አዛለች ወደ ፓርላማ (የምርጫ ጭውውት)
አዛለች ወደ ፓርላማ (የምርጫ ጭውውት)
ክፍል ሦስት
ዳግማዊ ዳዊት
ባላፈው መጋቢት - የአቦለት ቤተክሲያን
ጠጋ ብዬ ጠየቅሁ - ወረቀት ሲበተን
እንዲህ ይነበባል - በራሪው ወረቀት
ከላይ ምርጫ ብሎ - ከታች ንብ አለበት፤
አዛል ምርጫ ገባች- ሹርባ ተሰርታ
መረራ ጉዲናን - በድምፅ ልትረታ
ኢህአዴግ ፓርቲዋን - ወክላ ቀርባለች
ልማታዊቷ ሴት ምረጡኝ - ትላለች።
ፎቶውን አይቸ -
አንገቴን አቅንቸ
መፈለግ ጀመርኩኝ - አዛሉን ጓጉቸ።
መስቀል ሲሳለሙ - አየኋችውና - ለብሰው ጃኖ ኩታ
መንገዴን ቀጠልኩኝ - ከቆሙበት ቦታ።
“ዶ/ር አዛሉ! ዶ/ር …” - ብዬ ስጠራችው
የፌደራል - ፖሊስ ወገቤን ዠለጠው
“አተ… አታ ባለጌ” - ብሎ ሲጮህብኝ
መሬት ተሰንጥቃ - ትውጠኝ ተመኘሁኝ።
እኝህማ አዛሉ - እኔ የማውቃቸው
ጠላ ኮማሪዋ - አይደሉ እንዴ እሳቸው።
ፖሊስ ቢዠልጠኝ - በያዘውም ዱላ
ምን ሊባል - ይገባል ከብልግና ሌላ
እንዲህ ያለ - ጥሪ “ዶክተር!” ብሎ ማለት
ስድብ ብቻ ሳይሆን - ብልግናም አለበት
ከአንድም ሁለት ጊዜ - ለቀበሌ ሸንጎ
ራቦል ጥፌያልሁ - ለአዛለች ሽመኮ
ማንበብና መፃፍ - የማያውቁትን ሴት
ዱላ እማይበቃው ነው - ዶክተር ብሎ መጥራት
ፖሊስ አዋከበኝ - ዶለኝ ወኸኒ ቤት
አዋርዷል ተብዬ - ልማታዊቷን ሴት።
************
ሁለት ወር ታስሬ - የተፈታሁኝ ቀን
አሸነፉን ሰማሁ - አዛሉ መረራን።
የሰፈራችን ሹም - የወያኔው ኔጭ ሹም
እንዲህ አርጎ አሰማኝ - መቸም ጉድ አያልቅም።
“የሰፈር ወይዘሮ - የጠላ ኮማሪ
የትናንት ልማት ሴት - ሥራን አስተማሪ
ማንበብ መጻፍ ባይኖር - ማይምም ቢሏቸው
ሀገር መገንባትን - ዲሞክራሲ አውቀው
የመንግሥት አመራር - በደንብ ገብቷቸው
አዛሉ ዶከተሩን - ጥለው አሳይዋቸው
ፖለቲካ ሳይንስ - ዓለም አቀፍ ቢሉ
ዶክተር መረራ ነኝ - የታወቅሁት ቢሉ
መረራ ተረታ - ድል ሆነ በአዛሉ።
ወይዘሮ አዛለች ነች - የሆነች አንበሳ
እንግዲህ በጀ በል - አምቦም እጅ ንሳ።
አሜሪካን ሀገር ያለሽው ሂላሪ
ይልቅስ ነይና - ከአዛለች ተማሪ።”
በስጨትጨት ብየ - እልሄ መጣና
መናገር ጀመርኩኝ - ተራዬ ሆነና።
“ገና ዱሮ ነበር - ያኔ ሳይወጠን
አልነጋም ያልናቸው - የዛሬውን አይተን።
መለስ ወንፊት ሰፍቶ - ማበጠር አቅዶ
ልደቱ እህል ሆኖ - ኃይሉም ገብቶ ወዶ
ይኸው ተበጠረ - መረራም ወረደ
ግፍም ሕግ ሆነና - ውሸት ተለመደ።”
ብዬ ተናግሬ - ልጨምር ስሞክር
ስውር ፖሊስ ኖሮ - ከነጭ ለባሹ ጋር
ሽጉጡን አውጥቶ - እያንገራገረ - ማጅራቴን ይዞ
እስር ቤት ጨመረኝ - በመኪና አግዞ።
ዳግማዊ ዳዊት
ግንቦት 2002
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
መረራ ጉዲናን - በድምፅ ልትረታ 


