እንቆቅልሽ (ቦጋለ ዳኜ)
እንቆቅልሽ
ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርኒያ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
አልተው ካለን - ልጅነቱ
እንመለስ - ወደጥንቱ
ቀርቦልናል - እንቆቅልሽ
እስቲ እንበል - ምናውቅልሽ
“እንቆ … ቅልሽ!”
“ምና … ’ውቅልሽ!”
“ማርና ሬት - ተለውሷል
ለመለየት - ብልሃት ጠፍቷል።”
እንቆቅልሽ - በእንቆቅልሽ
ለመተርጐም - ቢገኝ ምላሽ
በተናጠል - ለማሸነፍ
በፉክክር - ጥሎ ማለፍ
ያም መጣ ያም መጣ - ተከታትሎ
ፊደላትን - አቀጣጥሎ …
ኢጭአት፣ ሰደድ፣ - ኢዴአፓ፣
መኢሶን፣ ሊግ፣ - ወይ ኢሠፓ፣
ኢዲዩ በል - ሕብረት፣ ጥምረት፣
ወይ ቅንጅት፣ - ግንቦት ሰባት፣
መላ አማራ፣ - ኦብኮ፣ ኦነግ፣
አረና በል - መድረክ፣ ኦብነግ፣
ብዙ ጠራን - ሌላም ሌላም
ጥያቄውን - ለመተርጐም
ይሁን እንጂ - እኚህ ሁሉ
መልስ አይደሉም - በመባሉ
በ“ዋለብህ - አደረብህ”
መልሱን መስጠት - ከተሳነህ
ሀገር ስጡን - አምጡ ተባልን
ከዚያም ሰጠን - ሀገር ቆርጠን …
ባሕረ ነጋሽ - ምድሪ ባሕሪን
አሰብ ጭምር - አዱሊስን
ነገር ግን - እኒህ ሁሉ
በቂ አይደሉም - በመባሉ
ኢትዮጵያን - አጠቃልለን
ተጨማሪ - ሀገር ሰጠን።
ከዚያም ተባልን - “ቁልጭልጬ
ኢትዮጵያ - ተቀምጬ
ምን አጥቼ - ሁሉ በእጄ
ሁሉ በእጄ - ሁሉ እደጄ
እንዳልሰድብህ - ወንድሜ ነህ
እንዳልተውህ - ጠላቴ ነህ
ቁልጭልጬ - ቁልጭልጬ
ኢትዮጵያ - ተቀምጬ
ምን አጥቼ - ሁሉ በእጄ
ሁሉ በእጄ - ሁሉ እደጄ
ንግዱ በእጄ - ባንኩ በእጄ
ብሩ በእጄ - ወርቁ በእጄ
ምርጫው በእጄ - ሳጥኑ በእጄ
ሥልጣን በእጄ - ፖሊስ በእጄ
ዳኛው በእጄ - ሸንጎው በእጄ
ጦሩ በእጄ - ታንኩ በእጄ።”
ስለዚህ - መላው ጠፍቶ
በዝቶ - ትብትቡ
ከምንባል - ሀገር የለም
ገደል ግቡ - እንባ አንቡ
ማሩን ከሬት - የሚለዩ
ማር እንጀራ - የሚያቀርቡ
ንብ አንቡ - ንብ አንቡ
ንብ አንቡ - ንብ አንቡ
ጥያቄው - ቢኖረውም
አያሌ መልስ - ሀለሐመ
ተመርጦ - በትክክል
አንደኛው - ካልቀለመ
መውደቅ ነው - በፈተና
ሀገር የለም - አከተመ።
እንቆቅልሽ - ለማስፈታት
ወርቅና ብር - ሽቶ ጭና
ሠሎሞን ዘንድ - ባሕር ማዶ
የምትሔድ - እንደገና
አንፈልግም - ያዜብ ንግሥት
እውቀት ጠፍቶ - መች ሆነና?
ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርኒያ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



