ሞት ይብቃን!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የ2019 (እ.ኤ.አ) የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን የተቀበሉበት ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ በኖርዌይ ርዕሰ ከተማ ኦስሎ ነበር።
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የፊታችን መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን የተረከቡበት ሦስተኛ ዓመታቸውን ሊያከብሩ ጥቂት ቀናት ቀርቷቸው፤ አሁንም ሰዎች በዘራቸውና በሃይማኖታቸው መገደላቸው ያልቆመው ለምንድነው?
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የንጹሐን ዜጐች ሕይወት ሲጠፋ ነበር። ከለውጡ ወዲህም ንጹሐን በሰበብ በአስባቡ ደማቸው ሲፈስ፤ አካላቸው ሲጐድል ዓይተናል። ሰምተናል። እየሰማንም ነው። ቤት ንብረታቸው ሲቃጠል፣ በገዛ አገራቸው ስደት እጣ ፈንታቸው የኾኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች የአገሪቱን ፖለቲካ ቅጥ ማጣት የሚያመለክት ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል። ዜጐች በብሔራቸው፣ በሃይማኖታቸው እና በማንነታቸው እየተለዩ በቁማቸው እላያቸው ላይ እሳት ሲለኮስ፣ አንገታቸው ላይ ካራ ሲያርፍ፣ ደረታቸው ላይ ቀስት ሁሉ ተወንጭፎ እስከ ወዲያኛው ሲያሸልቡ ማየት ያማል። አንዱ ጋር የተለኮሰ እሳት ጠፋ ሲባል፤ ሌላ ቦታ እንደገና ሲንቦገቦግ። በእሳቱ የተለበለቡት ዜጐቻችንን ቁጥር ካሰላን የትየለሌ እየኾነ ነው። መቁጠር ስላቆምን ቁጥር መጥቀስ አያስፈልገንም።
ዜጐች በገዛ አገራቸው ሃይማኖታቸው፤ ብሔርና ዘራቸው እየተቆጠረ የሚፈጸምባቸው ዘግናኝ ተግባራትን ማንም ይፈጽመው ማንም፤ በብርቱ የሚወገዝ ነው። ኢትዮጵያዊም ሰዋዊም አይደለምና። በሃይማኖት ደረጃ የትኛውም ሃይማኖት የሰውን ልጅ ሕይወት ቅጠፍ ብሎ አያስተምርምና። ከሃይማኖት ውጭም ኾነ በሰውኛ፤ ካንተ ውጭ የሌላኛውን ሰው ሕይወት ቅጠፍ የሚል አስተምሮት በተለይ በኢትዮጵያ አልነበረምና።
እነዚህን በዘር፣ በብሔርና በሃይማኖት ምክንያት በአደጋ የተከበቡ ዜጐችን ለመከላከልና ቢያንስ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ያለመቻሉ ደግም ይቆጫል። ከቁጭትም በላይ ነገሩን የበለጠ የሚያደርገው፤ ይህንን ዘግናኝ ተግባር ይፈጽማሉ የተባሉ ቡድኖችን አደብ ማስያዝ ሳይቻል፤ አሁን ድረስ መቀጠሉ ነው።
በእርግጥ ባለፉት ሁለት - ሦስት ዓመታት የሞትና የግጭት ምክንያት የኾኑ ድርጊቶች በሕወሓት ቡድን ስፖንሰርነት ስለመካሔዳቸው የሚያረጋግጡ እውነታዎች ያሉ ቢኾንም፤ ከሕወሓት መፈረካከስ በኋላም የተደራጁ ቡድኖች ዛሬም የንጹሐንን ዜጐች ደም እያፈሰሱ ነው። ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደ ኦነግ ሸኔ ባሉ ቡድኖች እየተፈጸሙ ስለመኾኑ ሰሞኑን የፌዴራል ፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።
ስለዚህ በተለይ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የንጹሐንን ዜጐች ደም በማፍሰስ እነዚህ ቡድኖች ተጠያቂ ናቸው ከተባለ፤ ሰው እየገደሉ፣ ንብረት እያወደሙ እስካሁን ለምን ቀጠሉ? የሚለው ጥያቄ በደንብ መፈተሽ አለበት። በመንግሥት አገላለጽ በተበጣጠሰ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ቡድኖች የዜጐችን ደም እያፈሰሱ እንዳይቀጥሉ መንግሥት እየወሰድኩ ነው ያለው እርምጃ፤ ቡድኖቹን ያለማዳከሙ ወይም ጊዜ ጠብቀው ቦታ እየቀያየሩ የሚያደርጉት ጥቃት የመቀጠሉ ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ከዚህም አልፎ “እውነት አገሪቱን የሚመራ ‘መንግሥት’ አለ ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ዜጎች እንዲጠይቁ እያስገደደ ያለ ጉዳይ ነው።
ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ ባለፈው ዓመት በየሳምንቱ የዜጐችን ሕይወት የቀጠፉ ጥቃቶች ተፈጽመው እንደነበር ነው። ይህ እዚህም እዚያ የሚለኮስ ውጉዝ ተግባርን እያደመጥን ግን መቀጠል የለብንም። ዜጐች ሞቱ፣ ዜጐች ቆሰሉ፣ ዜጐች ንብረታቸው ተቃጠለ ሲባል፤ ገዳዩም፣ አቃጣዩም ይታወቃልና ይህንን በየጊዜው የሞት ድግስ የሚደግሰውን ማንኛውም አካል አደብ ማስገዛትና ለሕግ ማቅረብ የመንግሥት ኃላፊነት ነው።
እከሌ ተብሎ ከሚጠቀሰው እና ለዜጐች ሞት ምክንያት ከኾነው ቡድን ባሻገር ግን በመንግሥት ጉያ ሥር የተሰገሰጉ አስተኳሾችም እንዳሉ መካድ አይቻልም። ይኽ ካልኾነ በስተቀር እንዴት ላለፉት ሦስት ዓመታት በዜጎች ላይ እንዲህ ያለው የሞት ድግስና ጥቃት ይፈጸማል?
ከቀድሞ አመለካከታቸው ያልተለወጡ በመንግሥትና በመሪው ፓርቲ የታቀፉ የውስጥ ጠላቶች ባይደገፉ፤ ዜጐች እንደዋዛ በጠራራ ፀሐይ ደማቸው አይፈስም ነበር ብሎ ማሰብም ግድ ይላል።
የዶክተር ዐቢይ መንግሥት እንዲህ ያሉትን ምናልባትም የማይሽሩ ጠባሳዎች ሊፈጥሩ የሚችሉ ጥቃቶችን በአግባቡ ለመቋጨት ካልቻለባቸው ምክንያቱም አንዱ ይኸው በጉያው የያዙዋቸውና ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው አመራሮችን በአግባቡ ያለማጽዳት እንደኾነ ተደጋግሞ ተነግሯል። ይህም ቢኾን ግን መንግሥት የዜጐቹን ደኅንነት መጠበቅ ግዴታው እስከኾነ ድረስ፤ ጊዜ እየጠበቀ የሚሰማው ዘግናኝ የዜጐችን ሞት ማስቆም ያለበት አሁንም መንግሥት ነው። ኃላፊነቱም የራሱ የመንግሥት ብቻ ነው።
መንግሥት በሰበብ በአስባቡ በሚፈጸሙትን ጥቃቶች እና የዜጐችን ሞት ሊያቆም ይገባል። አንዱን ቀብረን ሌላውን ለመቅበር የምንጠብቅ ኾነን መዝለቅ አይቻለንም።
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የፊታችን መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (ከዛሬ አሥራ ሁለት ቀናት በኋላ) ሦስተኛ ዓመት የሞላውና የአገሪቱን የመንግሥት ሥልጣን የተረከቡበት ዕለት ነው። ዛሬም ድረስ ላለፉት ሦስት ዓመታት ዜጎች በዘራቸው፣ በማንነታቸው እና በሃይማኖታቸው እየተገደሉ ይገኛሉ። ግን ለምን? የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት እንዴት ነው በሦስት ዓመት ውስጥ የዜጎችን በሃይማኖት፣ በዘር እና በማንነት መገደል ማስቆም ያቃተው? ገዳዮቹ ሕወሓትና መሰሎቹ ኦነግ ሸኔዎች መኾናቸው ተደጋግሞ ተነግሮናል። ታዲያ መንግሥታቸው የንጹሐን ዜጎችን መገደልና ጥቃት በሦስት ዓመት የሥልጣን ዘመኑ እንዴት ማስቆም ያቅተዋል? አሁንም ለምን ዜጎች ይገደላሉ፣ ይጠቃሉስ?
ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታ የማታውቀውን ሰውን ዘቅዝቆ እስከ መስቀል የደረሰ አረመኔያዊ ተግባርና ሃይማኖትን፣ ዘርን እና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ዋነኛ ምክንያት ግን በኢትዮጵያ የተተከለው የዘር ፖለቲካ ውጤት መኾኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። አሁንም የምናያቸው ጥቃቶችና ውዲቷን የሰውን ልጅ ነፍስ የሚያሳጡ ድርጊቶች በዚሁ ከዘር ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ስለመኾናቸው እርግጥ ነው።
ስለዚህ ይህንን ኢትዮጵያን እየቧጨረ፣ ዜጐቿን እያሸማቀቀ፣ ነፍሳቸውን እየቀጠፈ እና አገሬ ብሎ በሰላም እንዳይኖር እያደረገ ያለው የብሔር ፖለቲካ ይብቃህ ሊባል ይገባል። ዘርን መሠረት ያደረጉ ግድያዎች አደገኛ የሚኾኑት ዛሬ በአንድ ወገን የተወረወረው ቀስት፤ በሌላ ጊዜ ከሌላኛው ወገን ምላሽ ሊሰጥበት የሚቻልበት አጋጣሚ የመፈጠሩ እውነታ የሁላችንም ሥጋት ጭምር በመኾኑ ነው።
ዕድሜ ልካችንን አንዱ ተኳሽ፤ ሌላው ተመቺ። በሌላ ጊዜ ደግሞ፤ ተኳሽ የነበረው የሚተኮስበት እየኾነ ታሪካችንን እንዲህ በደም ዕዳ ማጠላለፍ ፈጽሞ የሚጠቅመን ባለመኾኑ፤ ኢትዮጵያችን ከዚህ አዙሪት ትወጣ ዘንድ ሁሉም ወደቀልቡ ይመለስ። በተለይም መንግሥት የዜጎቹን የመኖር፣ የማንነት፣ የነፃነት፣ … መብት ይከበር ዘንድ ከማንም በላይ የመሥራትና የማረጋገጥ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል።
ሞት ይብቃን!! ዘርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካችን ማብቂያ ይኑረው!!! በአንድነት ስለ አንዲቷ ኢትዮጵያ የምንሠራና የምንተጋ እንኹን። ይህንን መስመር ለማስያዝ የዘር ፖለቲካን በማውገዝ ሁሉም ይተባበር!!!! የዜጐቻችንም ሞት ይቆም ዘንድ አሁንም የመንግሥት ብርቱ ሥራ ወሳኝ ነው። መንግሥት ዜጐቹን የመታደግ፣ የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ሞት ይብቃን!!!!! (ኢዛ)



