በል ሚስቴን አዋልዳት! (ወለላዬ)
"በል ሚስቴን አዋልዳት!"
ወለላዬ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ከጥንት ጀምሮ ታሪክ ሲመረመር፣
በዚህ በሃያ ዓመት የደረሰው ነገር፣
በመሆኑ እንግዳ እጅግ አስገራሚ፣
ማመን ያስቸግራል ለአዳማጭ ለሰሚ።
በቶጫ ወረዳ በደቡብ ዳውሮ ዞን፣
ሕክምና አዋቂ የሚረዳ ህዝብን፣
ብዙ ስለሌለ ይሄን ያወቀ ነርስ፣
ወያኔ ባመጣው ምድብ በመተራስ፣
በራሱ ፍላጎት ከጅማ ሆስፒታል፣
ዝውውር ጠይቆ ሄደ ሊያገለግል።
ይሄ ሰው በሥራው በመሆኑ ብርቱ፣
ምንም ሳይሰማው ልፋት እንግልቱ፣
እየተዟዟረ ከተማ ከገጠር፣
ያገልግሎቱን ልክ የሥራውን ፍቅር፣
ስላስመሰከረ ሁሉ ሰው ወደደው፣
ከምስጋና ጋራ አክብሮትም ሰጠው።
ይሄን ያልወደደው ገዢው አቶ ካሣ፣
ነርሱን ከወረዳው ሊያጠፋው ተነሳ።
ይሄ አስተዳዳሪ በተለይ አማራ፣
አይወድም ነበረ ስሙ እንኳን ሲጠራ፣
ስለዚህ ያንን ነርስ ቢሮው አስጠርቶ፣
ግንባሩን ጨምድዶ በጣም ተቆጥቶ፣
አንተ በመሆንህ የአማራ ነፍጠኛ፣
እስከሙያህ ጭምር አትበጀንም ለኛ
በዚህ ወረዳችን አንተን መሳይ ሐኪም፣
ከዛሬ ጀምሮ ፈጽሞ አንፈልግም
ጨርቅህን ጠቅልለህ ነገ ዛሬ ሳትል፣
ክፉ ሳይደርስብህ ጥፋ ከዚህ ክልል።
ብሎ ባሸከመው አስቀያሚ መርዶ፣
ነርሱ ግራ ገብቶት አዝኖና ተናዶ፣
ለበላይ አለቆች ያለበትን ችግር፣
ጽፎ በአካል ሄዶ ቢያስረዳም ቢናገር፣
መልስ በማጣቱ ቆይቶ ሲበሳጭ፣
መጨረሻ ወስደው መደቡት አርባ ምንጭ።
ከሁሉ እሚገርመው የሚደንቀው ነገር፣
አባቱ አማርኛ አይችሉም መናገር።
ይሄ ተፈጽሞ ወር እንኳን ሳይሞላ፣
አንዷ በምጥ ሳቢያ ታመመች በጠና
ዙርያዋን ቢከቡ የልምድ አዋላጆች
ወዲያ ወዲህ ቢሉ የጤና ረዳቶች፣
ተጨንቀው ተጠበው አስሩን ቢጠሩ፣
ዘዴ ቢፈልጉ ብዙ ቢማከሩ፣
መውለድ ስላልቻለች ቢያጠጧትም ጠበል፣
ሰው ሁሉ ተረዳ የዛን ነርስ ማጉደል።
ይሄኔ ባልየው አዝኖና ተናዶ፣
አስተዳዳሪው ዘንድ ሚስቱን ይዞ ሄዶ፣
“ሐኪም ስላባረክ ከሰህ በአማርነት፣
የኛ አስተዳዳሪ በል ሚስቴን አዋልዳት!
በዚህ የተነሳ ብትሞትብኝ ሚስቴ
ማንም እንዳይመስልህ አንተ ነህ ጠላቴ …”
እያለ እንደ እብድ እየለፈለፈ፣
ህዝቡ ቢሮው ዙሪያ እንደተሰለፈ፣
የዛች እናት ሕይወት እስከልጇ አለፈ።
እንግዲህ ጉድ እዩ በዘረኛ አጀንዳ፣
እንዴት እንደሚረግፍ ህዝብ እንደሚጎዳ
ይሄን በመረዳት እርስ በእርስ አንፋጅ፣
በዘር መከፋፈል ለአንዳችንም አይበጅ
(በአንድ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ አንድ ተናጋሪ በዘር በመከፋፈል ሳቢያ ህዝብ እንዴት ሊጎዳ እንደሚችል በምሳሌነት ከጠቀሱት እውነተኛ ታሪክ ተወስዶ በግጥም የተዘጋጀ።)
ወለላዬ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ግንቦት 23 ቀን 2002 ዓ.ም. / May 31, 2010



