ጮክ ብለህ ተናገር (ዳግማዊ ዳዊት)
ጮክ ብለህ ተናገር
ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ልቤ እስከሚሸበር - መልካው እስኪናጋ
ወፎች ግ … ር እስኪሉ -እስኪበተን መንጋ
ጀግና እስከሚፎክር - ፈሪ እስከሚያመልጠው
ልጆች እስኪሮጡ - መዓት መጣ ብለው
ቄሱ እስከሚያማትብ - እስኪል “በሥላሤ”
ሠባኪው እስከሚል - “በጌታ እየሱሴ”
ሸኹ “ያ - አላህ” ብሎ - አዛን እስኪያሰማ
ሾፌሩ ለመሄድ - ለመቆም ሲያቅማማ
እናት “ውይ!” እስክትል - ደረቷን ስትመታ
ሌባ እስኪበረግግ - እስኪሮጥ በአፍታ
እስከሚያስተጋባ - ሸንተረር ሸሎቆው
ተራራና ወንዙ - ዛፉና ቁጥቋጦው
ጮክ ብለህ ተናገር - እኔም ልበል አሜን
እስካዳነ ድረስ - ሀገሬን ወገኔን
ላይጠራ አይደፈርስ - ሣይጨልም አይነጋ
በለው ተናገረው - መልካው እስኪናጋ።
መነኩሴው ሲረሸን - ቤተመቅደስ ገብቶ
ዔሎሄ ሀገሬ - ወገኔ እሚል ጠፍቶ
ሚስት ስትገደል - ሥለባሏ ጮሃ
ወገኔ በሥደት ሲሞት በበረሃ
አዛውንት ሲታሰር - እህት ስትደፈር
ፍትህ ስትዛባ - ኃይማኖት ስትሻር
ዝምታው ምንድን ነው - ተናገር ላዳምጥህ
ወርቅ ነው እሚነጥር - አንጥረው ተናግረህ።
የውንድምህ ግጭት - ያኮረፍክበቱ
አያስደነግጥም - ቢታይም ውጤቱ
ሀገር አያጠፋ - አይገድል ወገን “ያዝ … ያዝ” መባባሉ ማውራት ይህንን
ለእኔ ይመስለኛል - ጊዜ ማባከን
እንኳንስ የሰው ልጅ - እኩይ ምላስ ያለው
ድንጋይም ይጋጫል - የማይናገረው።
ይልቅ፤
ሠላምን ሥትሻ - ፍትህ እና መብት
ፍቅርን በልብ ይዘህ - ስትል ለእኛ መንግሥት
ይህን ስትጠይቅ - በአንተ በፈረደ
አንተ ስትገነባ - እራሱ እየናደ
ያለውን ታገለው - “መለስ” የሚሉትን
ሀገር አፍራሽ ይጥፋ - ቅድሚያ ለእርሱ ይሁን።
ዝምታ ወርቅ ቢሆን - ቢያስከብር በወገን
አክባሪው ሲገደል - ዝምታ ምን ይሆን?
ድሮም ይባል ነበር - ለመሾም በመንበር
ዝምታ አይሆነውም - ከመናገር በቀር
መሾም አይገኝም - ደጃዝማችነቱ
በመናገር ጥረት - የምትገኝቱ።
ግና፤
መቋመጥ ለመውጣት - ከሥልጣን ኮርቻ
ላገር ሳይሞቱላት - ልክ እንደነ ባልቻ
እንደነ አባ ታጠቅ - እንደነ አባ ዳኘው
እንደነ አባ በዝብዝ - እንደነ አባ ዳጨው
እንደነ አባ መላ - እንደነ አባ ውቃው
እንደነ አባ ኮስትር - እንደነ አባ ነጋ
እንደ ዘረዓይ ድረስ - እንደነ አብዲሳ አጋ
ካላወጡ ወገን - ከጠላት መንጋጋ
መናገር ቧልት ነው - የመለፍለፍ ዓመል
ሐኪም የሚያሰኘው - ቃልቻ ወይ ፀበል
እና፤
ጮክ ብለህ ተናገር - እኔም ልበል አሜን
እስካዳነ ድረስ - ሀገሬን ወገኔን
አሳርግ ለፍትህ - ለሠላም ለመብት
ለሀገር ብልፅግና - ለወገን ለአንድነት
ላይጠራ አይደፈርስ - ሣይጨልም አይነጋ
ጮክ ብለህ ተናገር - ዙፋኑ እንዲናጋ።
ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ሐምሌ 2001 ዓ.ም.