በብልሹ አሠራሮች ጭምር በእዳ የጐበጠች አገር
ከ780 ቢሊዮን ብር በላይ በእዳ የተዘፈቁት ሰባት የመንግሥት ድርጅቶች
ወያኔ ሲያራምደው ከነበረውና አገርን ካጎበጠው ብልሹ አሠራር አሁንስ ተላቀናልን?
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ኢትዮጵያ የውጭም የውስጥም እዳ ወገቧን አጉብጧታል። እንደ መንግሥት ከዓለም አበዳሪ ተቋማትና አገሮች ካለባት የእዳ ሸክም ራስዋን ለማቃለል ብርቱ ሥራ ይጠብቃታል። የመንግሥት ብድር ከውጭ ብቻ ሳይኾን ከአገር ውስጥ በተለይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ጭምር ነው።
ከአገር ውስጥ ደግሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሚል የተቋቋሙት ተቋማት ደግሞ ከአገር ውስጥ ባንኮች እኛ ከውጭ አበዳሪዎች ያለባቸው እዳ አጀብ የሚያሰኝ ነው።
እንደ መንግሥት ኢትዮጵያ ያለባት የእዳ መጠን ከ21 ትሪሊየን ብር በላይ ነው። የኢትዮጵያ እዳ እየቀነሰ ቢመጣም ሸክሟ አልቀለለም።
ይህ ሁሉ እዳ የተከማቸው ሕወሓት መራሹ አስተዳደር ጊዜ መኾኑ ግልጽ ቢኾንም፤ የአገር እዳ ነውና ይህ እና መጪው ትውልድ የመክፈል ግዴታ ስላለበት አቅም የፈቀደው እየተከፈለ ነው። ይህ ሁሉ ብድር ምን ያህል ለተፈለገው ዓላማ መዋል አለመዋሉን በቅጡ ለመተንበይ የምንቸገር ቢኾንም፤ እዳው የአገር ኾኖ እየገፈገፍን መቀጠላችን ግን ግድ ነው።
ከውጭ ካለብን እዳ ባሻገር በአገር ውስጥ የመንግሥትና የመንግሥት ተቋማት አለባቸው ተብሎ የሚታመነውን ብድር ለብቻው ነጥለን ካየነው፤ የሕዝብ ሀብት ምን ያህል ይባክን እንደነበርና እንደ አገር እያስከፈለን ያለው ዋጋ ነገም ጦስ ኾኖ ሊቀጥል እንደሚችል ነው።
አገር በምን ያህል በተዝረከረከና ለሌብነት ያመቸ አስተዳደር ትመራ እንደነበር ለማወቅ፤ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ተብለው ከአገር ውስጥም ከውጭም የተገኙ ናቸው የተባሉ ብድሮችን ወስደው ለመክፈል ባቃታቸው ተቋማት ምክንያት የተፈጠሩ ቀውሶች በርካታ ናቸው።
ሌላውን ትተን ከሰሞኑ የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ሰባት የመንግሥት ተቋማት ብቻ 780 ቢሊዮን ብር እዳ ያለባቸው መኾኑን አረጋግጫለሁ ማለቱ፤ ተሠርቶ ሊከፈል ያልቻሉ ተቋማቶችን እናያለን።
በመንግሥት ሥር ከሚተዳደሩ ተቋማት ቁጥር አንጻር ሲታይ ጥቂቶቹ የምንላቸው እነዚህ ሰባት ተቋማት የተሸከሙትን እዳ መክፈል አቅቷቸው በጨበጣ የሚጓዙ እንደነበሩም እንረዳለን።
ይህ ገንዘብ በአመዛኙ ከመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደ ስለመኾኑ የሚታመን ሲሆን፤ ባንኩን በአጥንቱ እንዲቀር አድርገውታል ተብሎ ሊገመት ይችላል።
ምናልባትም እነዚህ ተቋማት ከመንግሥት ባንክ መበደራቸው እንጂ፤ ብድሩ ከሌሎች ምንጮች ተገኝቶ ቢኾን ኖሮ ብድሩን ባለመክፈላቸው ሀብት ንብረታቸው ገቢ ኾኖ ነበር ማለት ይቻላል፤ ወይም ከውጭ ያገኙትን ብድር መንግሥት ዋስትና ወስዶ እዳውን እንዲሸከም ተደርጓል ማለት ነው።
የመንግሥት ተቋማት ናቸውና ብድር እያለባቸው ብድር ይፈቅድላቸው ነበር የሚለውንም ነገር እናያለን። ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉት ትላልቅና ሜጋ ፕሮጀክቶች የተሰጣቸውን ብድር በአግባቡ አለመጠቀማቸው እየታወቀ፤ በአናት በአናቱ ብድር ይለቀቅላቸው እንደነበር ስለሚታወቅ ነው።
ለነገሩ ለእነዚህ ተቋማት ከፍተኛ የኾነ ብድር ሲፈቀድ፤ ፈቃጅና አጽዳቂዎች እነማን እንደነበሩ ከተፈተሽ እጃችንን ወደ አንድ አቅጣጫ ልንጠቁም እንችላለን። በሰባቱ ተቋማት ሥር ለነበሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ብድር የሚለቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበሮች የሕወሓት ቱባ ባለሥልጣናት ሲሆኑ፤ ብድሩ የሚለቀቅላቸው ደግሞ እንደ ሜቴክ ያሉ ተቋማት መኾናቸው ነገሩን ግልጽ ያደርግልናል።
ብድር የተለቀቀላቸው እንደ ስኳር ፋብሪካዎች ያሉ ፕሮጀክቶችና ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ስናስብ፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ብድር ተወሰደባቸው እንጂ ተጠናቀው ብድር መክፈል አይደለም፤ በወጉ ፕሮጀክቶችን ማስኬድ ያልቻሉ፣ ከአሥር ዓመታት በላይ የዘገዩ፣ በቢሊዮኖችን የሚቆጠር ገንዘብ የሚፈልጉ ናቸው። እንደ ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉት ደግሞ በተደጋጋሚ ቢሊዮን ብሮችን ፈጅተው ጭምር ሥራቸው እዚያው እየወደመ በመኾኑ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ውኃ የበላው እንደኾነ ያመላክተናል። በጥቅል ሲታይ እነዚህ ሰባት ተቋማት የወሰዱት ብድር እስካሁን የእዳ መጠናቸው ካልተገለጸው ተቋማት ጋር ሲደመር ደግሞ፤ የአገር ሀብት ብክነት ገዝፎ ይታያል። በእነዚህ ፕሮጀክቶች የተከማቸው እዳ ሰቅጣጭ የምንለው ዐይነት ነው። የፈለገውን ያህል ኢንቨስት ቢደረግባቸው ፕሮጀክቶቹ ነፍስ የማይዘሩ መኾኑ ያማል።
እነዚህ ሰባት መንግሥታዊ ተቋማት የተቆለለባቸውን ብድር ለመክፈል የፕሮጀክቶቹን መጠናቀቅ ይጠይቃል። ስለዚህ እነዚህ ጅምር ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስትም ማድረግ መተውም የሚከብድ ነው።
እዚህ ላይ በጣም መታሰብ ያለበት፤ አበዳሪ ባንኮች ላይ ይተላለፉ የነበሩ ትላልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችና ትእዛዞች አገርን ዋጋ ማስከፈላቸውን ነው። አሁን እዳ አለባቸው የተባሉ ተቋማት የፈጸሙት የተበላሸ ተግባር ጦሱ ለነገም የሚተርፍ ነው።
ስለዚህ እነዚህ ተቋማት መፃኢ እድል ምን ይኾናል የሚለው አንኳር ጥያቄ እንደተጠበቀ ኾኖ፤ እንዲህ ካለውና አገርን ከሚያጐብጥ ብልሹ አሠራር አሁንስ ተላቀናል ወይ? የሚለው ነው። እግዚኦ ለኢትዮጵያ!! (ኢዛ)



