረተባቸው በመኾኑ፤ ይህም ወንጀል 20 ዓመት ፅኑ እስራት ስለሚያስቀጣቸው ዋስትናው መፈቀድ የለበትም ብሏል።

ሰፊ ክርክር የተካሔደበትን የሁለቱን ወገኖች መከራከሪያ የሰማው ፍርድ ቤት በክርክሩ ላይ ብይን ለመስጠት ለማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢዛ)

የእነአቶ ጃዋር መሐመድ ለኅዳር 18 ተቀጠረ

እነአቶ ጃዋር መሐመድ የተመሠረተቸውን ክስ ያደመጡት በዚህ ሳምንት ነበር። ከማረሚያ ቤት የቀረቡት እነአቶ ጃዋር የክስ መዝገቡን ከተደመጠ በኋላ ጉዳዩን ለመመልከት ለኅዳር 18 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በዚህ ሳምንት አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት የቀረቡት በካቴና ታስረውና የማረሚያ ቤት መለያ ልብስ ለብሰው ነው። ጠበቆቻቸው እነ ጃዋር በካቴና መታሰር የለባቸውም፤ የማረሚያ ቤቱንም መለያ ልብስ መልበሳቸው አግባብ አይደለም በሚል አቤት ያሉ ቢኾንም፤ ዓቃቤ ሕግ ለሁሉም የሚሠራ በመኾኑ መልበሳቸው አግባብ ነው ብሏል። ፍርድ ቤቱ በካቴና ታስረዋል በሚለው ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠውም አዝዟል። (ኢዛ)

የታላቁ ኢትዮጵያዊ ሕልፈተ ሕይወት

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ አንድ አሳዛኝ ዜና የሰማንበት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ስለኢትዮጵያ እና ስለ ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሞጋች በመኾን የሚታወቁት ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዜና እረፍት የተሰማበት ሳምንት ነው።

በተወለዱ በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ታዋቂ የጂኦግራፊ መምህር፣ ደራሲ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛም ነበሩ። በእርሳቸው ሞት ብዙኀን ኀዘናቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ በክብር ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸም ዘንድ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም ኾነ ኢትዮጵያን በተመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮችን ማንንም ሳይፈሩ ስሜታቸውን በመግለጽ የሚታወቁት ለዜጐች ሰብአዊ መብት መከበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋም በማቋቋም ፊት አውራሪ የነበሩት ፕሮፌሠር መስፍን፤ ዜና እረፍታቸው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ምሁራንና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ኀዘናቸውን በተለያዩ ሁኔታዎች እየገለጹ ነው።

ፕሮፌሰር መስፍን እንደ አገር ምልክት የሚቆጠሩ ናቸውና በስማቸው ማስታወሻ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባና ሥርዓተ ቀብራቸውም እንደ አንድ ታላቅ ዜጋ በክብር እንዲፈጸም እየተጠየቀ ነው።

ከቀናት በኋላ ይፈጸማል ተብሎ የሚጠበቀው የፕሮፌሠር ሥርዓተ ቀብርን ለማስፈጸም የተዋቀረው ኮሚቴ፤ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተነጋገረ ሲሆን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተወካዮችም ከዚሁ ኮሚቴ ጋር የመከረ ስለመኾኑ ተገልጿል። ከቤት ሠራተኛቸው የተላለፈ ነው በተባለ የኮሮና ቫይረስ ሕይወታቸው ያለፈው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በኢትዮጵያ ታሪክ ሁሌም የሚታወሱ ስለመኾናቸው ምስክርነት እየተሰጠ ነው። (ኢዛ)

በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩት ላይ ክስ ተመሠረተ

በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የነበሩት አራት ተጠርጣሪዎች ላይ መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው አራት ተጠርጣሪዎች ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ፣ አብዲ ዓለማየሁ፣ ላምሮት ከማል የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

ግለሰቦቹ የተከሰሱት የሽብር ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ጭምር ነው። በክሱ መዝገብ ግድያው የተካሔደበትን ዝርዝር ሒደት ያካተተ ሲሆን፤ ተከሳሾች ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

በዕለቱ ዳኞች ተሟልተው ባለመቅረባቸው ምክንያት ክሱን ለመስማት ለመስከረም 26 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!