የሞት ዕኩልነት

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

እግዜር በፈጠረው - ሰማይና ምድር

ተራራ ሸንተረር - ውቅያኖስ ባህር

ያገባኛል ብሎ - ሰው ባለቤት ሆኖ - ድንበር አበጅቶ

የከርሰ-ምድር ሀብት - በስፋት አካብቶ

አንተ ከዚያ ወዲህ - አንች ከዚህ ወዲያ - ብሎ ተከፋፍሎ

አንዱን እጅግ ደልቶት - ሌላው ተበድሎ

ይኖራል ይሞታል - የመኖር-ሕግ ሆኖ።

 

 

አንዱ ባለፀጋ - የተትረፈረፈው

ሌላው ምስኪን ደሃ - ይበላው ይጠጣው

- ይለብሰው የሌለው

የዓለም መልክ ሆነና - ሕይወት ዥንጉርጉሩ

የሰው ልጅ ይኖራል - ገንዘብ ሆኖ ነውሩ

ንብረት በለጠና - ከሰብዓዊ ክብሩ።

 

ሠራዊት መንግሥታት - አቤት ብለውለት

ሀብታሙ ይኖራል - ዓለም አድልታለት

ከውሻ አንሶ ደሃው - ማጣቱ ወንጅሎት

እሱም ኖረ ተብሏል - ዓለም አድማበት

የሰው ልጅ ኅሊና - እንዲህ ተመሳቅሎ

 

ፀጋን አመሥግኖ

ድህነት ኮንኖ

ለኃይል አቤት ብሎ

ደካማውን ገድሎ

ሕይወት ነው ይለናል - “መኖር” ስሙ ሆኖ።

 

ልክ እንደ እግዜር ሆኖ - ሰው ቢሠራውማ - ሰማይና ምድሩ

ደሃና ደካማ ባልኖሩበት ነበር - ገና ከጅምሩ

ጉልበታም ለብቻው - ልክ እንደሂትለር

ሞልቶ ከተረፈው - ከባለፀጋው ጋር

እኛ ብቻ እንኑር - ብሎ ባለን ነበር

ዳሩ አምላክ ሆነና - የዚህ ዓለም ንጉሥ

ደሃውም ሀብታሙም - ደካማና ኃይለኛ እኩል ባይወደስ

የሞት ቀን ሲመጣ - ሰው ሲመለስ ከአፈር

ዕኩል መሆናቸው - ያኔ ነው የማይቀር።

 

እናም ሂሳብ ሳስብ - አንድና አንድ ደምሬ

ዕልፍ አዕላፍ ብደርስ - ከአሃዱ ጀምሬ

አራት ነጥብ ሳደርግ - ስንኝ ቋጥሬ

መደምደሚያው ሆነ - የድምር ውጤቱ

ዕኩል የሚሆነው - ሰው በሰውነቱ

ሲሞት ብቻ ሆኖ - አፈርኩ በስሌቱ

በአንድዬ እምላለሁ - ቀፈፈኝ እውነቱ።


ዳግማዊ ዳዊት

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሰኔ 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ