ጌታቸው አበራ

ለ’ክቡር’ ጠቅላይ ሚኒስትር፣
ለኢህአዴግ ሊቀ-መንበር፣
ጠቅላይ ‘አዛዥ’ ለ”ኣግዓዚ” ጦር ...፤

ይድረስ ለአቶ ኃይለማርያም!
በስምዎ ባዘሏት ወላዲተ-አምላክ ...
በወልድ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ልያዝዎ፣
ኢትዮጵያን በጥይት አያቃጥሏት ...
እግዚአብሔር አባት ይቅር ይበልዎ!

በደርግም ሆነ በወያኔ ዘመን ባገር ያሴሩ፣
እስከዛሬ ህዝብን ሲያስጨፈጭፉ የኖሩ፣
“እግዚአብሔርን አናውቅም” ብለው የካዱ ነበሩ፤
እርስዎ ግን፣
ከቤተሰብዎ ጋር ማዕድ ሲጋሩ፣
የየዕለቱን ጸሎትዎን ሲያበስሩ፣
የአምላክን ስም ነጋ-መሸ እየጠሩ፣
ይመስለኝ ነበር በእምነት የከበሩ፤

... ግና ከልብ እውነት ካልዘመሩ፣
ትዕዛዛዊ ቃላቱን ካልተገበሩ፣
እምኑ ላይ ነው ታዲያ አምልኮዎ?
የአምላክን መሻት መፈጸምዎ?
ከአረመኔዎች ጋር ተሰልፈው፣
እግዜርን ከካዱ ጋር አብረው፣
እባክዎን ህዝቡን አያስጨርሱት፣
ይተዉማ ይመልሱት፣ አዋጅዎን ይቀልብሱት፣
ለዕልቂት “ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” ያሉትን ...
ተጸጽቻለሁ ብለው ይሻሩት!
ካልቻሉም ይመንኑ፣
ባገር ላይ ቅስፈት ከሚተውኑ!

የእነሱንማ ይተዉት ...
የነያሬድ፣ የነገብረመስቀል ... ዘሮች ሆነው፣
ከጽላቱ ማደሪያ ምድር ተፈጥረው፣
መስቀሉን ያሳደዱ፣ ታቦቱን ያዋረዱ፣
ፈጣሪያቸውን በይፋ የካዱ ...፣
በደም ልክፍት ያበዱ ...፣
ናቸውና ባገርና በህዝብ ሕይወት የሚቀልዱ ...፣
ይድረስ ለርስዎ - ለኃይለማርያም የምልዎ፣
“እምነት ማተብ አለኝ” ስለሚሉ፣
በእየሱስ ክርስቶስ ስለሚምሉ፣
እውን ከሆነ ማተብዎ - እንዲከበር ነው ህያው ቃሉ!

... የወለምታውን ጉዞ - ገና ከጠዋቱ ሲጀምሩ፣
የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊነት - ለ”ከንቱው የሰው ልጅ” ሲቸሩ፣
ትንሿ ልጅዎ ነበረች - “ምነዋ አባዬ ...” ብላ ያረመችዎ፣
በዜጎችዎ ላይ ጦርነት ሲያውጁ - ዛሬስ ማን “ሃይ” ይበልዎ?!
የዓለምን ገዢ ጌታ - ክቡር እግዚአብሔርን ከፈሩ፣
ቃለ-እየሱስ ክርስቶስን - በእውነት ከልብዎ ካከበሩ፣
እባክዎ ጦርዎን መስበቅ ያቁሙ - ጎራዴዎንም ወዳ’ፎቱ ይመልሱ፣
ባረመኔ ኣግዓዚዎች - የንጹኃን ዜጎችን ደም አያስፈስሱ!


ጌታቸው አበራ
ነሐሴ 2008 ዓ.ም.
(ኦገስት 2016)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ