Yared Tibebu. ያሬድ ጥበቡበፍቃዱ ደረጀ

- ጻድቃን እንደ እኛ ሊያስብ ይችላል፣
- ሕጋዊ ማዕቀፎችን እንጠቀም፣
- አዲስ አበባ አድጋለች መጎብኘት ባልችልም፣
- የመለስ ጥሩ ስራ ህወሓትን ከሌሎች ድርጅቶች እኩል አድርጎት መሄዱ ነው

ያሬድ ጥበቡ ኢህዴን የተባለውን ብአዴን ከመሰረቱ ግለሰቦች አንዱ ነበር። ሲታገል ሲታገል ቆየና ከዕለታት አንድ ቀን የዓመት እረፍት ተሰጠው፤ ይህንን የእረፍት ጊዜውን በዋና እንደሚያሰልፍ ቀድሞ የተረዳው ወዲ ዜናዊ፤ ተከዜ ላይ ለምን አንዋኝም ሲል ግብዣ አቀረበለት። ሳያቅማማ ተቀበለው። የመለስ ዜናዊ ጦር እየወጋው ቢሆንም ያሬድ አንዳች ነገር ሳይሰማው ወደ ተከዜ ወንዝ ተጓዘ። እንደደረሱም ጨዋታ ፈረሰ፣ ዳቦ ተቆረሰ። ከዛሬ ጀምሮ የኢህዴን አመራር አይደለህም፤ ሁለት ምርጫዎች አቀረበለት … ብርሀኑ ነጋ የሄደበትን መንገድ መርጦም፤ በፓርት ሱዳን አድርጎ ዲሲ መኖር ከጀመረ 30 ዓመት ሊሞላው የጳጉሜን መጥባት እየተጠባበቀ ነው።

በነዚህ ወቅቶች ያሬድ ጥበቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዎንታዊም አሉታዊም ማልያ በማጥለቅ፤ ለደደቢትም ለፋሲል ከነማም ሲጫወት ታይቷል። አንዳንዴ የሚሰጣቸው አስተያየቶች ሲያስገርሙ፤ እንዴ ሰውየው ሲያስብሉት ኖረዋል። በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት ለኃይሉ ሻውል ወግነሀል ያሉት ወገኖች ውርጅብኛቸውን በአካል፣ በኢሜይል፣ በስልክ ሲያከናንቡት እንደነበረ “ኑዛዜ ዘያሬድ” በተሰኘው መጣጥፉ ተናግሯል። ይህ ሁሉ ግን ያመነበትን በአደባባይና በድፍረት ስለሚናገር ነው።

የያሬድ ፖለቲካ ይመቸኛል፤ ከመንጋው ተለይቶ ማሰብን ተክኖታል። ከጎኑ እልፍ አእላፍም ቆሙ፤ እልፍ ብለውትም ቢቆሙ ያሬድ ያው ያሬድ ነው። ለሀገራችን በተለይም አዲስ ለሚመጣው ፖለቲከኛ ማሸጋገር ካለብን የያሬድን ፖለቲካ ከፓኬጆቹ መሀል ማስገባት ብልህነት ይመስለኛል።

ያሬድ ጥበቡ ከኢሳት ቲቪ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስም በጥሞና እንዳያልቅብኝ በመሳሳት ተከታትየዋለሁ። ከኤርምያስ ለገሰ ጋር የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ቢኖርም ሁለቱም የወያኔን ፖለቲካ ጠንቅቀው ማወቃቸው ነው። ከውስጥም ከውጭም ሆነው ወያኔን አይተውታል፤ ውይይታቸውም መደማመጥና ክርክር የነበረበት ነው፤ ያሬድም አቅዋሙን በማያሻሙ ቃሎች ሲገልጽ ጥያቅዎቹን ሲመልስ ታይቷል።

ፖለቲካ እንደጊዜው ሁኔታ መቀየር አለበት ሲል ተናግሯል። አሁን ያለውን የወልቃይት ችግር ከህዝቡ ጋር የቆሙ የብአዴን አባላት ይዞ ቢጓዝ ውጤታማ ያደርጋል፤ እነሱንም አይዟችሁ ስንላቸው ህዝብ የላከው ምንም አይፈራምና ትግሉ ውጤታማ ይሆናል ሲል ተናግሯል። የብአዴንን አመራርና ህዝብ አይዟችሁ ስንላቸው፤ አሃ ወያኔ ቢገፋን እንኳ የሚቀበለን ህዝብ አለ የሚል ልብ ልብ ይሰጣቸዋል።

ያሬድ እውነቱን ነው ሶቭየት ሕብረትና አሜሪካ፤ ጀርመን የተባለችውን ሀገር ለሁለት ሲገዟት ከቆዩ በኋላ፤ አሜሪካ የመጠቅለል ፍላጎት አደረባት፤ ስለሆነም በሶቭየት እጅ የነበረውን ምስራቅ ጀርመን ግዛት ባለሥልጣኖች በሄዱበት ስታስቀር፣ የምስራቅ ጀርመን ወታደሮችም ወደ ምዕራብ ጀርመን እየከዱ ሲገቡ፤ ህዝቡ ሆ ብሎ ሲቀበላቸው፤ ምስራቅ ጀርመን ተንኮታኮተ። በሂደትም የበርሊን ግንብ ፈርሶ ሀገራቱ አንድ ሆኑ።

የኢያሪኮ ግንብ የሆነውን ወያኔን ለማፍረስ፤ ሥርዓቱን ከድተው ለሚመጡ ባለሥልጣኖች ዋስትና ልንሰጣቸው ይገባል። የሥርዓቱ ዋነኛ አሽከርካሪዎችም ካጠገባቸው የነበረ ታማኝ ሎሌያቸው ሲጠፋ፤ ብቻቸውን እንደቀሩ ይገባቸውና እነርሱም መውጫቸውን ይፈልጋሉ።

እንደ ያሬድ አባባል፤ ብአዴን ለወያኔ አልገዛም፣ የእስከዛሬው ይበቃል ቢል፤ ሌሎች አጋር ድርጅቶችም ሊከተሉት ይችላሉ። 6 ከመቶ የሚሆን ህዝብን የሚወክለው ፓርቲ (ህወሓት) 94 ከመቶውን የሚያንበረክክበት ምንም ምክንያት የለውም። ስለሆነም ፓርቲያዊ እምቢተኝነት ከብአዴን ቢጀመር፤ አጠቃላይ ሀገራዊ አብዮት ያስነሳል።

በአፍላዎቹ ዕድሜው ለአስር ዓመታት በኢትዮጵያ በረሃዎች ሲታገል የነበረው ያሬድ፤ ዛሬም በጉልምስናው ወራት የሕብረ ብሔር ካባውን ለብሶ በለው ሲል ይሰማል። ይህ እድለኛም ቆራጥም መሆንን ይጠይቃል። በነገራችን ላይ ወልቃይት አማራ ነው፣ ትግራይ ነው የሚለው ሰሞነኛ ክርክርን ለመጀመሪያ ጊዜ ወልቃይት አማራ ነው፤ እኔም በቦታው ነበርኩኝ፣ ከወልቃይት ህዝብ ጋር ታግያለው ሲል በፌስቡክ ገጹ የመሰከረው ራሱ ያሬድ ነው።

የያሬድን መንገድ ተከትሎ የብአዴን አባላትን እስከ አመራሩ ድረስ ደጀን ቆመን የወልቃይት ህዝብ ያነሳው ጥያቄ እልባት እንዲያገኝ መስራት ብልህነት ነው። ጊዜ የለም አዎን፤ እንፍጠን ወገን እየተዋደቀ ነው፤ ነጻነት ከደጃፋችን ናት፤ በራችንን እያንኳኳች ነው፤ አዎንታዊ ምላሽ እንስጣት ... የትግል ንድፈ ሃሳቦችን እያዋጣን ወደ ተግባር እንመንዝረው።


* ይህንን ርዕስ (ወልቃይት፣ ያሬድ ጥበቡና ጄኔራል ጻድቃን) ሳላስፈቅድ የወሰድኩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባንድ ወቅት በፌዴራል ፓሊስ አዛዥ የተወቀሰበትን ጄኔራል ጻድቃንና የሰሜን አፍሪካ አብዮት ብሎ ከሰየመው መጣጥፉ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ