ከተለየኸን … ደህና ሁን!
ኩችዬ - ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. (April 20, 2009) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ለጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ ሙት መሆኔን ሀገር ያውቃል። የእርሱ ሙዚቃ ዳግም ላይሰማ ይታገዳል ያሉኝ ይመስል ከሰሞኑ መልሼ መልሼ የማዳምጠው እሱኑ ብቻ ነበር።
እንደኔ ሙዚቃን የሚያሻምድ ሰው ጥላሁን ለትውልዳችን የተሰጠ ልዩ በረከት፤ የዕምነታችንና የሁሉም ዓይነት ምኞታችን መገለጫ ነው ብሎ ከደመደመ ቆይቷል። አጋነንክ የሚል ከመጣም እስከመጨረሻው እሞግተዋለሁ እንጂ እንደ ሉሲና እንደ አክሱም ሐውልት ብሔራዊ ቅርሳችን ነው ባይ ነኝ። ለዚህ ይመስለኛል የጥላሁን ዜና-ዕረፍት እንደተሰማ ሚሊዮኖች በመብረቅ የተመታ ያህል ባሉበት የደረቁት፣ ያነቡትና የተከዙት።
የኔው ድንጋጤና ኀዘን ግን ወደ ፍስኀና ወደ ምስጋና ሲለወጥ ፋታ አልፈጀበትም። ልማድ ሆኖብኝ ሲከፋኝና ፍቅር-ፍቅር ሲለኝ ኮምፒዩተሬ ላይ ዘወትር በተጠንቀቅ የሚጠብቀውን የጥሌን ሙዚቃ ነው ጠቅ የማደርገው። ዛሬም ያንኑ አደረግሁና ወደ ትራክ ስድስት መራሁት። የሙዚቃው አጀማመር ገና ከመነሻው ምድርን ቃጤ የሚያደርግ ዓይነት ነው። በጣም የተሟሟቀ፤ የጥድፊያ ጥሪ ያለበትም የሚመስል … ጥሌን የሚጣራ የሚመስል። ወዲያው ተቀላቀሉ ጥሌና ሙዚቃ … ይለቀው ጀመራ ጥሌ በዚያ መረዋ ድምፁ! …
“… ያሳለፍነው ዘምን ደስታን ያየንበት … ተመልሶ ቢገኝ አሁን ምን አለበት?! …
እ … ህህ! … እህ … እህህ! … አይይይይ! …”
ይሄን ሙዚቃ ስንቴ እንደሰማሁት የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ መሆን አለበት። ጥላሁን እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ኖታዎችን አዋህዶ የዘፈነበትና የድምፁ ቅላፄ ጐልቶ የወጣበት በዚህ ዘፈን ይመስለኛል። ቢሮዬ ወዲያው ተሟሟቀ። ለቀቅሁት እኔም እንዳቅሜ … አጀብኩት ጥሌን። ቢሮዬ ውስጥ ማን ለሰማኝ? ምድረ ፈረንጅ “ምን ተፈጠረ?” ብሎ ቢመጣም በቂ ምክንያት አለኝ አልኩ። “የከበረና የተባረከ ሕይወትን እየተሰናበትሁ ነው” ካልኳችው እንደሚገባቸው አልተጠራጠርኩም። መቼም ፈረንጆች አይደሉም? ቀጠልን እኔና ጥሌ! … “እ … ህህ! … እህ … እህህ! … አይይይይ! …” አልን። ስንቱን ባነሆለለ ፈገግታው አየት ያደረገኝና “ቀጥል! ጥሩ ይዘሀል” ያለኝ መሰለኝ!” ምን ገዶኝና ማንን ፈርቼ? … ቀጠልኩ … የጥሌን ትዝታና ውለታውን በልቤ እየመዘገብሁ።
“ይሄ ነው እንጅ!” አልኩ፤ እንዲህ ነው እንጅ ጥሌን ማስታወስ! … 55 ዓመት ሙሉ የምድረ ሐበሻን ቤት በደስታና በፈንጠዝያ የሞላ፣ ያሳቀ፣ ያስደለቀ፣ መድረኮችን ያስጨነቀ፣ የወደደና ያዋደደ፣ …፤ ሽኝቱ በተለየ መሆን አለበት አልኩ። ልንሸኘው የሚገባው በትዝታ ቅኝት፣ በባቲ ለዛ፣ ባንች-ሆየ ቃና፣ በ“ሠላመካ” ዝማሬ መሆን አለበት ብዬ ወሰንኩ። የ“አልቻልኩም”ን ጀግና፣ የ“ይህ ነው ፍላጎቴን” መሪጌታ የምንሸኘው ከበሮው እየተደለቀ፣ ሳክሱ እየሳቀ፣ ትራንፔቱ እያማለለ ሊሆን ይገባል አልኩ።
ጥላሁን ዝንተ ዓለም አይረሳም። መሰል-የለሽ እንጉርጉሮዎቹን፣ ግርማ ሞገሱንና የእርሱ ብቻ የሆነ ለዛውን በውስጠኛው የምናባችን ክፍል አትሞብናልና። የዘመናችንን የኪነት የበህር ልጅ እንዴትስ ልንረሳው ይቻለናል?
በል ደህና ሁን ጥሌ! ከተለየኸን … ደህና ሁን!
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.