ወግድልኝ ወዲያ (አሥራደው ከፈረንሣይ)
አሥራደው (ከፈረንሣይ)
ሲጭኑህ አጋሰስ፤
ሲጋልቡህ ፈረስ፤
ጠምደው ሲያርሱህ በሬ …
ስትታለብ ጥገት፤
በቁም ሲያርዱህ ሙክት፤
ሲጣልልህ ውሻ - የጅ ዕባሽ ናፋቂ፤
አዳሪ ለሆዱ - ክብሩን አስነጣቂ፤
ጫንቃህ የደለበ - ለመሸከም ቀንበር፤
እንቢኝን የማታውቅ - ከእሽታ በቀር፤
እንዳህያ ጭነት - ሸክም ያስለመዱህ፤
ሲገፉት ነፃነት - የማይበርደው ገላህ፤
አጎንባሽ ለመጣው - የሞትክ ነህ በቁም፤
ወግድልኝ ወዲያ ጭራሽ አላውቅህም!
እንዳንተ ያለውን አገሬ አትናፍቅም።
የአያት የቅድም አያት - ጀግንነቱ ቀርቶ፤
ሽለላ፤ ፉከራው - ዕምቢልታ ቀረርቶ፤
በጦር ደረት መብሳት - በጋሻ መክቶ፤
አሻፈረኝ ማለት - ለበደል ለጥቃት፤
በጀግንነት መሞት - ላገር ለነፃነት፤
መሆኑ ቀረና፤
የጀግና ልጅ ጀግና፤
ሰብዕናህ ተገፎ - ዝቅ ብለህ ወደታች፤
ባይተዋር ያገሩ - የበይ ተመልካች፤
ውሎ ጦም አዳሪ - የሀብቱ ተመጽዋች፤
እራስክን ዝቅ አርገህ - ክብርህን ያዋረድክ፤
የት ቦታ ተዘርተህ አገሬ ላይ በቀልክ?!
ወግድልኝ ወዲያ ጭራሽ አላውቅህም!
ለወለደህ ዕዳ ላገርህ ነህ ሸክም።
ንቀት ብርድልብስህ፤
ውርደት ሆኖ አንሶላህ፤
ነፃነት ሲገፉህ - ዝም ብለህ የተኛህ፤
ጭቆና ተስማምቶ - የማይቆረቁርህ፤
በደል የተመቸህ - ጥላቻ እማይገባህ፤
ዕንቢኝን የማታውቅ - እሺን ያስለመዱህ፤
ኧረ ለመሆኑ ከወዴት ተገኘህ?!
የቱ አባት አግኝቷት - ከምን ጉድ ጸነሰች፤
የቷ እናት አምጣ - ከቶ አንተን ወለደች?!
እንዳንተ ያለውን ወልዳ ከምታፍር፤
ምንኛ ደስ ባላት - ጨንግፈህ ብትቀር?!
አላውቅህም ጭራሽ ወግድልኝ ወዲያ!
እንዳንተ ያለውን አትሻም ኢትዮጵያ!!
አሥራደው (ከፈረንሣይ)
መስከረም 4 ቀን 2005 ዓ.ም (September 14/2012)