በዓይናችን አሳየን (ብርዞ)
በዓይናችን አሳየን
ብርዞ ከፍራንክፈርት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ኅዋ ድረስ ያመጠቀን ጥዑመ ዜማ ቅኝት
ድንበሩን ጥሶ ያለፈ የማይታዘዝ ለምድር ስበት
በስሜት ተውጦ አካልህ ሲፈነዳ ተመንጭቆ
ልሳንህ በኛ ላይ ገዝፎ ስነልቦናችን ተሰርቆ
ሲታደስ በዜማህ ነፍሳችን ሲርመሰመስ በደማችን
የፈቃድ ሞት እየሞትን በመድረክ ድል ተደርገን
ተቃኝቶ ተቀናብሮ መሣሪያው ሲያስተጋባ
እንደ አውሎነፋስ ተሽከርክሮ በጆሮአችን ሲገባ
ጣዕመ ዜማህ ሲንቆረቆር ቆልምመህ ስትንሳፈፍ
ከመስማት አልፎ አየነው ሕይወት አግኝቶ ሲከንፍ
ምዕተ ዓመት የሰው ልጅ ዜማን ሲሰማ ቆይቶ
እንድናይ አረገን ማይክል በአካሉ ኖታውን ሠርቶ
ፀሐይ ግለትዋን አውሳህ አዝጋሚ ጉዞን ጨረቃ
በማይታመን ተሰጥዖህ መሬት አንተን አድንቃ
እያየ ኪነ ተዓምር ፍጡር ተወልዶ ሲከስም
እየመሸ እየነጋ እስከወዲያኛው ዝንተዓለም
ፈቃድዋ እስካለ ምድር በሰው መኖሪያነትዋ
የማይደገም አቀንቃኝ ማይክል ይሆናል አንደበትዋ
ነፍስህ ፀጋን ትታደል የማያልቀውን የገነት
የአቢሲኒያ ምርኮኞችህ ያስታውሱሃል በፀሎት
ለጋሽ ጥላሁን አድርስልን የከበረውን ሠላምታ
ከኛ ጋር አብሮ አለ በዕለት ተለት ትውስታ
ለማይክል ጃክሰን መታሰቢያ
ብርዞ ከፍራንክፈርት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.