Stop Genocide in Ethiopia

ዘር ማጥፋት ይቁም!

ዓለም አንድ በኾነበት ዘመን የአንዱ መኖር ለሌላው ሕልውና መኾኑ በማይታበልበት ዘመን ኢትዮጵያውያን በቀበሌና በብሔርተኝነት በሽታ እየቃተቱ ወገን ወገንን ሲገድል፤ እከሌ ውጣልኝ እያሉ ማንፏለል መቼም ይሁን መቼም ዋጋ ማስከፈሉን ያለማወቅ ጅልነት ነው

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - አገርን ለማሻገርና የተሻለ ለማድረግ፣ ለመልካም የሚደረጉ ጥረቶች እንደተጠበቁ ኾነው፤ ከዚህ ባሻገር ግን የሰው ልጆች ያለምንም ጥፋታቸው በገዛ ወገናቸው እየተገደሉ የትም እየተጣሉ በየዕለቱ መቀጠሉ የዚህች አገር ቀዳሚ ፈተና ኾኗል። መንግሥት እንደ መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የሚለው ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንድንጠይቅ እያስገደደን ነው።

ጊዜ እየጠበቀ በሚፈጸም ጥቃት ንጹሐን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ ሕሊናችንን እያደማ ነው። ነገ ከነገ ወዲያም የምንቆጭበት ብቻ ሳይኾን ከዚህ በኋላስ ተረኛው ማን ይኾን እንድንል ሁሉ እያደረገን ነው።

በወለጋ፣ በመተከል፣ በጉራፈርዳ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰማው የዜጐች ግድያ፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም ማብቂያው መቼ እንደሚኾን ግራ ያጋባል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኃላፊነት የቆዩበት ሦስተኛ ዓመት ዋዜማ ላይ በተከታታይ በአጣየና በአካባቢዋ፣ በምሥራቅ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች በታጠቁ ኃይሎች የተፈጸሙት ጥቃቶች አዲስ ባይኾኑም፤ እንዲህ ዐይነት ጭካኔ የተሞላባቸውን ድርጊቶች ለማስቆም ያልተቻለበት ምክንያት ግን ሁሉንም ግራ እያጋባ ዛሬ ላይ ደርሰናል።

በኦነግ ሸኔና ባልታወቁ ታጣቂዎች እየተሳበበ አየር ላይ የተበተነ ዱቄት መኾኑ የሚነገርለት ሕወሓት እያሳበቡ መቀጠላቸው የሚያዋጣ አይደለም። ምንም ስም ይሰጣቸው፤ መንግሥት የዜጐችን ሕይወት የሚቀጥፉ ታጣቂዎችን ማስቆም ያልቻለበትን ምክንያት ለማወቅ ከባድ ኾኗል።

ጥቃቶቹ በዘመናዊ መሣሪያ ጭምር የታገዙ መኾኑን ስንገነዘብ ደግሞ፤ እንዲህ እስኪደራጅ ምን ሲጠበቅ ነበር የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ትልቁ ችግር ደግሞ በየቦታው የሚፈጸሙት ጥቃቶችና ግድያዎች ዘር ተኮር ኾነው መገኘታቸው ሁኔታውን የበለጠ ያወሳስበዋል። ስለዚህ የአገር ነቀርሳ ኾኖ የቆየውን ሕወሓት በሳምንታት ውስጥ መፈረካከስ የቻለ የመንግሥት ጉልበት፤ ዛሬ ቀን እየጠበቀ የንጹሐን ዜጐችን ደም እያፈሰሱ ዓመታትን ያስቆጠሩ ታጣቂዎችን አደብ ለማስገዛት ያልተቻለው ምን ቢኖር ነው? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

በእርግጥ አገሪቱ የነበረችበትና ሕወሓት ቀብሮ የሔደውን ፈንጂ አፈንድቶ ለመጨረስ አሁንም ጊዜ የሚያስፈልግ ቢኾንም፤ ዘላለም እሱን እያሳበቡ፤ የሱ ተላላኪ ናቸው የሚባሉ ታጣቂዎችን እያባበሉ መቀጠል አይቻልም።

ነጋ ጠባ የወገን ሕይወት እየጠፋ የኀዘን መግለጫ እያወጣን እርምጃ እንወስዳለን እየተባለ ቃል እየተገባልን ስንት ዓመት ልንቆይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ላይ የተቀመጡባቸው ሦስት ዓመታት አይበቁንምን?

የተረጋጋ አገር እንዳይኖር የሚሹ ቡድኖች መንግሥትን ለመገዳደር የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ይታወቃል። በጽንፈኝነት የመከሩትም የሰው ሕይወት የሚጠፋበትን ጥቃትና ትንኮሳ ለማጋጋል እንቅልፍ እንደማያጡም የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለዚህ እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ገና በጠዋቱ አደብ እንዲገዙ ያለማድረጉ አንድ ችግር እንደነበር መገንዘብ ይቻላል።

ዛሬ የመንግሥት ኃላፊነት የተቆናጠጠው የብልጽግና ፓርቲ በውስጡ ሸሽጐ የያዛቸው ጽንፈኝነትና ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅኑ አባላቱን ያለማጽዳቱ አሁን በየቦታው ለሚጠፋው የሰው ሕይወት ቁጥር መጨመርና ጥቃቱ እንዲቀጥል የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታወቃል። ችግሩ ግን ይህ እየታወቀ ቆራጥ እርምጃ ሊወሰድ አለመቻሉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋውን ሊያብሰው ችሏል። ሔዶ ሔዶም “መንግሥት ሆይ! ከወዴት አለህ?” የሚለው ድምፅ ከሹክሹክታ ወደ አደባባይ እንዲወጣ እያደረገው ነው።

የዜጐችን ሕይወት በየዕለቱ የሚቀጥፉ ታጣቂዎች የቱንም ያህል ቢደራጁ መንግሥት ካለው ጉልበትና ኃይል አንጻር በንጽጽር የሚቀርቡ ስላልኾነ፤ መንግሥት ለዚህች አገር እና ለሕዝብ ደኅንነት እጅግ አደገኛ የኾነ ድርጊት ካላስቆመ ለራሱም አደጋ ነው።

የአገሪቱ የፖለቲካ ትግል ውል የሌለው ከመኾኑ አንጻር ችግሩ የበዛ ቢኾንም፤ አሁን ላይ ግን ከችግሮች ሁሉ ችግር ኾኖ የቆየው የዜጐች ግድያ እንዲያበቃ አሁንም እንጮሃለን። በተለይ ዘር ተኮር ጥቃቶች (ዘር ማጥፋት) ተደጋግሞ የሚታይበት የኦሮሚያ ክልል ጉዳይ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው መኾን አለበት።

አንዳንዴ ነገሩን ጠለቅ ብለን እንመልከት ካልን፤ ይህ ሁሉ ሰው በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ ሲፈጸም ታች ድረስ አደረጃጀቱን ተጠቅሞ ለምን ማስቆም እንዳልቻለም መታወቅ አለበት። እነዚህ ዘር እና ሃይማኖት እየመረጡ ግድያ የሚፈጽሙ ሰዎች፤ ምስላቸውን እና ድርጊታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በድፍረት እየለቀቁ ሳለ፤ እንዴት ነው መንግሥት ፈልጎ ሊይዛቸው እና ሊያስቆማቸው ያልቻለው?

ዓለም አንድ በኾነበት ዘመን የአንዱ መኖር ለሌላው ሕልውና መኾኑ በማይታበልበት ዘመን ኢትዮጵያውያን በቀበሌና በብሔርተኝነት በሽታ እየቃተቱ ወገን ወገንን ሲገድል፤ እከሌ ውጣልኝ እያሉ ማንፏለል መቼም ይሁን መቼም ዋጋ ማስከፈሉን ያለማወቅ ጅልነት ነው። የገደለም ኾነ ያስገደለ ሁሉ እንዲሁ ሊቀጥል አይችልም። በጠባብ አመለካከት የሚተኮስ ጥይት ውሎ አድሮ ወደ ራስ መተኮሱ አይቀሬ ነው። “የሕወሓትን ጠባሳ ያየ በዘር ማጥፋት አይጫወትም!” የምንለው ለዚህ ነው። ስለዚህ ከግድያ የሚገኝ ድል የለም። በመንደር አመለካከት አገር ማቅናት አይቻልም።

የሚያምርብን አብሮ መኖር እና መከባበር እንጂ፤ ውጤት ለሌለው ነገር ደም መቃባት ኢትዮጵያውያንን የማይገልጽ ከመኾኑም በላይ አሻጋሪ አይኾንም።

ስለዚህ ግድያ ይብቃ! መንግሥት ያለምንም ማንገራገር የዜጐቻችንን ገዳዮች፣ አስገዳዮች፣ ተኳሽ፣ አስተኳሽ፣ … የኾኑትን ያስቁም፤ ሕግ ፊት ያቅርብልን። ይህንን ስለመፈጸሙም በቃላት እና በመግለጫ ጋጋታ ሳይኾን በተግባር ያሳየን!! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ