አትነካኩት ቁስሉን (አቢይ ኢትዮጵያዊ)
አትነካኩት ቁስሉን
አቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወ-መንፈሳዊ
መድኃኒቱ ሳይኖር፣ ይድናል አትበሉን፤
ሐኪሙ እስኪመጣ፣ አትነካኩት ቁስሉን።
ህዝቧ እየረገፈ ሁሌ እየታገለች፣
ይባስ በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ቆስላለች።
በግልምቢጥ ዘመን፣
በደሟ የጨቀዩ፤
ነፃነቷን ዘርፈው፣
ሕዝብ እያሰቃዩ፤
ጊዜን ተጠልለው፣
በትዕቢት ያበጡ፤
ጉጅሌዎች ናቸው፣
ግፍን የሚያምጡ።
ከፈረሱም በፊት ጋሪ ያስቀደሙ፤
ዛሬም ግድብ ብለው ደም የሚቃርሙ፤
በዘር ፖለቲካ ሕዝብ እያታለሉ፤
ቢሊዮን ዘርፈዋት ጎኗን ያቆሰሉ፤
የሚቃወመውን በህቡዕ ሲገድሉ፤
ግና ባደባባይ በሠላም ይላሉ።
እናም መድኃኒት ሳይኖር፣ ይድናል አትበሉን፤
ጀግናው እስኪመጣ፣ አትነካኩት ቁስሉን።
ቁስልን ሲነካኩት፣ ላይ ላዩን ደስ ይላል፤
ግና አመርቅዞ ውስጥ ውስጡን ይገድላል።
ግድብ ቢሉት ሕንፃ፣
መንገድ ወይም ሌላ፤
የሕዝብን ነፃነት የብር ደም ከበላ፤
ሁሌ እየተራበ ታርዞ የጠማውን፤
ሃያ ዓመታት ሙሉ ኑሮውን ያጣውን፤
የአመፅ ምጥ ይዞታል በትግል አርግዞ፤
ሰበብ ነው የቀረው ከመከራው ጉዞ።
በብረት በግዱ ዛሬም ነገም ቢሉት፤
በትዕግስቱ ፀንቷል በቁሙ ሲገድሉት።
እናም፦ መድኃኒት ሳይኖር፣
ይድናል አትበሉን፤
ጀግናው ሊመጣ ነው፣
አትነካኩት ቁስሉን።
አቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወ-መንፈሳዊ



