ጠላትህን ዕወቅ! (ገ/ኢ. ጐርፉ)
ጠላትህን ዕወቅ!
ገ/ኢ. ጐርፉ
ዓይኔን ግለጡልኝ፣ ጠላቴን ልየው፣
’ባካችሁ ጠቁሙኝ፣ ንገሩኝ ማነው?
ጠላትህ በሽታ፣ ማጣት፣ ድኽነት፣
የአየር መለዋወጥ፣ የመሬት ድርቀት …
ነው እያሉ ሲሉኝ ከጥንት ከጥዋት፣
በጣም ያጠቃኝስ ድንቁርና ዕሬት!
አካላቴ ደርቆ፣ ቆዳየ ሲፋቅ፣
በድኽነት ስቃይ ሁሌ ስማቅቅ፣
ዋናውን ጠላቴ ስሙን እንኳን ሳላውቅ፣
ተከናንብያለሁ ድንቁርና ማቅ!
አደራ በሉልኝ የሀገሬን ሰው፣
ቶሎ እንዲገላገል ከድንቁርናው፣
በብዙ ምክንያት ኋላ ያስቀረው፣
ጠላቱን መለየት እንዳይሳነው!
በተንኮል፣ ሽንገላ ሁሌ እያታለለ
በዘር፣ ጎሣ፣ ቋንቋ፣ እየከፋፈለ
ወንድምን ከወንድም ሰው እያጋደለ
ግብፅ የሚሉት ከይሢ ከጎረቤቴ አለ!
እኔን ጥም ሲገድለኝ ውሃየን ጠጥቶ፣
እኔ በራብ ስሞት እርሱ ጠግቦ፣ በልቶ፣
ይህም አልበቃውም ሰው ከሰው አጣልቶ፣
ተከብሮ ይኖራል እኔን አደኽይቶ!
በገብስማ ዶሮ እየተመኻኘ፣
በወሰራ ዶሮ እየተመኻኘ፣
በኤርትራ፣ በሶማል፣ እየተመኻኘ፣
ዋናውስ ጠላቴ ግብፅ ሆኖ ተገኘ!
አደራ በሉልኝ የሀገሬን ሰው
ጠላቱን መለየት እንዳይሳነው!
ገ/ኢ. ጐርፉ
Ethiopian Historic Conservation Council 9852 Stanford Av., Garden Grove, CA. 92841



