ያሬድ ጥበቡ

የኢትዮጵያዬ ጭንቋ
ግፍ አለማወቋ
እንደ ሌሎች ህዝቦች፣ አለመጨፍለቋ
አለማዋሃዷ፣ አለመለንቀጧ
አንድ አለማድርጓ
በሆደ ሰፊነት ልዩነት ማክበሯ
ነው ያገሬ ታሪክ፣ ነው ያገሬ ክብሯ።


ሆኖም በዚህ ቻይነቷ የተመነደጉ
የከበዱ ያደጉ
ክብሯን ሊያሳንሱ
ታሪኳን ሊያጎድፉ
ሰንደቋን ሊያወርዱ
መዝሙሯን ሊፍቁ
ተነሰተው ቆመዋል
ይሄው ይፎክራሉ
ድምፃቸው ይሰማል
አገሬን ሊያጠፉ ቆርጠው ተነስተዋል።
አይሆንም እላለሁ
ኢትዮጵያ አትጠፋም ብዬ እዘምራለሁ።
ኢትዮጵያ ምንድን ናት ለሚለው ጥያቄ፣
አገር ናት ይሉኛል
መንግሥት ናት ይሉኛል፣
አገሬ የፓስፖርት ሰነድ ናት ይሉኛል፣
ማንነት የሌላት፣
ካለም የተለየች፣
ሆደሰፊነቷ ምንም ያደረጋት
የአብሮነት እምነቷ ማንነት ያሳጣት
የቻይነት ብሂሏ ራሷን ያጠፋት
የማይሞትላት፣ የማይሰየፉላት
የማይራራላት፣ የማይዋደቁላት
ማንነት የሌላት፣ ምንነት የሌላት
ፈርሳ ምትሰራ፣ የሸክላ አፈር ናት
ብለው ይዘምራሉ።
በግፍ በተሠራ ዜግነት ስር ቆመው፣
አቦሪጂን ሰልቅጦ
ቀይ ህንድ አላምጦ
ነጭ ባረገ አገር፣ ደመና ስር ቆመው
ያፍሪካን ጥቁርነት የወሰነችውን
ያቺን ኢትዮጵያዬን
ይወነጅሏታል፣
ስሟን ያጠፏታል፣
ማንነት የሌላት ብኩን ያደርጓታል።
እንደ ሸክላ ሰብረው፣
አድቅቀው አለንቁጠው፣
እንደ አዲስ ሊሠሯት ይመካከራሉ
አቦ፣ አይሆንም በሏቸው
እረፉ በሏቸው
የገረሱን አገር፣
የአቢቹን ምድር
የጃጋማን አፈር፣
የአበበ ቢቂላን፣
የጥላሁን ገሰሰን፣
የደራርቱ ቱሉን
የታላቁን ወታደር የአበበ ገመዳን
የጄኔራሎቹ ዋነኛውን ቁንጮ፣ የሙሉጌታ ቡሊን፣
ጀግናው ቀነኒሳ በደረቱ ይዞ የመረሸላትን፣
እንዴት ቢደፍሩ ነው?
ማንነት የሌላት ወድቃ ምትሰበር የሸክላ አፈር ናት
ብለው የሚያረዱን።
ለምን?
በበቀል፣ በኃይል ስላልጨፈለቀች?
በሕገመንግሥቷ "ያንተ ዜግነትህ፣
ሲሶ ነው፣ ሩብ ነው" ስላልደነገገች?
ወይስ እንደ ቀዩ ሕንድ
በክልል አጥር ውስጥ፣ አስራ ስላልያዘች?
ከቶ ምን አጠፋች?
ምንስ ተገኘባት?
ከዓለም አስለይቶ ባይተዋር ያረጋት
ማንነት የላትም የተፈከረባት
ከቶ ለምን፣ ለምን?

ዛሬ ቅዳሜ ኖቬምበር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የፕሮፌሰር ፀጋዬ አራርሳን "ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነት የለም" የሚለውን ከSBS ሬዲዮ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ ከሰማሁ በኋላና አርቲስት እይዩ ፈንገስ ያነበበውን "አገሬ" የተሰኘውን የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥም ካደመጥኩ በኋላ የተሰማኝ ስሜት፣

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ