ጉድ ነው - ጉድ ነው ዘንድሮ

ፍሬው አንተነህ

ነጋዴ ሊነግድ፤

አገር አቋርጦ ቢሄድ፤

ማረፍ ነበር ግድ፤

ከወንድሙ ዘንድ።

 

 

አሞሌ በቀንቀሎ በቁጥር፤

ተቀፍድዳ እንዳትበር፤

ለካ ወንድሙ አስተውሎ አጎደለው፤

ሳይነጋ እንግዳ ሳይደርስ መሔጃው።

 

ነጋዴ ይህን አሰተውሎ፤

ማሚቱን አፍፈ በቶሎ፤

ሰወራት ለመያዣ በተንኮል፤

ተካት በሜዳ ዝንጀሮ-ቀመል፤

እርስ በርስ ተግባብተው ካለጥል።

 

ይለዋል ወንድሙን ባለቤት፤

እንግዳውም መለሰለት፦

 

ጉድ ነው ጉድ ነው ዘንድሮ፤

ማሚቱ ሆነች ዝንጀሮ። (ባለቤት)

 

ጉድ ነው ሩድ ነው ጉድ ባይ፤

አሞሌ ሆነ ድንጋይ ። (እንግዳ)

 

ማሚቱም አለች ካጎቷ (እንግዳ)

አሞሌም አለ ከጎታ። (ባለቤት)

 

እንዲሁ ተለዋወጡ ድል፤

ዜሮ ለዜሮ ይባላል።

ይገርማል ሲበዛ ይደንቃል፤

በአበሻ አገር የማይሆን ሆኗል!!!

 

ነገር ተዘብርቋል፤

የዚቅ ዚቅ ይታያል፤

ቅል ድንጋይን ሰበሯል፤

ውሀ ሽቅም ፈሷል።

 

ያልታየ ያልተሰማ፤

ታየም ሆነም አንዳይለማ፤

አሞሌ ድንጋይ ይላል?

እረ ወርቁ ብረት ሆኗል።

 

ዝንጀሮ አለች ጋጎቷ፤

አሞሌም አለ ከጎታ፤

አንዴት ነገሩ ይምታታ።

ወርቅ እግር አውጥታ፤

ዘምታ ካገር ወጥታ፤

በየባንኩ ገባች አሉ፤

እንደ አሞሌ ሁሉ።

 

እቱም እንደፈረደባት፤

አገርዋን ለቃ ስደት፤

ጠቅልላ ርቃ ሄደች፤

ለባእድ ዋለች አደረች።

 

አባቴ ሲያወጉኝ ይህን ተረት፤

እንደዘበት አደመጥሁ ሰማሁት፤

ለካ ነገሩ ይህ ነበር፤

የአባት ትንቢት ምስጢር!!

 

የሚገርምን ማየታቸው፤

አልቀው ከዘመን አሻግረው፤

ለጤናም አልነበር ለትንግርት፤

የማይሆነው ሊሆንበት።

 

ጊዜ እንዲህ አሾፈች፤

ሁሉንም ደበላለቀች፤

ደምጥጣ ጨፈለቀች፤

መልካሙን ከዳች፤

እንዲሁም ክፉን ሁሉ ባንዴ አረገች።

 

የሚሆን ይሆናል የማይሆን አይሆንም፤

ምንግዜም የእውነት ዘንግ ወድቃ አትሰበርም፤

ይለኝ ነበር ጓጌ እንደ ዛሬ ሳይሆን፤

እውነት ሳትሰበር የማይሆነው ሳይሆን።

 

ዛሬ የጨለመ ነገ እንደማይበራ፤

አጥንትን ከስክሶ በደም እያጎራ፤

ታሪክ እየሻረ ሀሰት እያወራ፤

ያገኘውን ሽጦ ቀሪን እያሰማማ፤

በዝርፊያ ከድሀ በግፍ እየቀማ፤

ማጠፊያው ያጥረዋል በፍርድ ቀንማ፤

አገር ሲገነዘብ ታሪኩን ሲሰማ፤

ሚስጥሩ ሲወጣ ያለመው አላማ።

 

እንደምን ይማራል በጥቅም ታውሮ፤

አዕምሮው በልዞ ጆሮውም ደንቁሮ፤

በምን ምናምኑ ደንዝዞና ሰክሮ።

 

ከእባብ እንቁላለ እርግብን መጠበቅ፤

አንድም የዋህነት አንድም አልማውቅ።

 

አንዴ ከሰረቀ ለሌላው ያደባል፤

መቼ ጊዜ አግኝቶ ቅንነት ያስባል።

 

ሌብነት ተክና አደባባይ ወጣች፤

ባማረ ስያሜ ሙስና ተባለች።

 

በ(እ)ንቁላሏ ሲጀምር ያልቀጣች እናቱ፤

በሬ ሰርቆ መጣላት እስከነጅራቱ።

 

ልማድ ነው ሌብነት የማይሽር ጠባይ፤

ከመልካሙ ምግባር አእምሮንም ከላይ።

 

እጅ ከፍንጅ ያዙኝ ብሎ ከመስጋቱ፤

መቼ ይታየዋል መልካም በህይወቱ።

 

ሁሉም መልካም ሆኖ እንዳልተፍጠረ፤

ሌባም በመንገዱ ሄደ እየከረረ፤

እንደምን ይማራል በጥቅም ካወረ!!!!

 

ሌባ ተይዞ ዱላ ፊልጋ፤

ዳግም መጋበዝ ሌላ አደጋ።

ይባላል ከጥንት!

ለሌባ ቅጣት መልካም ትምህርት።

 

የሚሰማ ይስማ የሚማርም ይማር፤

ከሌባ ቅንነት የለም መልካም ምግባር።

 

ሰምተሀል አቅጩን ምንም አትጠብቅ፤

ባመቸህ ጎዳና ነጻነትክን ንጠቅ።

 


 

ፍሬው አንተነህ

03 01 2012

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ