ምርቃትና እርግማን

ከትንሣዔ - ሐምሌ 2000 ዓ.ም. (በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ)  

 

የእውኑን አለም በምኞት ዳበሳ፣

ስንዘግን ስንበትን ስንወድቅ ስንነሳ።

ወይም ስንማማል እቴ ሙች እቴ ሙች፣

ዘመን እያለፈ ዘመን ይልና ከች፤

በታሪክ አጊጠን የዛሬን ተዋርደን፣

እንዲህ ነው እንዲያ ነው ጥግ ይዘን ዳር ቆመን።

አልያም ስንሰደድ ከሀገር ስንጠፋ፣

አገርም ሲሸቀጥ ጎርቤት ሲስፋፋ።

አንዴ በምርቃት አንዴ በእርግማኑ፣

ስንቀባባበት መሽቶብናል ቀኑ።

ነገንም ብንተወው ሰጥተነው ለእግዜሩ፣

መክሊቱን ለጣለ የርሱም ዝግ ነው በሩ።

 

አይለየን አንድ ያርገን መጥተን አንጣችሁ፣

ገደል ግብት ይበል በክፉ ያያችሁ።

እደጉ ተመንደጉ ውለዱ ክበዱ፣

ጎተራችሁ ይሙላ ምቀኞች ይንደዱ።

ምርቃት ስንሰጥ ምርቃት ሲያድሉን፣

ሁለት እጅ ዘርግተን ስንል አሜን አሜን።

ምርቃቱ ሁሉ አልሆን ብሎ እንጀራ፣

ስደት ብቻ ሆነ ሁሉም በየተራ።

ይኸው ስደት አገር ጎተራ ተሞልቶ፣

ለሰው አገር ልማት ይባዝናል ተግቶ።

መጥተን አንጣችሁብለው የመረቁ፣

ፈረንጅ አገር ድረስ በ’ኢንቪቴሽን’ መጡ።

ይቺን አገር ስጠን ባሻን እንፈንጭባት፣

ብለው የተሳሉም ይኸው ቦረቁባት።

 

አልገባም ላላቸው እውቀት በምርቃት፣

እርግማን ዘነበ የሚያወርድ መዓት።

ያጥፋህ የአባቴ አምላክ ጊዮርጊስ ድፍት ያርግህ፣

መልአከ ሚካኤል ይስበር ይሰንጥርህ።

ወልደሽ አትሳሚ መሀን ሆነሽ ቅሪ፣

ባክነሽ ባክነሽ ሙቺ ያሳጣሽ ቀባሪ።

እርግማኑ ሁሉ ሰይጣን ጆሮ ገብቶ፣

ያድለው ጀመረ ጨምሮ አብዝቶ።

ጧሪም የሌላቸው ወልደውም ያልሳሙ፣

የሚቀጠፍ ወጣት የሚፈሰው ደሙ።

ስፍር ቁጥር አጣ እግዜርም ጨከነ፣

ጣልቃ አልገባም ብሎ ሰዉ በለመነ።

 

ኢትዮጵያ አልቀደመች በመፈክር ብዛት፣

ልቦና አላስገዛን ቢበዛ ፀሎት ቤት።

አእምሮ ከሰጠን አስቦ እሚሰራ፣

ምርቃቱ ባዶ እርግማኑም ተራ።

እስቲ እርግማን ይብቃ ምርቃት ይቀነስ፣

እውቀት እንዲከበር ስራም እንዲወደስ።

ልዩነት አክብረን በአምሳያ እንስማማ፣

እውን ሊሆን የሚችል ይኑረን ዓላማ።

ጸሎታችን ሁሉ ፍቅር ይሁን አንድነት፣

ለእድገት ብልጽግና እናስገባ ሥለት።

ከ ትንሣዔ

ሐምሌ 2000

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ