አሳታሚዎቹ 300 ሺህ ብር መክፈል አለባቸው

"ግፊቱ ቢበዛብንም ሀገራችንን ለቀን አንወጣም" ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

"የሚመጣብንን ለመቀበል ዝግጁ ነን" ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና

Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም. July 4, 2008)፦ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ታስረው ድርጅታቸው እንዲፈርስና በገደብ እንዲቀጡ የተወሰነባቸው አራት የጋዜጣ ድርጅቶች ውሳኔው ከተሰጠ ከ11 ወራት በኋላ በቅጣት የተወሰነባቸው ወደ 300 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመንግሥት እንዲያስገቡ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ምንጮች ገለፁ።

 

በኢ/ር ኃይሉ ሻውል የክስ መዝገብ ተከሰው የነበሩት ሲሳይ አሳታሚ፣ ሰርካለም አሳታሚ፣ ፋሲል አሳታሚ እና ዘካርያስ አሳታሚ - አሳታሚዎቹ፣ ዋና አዘጋጆቹና ም/ዋና አዘጋጆች ታስረው የነበረ ሲሆን፤ በብይን ወቅት ሕጉ የሚለው፣ በፕሬስ ሥራ ላይ አሳታሚው ሳይሆን ተጠያቂ የሚሆነው ዋና አዘጋጁ በመሆኑ አሳታሚዎቹ፣ አዘጋጆቹና ያልታሰሩባቸው ጋዜጦች ብቻ ም/ዋና አዘጋጆች እንዲቀሩ ሲደረግ፣ አሳታሚዎችና ም/ዋና አዘጋጆች በነፃ ተሰናብተዋል። በተጨማሪም ድርጅቶቹ ብቻቸውን እንደ አንድ የሕግ ሰውነት ተቆጥረው ተከሳሽ ሆነው ቀጥሏል።

 

በመጨረሻም ውሳኔ ሲሰጥ ዋና አዘጋጆቹ ዕድሜ ልክ ሲፈረድባቸው፣ ድርጅቶቹ እንዲፈርሱ ሲወሰን፣ በተጨማሪም የኢትኦጵ ጋዜጣ አሳታሚ የነበረው ሲሳይ አሳታሚ 100 ሺህ ብር፣ የአስኳል፣ የምኒሊክ እና የሳተናው አሳታሚ የሆነው ሰርካለም አሳታሚ 120 ሺህ ብር፣ የአዲስ ዜና ጋዜጣ አሳታሚ የሆነው ፋሲል አሳታሚ 15 ሺህ ብር እና የነፃነት ጋዜጣ አሳታሚ የነበረው ዘካርያስ አሳታሚ 60 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ከ11 ወራት በፊት ተወስኖ ነበር።

 

ከትናንት በስቲያ ከፍርድ ቤት የወጣው ውሳኔ እንደሚያሳየው፤ ድርጅቶቹ የተወሰነባቸውን የገንዘብ ቅጣት ለመንግሥት ያላስገቡ በመሆኑ፤ ፖሊስ ተከታትሎ እንዲያስፈፅም እስከዚያው የማይፈፀም ከሆነ አሳታሚዎቹ ታህሳስ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ያስረዱ የሚል ትዕዛዝ ያዘለ መጥሪያ ያወጣባቸው መሆኑ ታውቋል።

 

ትዕዛዙን በሚመለከት ያለውን አስተያየት እንዲሰጠን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ያነጋገርን ሲሆን፣ ማናቸውንም የሚመጣባቸውን ግፍም ሆነ መከራ ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ከሀገራችን ጥለን እንዲወጡ ከዲፕሎማቶች ጭምር ከፍተኛ ግፊት ሲደረግባቸው መሰንበቱን ጠቁሞ፤ ግፊቱ በየጊዜው እየጨመረ ቢመጣም ሀገራችንን ጥለን ለመውጣት ምንም አይነት የሞራል ዝግጅት የለንም ሲል አስተያየቱን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጿል።

 

የሲሳይ አሳታሚ ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ደግሞ በ1997 ዓ.ም. የደረሰባቸውን ኪሳራ በበቀል ለመወጣት በገዛ ሀገራችን ሃሳባችሁን በነፃነት መግለጽ አትችሉም ተብለንና ሥራ እንዳንሠራ ታግደን ከተቀመጥን ከዓመት በኋላ መቀጫ ክፈሉ ተብሎ መጠየቅ ሆን ተብሎ ሀገር ጥለን እንድንሰደድ የታለመ ይመስላል። ነገር ግን የሚመጣብንን ለመቀበል ዝግጁ ነን ሲል አስተያየቱን ለኢትዮጵያ ዛሬ ሰጥቷል።

 

አንድ በሰሜን አሜሪካ በስደት የሚኖር ጋዜጠኛ በነፃው ፕሬስ አባላት ላይ የሚደረገውን ከፍተኛ አፈናና እንግልት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች ምንም አይነት የሚገባውን ትኩረት አለመስጠታቸው እንዳሳዘነው ገልጾ፤ አሁንም ቢሆን እነኝህ የጋዜጣ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች ለሀገራቸው የሃሳብ ነፃነት መጎልበት ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!