”ድመት መንኩሳ ...” (ገረመው ደፋሩ)
”ድመት መንኩሳ ...”
ገረመው ደፋሩ
ምንም ብትመነኩስ፣ ቆብ ብትደፋ ድመት፣
እፆማለሁ ብላ ብትጀምር ስግደት፣
ወተት ባይኗ ካየች በቅርብም በርቀት፣
አመሏን አትረሳም እስከ ዕለተ ሞት።
የልዴቱም ነበር እንደ ድመቷ ነው፣
ትንሽ ወተት ካየ የሚቀማምሰው፣
ወደዚያ መሄዱ ፍፁም የማይቀር ነው።
እንደሌሊቷ ወፍ ሁሉን ያታልላል፣
”ወፍ ነህ እንዴ?” ሲሉት፣ ”እዩት ጥርሴን” ይላል፣
”አይጥ ነህ?” ሲሉትም፤ ክንፎቹን ያሳያል።
ያ’ኔ ህዝብ ተፍቶት በክፉ አመሉ፣
እንዳልተደበቀ፣ እንዳልጠፋ ሁሉ፣
መናኛ፣ ማፈሪያ፣ በጣም የዘቀጠ፣
ያለምንም ሀፍረት እያጉረጠረጠ፣
”አለሁ! አለሁ!” አለ ዓይኑን አፈጠጠ፣
ትላንት ስለምርጫው የተዛባ ሂደት፣
ያለውን ዘገባ ሲያጋልጥ ፊት ለፊት፣
ልክ እንዳልነበረ (ኢ-ፍትሐዊነቱን፣ እያስተባበለ፣
በደል ተፈጽሟል፣ ግፍ ነው እንዳላለ፣
ወዲያው ግልብጥ ብሎ በአንድ ቀን ጀምበር፣
”ምርጫው አይደገም፣ ይቀበለው ሀገር፣”
እንዴት ሊል ይችላል?! በጤናው ነው እንዴ?!
ወይስ ተደለለ? ባስለመዱት ዘዴ?!
ገና ከጅምሩ ደፍሮ ሲደሰኩር፣
እስከማውቀው ድረስ ባለሁበት ሀገር፣
ከውስጥም ከውጭም ህዝብ ደግፎት ነበር፣
ወላዋይ፣ ደጅ ጠኝ፣ ዓላማ የሌለው፣
እንዴት ህዝብን ያማል እውን በጤናው ነው?!
ሠላሳ አንድ ነጥብ ባለው ዝርዝር ”ጥናት”፣
በሙሉ ኮንኖ የምርጫውን ሂደት፣
እንዴት ይቀበላል ኢ-ፍትሐዊ ውጤት?!
ያኔ በድል ጊዜ በዘጠና ሰባት፣
ቅንጅት ሲከተል የህዝቡን ፍላጎት፣
ዘሎ ሸንጎ ገባ ለራሱ በማድላት፣
”ያሁኑ ይባስ! ያሁኑ ይባስ!” ዘንድሮስ ለየለት።
የአንድነት ተውሳክ፣ የመለስ ባለሟል፣
እንዴት ”አንድ ሁነን አንታገል” ይላል፣
ደግሞ እንደ ቅንጅት መድረክን ሊበክል?!
ከእንግዲህስ ይብቃው ማንም አይታለል!
ህዝብን ከማታለል ከ’ንግዲህ ይጠንቀቅ፣
የሚጥሉለትን ቁራሽ ይጠባበቅ።
የትግል ስልቴ ነው ያዋጣል የሚለው፣
ሦስተኛው አማራጭ ወላዋይነት ነው፣
የኢዴፓ አባል በመላ ይወቀው።
ገረመው ደፋሩ



