አይደለንም ጀግና (ከሀገሬ)
ከሀገሬ - ነኀሴ 2000 ዓ.ም.
ኧረ እነግርሃለሁ አይደለንም ጀግና
ዓለም ያደነቀን እኛን መች ሆነና
በአያት ቅድም አያት በጥንት ታሪካችን
በእርግጥ ተከብረናል በጀግንነታችን
አልዋሸህም እኔ ያ እኮ ድሮ ቀረ
ለሀገር መሰዋት ጀግንነት ነበረ
ዛሬ ግን እውነቱ ካላልን እንዋሽ
ጀግኖች አይደለንም በፍፁም በጭራሽ!
ምናልባት ሆነን እንደው የጀግኖቹ ልጅ
አልያም ከሆንን የጀግኖች የልጅ ልጅ
ከሆነ ነው እንጂ እኔ አልስማማም
ጀግና ባሁን ዘመን ኧረ ፍፁም የለም
አትንደድ በቁጣ አይጣልህ በሽታም
ይህ እውነታ ነው ጀግናስ ዛሬ የለም
ብንሆንማ ጀግና ልክ እንዳባቶቻችን
ዝም አንልም ነበር ሲሸጥ መሬታችን
እስቲ አንተ ንገረኝ የታል ጀግንነቱ
ማንስ ምን አረገ ሲወሰድ መሬቱ
እባክህ ወንድሜ ጀግኖቹን ተዋቸው
ነቅተው እንዳያፍሩ አትቀስቅሳቸው
ዝም እንበል እኛ እነሱን አናንሳ
መሆን አቅቶናል እንደነሱ አንበሳ
በል እስቲ ንገረኝ አንተ የጠየከው
ወለላዬ አልከኝ ከስዊድን ያለኸው
እውነት ጀግና ብንሆን ዓለም ያደነቀን
እንተኛ ነበር አሁን በዚህ ዘመን
የቋራው መሬት ሲወሰድ እያየን
ሊያውም የጀግናችን የቴዎድሮስ ካሣ
ለሀገሩ የሞተው ለሕይወቱ ሳያሳሳ
ስለዚህ ወንድሜ ብትወድም ብጠላም
ዋጥ አርገው እውነቱን ጀግናች አይደለንም!
ከሀገሬ
ነኀሴ 2000 ዓ.ም.
(“ጀግና አይደለንም ወይ?” ለሚለው የወለላዬ ግጥም የተሰጠ ምላሽ)