ጀግና አይደለንም ወይ?

ከወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

(Read on PDF)

መቼም የሚያቃጥል የሚያጨስ አይጠፋ

አንዱ ትናንትና እሰው ፊት በይፋ

በጀግንነታችን እንደሚጠራጠር

ቃላት አሳምሮ ሰማሁኝ ሲናገር

 

”ለሦሰት ሺህ ዘመን ድንቁርና ማርኮን

ከክፉ አስተዳደር መላቀቅ አቅቶን

ኋላ ቀርነትን ረሃብ ሳንዋጋ

ጀግና ነን ብትሉኝ አልሰጠውም ዋጋ

መሬቱን ጠብቀን ብንይዝም ከጠላት

እንደልብ በልተን ካላጋሳንበት

እላዩ ገንብተን ካላስተማርንበት

ወንዞቹን ለልማት እንዲውሉ አድረገን

ገቢ ካላመጣን በብዛት አምርተን

ምኑን ጨብጠን ነው የምንባል ጀግና

አልሸትህ ብሎኛል የወኔያችን ቃና

ነጭን ብናስወጣም አባረን ከሀገር

ሥልጣን የጨበጠ እኛን መሳይ ጥቁር

በዘር ተደራጅቶ ተነስቶ በእብሪት

አሳጥቶ ነፍጎን መብትና ነፃነት

በቁም እየሞትን ምንድነው ጀግንነት

ማፍረጥረጥ አለብን ይሄንን ገበና

አገር ወዳድ እንጂ አይደለንም ጀግና

የትም አያደርስም በከንቱ መጎረር

ጀግንነታችንን እናሳይ በተግባር

እሱ እራሱ መሪው በፍርሃት ታምቆ

ሲወጣ ሲገባ ተጠቦ ተጨንቆ

ህዝቡን እያዞረ እሱ ባለፈበት

እምኑ ላይ ይሆን የኛ ሰው ጀግንነት

ዘመኑ ሠልጥኖ ባይኖር ቴሌቭዥን

ባላወቅነው ነበር ገጽታውን የሱን

የቀድሞ ሠራዊት የመንግሥት አመራር

እንደዛ ሲጠፋ በአንድ ቀን አዳር

ጀግና ነን ማለቱ አይገባኝም ጭራሽ

ፍራቻም እንዳለች ጠፍቶ ነው አስታዋሽ”

በማለት አንስቶ ፈጥሮብን ጭቅጭቅ

አመሸ ሲያጨሰን ልባችንን ሲያደርቅ

አያትና አባቴ ከጠላት ተናንቀው

ላገራቸው ክብር እጦር ሜዳ ወድቀው

እኔ በሶማሌ የቀድሞ ወረራ

በሰሜኑ ክፍል በኋላም ኤርትራ

በፈጸምኩት ጀብዱ ስሜ የተጠራ

መሆኔን ዘንግቶ ሲናገር እኔ ፊት

ንቀት አይደለም ወይ ዓይን ያወጣ ድፍረት

ግድ የለም ይቅርብን እኛስ እንረሳ

ላገሩ የሞተው የቋራው አንበሣ

እነ ዘርዓይድረስ እነዛ እነ አብዲሳ

እነ አሞራው ውብ ነህ እነ አበበ አረጋይ

ጠላትን ያሰኙት እጦር ሜዳ ዋይ ዋይ

ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ

ፈረሱን እንደሰው ያስታጠቁት ሱሬ

አሉላ አባ ነጋ እነ እራስ ጎበና

ምን እንበላቸው ካልተባሉ ጀግና

ቆራጡስ አርበኛ ያ በላይ ዘለቀ

ምን ታሪክ ሊኖር ነው ሥራው ከተናቀ

ያሁኑ የቅርቡ ለገሠ ተፈራ

በጀት ያነደደው የጠላትን ጎራ

የፈጸመው ጀብዱ ምን ይባል ሲወራ

ወራሪን ተናንቀው በየጦሩ ሜዳ

ተቀብረው የቀሩት የቆጠሩት ፍዳ

ለዲሞክራሲና ለህዝብ እኩልነት

ተሰልፈው ወጥተው ሕይወት የገበሩት

ጀግና አይደሉም ካልን ጭራሽ ከተረሱ

ምን አይነት ሰው ይሆን ታሪክ ሠሪ ለሱ

እንደ ወሬውማ እንደሱ አነጋገር

ኖረች ማለቱ ነው በታምር ይቺ ሀገር

ያውም ተምሬአለሁ ነኝ የተመራመርኩ

የሚል በመሆኑ ተናደድኩም አፈረኩ

በሌላው ግድ የለም ጨዋታ ቢያመጣ

ይሄ ግን አጉል ነው ያስከትላል ቁጣ

በዚህ ተናድጄ ስጨስ በማደሬ

ደሜ ሰማይ ወጣ ከፍ አለ ስኳሬ

በሉ ተናገሩ ቁርጡን በዚህ ጉዳይ

ዓለም ያደነቀን ጀግና አይደለንም ወይ?


 

ከወለላዬ ሐምሌ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. ስዊድን

July 31, 2008 Sweden

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ