ወለላዬ ከስዊድን

ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ! 

ከልቦናህ ወሬ ለመቅዳት፤
ከአፍህ ነገር ለመስለብ
ወያኔ በነካካህ በቆሰቆሰህ ቁጥር፤
ተጠራርተህ በመሰባሰብ
ቁጣህን በአደባባይ ዘርግፈህ
ይውረድ በቃ! ብለህ ጮኸህ


አንድ መስለህ
አብረህ ቆመህ
በማግስቱ ተለያይተህ
ቡድን ፈጥረህ ተበጣጥሰህ
ተሰዳድበህ ተኮራርፈህ
ባንተው ዱላ አንተን መተህ
እንደገና ደግሞ በዓመት
ተገናኝተህ ጮኸህበት
ብትመለስ ሰዳድበኸው
ምን ሊጠቅምህ? ምን ልትጎዳው?
ምኞት ህልምህ ነፃነትህ
እየራቀ የድል ቀንህ
ይጨምራል ግፍ በደልህ
አሸንፈው በአንድነትህ

 

አለዛ ግን ጥንካሬውን እየለካ፤
ባንተ ሰቀቀን
እየዶለተብህ ሌት ተቀን
እየከፋፈለ በታትኖህ
አራርቆ አለያይቶህ
የሀገር ፍቅርህን አልቦ
ወኔህን ከልብህ ሰልቦ
ድምጥማጥህን ሳያጠፋ
ሳያጨልም ያንተን ተስፋ
እመነኝ እንደማያንቀላፋ።

 

አይግረምህ ይሄን ቢያደርግ
የጭካኔ ስራ'ኮ ነው የሱማ ወግ
እንደወባ ህመምተኛ፣ መጥፎ ቅዠት
መጨበጫ አሳጥቶህ፣ ባጉል ውሸት
የዘረኛ መለያውን ያንገት ክታብ
እላዩ ላይ አንጠልጥሎ በማዋከብ
በስቃይህ በርሃብህ በሞትህ ላይ
አይደል እንዴ? የሚአፈራው የሱን ሲሳይ

 

ከወጣማ ከበደል ሕግ
ካሳደረህ በወግ ማዕረግ
ኑሮህን ሳያዋክብ
አፍህን ሳይሸብብ
ነፍስህን ሳያሳቅቅ
አቅምህን ሳያደቅ
ዝም ብሎህ ከነጋበት
ሳያቆስልህ ከመሸበት
አንድ ሆነህ ተሰባስበህ
ጊዜ አግኝተህ ተመካክረህ
ታጠፋው የል ምን ያድርግህ
ደግሞስ እንደው ያ እንኳን ባይሆን
እንዴት ይስጥህ ሠላምህን?
ከየት ያምጣው አላመሉ
አለ ውልዱ አለ ትክሉ

 

ኢትዮጵያዊ ቅድመ ነፍሱ
ብሔራዊ እስትንፋሱ
በዘር ደዌ ተመርዞ
ውስጡ ሞቶ ተገንዞ
ሀገር ውደድ የምትለው
ያንን ፍቅር ከየት ያምጣው?
ለእኩልነት ምታንጋጥጥ
ነፃነትን ምትቀላውጥ
የት ኖሮት ነው ላንተ የሚሰጥ?

 

ምክር ልስጥህ ስማኝ ይልቅ
ሳትለያይ ሳትራራቅ
ሳትባባል ትንሽ ትልቅ
ከየቦታው ተሰባስበህ
ተመካክረህ ከስር ነቅለህ

 

ስቃይህን ስትግተው
ርሀብህን ስትጋብዘው
የሚሸሸው የፈራው ሞት
እላዩ ላይ ሲሰፍርበት
ያን ጊዜ ነው የሚአልቅለት

 

አለዛ ግን አንዳንድ ቀን ተሰባስበህ
ይውረድ በቃ! ብለህ ጮኸህ
ሰው ሲታሰር ፎቶ አውጥተህ
ሲሞትብህ ሻማ አብርተህ
አንድ መስለህ
አብረህ ቆመህ
በማግስቱ ተለያይተህ
ቡድን ፈጥረህ ተበጣጥሰህ
ተሰዳድበህ ተኮራርፈህ
ባንተው ዱላ አንተን መተህ
እንደገና ደግሞ በዓመት
ተገናኝተህ ጮኸህበት
ብትመለስ ሰዳድበኸው
ምን ሊጠቅምህ? ምን ልትጎዳው
ምኞት ህልምህ ነፃነትህ
እየራቀ የድል ቀንህ
ይጨምራል ግፍ በደልህ
አሸንፈው በአንድነትህ


ወለላዬ ከስዊድን
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ