ብሶት የወለደው

ዳዊት

እንዲህም ይባላል እኮ … ለመኖር ያለህን ፍላጎት ለሞት ስታጋራት (ስታካፍላት) ያን ጊዜ እውነቱን መናገር ትጀምራለህ(ሽ)። ይህ አባባል ከተጠናወተኝ ተሰነባብቷል፣ ኧረ ቆይቶአል። የለም ዛሬ በግጥም ልሞክር … ”ብሶት የወለደው ጀግናው የአጋዚ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬድዮ ጣቢያን ዛሬ ተቆጣጥሮታል። ግንቦት 20 ሺ ዘጠኝ መቶ 83 ዓ.ም.” ስንቶታችን ይሆን ይህን ቃል በወልጋዳ አማርኝ ቀኑን ሙሉ ሲያላዝንብን ጆሮአችንን ደፍነን የሰማነው … እኔ እንጃ! እኔ ግን አንዱ ነኝ።

ብሶት የወለደው ደደቢት የተቀናጀው

ብረት ሳይጨበጥ ነበሩ አምስት ሰው

ብሶት ለማራገፍ ተከዜን ሲጠጉ

ደግሞ ሰባት ሆኑ ሁለቱን አስጠጉ

 

ብሶት የወለደው መች በዚህ አቆሙ

ችፍርን ረግጠው ግራር ላይ እየቆሙ

በአልቢን በምንሽር ሰው እየለቀሙ

በየደረሱበት ብሶት እያሰሙ

የሀገሩን ፍቅር አጠቡት በደሙ

 

ሬሳ ትራሴ ምንሽር ሕይወቴ

ከፊቴ የመጣውን አጥፋልኝ ከፊቴ

ሃውዜን የኔ ሀገር ባለውለታዬ

ዶላሯን አመጣች ሞላ ኮሮጆዬ

ላበላ ነው ብዬ ወገኔን ማሽላ

ከሰባቱ አንዱን አድርጌ ከለላ

ዶላር በየፈርጁ ማዳበሪያ ሞላ

 

በቃ በኋላማ ሞላ ጎተራዬ

አሸዋውን ጥዬ ከማዳበሪያዬ

ሞርተር ክላሽንኮቭ ሆነ ዓላማዬ

ድሮስ ከየት ይምጣ ማሽላ ከቀዬ

እንኳን የዛኔና አሁንም አልታዬ

ብሶት የወለደው ደረሱ በሺዎች

የሚበላ ሞልቷል ከአረንጓዴ ሰዎች

 

ጠዋት ፍየል ጠቦት ማታ ፍሪዳ ነው

እንቢ ካልህ ደግሞ ጥይት ወዳጅህ ነው

በግራ እጅ ብሶት በቀኝ እጅ ብሶት

የተሰነቀችው የተቋጠረችው ከዚያ ከደደቢት

ደግሞ ባለተራ ደርሷል ሊቀበላት

ብሶት የወለደው ጀግናው የአጋዚ ሠ…

 

አለቀ ደቀቀ ብሶት ተበተነች

ለእያንዳንዱ ጦቢያ በየኪሱ ገባች

ከደደቢት አልፋ መርካቶ ደረሰች

አሁን ከእጅ በእጅ መቼ ተላለፈች

ሥፍራው ስላልበቃት ሞገድ ላይ አረፈች

አለቀ ደቀቀ ብሶት ደህና ሰንብች

 

ባለተራ ደግሞ እስቲ ይሰንቅሽ

በሞርተር አቅፌ እዚህ ያደረስኩሽ

በበረሃ አሸዋ ሳይታየኝ ኩስሽ

ሸርሙጣ ላይ ወዲ ሳልጨምር ቀስ ብለሽ

ከእንግዲህ ወዲህ በዓይኔ እንዳላይሽ።


ቸር ይግጠመን!

ዳዊት

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ