መንግሥት ለራሱም ሲል አፋጣኝ እርምጃ ይውሰድ
የኑሮ ውድነቱ መንሥኤ ብዙ ሊኾን ቢችልም፤ ቢያንስ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች በበቂ እንዲቀርቡና ዋጋቸውንም ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል።
ያለአግባብ የተበዘበዘ ሕዝብ፤ ውሎ አድሮ በዝባዡን መጠየቁ አይቀርም
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ኑሮ ተወደደ። አሁን በየአቅጣጫው የምንሰማው ወሬ ኾኗል። በእርግጥም ኑሮ ተወድዷል። የመሸመት አቅም ወርዷል። የብር የመግዛት አቅም ቁልቁል እየሔደ ነው። ገበያውም በዚያው ልክ ይፋጃል።
አንድ ኩንታል ጤፍ ለመሸመት አምስት ሺሕ ብር ይጠይቃል። አንዱ ኩንታል ዱቄት ለመግዛት አራት ሺሕ ብር ይጠራል። መላ ያጣው እና ሌብነት የሚያሽከረክረው የዘይት ገበያ፤ አሁንም አልተረጋጋም፤ ዋጋው ተሰቅሎ እንደቀረ ነው። እጥረትም አለ። በነጋዴ እጅ የሚገኝ ዘይት ከዚህም በላይ ይጨምራል በሚል እሳቤ እየተደበቀ ነው።
የኮንስትራክሽን ግብአቶች ዋጋ በተመሳሳይ እየጨመረ፤ የግንባታዎች እንቅፋት ከኾነም ሰነባብቷል።
መሠረታዊ ከሚባሉት ሸቀጦች ባሻገር እንደ መኪና ያሉ መገልገያዎችም ስንት ጨመሩ ሲባል በመቶ ሺሕ ብሮች ዋጋቸው ጨምሮ አጀብ እያሰኘ ነው። ከእንቁላል አቅም አንዲት ፍሬዋ ሰባት ብር እየተሸጠች ነው ሲባል፤ ጐበዝ ወዴት እየሔድን ነው? ያስብላል።
የዋጋ ውድነቱ ጐልቶ የታየው ደግሞ ነዳጅ ጨመረ ከተባለ ወዲህ ነው። የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ኋላቀርና በአቦ ሰጠኝ የሚካሔድ፣ ማንም እየተነሳ ዋጋን የሚሰቅልና የሚጥልበት ስለኾነ፤ የኾነ ምክንያት ከተፈጠረ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ጉድ የሚሰኝ ነው።
ሰሞኑን ነዳጅ 20 በመቶ ጨመረ ሲባል፤ በአዲሱ የነዳጅ ዋጋ ነዳጅ መሸጥ ሳይጀምር ወዲያው የሸቀጦች ዋጋ ጨመረ። ይህ የሚያሳየው የግብይት ሥርዓቱ ፍጹም ብልሹ መኾኑንና የስግብግብ ነጋዴዎች ይሉኝታ ቢስነትን ነው።
በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንተና የ20 በመቶው የነዳጅ ጭማሪ ኢኮኖሚ ውስጥ የተወሰነ የዋጋ እድገት ያስከትላል። የነዳጅ ጭማሪ የማይነካካው ነገር የለምና የዋጋ ለውጥ መኖሩ አይታበልም። ነገር ግን ቢበዛ በገበያ ውስጥ የሚያመጣው የዋጋ ለውጥ ከሦስት በመቶ ያልበለጠ ስለመኾኑ የሚገልጹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፤ አሁን የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ግን በመቶ እና በሁለት መቶ በመቶ መኾኑ የኑሮ ውድነቱን የበለጠ አብሶታል።
ቋሚ ገቢ ያላቸው ዜጐች ምንም የገቢ እድገት ባላገኙበት ሁኔታ ቀድሞም እየከበደ የመጣው የኑሮ ውድነት አሁን በነዳጅ ጨመረ ሰበብ እየታየ ያለው ሁኔታ አደገኛ እየኾነም ነው። ዜጐች ጐርሶ ለማደር የሚቸገሩበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ይህ ደግሞ በዚሁ ከቀጠለ እንደ አገር ፈታኝ ይኾናል።
መንግሥት ቅጥ ያጣውን የዋጋ ንረት በተገቢው መንገድ እየተቆጣጠረ አለመኾኑ ደግሞ ሁኔታውን አብሶታል። ሕገወጥ ተግባራት መበራከታቸውና ይህንን በአግባቡ ሃይ የሚል መጥፋቱ ለሁኔታው መባባስ የራሱ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ገበያውን ለማረጋጋት አሁንም መንግሥት ወሳኝ እርምጃ ካልወሰደ ጦሱ በራሱ በመንግሥት ላይ መኾኑም መታወቅ አለበት። ኑሮው እንዲህ ሊወደድ የቻለው ለምንድነው ብሎ መፈተሽ እና መፍትሔ ሊያመጣ የሚያስችል እርምጃ መወሰድ አለበት።
የኑሮ ውድነቱ መንሥኤ ብዙ ሊኾን ቢችልም፤ ቢያንስ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች በበቂ እንዲቀርቡና ዋጋቸውንም ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል።
በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ብዙ ማጭበርበሮች ያሉ በመኾኑ ይህንን ተከትሎ መፍትሔ ካልተሰጠም ችግሩን መቅረፍ አይቻልም።
ያለአግባብ ጭማሪ የታየባቸውን ምርቶች በመለየት ማነው ይህንን ያደረገው ካልተባለና ተጠያቂው ዛሬ ካልተለየ፤ ነገም ይቀጥላል።
ስለዚህ የኑሮ ውድነቱ የከፋ ኾኖ ለማስተካከል ከሚያስቸግርበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት፤ መንግሥት በራሱ በኩል መውሰድ ያለበትን እርምጃ ይውሰድ፤ የንግዱ ሕብረተሰብም ቢኾን ባልተገባ ጭማሪ ሕብረተሰቡ እንዲማረር ምክንያት ከመኾን መቆጠብ አለበት።
ያለአግባብ የተበዘበዘ ሕዝብ፤ ውሎ አድሮ በዝባዡን መጠየቁ አይቀርም። ሁሉም በየፊናው የበኩሉን በማድረግ የገበያውን ግለት መቀነስ ይኖርበታል። (ኢዛ)



