የተሰደዱ ጠጉሮች (ከትንሣዔ)
የተሰደዱ ጠጉሮች
ከትንሣዔ (ሰኔ 2000 ዓ.ም.) (በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ)
የጊዜ ዑደቱ በራስ ላይ የመጣ፣
ወለላዬም ሽበት ትንሣዔም መላጣ።
ሆነን አየንና በዘመን መስተዋት፣
ቁልቁልም ወረድን ወጣንም አቀበት፤
ግራ አጋባንና መመለጥ መሸበት።
ተረት ሆነን ልንሞት ታሪክ ሳንሰራ፣
ብልጭ ብለን ጥፍት እንደ ባለ ተራ።
እያልኩ ሳስተውል ሳስብ ስመረምር፣
እጅግ ጥልቅ ሆነብኝ የተፈጥሮ ምስጢር።
መመለጥም ይሁን የመሸበት ጣጣ፣
ምንጩ ከውስጥ ነው ፈንቅሎ እሚወጣ።
የንጥረ ነገር እጦት በማነሱ መብል፣
የከባቢው አየር ሂደቱን ሲያጋግል።
የራስ ቅል አጋላጭ ጦሰኛው መላጣ፣
ለካስ መገንጠሉ በዘር ነው እሚመጣ።
ብርዱንና ቁሩን ተጋፍጦ ፊት ለፊት፣
ሸፍኖ በኖረ ይህን የኔን አናት፤
በብሩሽም ስልግ ሳበጥር ጎፈሬ፣
እንዳሻህ ያለኝን ላንተ ነው መኖሬ፤
በጅ የያዙት ነገር ንቄው ከገለባ፣
እኔው አጣጣልኩት እንደ ጥቅም አልባ።
ከአናቴ ያልተለዩ በደጉም በክፉ፣
ጠጉሮችም ነበሩኝ ከራሴ የጠፉ።
ያልተንበረከኩ ቅጫም ሲንሰራፋ፣
ቆም ቆም የሚሉ ስናደድ ስከፋ።
ቅባት ጠፋ ብለው ያልተንከረደዱ፣
ከራስ ቅል መለየት ጨርሶ እማይወዱ።
ለካስ አሉኝ ጠጉሮች ከኔ ያልተለዩ፣
በስደት ስፍራ ላይ መከራ የሚያዩ።
የሚበጠር ጠጉር ከአናቴ የጠፋ፣
እነርሱ በቅለው ነው በገደል በፈፋ።
አወይ ስደት ክፉ ሁሉን የሚያሳንስ፣
መጠየፍ አይችልም ቁሻሻ ግሳንግስ።
ከአናት ተኮፍሶ እንዳልኖረ ኮርቶ፣
በአፍንጫ ቀዳዳ ይውላል ተኝቶ።
ደምቆ እሚበቅልበት የራስ ቅል ሳይጠፋ፣
ንፍጥ ውስጥ እየዋኘ ይኖራል በተስፋ።
ካልጠፋበት ቦታ የራስ ቅሉ ሜዳ፣
ጎፈሬ በቀለ በአፍንጫ ቀዳዳ።
ሌቶች እያነሱ ቀኖች እያጠሩ፣
አወይ የእድሜ ነገር መሮጡ መብረሩ።
የተገፉት ጠጉሮች ከመሀል እራሴ የተነቃቀሉ፣
ስደት መረጡና ቀን እስቲያልፍ እያሉ፤
ጆሮ ኩስ ላይ በቅለው ይተራመሳሉ።
ስደት መንከራተት መች አሸነፋቸው፣
የወዛቸው ማማር የአጠቋቆራቸው፤
ከቀጭኔ ጭራ ባይበልጥም እኩል ነው።
ይሁን ተመስገን ነው አለኝ ማለት ደጉ፣
ሰዋራ ስፍራም ቢሆን ይኑሩ ይደጉ።
የብብት፣ ያፍንጫ የጆሮም ቢባሉ፣
ይብዙ እንጂ ይባዙ ይኑሩ ይብቀሉ፣
በጥቅል ሲጠሩ ጠጉርም አይደሉ?
ፊደል እየገደፉ አሉ እንጂ መላ አጣ፣
የኔስ መጠርያዬ መላ አምጣ መላ ኣምጣ።
ከርስታቸው ከራስ ቅል መገንጠል ግድ ለሆነባቸው እንዲሁም ስደት ቁልቁል ላወረዳቸው ጠጉሮች መታሰብያ ይሁን። ነጥተውም ገርጥተውም ቢሆን የራስ ቅልን የሙጥኝ ያሉ ሽበቶችም ከፍ ከፍ ይበሉ።
በትንሣዔ ተጻፈ
ሰኔ 2000 ዓ.ም.