“ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ?” - እንካ ስላንቲያዎቹ!
ኩችዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ሰሞኑን በድረ-ገጾች ላይ የማነባቸው አስተያየቶችና ትችቶች ሁለት ቤሳ የምታወጣ ሃሳቤን እንዳካፍል ገፋፉኝ። “ኢህአዴግን ማስወገድ ወይስ መለወጥ?” በሚል ርዕስ ግርማ ካሣ፣ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ደግሞ “ሕብረትን በማስቀደም …”፣ ሮቤል አባብያ “አንድነት ፓርቲ ለሚከተለው የሠላም ጎዳና ይሁን ብለናል” በሚሉ ርዕሶች ያስነበቡን ሰነዶች “ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ ትግል” በሚለው ትኩስ መነጋገሪያ ነጥብ ዙሪያ የሚያንዣብቡ ናቸው። እነዚህንና ሌሎችንም ጽሑፎች በአቡጊዳ እና በሌሎች ድረ-ገጾች ማንበብ ይቻላል።
ነገሬን አጭር እና ግልጽ ለማድረግ እሞክራለሁ። “ከእንግዲህ ሠላማዊ ትግል አያዋጣም” ብለው የተነሱትና ግንቦት 7 የሚባለውን ድርጅት የፈጠሩት ወገኖች እስከትናንት ድረስ በሠላማዊ ትግል ይምሉ እንደነበር አያከራክርም። ሞኝ፣ ወረቅት፣ ቴፕ እና ቪዲዮ ያስያዟቸውን አይለቁምና ማስረጃዎች ሞልተዋል። የሰሞኑ እንካ-ስላንቲያ የጫራቸው ርዕሶች የቱን ያህል ነርቭ-ነክ ቢሆኑም መንገዳችንን አጥርተን ለመጓዝ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ስላላቸው እንዲድበሰበሱ መማጸን ትክክል አይመስለኝም።
የግንቦት 7 ንቅናቄ መቋቋም ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
እራሴን ፕሮግሬሲቭ ከሚባለው አምባ ልደብልና “ማንም ሰው የፈለገውን የኑሮ ወይንም የትግል ጎዳና ለመምረጥ ያለውን መብት አከብራለሁ” ልበል። የናንተን አላውቅም እንጂ አንዳንዴ ይህ አባባል ስድ ፍካሬ ሆኖ አገኘዋለሁ። ግለሰቦች እራሳቸውን ብቻ የሚመለከት የሕይወት ምርጫ ቢያደርጉ የሚጠቅሙትም የሚጎዱትም ያው ራሳቸውን ብቻ ስለሆነ ለዚህ ዓይነቱ ምርጫ ቁብ ሊኖረን አይገባም። ከግለሰብ አልፎ ማኅበረሰብንና ሀገራዊ እንቅስቃሴን በሚነካ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ውሳኔ ግን ጉዳያችን ይሆናል።
ከዚህ አንጻር የህዝብን አመኔታና አደራ የተቀበሉ መሪዎች የሚያደርጉት ውሳኔ የተከታዮቻቸውን ፍላጎትና ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት አያከራክረንም። ግልጽነትና ተጠያቂነት መመሪያዎቻችን ይሆናሉ ብለው ምህላ ፈጽመውልናልና። “ሠላማዊ ወይንም ትጥቅ?” በሚል ዓቢይ ጥያቄ ላይ አንድ ወይንም ሁለት ሰዎች ሆነው ውሳኔ ካደረጉ በኋላ የይስሙላ ወረቀት በትነው “ኑ ተከተሉን!” ቢሉ ለኅብረተሰቡ ያላቸውን ንቀት ከማንጸባረቅ በስተቀር ሌላ የሚያመላክተው ነገር የለም። የኃይሉ ሻውል ችግር ይህ ነበር፤ ከልክ በላይ ወጠርከው አትበሉኝና መለስ ዜናዊና ሥዩም መሥፍን ከሱዳን ጋር ያደረጉት ስምምነትም ከዚህ አሠራር ብዙ የተለየ አይደለም።
እንዲመራኝ የምመኘው ሰው፤ ይልቁንም ደግሞ ድጋፌን የሚሻ ፖለቲከኛ በራዕይ ጥራት፣ በሐቀኝነት፣ በመልካም ሥነምግባር እና በታማኝነት ባህርዮች የታነጸ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ከእብሪትና ከመሰሪ ጠባዮች የፀዳ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ባስቀመጥሁት ቦታ እንዳገኘው እፈልጋለሁ። ዛሬ እዚህ ነገ እዚያ የሚሉ ሰዎች የምይዘውንና የምጨብጠውን ያሳጡኛልና ቀልቤ አይቀበላቸውም።
አንደኛው የግንቦት 7 መሪ “ሠላማዊ ትግል ከንቱ ነው” ከሚለው ድምዳሜ ላይ የደረሱት እስር ቤት እያሉ እንደነበር ሰምተናል። ይህ ከሆነ ደግሞ በሠላማዊ ትግል ከሚያምነው የቅንጅት አመራር ጋር በአሜሪካን ሀገር መድረክ መቋደስ አልነበረባቸውም። የጉዞ ፕሮግራሙ መገባደጃ ድረስ ይህን ያህል ግዙፍ ምስጢር ከትግል ጓዶች ደብቆ ማቆየት መልካም የማኔጅመንትና የወዳጅነት ባህርይ አይነበብበትም።
የመሪዎች ባህሪ ሊቆረቁረን ይገባል ወይ?
ፈረንጆቹ በጣም ሊቆረቁረን ይገባል ይላሉ። መሪ ልሁን ብሎ የሚነሳን ሰው ከነአስተዳደጉ፣ ከነመሠረታዊ እምነቶቹ፣ ከነታሪከ ምግባሩ አበጥሮ ማወቅ ወደፊት ሊከሰት ከሚችል አደጋና ፀፀት ይሰውራል - ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በእጅጉ ይሰውራል። ለነገሩ ይህ ብልህነት የፈረንጆች ብቻ አይደለም። ያገሬ ሰው በሲራራ ነጋዴነት አብሮት የሚዘምትን ሰው እንኳ በቅጡ ካላጠናው ከቤቱ አይወጣም። ይችን ያህል ብልህነት እንዴት አጣን?
ለመሪነት የምናጫቸውን ሰዎች በቅጡ መመርመር ነውር የለውምና ይህን ለማድረግ ወኔው ሊኖረን ይገባል። ይህን ሳናደርግ እየቀረን ስንት ጊዜ እንደተበለጥን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ሞኝን እባብ የነከሰው ሁለቴ ነው ይባላል። አንዴ እባብ ምን እንደሆነ ሳያውቅ፤ ሁለተኛው ደግሞ ከልምዱ ባለመማሩ።
ሁለቱ ተፃራሪ ሃሳቦች ጎን ለጎን የመሄድ ዕድላቸውስ?
ብዙ አይመስለኝም። ግንቦት 7 ንቅናቄውን ከማወጁ በፊትና በኋላ በአባልነት ለመመልመል ሲባጅ የከረመው በሠላማዊ ትግል ዙሪያ የተሰባሰቡትን የቀድሞውን ቅንጅት ያሁኑን የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች ነው። እዚህም ላይ ትንሽ መሰሪነት ይታየኛል። ባንድ በኩል ለአንድነት መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ እያለ የትብብር ዘንባባ ይዘረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ “ሠላማዊ ትግል በተባለው ርዕዮት ቀመስ ትብትብ የታነቀ ትግል” (አንዳርጋቸው ጽጌ) ማካሄድ ፋይዳ ቢስ ነው እያለ የሚሊዮኖችን እምነት ያንኳስሳል።
የ1997ቱ የዴሞክራሲ መስኮት ገርበብ ብሎ ከመከፈቱ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበረው የፖለቲካ መልክዓ ምድር ውስጥ ህዝብን ማደራጀትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማብቃት ይቻላል ብለው የታገሉ ሰዎች ዛሬ ምን ሃሳባቸውን ሊያስለውጣቸው እንደሚችል አይገባኝም። የኢህአዴግ ባህሪ ትናንትም ዛሬም አንድ ነው። በጎሣ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚያራምድ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ በሽታ የተጠናወተው፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን የሚረግጥ መንግሥት ነው።
ይህን ሁሉ እያወቅን ነው ሥርዓቱን በሠላማዊ ትግል መለወጥ እንችላለን ብለን የተነሳነው። የ97ቱ የዴሞክራሲ ቀዳዳ የተከፈተው ህዝብ፣ ፓርቲዎች፣ ነፃው ፕሬስ እና ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በኢህአዴግ ላይ ባሳደሩት ተጽዕኖ ነበር። ኢህአዴግ የተከፈተውን ቀዳዳ ዘግቶ ለማቆየት የሚያስችል አቅምና ምቹ የፖለቲካ መልክዓ ምድር እንደሌለው ማመን አለብን። ኅብረተሰቡ መሃል የሰፈነ የሚመስለው ዝምታ አንድ የፖለቲካ ወይንም የኤኮኖሚ ቀውስ ሲፈጠር የሚለወጥ ነው። እየተደራጀና እያደራጀ በህዝብ መሀል የሚቆይ ፓርቲ መኖሩ ለቀውጢዋ ቀን ያስፈልጋል።
የትጥቅ ትግል ከማይመረጥበት ምክንያቶች
የትጥቅ ትግል ኮሎኒያሊስቶችንና አምባገነኖችን ለማስወገድ በአማራጭነት ያገለገለው ዓለም በሁለት የፖለቲካ ማዕዘኖች በተከፈልችበት ዘመን ነበር። ለዚያውም ቢሆን አንድን አምባገነን በሌላ አምባገነን ከመተካት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። ፋይዳ አስገኝቶ ከሆነም ከስንት አንድ ነውና ጂኦ-ፖለቲካው በተለወጠበት ባሁኑ ዘመን እንዳማራጭ መታየቱ ብልህነት ይጎድለዋል።
ሌላም አለ። ጎረቤት አገሮች መጠለያ መስጠት በማይፈልጉበት ዘመን፤ ከራስ ፀጉር የበዛ ሰላይ በከተማና በገጠር ነዋሪው መሀል ተሰግስጎ ባለበት ጊዜ፤ እልቆ መሳፍርት ያለው፤ በዘመናዊ መሣሪያና በሳተላይት መገናኛ የታጠቀ ሠራዊት በሚርመሰመስበት ሁኔታ፤ ምዕራባውያንና የቻይና መንግሥት እሹሩሩ የሚሉት ታዛዥ መንግሥት በነገሠበት ሁኔታ ለትጥቅ ትግል ምቹ አየር ያለ አይመስለኝም። እነዚህ የማያመቹ ሁኔታዎች የሚለወጡት መንግሥትን መውጫ ቀዳዳ የሚያሳጡ ኤኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲገኑ ነው። ያኔ የፖለቲካው ሜዳ ይለወጣል።
ሳላነሳ ማለፍ የማልፈልገው ሌላ ነገርም አለ። በትክክል ገብቶኝ ከሆነ ግንቦት 7 የትጥቅንም የሠላማዊ መንገድንም የሚከተሉ ፓርቲዎችን አስተባብሬ ኢህአዴግን አስወግዳለሁ የሚል ዓላማ ያለው ይመስለኛል። የትጥቅ ትግል ያካሂዳሉ ከሚባሉት መሃል ደግሞ ኦነግና ኦብነግ ሳይኖሩበት አይቀርም። ታዲያ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በኢትዮጵያ አንድነት የማያምኑ መሆናቸው ሲታወቅ ከእነርሱ ጋር ማኅበር መጠጣቱ ለምን ግብ ነው? ኤኤፍዲ በተመሳሳይ ዓላማ ሲቋቋም ሁለቱን ድርጅቶች ወደ መሃል ማምጣት ይቻላል በሚል ታሳቢ እንደነበር ትዝ ይለኛል። የሁለት ዓመት ዕድል ተሰጥቷቸው ካቋማቸው ትንሽ እንኳ ፍንክች የማለት አዝማሚያ አለማሳየታቸው እንድንጠረጥራቸው አያደርገንምን?
ይህንኑ ክርክር ልቀጥልበትና፤ የኢህአዴግ መንግሥት በግንቦት 7ም፣ በኦነግም፣ በኦብነግም የትጥቅ ትግል (በአመጽ) ይወገድ እንበል። አመጹ በሚያስከትለው ትርምስ ውስጥ ኦነግና ኦብነግ ለዓመታት ሲያልሙ የነበረውን የመገንጠል ሃሳብ ቢያውጁ ማን ያቆማቸዋል? ይህ ዓይነቱ ትግል በሚፈጥረው ቀውጢ ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስከብር የተማከለ ሠራዊት እንደማይኖር ከወዲሁ መገመት አያዳግትም።
ከሁለት ገጽ በላይ ላለመጻፍ ለራሴ የገባሁትን ቃል ስላፈረስኩ ይቅርታ በመጠየቅ እዚሁ ላይ አቆማለሁ። አይደግመኝም።
ኩችዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. July 11, 2008