Ali Mahfouz ወጣት ዓለም ደቻሳን አሰቃይቶና አንገላቶ በመኪና ያፈናት ዓሊ ማህፉዝ“አጥቂው ላይ ተገቢ ርምጃ እንዲወሰድበት ወስነናል” የሊባኖ የሥራ ሚኒስትር

Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 5 ቀን 2004 ዓ.ም. March 14, 2012)፦ በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ውስጥ ካለው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽ/ቤት ፊት ለፊት በአንዲት ኢትዮጵያዊት ወጣት ላይ ድብደባና እንግልት ሲፈጽምባት የሚያሳይ ፊልም ከተሰራጨ ወዲህ በአለም ዙሪያ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ክፉኛ ቁጣ እንዳስነሳ የተለያዩ አለም አቀፍ የዜና አውታራት ዘገቡ።

 

 

ይህ በሞባይል ካሜራ የተቀረጸ ፊልም ወጣቷ አረብኛ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች ተከባ ስትመታና ስትንገላታ ያሳያል። በመሀከላቸው አንዱ መሬት ላይ ወድቃ በጀርባዋ እንደተንጋለለች ክንዷንና ጸጉሯን እየጎተተ ሲያንገላታትና ጩኸቷንና ልመናዋን እየሰማ በቸልተኝነት በመተው በጉልበት መኪናው ላይ ሲጭናት ይታያል።

 

የፊልሙን መሰራጨት ተከትሎ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ቁጥር ቁጣቸውን እያሰሙ መሆኑንና በተለይ በፌስ ቡክ አማካይነት ውግዘታቸውን እየተቀባበሉ ስለመሆኑ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን አውታሮች እየዘገቡት ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያዊያኑ ቁጣ በወጣቷ ዙሪያ ቆመው ጥቃቷን የሚመለከቱ ሊባኖሳዊያን ዝምታን መምረጣቸው ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በተለይም በአጠገቡ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ሰራተኞች ከፊት ለፊታቸው የሚፈጸመውን ግፍ ለማስቆም ያለመሞከራቸውን አምርረው ኮንነዋል።

 

‘ያ ሊብናን’ (YA LIBANAN) የተሰኘው የሊባኖስ ጋዜጣም “ፊልሙ የሀገሪቷን መንግስትና መገናኛ ብዙሀን ያስገርማቸው እንጂ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን ግን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚሰሩ ሴት ዜጎቻቸው ላይ በየጊዜው የሚፈጸመውን ግፍ እንደ አንድ ማሳያ ሆኖ ነው ያገኙት።” ብሏል።

 

አለም ከዚህ ቪድዮ መታዘብ እንደሚችለው በመካከለኛው ምሥራቅ ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን በተመለከተ ያለው አያያዝ ሰብአዊነት የጎደለውና በጭካኔ የተሞላ ነው። ይህ ቁጥጥር የማይደረግበት ጭቆና መቆም አለበት።” ስትል በኒው ዮርክ የኢትዮጵያዊያን ማህበራዊ ትብብር ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆነችው ወ/ት ዘውዲቱ ፍስሃ ማሳሰቧን ያ ሊብናን አጣቅሶ ጽፏል።

 

“ድርጊቱን የተመለከቱት ሁሉ የተፈጸመው ወንጀል ስለመሆኑ አምነዋል።” ሲል የገለጸው ዋና ቢሮውን ቤይሩት ያደረገው የአገሪቷ ቴሌቭዥን ሲሆን፣ ሪፖርተሮቹም በቪድዮው ላይ የሚታየውን የመኪና ታርጋ ተከትለው ባደረጉት ምርመራ ወንጀለኛው አሊ ማህፉዝ የሚባል ሰው መሆኑን ደርሰውበታል።

 

ኢትዮጵያዊቷን ወጣት ያለርህራሄ ሲደበድብና ሲያንገላታ በግልጽ በቪድዮው ላይ የሚታየው አሊ ማህፉዝ  ግን ጥፋት መፈጸሙን ለማመን ፍቃደኛ ሆኖ አልተገኘም። እንዲያውም የቤት ሰራተኛዋ ከአንድ ጊዜ በላይ ራሷን ለማጥፋት ስትሞክር እሱ ሰብአዊነት በተሞመላ መንገድ እንዳረጋጋት ለቲቪው ጋዜጠኞች ገልጿል።

 

የሀገሪቱ የሥራ ሚኒስተር ሳሊም ጂሬይስቲ ግን አጥቂው ላይ የሚወሰድ እርምጃ እንደሚኖር ለጋዜጠኞቹ ጠቁመዋል።

 

አሊ ማህፉዝ በእሳቸው ስር በሚተዳደረው የቤት ሰራተኞችን ጉዳይ በሚመለከተው ቢሮ ውስጥ የሚሰራ ሰው ሆኖ በመገኘቱ ተጨማሪ ሀፍረት ውስጥ የከተታቸው የሥራ ሚኒስትሩ፤ “ጥቃት ፈጻሚውን በተመለከተ አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ወስነናል።” ያሉ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውንም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። (ኢትዮጵያዊቷ ስትንገላታ የሚያሳየውን ፊልም ለመመልከት የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!