“አትንገር” ብሎ ነገረው (ወለላዬ)
“አትንገር” ብሎ ነገረው (በPDF አስነብበኝ)
ወለላዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. July 31, 2009
“አትንገር” ብዬ እኔ ብነግረው፣
“አትንገር” ብሎ እሱም ነገረው።
እንኳን ነገረው እሰይ ይበለኝ፣
“ንገረው!” ነበር ማለት ያለብኝ።
“ንገረው!” ብለው “በደንብ አስረዳ”፣
አይነግርም ነበር እኔን ሊጎዳ
እኔን እራሴን ማን አወቀብኝ፣
“አትንገር” ብለው እንደነገሩኝ
ብንነጋገር ሁሉንም ነገር፣
“ንገር” - “አትንገር” ባልመጣ ነበር።
ፈስ አምልጧቸው እኔ ሰምቼ፣
“አትንገር” ብዬ ለሰው አውርቼ፣
እሱም “አትንገር” ብሎ ሲያሰማ፣
በቅብብሎሽ ሰፈሩ ገማ።
“አትንገር” ብዬ እኔ ብነግረው፣
“አትንገር” ብሎ እሱም ነገረው
እንኳን ነገረው እኔም ይበለኝ፣
“ንገረው!” ነበር ማለት ያለብኝ
ጉንድሻቸውን ሲያያቸው አይተው፣
ንጉሥ ያንን ሰው ብቻውን ጠርተው፣
“ይሄንን ነገር ብትነግር ለሰው፣
በአደባባይ ነው ደምህ ’ሚፈሰው ...”
ብለው ንጉሡ ስለነገሩት፣
እንዳያወራ ሞት አስፈርቶት፣
በዝምታውም በጣም ተጨንቆ፣
በረሃ ወርዶ እጫካ ዘልቆ፣
እዛ ላገኘው ዛፍና ጉድባ፣
“ንጉሡ ጉንድሽ ነው” ብሎ እቤቱ ገባ።
“አትንገር” ብዬ እኔ ብነግረው፣
“አትንገር” ብሎ እሱም ነገረው
እንኳን ነገረው እኔም ይበለኝ፣
“ንገረው!” ነበር ማለት ያለብኝ
ቤቱ ሲፀዳ ሰው ሲሰበሰብ፣
አለምክንያት ሲባል ሸብ እረብ፣
እሰው ጅሮ ላይ አፉን ሰክቶ፣
ወሬ ሲያጎርሰው ያኛውም ሰምቶ፣
እሱም ሌላውን ወጣአርጎ ከቤት፣
ሹክሹክታ ሲይዝ ያየች እመቤት፣
ባሏን ስታገኝ የማታ ማታ፣
እጎኑ ሆና አልጋ ላይ ወጥታ
“እንዴት ነው ዛሬ የማየው ነገር፣
ምን ሆነ ሰዉ? ... በዛ ግርግር”፣
ብላ ስትለው ባልየው ሰምቶ፣
አፉን ጆሮዋ ጥግ አስጠግቶ፣
“የናትሽን ሞት ጠዋት ሊያረዱሽ፣
ነውና ዝም በይ! ተኚ እንዳልሰማሽ ...”
ብሎ ተናግሮ ይችን ተንፍሶ፣
ለማታ ሆነ የጠዋት ለቅሶ።
“አትንገር” ብዬ እኔ ብነግረው፣
“አትንገር” ብሎ እሱም ነገረው።
ይልቅ ትልቁ ዋናው ቁምነገር፣
“አትንገር” ብሎ አለመናገር፣
አያድርም ውሎ ወሬው አለው ክንፍ፣
አንዴ ከወጣ ካመለጠ ካፍ
ዛሬማ ይበልጥ ነገሩ ቀሎ፣
ወሬው ይነፍሳል “ሃሎ!” ተብሎ
ካስፈለገውም ልዩ መረጃ፣
ያወራልሃል ደቅኖ መቅጃ
ይሻላል ጭራሽ አፍን መቆለፍ፣
በወሬ ትብትብ ከመቆላለፍ
በፖለቲካም በመወሻሸቅ፣
አንዱ ሊነግረው አንዱ ሲደብቅ፣
ያልተነገረው ያልሰማ መስሎ፣
በሌላ መልኩ እሱም ሰልሎ፣
በፀብ ጥላቻ በመለኳኵስ፣
ይጋብዙሃል ዘለፋና ክስ፣
የቆሙበትም አብይ ዓላማ፣
ሳይታይ ታሞ ውስጡ እየደማ፣
በወሬ ምች በሐሜት ካንሰር፣
ሠላሙ ጠፍቶ ከስሞበት ፍቅር፣
በባህል ኪኒን በቤት መድኃኒት፣
ሐኪም ሳያየው ይደርሳል ለሞት።
እንዲሁም ምስጢር ያሉትን ነገር፣
እንደማንችል አቅፎ ማሳደር፣
አፌ አውጥቶብኝ ልቤ እያወቀው፣
“አትንገር” ብዬ ለሱ ብነግረው፣
“አትንገር” ብሎ እሱም ነገረው።



