ፊልጶስ

እንደ ይሁዳ ከዱ፣ ልጆችሽ ሸፈጡ

እንደ ኤሳው ሆኑ፣ ቡክርናቸውን ሸጡ

በመታመን ፋንታ፣ ኑፋቄን መረጡ።

እንደ ባህር አሸዋ - እንደ ሰማይ ከዋከብት

ምነዋ ኢትዮጵያ ... በዛብሽ ጠላት? ...

 

አፈርሽ ”ሰለሰ”፣ ሜዳሽ ”አሜክላ” እሾክ አበቀለ

ተራራ ሸለቆሽ ”ጃርት” ተራባበት - ተራብቶም ፏለለ፤

ባላና ማገርሽ፣ ምሰሶሽ ተማሰ

ዞብ አምባሽ ተናደ፣ ወንዝሽ ደፈረሰ

ደም እንደ ጎርፍ ውሀ፣ በገላሽ ፈሰሰ

ውጭ ውስጥሽ ነቀዘ፣ ቤት አጉራሽ ፈረሰ

ምነዋ ኢትዮጵያ ... ምፅአት ለአንች ደገሰ?

የሚታመን ጠፋ፣ ለሰው ልጅ ያደረ

ውሸት ገኖ ናኘ፣ በቀየሽ ከበረ

ዘብጥያ ወረደ፣ እውነትም ታሰረ

ታሪክ ተረት - ተረት፣ ብስራት ተበሰረ፤

የውርጃ ”አደፍ” ቅሪት፣ ጭንጋፍ አሳድገሽ

”ቃልቻ ዘር - ጎጥን”፣ ደም ተጠማልሽ

ጉድ ውልዶ ”አነበረ”፣ ግዜ ማህፀንሽ

ምነዋ እናት ምድር… ያልታየ ታየብሽ?

እንደ ይሁዳ ከዱ፣ ልጆችሽ ሸፈጡ

እንደ ኤሳው ሆኑ፣ ቡክርናቸውን ሸጡ

በመታመን ፋንታ፣ ኑፋቄን መረጡ።

እንደ ባህር አሸዋ - እንደ ሰማይ ከዋከብት

ምነዋ ኢትዮጵያ ... በዛብሽ ጠላት? ...

በቆብ ደፊ ”ሻሻም፣ ቀሳሽ መሳይ፣ ኮከብ ቆጣሪ ”

በቀን ሰባኪ፣ ማታ ጎፈሬ አበጣሪ

በደብተራ፣ ረጅም ተላባሽ፣ ካባ ተሞሻሪ

በዘንግ ተውረግራጊ ፣ ወገብ አሳሪ፤

ማህደረ ቅርስ ”ፅባወተ - መምበርሽ” ታምሶ

በዛር ፈረስ ደመ ነውጠኛ፣ መቅደስሽ ‘ረክሶ፤

የአምላክ ጻድቅ - ሰማአታትሽ ማደሪያ

ተቸበቸበቸበ ወ’ቶ ባደባባይ ደርቶ በገብያ

ታበዩ በእግዚአብሔር … ምነዋ ኢትዮጵያ …?

አንድ ቀን ለተለበሰ ”ጥቁር ካባ”፣ ለተደፋ ”ጥቁር ቆብ”

በሚሉ ከ’ኔ ወዲያ የለም ልሂቅ፣ አዋቂ፣ ለሀገር የሚያስብ

በሚመስላቸው እነሱ ብቻ የሆኑ ህዝብ፤

እየተራበ ያጠገባቸውን - እየታረዘ ያለበሳቸውን

ሳይማር ያስትማራቸውን - ሳይከፍሉት የከፍላቸውን

እየናቁት ያከበራቸውን - እየሞተ ያኖራቸውን

በረሱት፣ በከዱት፣ የገዛ ማንነት ወገናቸውን፤

በ’ነ ከረባት … ማ’ረጋቸው

በ’ነ ሆድ … አምላካቸው፤

በነሰለጠን ባይ፣ ደንቁረው አደንቋሪ ውስጠ ”አንኮላዎች”

ያልሆኑትን ለመሆን፣ በመስሎ፣ ህሊና ቢስ ሸፍጠኞች

በጥራዝ ነጠቅ ”ርዕዮት አለም” ሰባኪዎች

ያዩትን ያላዩትን ናፋቂ፣ በብልጭልጭ ኰተት ጎታች ተሸካሚዎች

የሀገር ርዕይ በሌላቸው፣ በቅዥታም፣ ተቀጥላ ጅራቶች፤

ተገዘገዝሽ! ... ተቦረቦርሽ! ... ተከፋፈልሽ! …

እንደ ቅርጫ ስጋ ገነጣጠሉሽ - ቸበቸቡሽ!

ምነዋ ኢትዮጵያ …………………..?

ምነዋ ኢትዮጵያ …………………...?

ባጠባሽ ተነከስሽ፣ ባጎረስሽ - ተበላሽ

አመድ አፋሽ ሆነ፣ የዚህ ዘመን እጅሽ።

እንደ ይሁዳ ከዱ፣ ልጆችሽ ሸፈጡ

እንደ ኤሳው ሆኑ፣ ቡክርናቸውን ሸጡ

በመታመን ፋንታ፣ ኑፋቄን መረጡ።

እንደ ባህር አሸዋ - እንደ ሰማይ ከዋከብት

ምነዋ ኢትዮጵያ ... በዛብሽ ጠላት? ...

ወግ ነው ሲዳሩ እንዲሉ፣ ”ተማሪ” ነኝ በሚሉ

ይይዙትን አ’ተው፣ ይጨብጡትን በዋለሉ

በመማሪያ የብእር ደም ብልቃጥ፣ ውሀ በሞሉ፤

በኮሌጅ - ዩኒቨርስቲው፣ በየትምህርት ቤት

የሚማሩት፣ የሚያገኙት የእውቀታቸው አይነት

የአድማሳቸው ልእልና፣ የ’ርካታቸው ጥማት

የወጣትነት ህይወታቸው፣ የጥበባቸው እድገት፤

አባትን ሳያውቁ፣ አያትን መጠየቅ

ሱሪ በአንገት ማጥለቅ፣ በጎጥ እድር መድረቅ፤

ዲስኮ … ጫት … ሀሽሽ ”ፓሪ” መንጎድ

ምነዋ እናት ሀገር …. ምነው ጠፋ ትውልድ።

እንደ ይሁዳ፣ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ

እንደ ኤሳው ሆኑ፣ ቡክርናቸውን ሸጡ

በመታመን ፋንታ፣ ኑፋቄን መረጡ።

እንደ ባህር አሸዋ - እንደ ሰማይ ከዋከብት

ምነዋ ኢትዮጵያ ... በዛብሽ ጠላት? ...

ርሀብ - እርዛት፣ ሰቆቃና ስደት

ስም መጠሪያሽ ሲሆን፣ አንች ባለሽበት፤

እርስ በርስ መባላት፣ ትውልድን ሲጨርስ

የፍትህ ያለህ ባይ፣ ዓለምን ሲያዳርስ፤

ወገኑን - ወገኑ፣ ገሎ ሲፎክር

ሀውልት ሲገነባ፣ በአንች ምድር አፈር

ምፃ’ተኛ ‘ሲኮን’፣ በገዛ ሀገር፤

ጥቂቶች ሲስቁ፣ ብዙሀን ሲያለቅስ

ኃጢአት ተትረፍርፎ፣ ፅዋው ሞልቶ ሲፍስ

ዘመን አልፎ ዘመን፣ ዛሬም ደም ስናፈስ

ምነዋ ኢትዩጵያ …………………?

ምነዋ እናት ምድር … ዝም አለ የአ’ች ነፍስ?

ፍርድ ስጭ ዝም አትበይ፣ ተይ አትታበይ

ዋጋ ይከፈለው፣ በዳይ - ተባዳይ

ይቅርም አባብይን፣ ወደፊት እ’ድናይ። …

የነፃ ህዝብ መልኩ ሰንደቅ አላማቸው

ባላደራ እናት ነሽ ቅርስ ያ’ርነታቸው።

አለሁ ካልሽ አለው፣ በይ መስክሪ በራስሽ

ከአንገቱ ተቃንቶ፣ ማየት የሚሽ ይይሽ። …

”ያላያ ኢትዩጵያ … የለሽም - እያለሽ

የጀመረሽ ምፅአት፣ ፍፁም ይጨርስሽ

ፀሀይ ከጨረቃ፣ ይጨላልሙብሽ

ከዋከብት ይርገፋ፣ ሰማይ ይደፋብሽ

እሳት ገሞራ፣ ይንደድ በላይሽ፤

ከምድር ገፅ ላይ ጠፍቶ ‘ምስልነትሸ’

ሲኦል ውረጅና ከነ-ግሳግስሽ

ዓለም ታሪክ ይፃፍ፣ እፎይ ይበልልሽ።”

-----//------

ፊልጶስ

/በመጨረሻወቹ ስንኞች ምን ለማለት እንደፈለኩ ፣ ወድ ኢትዮጵያዊያን እንደምትረዱልኝ እምነቴ ነው።/

ለአስተያየት በኢሜል፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ