የዓድዋ ድል የአንድነት ውጤት ማሳያ ነው!
125ኛ የዓድዋ ድል በዓል
ለዛሬው ማንነታችን ያበቁንን እኒያ ጀግኖች ያቆዩልንን አገር ለማሻገር ውለታቸው ቢኖርብንም፤ በዘር፣ በብሔር፣ በቋንቋ ተቧድነን ስንራገጥበት ማየት ያሳፍራል
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ኢትዮጵያውያን የዛሬውን የካቲት 23 ቀን በየዓመቱ ማክበራቸው ግድ ነው። የዛሬ 125 ዓመት ኢትዮጵያውያን በቅኝ ገዥዎቹ እጅ እንዳትወድቅ የፈጸሙት ገድል እና ያገኙት ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለድፍን ጥቁር ሕዝብ አንፀባራቂ ኾኖ ዘላለም የሚወሳ ጭምር ነው። ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለምን ሕዝብ በማስደመም የሚገለጽም ነው። ምስጋና ለኒያ አያት ቅድመ አያቶቻችን ይሁንና፤ ኢትዮጵያውያን አትንኩኝ ባይነትን ያረጋገጡበትም ነው።
ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥዎች መዳፍ እንዳትወድቅና ነፃነቷ ተጠብቆ እንድትኖር ካደረጉ ድሎች ሁሉ የዓድዋ ድል ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው በመኾኑ፤ ሁሌም የምናከብረው ይኾናል። አፍሪካውያን ድል ማድረግ እንደሚችሉ ምሳሌ የኾነውን ለሌሎች ቅኝ ተገዥ አገሮች ድል ፋና ወጊ ነው።
የዓድዋ ድልን ስናስብ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ተነቃንቀው በአንድነት ኾነው ያስገኙት ውጤት መኾኑ በተለየ የምናስበው ነው። የድሉ መሠረትም ከአገር ማፍቀር እና መውደድ በላይ፤ በአንድነት በመቆም የተገኘ ውጤት ነው። ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጾታ ሳይለይ በአንድነት ተጋምዶ የተከፈለው መሥዋዕትነት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አገር ለመኾን ያበቃ ጭምር ነው።
አገር ሲደፈር ልዩነትን አስወግዶ፤ “እንቢኝ ለአገሬ” ማለት የኢትዮጵያውያን መለያ ኾኖ ዛሬም ድረስ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲዘልቅ ካደረጉ የኢትዮጵያውያን የጋራ ገድሎች ውስጥ የዓድዋ ድል ተጠቃሽ ነው።
ስለአገር በአንድ መቆም አሸናፊ የሚደረግ ስለመኾኑም ጥሩ ማስተማሪያ ነው። በዓድዋው ጦርነት ከአራቱም የአገሪቱ ማዕዘን የተመመው ኢትዮጵያዊ በአንድ ኾኖ ያስገኘው ድል ነው።
ዛሬ በኩራት የምንዘክረው የዓድዋ ድል የትብብር ውጤት ነው። ለዛሬው ማንነታችን ያበቁንን እኒያ ጀግኖች ያቆዩልንን አገር ለማሻገር ውለታቸው ቢኖርብንም፤ በዘር፣ በብሔር፣ በቋንቋ ተቧድነን ስንራገጥበት ማየት ያሳፍራል። ተባብሮ ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር የታዩ ድሎቻችንን ወደ ጐን ገፍተን፤ በመንደርና በጐጥ ተቧድኖ የአገር ሾተላይ ሲበቅል ማየታችን፤ ከአያትና ከቅድመ አያቶቻችን ድል በተፃራሪ መቆም ይኾናል። ስለዚህ ኢትዮጵያን ስናስብ ልክ እንደ ዓድዋው ጀግኖቻችን በአንድነት ቆመን ስለአንድ አገራችን ልንሠራ ይገባል።
በዘር ተቧድኖ፣ በመንደር ተከፋፍሎ ጉዞ፤ አገርን የሚያሻግርና ለዜጐች የሚፈይደው ነገር ባለመኖሩ፤ አንድ በመኾን ድል ማድረግ እንደምንችል በየዓመቱ በዛሬው ዕለት የምንዘክረው የዓድዋ ድል በዓል ምሳሌ ይሁነን!
በየትኛውም መስክ አሸናፊ የሚኾነው ተባብሮና ተሳስቦ ሲሠራ ብቻ መኾኑንም እንቀበል። አገር ከሚበታትን ከፋፋይ የፖለቲካ ቁማር በመውጣት፤ በጋራ ሠርተን የጋራ ድል ባለቤት እንሁን! የቀደሙ ኢትዮጵያውያንም ይህንን አሳይተውናልና ቀጣዩ ትውልድም የዓድዋ ድል የነፃነት ገድላችን ብቻ ሳይኾን የትብብር እና የአሸናፊነት ምሳሌ በማድረግ ይቀጥል።
ከብሔርተኝነት የጸዳ ፖለቲካ ይኑረን። ኢትዮጵያውያን ነን ብለን እናስብ። የሚያምርብንም የምናሸንፈውም በጋራ ስንኾን ብቻ ነው። (ኢዛ)



