Ethiopia Zare's weekly news digest, week 6th, 2013 Ethiopian calendar

ከጥቅምት 9 - 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ስድስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጥቅምት 9 - ጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት ዐበይት ጉዳይ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከወደ አሜሪካ የተሰማው አወዛጋቢ ዜና ለኢትየጵያውያን የሚጐረብጥ ግን የሚያጀግን ነው። ከነጩ ቤተ መንግሥት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ አንደበት የወጡት ቃላቶች የድፍን ኢትዮጵያውያንን ጆሮ የያዘ በእጅጉም ተቃውሞ ያስነሳ ኾኗል። ግብጽ የህዳሴውን ግድብ ታፈነዳለች የሚል አንደምታ ያለው ቃላቸው በአዲሱ ግድብ ዙሪያ አዲስ መነጋገሪያ አጀንዳ ወደመኾን ተሸጋግሯል። በአገርም በውጭም ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን እያሰሙበት ነው።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር አደገኛ የሚባልም ኾኖ በመንግሥት መግለጫ የተሰጠበት ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ቀዳሚ አጀንዳ ለመኾን በቅቷል። በጉዳዩ ላይ መንግሥት አቋሙን ያስታወቀ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደርን አስጠርተው ማብራሪያ እስከመጠየቅ የደረሱት የሁኔታውን ክብደት አመላክቷል።

ከዚህ ወቅታዊ አጀንዳ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ቀርበው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ማብራሪያም ከሳምንቱ ቀዳሚ ዜናዎች መካከል የሚጠቀስ ነው። በርከት ባሉ አገራዊ ጉዳዮች በይበልጥም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት አሳዛኝ የኾነውና የአገሪቱን የፖለቲካ ጉዳይ አሁንም እንቆቅልሽ እያደረገው ያለውና በደቡብ ክልል በጉራ ፈርዳ የተፈጸመው ማንነት ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ግድያ ነው። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በንጹኀን ላይ በተፈጸመው ግድያ በተመሳሳይ የሚታየው የጉራ ፈርዳ ግድያ እንደተለመደው ያልታወቁ ታጣቂዎች የተፈጸመ ነው የተባለ ሲሆን፤ 13 ሰዎች ተገደሉ በሚል የጀመረው ዜና በሳምንቱ መጨረሻ የንጹኀን ሟቾች ቁጥር ላይ ከ46 በላይ ደርሷል። በዚሁ ጉዳይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ያሰፈሩት ጽሑፍ ጠንከር ያለ ኾኖ ወጥቷል። ይህ የጉራ ፈርዳው ግድያ ብዙ ተቃውሞ እያስነሳ ሲሆን፤ እንደ አብን ያሉ ፓርቲዎች ጥቃቱን በመቃወም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የፌዴራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል መንግሥት ውዝግብ ቀጥሏል። የገንዘብ ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል ለቀበሌ፣ ለወረዳና ለከተማ አስተዳደሮች የበጀት ደጐማ ለማድረግ የሚያስችለውን ቀመር እየጠቀለልኩ ነው ሲል፤ የትግራይ ክልል ደግሞ ለትግራይ ገበሬዎች የሚሰጥን የሴፍቲ ኔት ገንዘብ የፌዴራል መንግሥት ከለከለ በማለት መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል። ከስፖርት ጋር ተያይዞም አወዛጋቢ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ባሳለፍነው ሳምንት ዐበይት የቢዝነስና ኢኮኖሚ ዜና ኾኖ የሚጠቀሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወቅታዊውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ አቋም ያብራሩበትና የተነተኑበት ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት 6.1 በመቶ መኾኑ የተገለጸበት ነው። የአገሪቱ ባንኮች በሦስት ወር 105 ቢሊዮን ብር ቁጠባ ማሰባሰባቸውና ይህ ውጤት በኢንዱስትሪው ታሪክ ያልተመዘገበ መኾኑ ተገልጿል።

የአገሪቱ ትልቁ ባንክ የኾነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ አዲስ ሊደራጅ ስለመኾኑ በይፋ መነገሩና ይደረጋል የተባለው ለውጥ ሥር ነቀል እንዲኾን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እንዲህ ካሉት የሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮች የተመረጡት እንደሚከተለው በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ተቀናብሮ ቀርቧል። መልካም ንባብ!

አሰቃቂው ግድያ ዘመቻ ከመተከል ወደ ጉራ ፈርዳ

በኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያ የሚታየው የጸጥታ ችግር አሁንም መቋጫ ያልተገኘለት ኾኗል። በቀደሙት ሳምንታት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንጹኀን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ኀዘኑ ሳይወጣ አሁን ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ያልታወቁ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ ውስጥ ተፈጽሟል።

ከሰሞኑ ከተሰማው ዜና መረዳት እንደተቻለው በቤኒሻንጉል ንጹኀን ዜጎችን ገድለዋል የተባሉት ታጣቂዎች ይዘዋቸው የነበሩትን ቀበሌዎች ለማስለቀቅ፤ መከላከያ ሠራዊቱ ከእነዚህ ታጣቂዎች ጋር በመታኮስ ቀበሌዎቹን ነፃ አድርጎ መቆጣጠር ችሏል። በዚያ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም ታጥቀው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ሥልጠና መሰጠትም ተጀምሯል። አሁን በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ተብሏል።

ይህ ዜና እየተሰማ ባለበት ባሳለፍነው ሳምንት ላይ ግን ሌላ ተመሳሳይ አሰቃቂ ዜና ከጉራ ፈርዳ ተሰምቷል። ይህም ያልታወቁ ታጣቂዎች የተባሉ ግለሰቦች እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ከ46 በላይ ንጹኀንን መግደላቸው ነው። ንብረት መውደሙና መፈናቀልንም ያስከተለ ኾኗል።

ሆን ተብሎ በተደራጀ ሁኔታ የተፈጸመ ነው የተባለው ድርጊት ፈጻሚዎች፤ ከአንዳንድ የአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በቅንጅት የተተገበረ ስለመኾኑ እየተነገረ ነው።

መንግሥትም በዚህ አሰቃቂ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላት በቁጥጥር ሥር እያዋለ ሲሆን፣ ሁኔታውን ለማረጋጋትና ያለውን ችግር ዓይቶ ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ የመከላከያ ኤታማዦር ሹምን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ ጉራ ፈርዳ ያቀኑት በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎም የልዑካን ቡድኑ አባል የነበሩ ሲሆን፤ ከጉራ ፈርዳ ነዋሪዎች ጋር ስለመምከራቸው ተገልጿል።

ይህ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው የተባለው ጥቃት ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ውግዘት እየደረሰበት ነው። 21 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ተብሏል። በሌሎች የአካባቢው አመራሮች ላይ ማጣራት ተደርጐ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።

አቶ ታገሰ እንደገለጹት ድርጊቱ በሕዝቦች መካከል የተፈጸመ ጥቃት ሳይኾን፤ በጥቂት ሕገወጥ ቡድኖች የተፈጸመ መኾኑን አመልክተዋል። አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) በበኩሉ የድርጊቱን አሳዛኝነት ጠቅሶ በይፋ ለማውገዝም ጥሪ ያስተላለፈበትን መግለጫ አውጥቷል። (ኢዛ)

የአዛውንቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አንደበትና የኢትዮጵያ ምላሽ

አወዛጋቢው አዛውንቱ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ሰሞነኛ አንደበት በኢትዮጵያውያን ዘንድ በበጐ ያልታየ፤ ይልቁኑም ቁጣን የቀሰቀሰ ኾኖ እየተወገዙበት ነው። በእርግጥም ይህንን ንግግራቸውን እንደ ኢትዮጵያዊ ኾኖ ለተመለከተው ሁሉ፤ እኒህን አዛውንት ማውገዙ፣ እንዲሁም ምን አግብቷቸው ነው ማለቱ አይቀርም። ወትሮም ቢኾን በህዳሴ ግድብ ላይ የተንሻፈፈ አመለካከት ይዘው የቆዩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ አንደበታቸውን አሰምተዋል።

ግብጽ የሕልውናዋ ጉዳይ ስለኾነ የህዳሴ ግድቡን ማፈንዳት እንደምትችል የገለጹበት መንገድ፤ ጦርነት ቀስቃሽ ጭምር በመኾኑ፤ ንግግራቸው ከተሰማ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥትና በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።

መንግሥት በአንድነት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን 24 ሰዓት እንዲጠብቁ ሲያሳስብ፤ ኢትዮጵያውያን ለማንም ያልተንበረከኩና አሁንም የማይንበረከኩ መኾኑንም ጠቅሷል።

ነገሩ የዋዛ አይደለምና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው መቀመጫቸውን አዳስ አበባ ያደረጉትን የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነርን ቢሯቸው በማስጠራት በትራምፕ ንግግር ላይ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው አምባሳደሩን ቢሯቸው ጠርተው ማብራሪያ ይሰጠን ብለው ከመጠየቃቸውም ባሻገር፤ የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ ለአምባሳደሩ አስረድተዋል።

በየትኛውም መስፈርት የትራምፕ ንግግር ተቀባይነት የሌለው መኾኑን የገለጹት አቶ ገዱ፤ ንግግሩ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ጦርነት እንዲጫር የሻተ ነው እስከማለት ደርሰዋል። በእርግጥም እንዲህ ያለው አንደበት ግብጽ ግድቡን ትደርምስ ከማለት ሌላ ትርጉም የሌለው መኾኑንም ብዙዎች እየገለጹ ነው። በመንግሥት ደረጃ የወጡ መግለጫዎች በግልጽ ያስቀመጡት፤ የትራምፕ ንግግር ከአንድ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት የማይጠበቅ አጉል ንግግር ነው።

በመንግሥት ደረጃ ግን የህዳሴ ግድብ የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ ኾነው ግድቡን እንዲጨርሱ አሁንም በንቃት እንዲጠብቁ የሚያሳስብ ነው።

አወዛጋቢው ንግግር አሁን እየተገለጸ ባለው ሁኔታ ብቻ የሚገደብ እንደማይኾንና ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያላትን አቋም የበለጠ እንድታጠናክር የሚያስገድዳት ይኾናል። የኢትዮጵያውያን ስሜትም ይህንኑ የሚያሳይ ነው። በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በትራምፕ ላይ ተቃውሞ ለማሰማት እየተዘጋጁ ነው። የትራምፕ ንግግር ውኃ የማይቋጥር አጉል ንግግር ስለመኾኑ የውጭ ተቋማትም እያመላከቱ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን አስተያየት ወደ ጐን በመተው የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ የአፍሪካ ሕብረት በጀመረው የድርድር ሒደት መቀጠል የሚኖርበት መኾኑንና የአሜሪካንን ጣልቃ ገብነት የተቸ ኾኗል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ ሴናተሮችም በየፊናቸው የትራምፕን አቋም ሚዛናዊ አለመኾን በመጥቀስ የፕሬዝዳንቱን ንግግር እያወገዙ ነው። (ኢዛ)

ግብጾች ትራምፕን ሰምተው ምንም አያደርጉም

የሰሞኑን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር ተከትሎ ማብራሪያ ከሰጡት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ዲና ሙፍቲ፤ የህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ያለ ማንም እርዳታና ድጋፍ የተገነባ፤ ከፍጻሜ ሊደርስ የተቃረበ የማንነት ፕሮጀክት መኾኑን በመግለጽ፤ የህዳሴ ግድቡንም ኾነ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መዳፈር ለማንም የማይጠቅም ስለመኾኑ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚሰጥ ማንኛውም አፍራሽ ሐሳብ ለማንም የማይጠቅም፣ ሉዓላዊነትን የሚጋፋና የሕዝቦችን ነፃነትና የመልማት ፍላጎት የተጋፋ ነው በማለት የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግርን ኮንነዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት አልምታ የመጠቀም ፍላጎቷንና መብቷን ማንም ሊነጥቃት አይችልም፤ ሥጋትም የለባትም የሚሉት ዲና ሙፍቲ፤ ኢትየጵያ ለድርድር፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት እንደ ከዚህ ቀደሙ ትሠራለች፤ ከዚህ ውጪ በህዳሴ ግድቡ ላይ በማስፈራሪያና በዛቻ የሚመጣ ለውጥ እንደማያመጣ አመልክተዋል።

የህዳሴው ግድብ ላይ ከስምምነት ሊደረስባቸው የሚገቡ የቀሩ ሐሳቦች በድርድርና በሰላማዊ የዲፕሎማሲ ሥራ መፍትሔ ያገኛሉ የሚል እምነት ያላቸው ቃል አቀባዩ፤ ሁሉን ተጠቃሚ ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ድርደር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ አሁንም አቋሟ መኾኑን አረጋግጠዋል። ይህም ጥረት የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካዊ መፍትሔ እንዲያገኙ የማድረግ ጭምር ነው።

“ግብጻውያን የፕሬዝዳንት ትራምፕን አስተያየት ተቀብለው የእብደት ተግባር ይሠራሉ ብዬ አላምንም” የሚሉት አምባሳደር ዲና፤ ከግብጽ አንጻር ሊያደርጉ ይገባል ብለው ከገለጹት ውስጥ፤ ግብጾች የሚያዋጣቸው የሰላም ስምምነት ብቻ መኾኑን ነው። ግብጾች የሰላም ስምምነት አዋጫቸው መኾኑን ከዶናልድ ትራምፕ በተሻለ ይረዳሉ ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ወደ ግጭት የሚያስገባቸውን መንገድ አይመርጡም የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር የኢትዮጵያን እና የአሜሪካንን የቆየውን መልካም ግንኙነት ሊያሻክረው እንደሚችልም ግን ሳይጠቁሙ አላለፉም።

የግድቡ ሥራ ፍጻሜ እክል እንዲገጥመው እንቅልፍ አጥተው የሚሠሩ ከውስጥም ከውጭም ያሉ ባንዳዎችን ተቋቁሞ በአገር ጉዳይ ላይ የአንድነት ከፍታ ማሳየት እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም “ለችግሮች እጅ የማንሰጥ ጽኑ ሕዝብ መኾናችንን፤ ግድባችንን አጠናቀን ማሳየት ይኖርብናል” በማለት በሰሞናዊ ጉዳይ ላይ የአገራቸውን አቋም እና መኾን ይኖርበታል ያሉትን ገልጸዋል። (ኢዛ)

የጉራ ፈርዳው ጥቃትና የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አነጋጋሪ ምልከታ

ከሰሞኑ በጉራ ፈርዳ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን በማስመልከት፤ እንዲህ ያለውን ጥቃት የሚያወግዙ በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሰሞኑ ጠንከር ያለ ሐሳባቸውን ካሰሙት መካከል አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተጠቃሽ ናቸው።

አቶ ገዱ በፌስቡክ ገጻቸው ያሰፈሩትን ጽሑፍ የጀመሩት፤ “የአማራ ሕዝብ ለፍትሕ፣ ለነፃነት እና ለአብሮነት ሲታገል ቢኖርም፤ እስካሁን በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ ፍትሕና የሕግ የበላይነት ሰፍኖ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገራችን ክፍል በሰላም፣ በነፃነት እና በደስታ መኖር የሚችሉባት አገር ባለቤት መኾን አልተቻለም።” በማለት ነው።

አያይዘውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግፍና መከራው እየተጠናከረ በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፉና በገፍ መፈናቀሉ ተስፋፍቶ ስለመቀጠሉ አመላክተዋል። ይህንን ሁኔታ ለመረዳት ብዙም ሩቅ ሳንሔድ፤ ይህንን አንድ ዓመት ብቻ ወስዶ አዝማሚያውን መገምገሙ ብቻ በቂ ስለመኾኑ በማተት፤ ከጥቅምት እስከ ጥቅምት ያለው አንድ ዓመት ብቻ በግልጽ የሚነግረን ግፍና መከራው ተጠናክሮ መቀጠሉን በዚሁ የፌስቡክ ገጻቸው አመልክተዋል።

“ማለቂያ የሌለው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በገፍ መፈናቀል፣ የዘመናት የልፋት ውጤት የኾነ ንብረት ውድመት የየሳምንቱ መርዶ መስማት የተለመደ እየኾነ መጥቷል።” ያሉት አቶ ገዱ፤ ስለኾነም ነገሩን ላለማባባስ ሲባል በዝምታ ማለፉ የሚጎዳ መኾኑን በተግባር እያየነው በመኾኑ፤ ያገባናል ባዮች በሙሉ ልንነጋገርበት ይገባል ብለዋል።

“ይህ በአማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈጸመ ያለው በማንም ሕዝብ ሳይኾን በጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች ሴራ መኾኑን በመገንዘብ፤ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጋርነት የሚያሰልፍ የትግል አቅጣጫ ነድፎና ስትራቴጂያዊ ግብ ወስኖ በጋራ መንቀሳቀስ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።” ያሉት አቶ ገዱ፤ የመልእክታቸውን መቋጫ ያደረጉት በክስተት ላይ ያነጣጠረ ጩኸት እልቃሻ ከማድረግ የዘለለ ጥቅም የሌለው መኾኑን በመጥቀስ ነው። (ኢዛ)

6.1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ

ከሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮች ውስጥ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ የሰጡበት ክንውን ይጠቀሳል። በዚህ የፓርላማ ቆይታቸው ሰፋ ያለውን ጊዜ የወሰደው ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ማብራሪያ ነበር።

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ኮቪድም ኖሮ በተሻለ አፈጻጸም 2012 መጠናቀቁን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአገሪቱ ዓመታዊ ኢኮኖሚ እድገት 6.1 በመቶ መኾኑን ይፋ ያደረጉበትም ነው። እንደ መንግሥት የ2012 የኢኮኖሚ እድገት ዘጠኝ በመቶ እንዲኾን ታቅዶ የነበረ ቢኾንም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝንና ተያያዥ ጉዳዮች፤ የእድገት መጠኑን በተወሰነ ደረጃ ዝቅ አድርጐታል። ይህም ቢኾን ግን ከአብዛኞቹ አገሮች የኢኮኖሚ እድገት መጠን አንጻር ሲታይ፤ የኢትዮጵያ በእጅጉ የተሻለ ስለመኾኑ ያመላከተበት ነው።

በተለይ በፋይናንስ ዘርፉ አገሪቷ ከ10 በመቶ በላይ እድገት ማሳየቷን፤ በሌሎች ዘርፎችም ቢኾን እድገት መታየቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ አመልክቷል። በወጪ ንግድ ዘርፍ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ብልጫ ያለው አፈጻጸም መገኘቱ፤ በተለይም ወድቆ የነበረው የወርቅ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱንም ጠቅሰዋል። (ኢዛ)

የትግራይ ክልል 285 ሚሊዮን ብር ተከለከልኩ በማለት መንግሥትን ከሰሰ

የፌዴራል መንግሥት በሕገወጥ ምርጫ ለተመሠረተው የትግራይ ክልል ምክር ቤት እውቅና መንሳቱንና የበጀት ድጐማ የማያደርግ መኾኑን ካሳወቀ ሰነባብቷል። የፌዴራል መንግሥት ይህንን ውሳኔ ቢያስተላልፍም፤ አስፈላጊ የፋይናንስ አቅርቦቶችን በወረዳ፣ በቀበሌና በከተማ አስተዳደር በኩል ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መኾኑንና ይህም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ያስታወቀው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

በአንጻሩ ደግሞ የትግራይ ክልል ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ የፌዴራሉ መንግሥት ለትግራይ አርሶ አደሮች የሴፍቲ ኔት ወይም የምግብ ለሥራ ፕሮግራም በጀት የሚውል 285 ሚሊዮን ብር ከለከለ ብሏል።

እንደ ትግራይ ክልል መግለጫ ለሴፍቲ ኔት የሚውለው በጀት መከልከሉ አግባብ ያለመኾኑን በመጥቀስ፤ የፌዴራል መንግሥትን ኮንኗል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ በሰጠው መግለጫ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ መንግሥት በቀጥታ የሚሰጥ ምንም ዐይነት የበጀት ድጋፍ እንደማይኖር አስታውቆ፤ የድጎማ በጀቱ ለትግራይ ወረዳዎች፣ ከተማዎችና ቀበሌዎች የሚሰጥበትን አሠራር ማዘጋጀቱንና በቅርቡ ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቅ መኾኑን አሳውቋል።

በተያያዘ ዜና የትግራይ ክልል ልዩ የኮማንዶ ኃይል ለሁለተኛ ጊዜ ያስመረቀ ሲሆን፣ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “የትግራይ ሕዝብ እንዲራብ ፌደራሉ መንግሥት ከአንበጣ ጋር ወግኖ እየሠራ ነው” ሲሉ አስገራሚ የተባለ ንግግር አድርገዋል። (ኢዛ)

በአንድ ወር በባንክ በኩል 2.8 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መኪኖችና መኖሪያ ቤቶች ተሸጡ

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አዲሱን የብር ለውጥ ተከትሎ የሽያጭ ውል የገንዘብ ቅብብሎሽ በባንክ በኩል ብቻ እንዲፈጸም ከተወሰነ ወዲህ፤ ከመስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በአንድ ወር ውስጥ 2.86 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የመኪናና የመኖሪያ ቤት ግብይት መከናወኑን አስታውቋል።

በኤጀንሲው መረጃ መሠረት በተጠቀሰው ጊዜ 2,797 የመኪኖች ሽያጭ ተፈጽሟል። ይህ በባንክ በኩል የተፈጸመው የ2,797 የመኪኖች ሽያጭ 1.27 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ነው። በተመሳሳይ በባንክ በኩል በሚፈጸም ግብይት 602 የመኖሪያ ቤቶች 1.5 ቢሊዮን ብር ሽያጭ የተፈጸመ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከሁለቱ የሽያጭ ዐይነቶች 2.86 ቢሊዮን ብር በባንክ በኩል ግብይቱ መፈጸሙን አስታውቋል።

አዲሱን የብር ለውጥ ተከትሎ በባንክ የተደረገው የገንዘብ ቅብብል ትክክለኛና ሥርዓትን የጠበቀ ከመኾኑም በላይ፤ በቀጣይም ሕብረተሰቡ በባንከ የመጠቀም ልምድ እንዲያዳብር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ኤጀንሲው አስታውቋል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ አዲስ ተደራጅቶ ሊሠራ ነው

ብዙ ችግሮች የሚታዩበትና ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል የተባለው ትልቁ የአገሪቱ ባንክ በመኾን የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደ አዲስ ለማደራጀት መንግሥት ወስኖ ወደ ሥራ መገባቱ ተገለጸ።

የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ ገበያ ከ60 በመቶ በላይ የያዘውና በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደ አዲስ ማደራጀት ያስፈለገበት ዋና ምክንያት፤ ለዓመታት የቆየውን ችግሩን ለመፍታትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲኾን ለማስቻል ነው።

ባንኩን እንደ አዲስ ለማዋቀር እስካሁን ያሉትን ችግሮችን በመለየትና ምን ዐይነት አደረጃጀት ይያዝ የሚለውን አጠቃላይ ጥረትና የባንኩን አዲሱን አደረጃጀት ለማዘጋጀት የውጭ ኩባንያዎች እንዲሠሩት በመወሰኑ፤ ለሥራው ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጐ፤ ከ40 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነዱን ገዝተዋል።

በዚሁ መሠረት አሸናፊው ድርጅት አዲሱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አደረጃጀት በመቅረጽ፤ አዲሱ መዋቅር በመንግሥት ከጸደቀ፤ በዚህ ዓመት ይተገበራል ተብሏል። ይህ የታሰበው ለውጥ አጠቃላይ የባንኩን መዋቅር አሠራር የሚለውጥ ሲሆን፤ ብዙ ማስተካከያዎችን የሚያመጣ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለይ ከ600 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች በማበደር ይህንን ገንዘብ ለማስመለስ በመቸገሩ፤ መንግሥት የእነዚህን ዕዳዎች እንዲሰረዝ በማድረግ ባንኩን ከውድቀት ማዳን ስለመቻሉ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፓርላማ መግለጻቸው ይታወሳል።

አሁን ባንኩ በአዲስ እንዲደራጅ ሲደረግም፤ እንዲህ ያሉ የብድር አሰጣጦችን በማስቀረት እንዲሠራ ለማድረግ ጭምር የታሰበ ነው ተብሏል። አወቃቀሩ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ እንዲኾን የተፈለገበትም በተለይ ከብድር አሰጣጥ ጋር ያሉ ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ ታስቦ ስለመኾኑ ተገልጿል። (ኢዛ)

ባንኮች ባለፉት ሦስት ወራት 500 በመቶ እድገት ያለው ተቀማጭ ገንዘብ ሰበሰቡ
በሦስት ወር 105 ቢሊዮን ብር ሰብስበዋል

በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ የሚገኙት 16ቱ የግል ባንኮችና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎች ሦስት ወራት ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በአገሪቱ የባንክ ታሪክ እስካሁን ያልተመዘገበ እድገት የታየበት መኾኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ በሦስት ወር ውስጥ 105.1 ቢሊዮን ብር አዲስ ቁጠባ ሰብስበዋል።

ባንኮቹ የሰበሰቡት ይህ የቁጠባ ገንዘብ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ500 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ እስካሁን በዚህን ያህል ደረጃ የቁጠባ ሒሳብ የተከፈተበት ወቅት እንደሌለም ተጠቅሷል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ባንኮች በዚህን ያህል ደረጃ የቁጠባ ሒሳብ ያሰባሰቡበት ዋነኛ ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዕለቱ ከባንክ የሚወጣውን የጥሬ ገንዘብ መጠን ገደብ እንዲበጅለት ማድረጉ እና ማንኛውም ግለሰብም ኾነ ድርጅት ከባንክ ውጭ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ መያዝ እንደማይችል በመደንገጉ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ገለጻ፤ ባንኩ ካወጣው ከእነዚህ አስገዳጅ መመሪያዎች ሥራ ላይ መዋል ሌላ፤ በቅርቡ የተደረገው የብር ኖት ለውጥ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በእጅጉ እንዲጨምር አስችሏል።

የባንኮች የተቀማጭ ገንዘባቸው መጨመሩ፤ የሚሰጡትን የብድር መጠን ከማሳደጉም በላይ፤ በተለይ ባለፈው ዓመት ባንኮች አጋጥሟቸው የነበረውን የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲቀርፉ እንደሚያግዝም ዶክተር ይናገር አመልክተዋል። (ኢዛ)

ባለፉት 15 ወራት ባንኮች ካበደሩት ገንዘብ 85 በመቶውን የግል ዘርፉ ወስዷል
በ2012 ዓ.ም. 279 ቢሊዮን ብር ብድር ሲሰጡ፤ በሩብ ዓመቱ 55 ቢሊዮን ብር ሰጥተዋል

ከሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ በ2012 በጀት ዓመት የአገሪቱ ባንኮች ለብድር ካዋሉት 279 ቢሊዮን ብር ውስጥ 85 በመቶው ለግል ዘርፉ የተሰጠ መኾኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ እንዳስታወቁት እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ ለብድር ከዋለው ብድር ውስጥ 85 በመቶው ለግል ዘርፉ የተሰጠ መኾኑን አስታውቀዋል።

ሰሞኑን የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ሪፖርት ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ የአገሪቱ ባንኮች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት (ሦስት ወር) 55 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር የሰጡ ሲሆን፣ ከዚህ ብድር ውስጥ 85.3 በመቶው ለግል ዘርፍ የተሰጠ ነው ብለዋል።

ይህ አካሔድ እስካሁን ከባንኮች ብድር ውስጥ አብዛኛውን መንግሥት ይወስዳል የሚለውን አስተያየት ያስቀረና አብዛኛው ብድር ለግል ዘርፉ እየተሰጠ ስለመኾኑ የሚያመላክት እንደኾነ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ በየፊናቸው በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል።

ሰሞኑን በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት አፈጻጸም ዙሪያ ከተሰጡ አኀዛዊ መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው፤ በ2012 በጀት ዓመት 18ቱ የአገሪቱ ባንኮች ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!