ከእናት ጥያቄ ...

ሚሊዮን ጎሣዬ - ከኦስሎ (ኖርዌይ)

በረሃብ ቸነፈር ተይዛ

በኀዘን በብሶት ተክዛ

አየኋት ተከፍታ እናቴን

ተስፋ እንደቆረጠች ሀገሬን

 

ተጠግቼ የሆነችውን ብጠይቃት

ሕመም ችግሩዋን ልጋራት

ሲቃ ተናንቋት የእምባዋ

ታወጋኝ ጀመረች በደሉዋን

 

”ልጅ አልወጣልሽ እያለኝ

ዘመን ተቆጠረ ዘመን አለፈብኝ

ብወልድ ወንድሙን የሚወጋ

ብደግም እናቱን የሚከዳ

ብጨምር ወንድሞቹን የሚለያይ

ባበዛ ተጣይ ተገንጣይ

እየሆኑ ተቸገርኩ ልጆቼ

አይዞሽ ባይ ከጎኔ አጥቼ

 

”የቀድሞዎቹ ከአሁኖቹ ላይሻሉ

ዘመነኞቹ ካለፉት ላይለዩ

የተስማሙ ይመስላሉ ምለው

ላይግባቡ ላይዋደዱ ፈቅደው

ሠላምን ፍቅርን ላይፈልጉአት

መቻቻልን አውጥተው ሊጥሏት

መከባበርን እንደውርደት ቆጠሩ

እውነትን በክህደት ለወጡ

 

”ለኔ ያዘኑ እየመሰሉ

አይዞሽ ብለው እየማሉ

ታጥቀው ይገባሉ ወደጫካ

በኔ ስም የራስ ጥቅም ፍለጋ

ወንድም ወንድሙን ይገልና

ደም እንደጎርፍ ይፈስና

ሕይወት እንደዋዛ ይጠፋና

ሥልጣን ይይዛል ባለተራ

ወንበሩን ይዞ ሲደላደል

የማይሞት የማያልፍ ይመስል

መሃላውን ሁሉ ረስቶ

የሀገር ፍቅሩ ጠፍቶ

’እኔ’ ይሆናል ዘፈኑ

አልወርድም ይላል ከዙፋኑ

 

”ይነሳል ደሞ ሌላው

ባለጊዜው ግራ ሲያጋባው

ለውጥ ፈልጎ ሲጠፋ

ህዝብ ሲያዝን ሲከፋ

ብረት አንግቦ ወደጫካው

ይሮጣል ወደ ፍልሚያው

እንደገና ሊደግምልን ቅኔውን

ሳይለውጠው የቀድሞውን

 

”ዛሬም የዚህ ዘመን ልጆቼ

የስጋዬ የአብራኬ ክፋዮቼ

ይህንኑ ዜማ አዚመው

ወንበር ያዙ ዋጋ ከፍለው

ለውጥን ጠበቅሁ ተስፋ አድርጌ

አዲስ ነገር ይመጣ እንደው ብዬ

ለሃያ ዓመት በምርጫ ስም ሲያደናብር

ዲሞክራሲን ያለተግባር ሲደሰኩር

ትሁንን ትቼ ትብስን እንዲሉ

ተንገሸገሽኩ ተማረርኩ በአሁኑ

የልጆቼን ድምፅ እየሰረቀ

ምረጡ እያለ እያሳበቀ

ቢያታልልም በምርጫ ስም

ከአምባገነንነቱ ሌላ አላየሁም

 

”ለምን ታዲያ አልከፋ

አይዞሽ ባይ ደጋፊ ሲጠፋ

ለብቻው ሲፏንንበት ሀገሩን

ሁሉን አውጥቶ ሲበትን

እኮ እስከመቼ ልታገስ

እውነት ወደቤቴ እስኪመለስ ...”

ብላ ስትጠይቀኝ የውስጧን

ስትነግረኝ የዓመታት ብሶቷን

በእኔ አቅም ብቻ

መልስ ልሰጣት ከበደኝ

ይህው ጥያቄዋን ለሁሉ አቀረብኩኝ


ሚሊዮን ጎሣዬ

ከኦስሎ - ኖርዌይ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ