ቴዲ አፍሮ ተፈታ - አንድ ብለናል፤ ብርቱካን ትቀጥል! (ግርማ ካሣ)

ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ነሐሴ 18 ቀን 2001 ዓ.ም.
ሰሞኑን የተፈጠረውን ክስተት ከግምት ውስጥ በማስገባት ኅዳር 24 ቀን 2001 ዓ.ም.፣ “የቴዲ አፍሮ መታሰር በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ ነውን?” በሚል ርዕስ ያቀረብኩትን ጽሑፍ አሻሽዬ እንደሚከተለው ለአንባብያን አቅርቤዋለሁ።
ከአሥራ አራት ዓመታት ስደት በኋላ ሀገሬን ለማየት ግንቦት ሰባት 1997 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባሁ። የታሪካዊውን ምርጫ ሁኔታ ለመከታተል ዕድል አግኝቼ ነበር። ያኔ ስለተደረገው ምርጫ አሁን ብዙም ማወራት አልፈልግም። ነገር ግን ከፒያሳ ወደ መገናኛ ለመሄድ ሚኒባስ ውስጥ ገብቼ ያጋጠመኝን አንድ የማልረሳው ክስተትት ላጫውታችሁ።
አውታንቲው “መገናኛ፣ ኮተቤ፣ …” እያለ ተሳፋሪዎችን ይጠራል። ትንሽ እንደቆየን ሚኒባሱ ይሞላና ጉዞ እንጀምራለን። ከጎኔ አንዲት ወጣት ሴት ነበረች። ትንሽ እንደሄድን እንባ በዓይኔ መፍሰስ ጀመረ። ከዚህ በፊት ሰምቼ የማላውቀው አይነት በሬጌ ቢት የቀረበና ልብን የሚሰበር ቃላት ያሉት ዜማ ሹፌሩ ያጫውት ጀመር። “ይሄ ማን ነው?” ብዬ ከጎኔ ያለችውን ወጣት ጠየቅኋት። በመገረም አይታኝ “ቴዲ አፍሮ ነዋ!” ብላ መለሰች። ብዙ ጊዜ መንፈሣዊ መዝሙሮችን ስለምሰማ ድሮ ከማውቃቸው ከእንደነ ነፃነት መለሰ - ‘አረንቻታ’ እና ከቴዎድሮስ - ‘ጉዱሮዬ’ ውጭ ብዙም የዘመኑ የኪነት ባለሙያዎችን አላውቃቸውም ነበር።
“… ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ፣
ምህረት አስተምረን አንድ አርገን መልሰህ
ዘጸዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ፣
ባህር የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ፣
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳዔ፣
በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባዔ
ፍቅር አጥተን እንጂ በረሃብ የተቀጣን፣
አፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን
ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ፣
ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ቢላ
በተስፋዋ መሬት እንዲፈጸም ቃሉ፣
ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ …” እያለ ነበር ቴዲ አፍሮ የሚያቀነቅነው።
ትዝ ይለኛል በምርጫው ውዝግብ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህን በኔ ግምት እንደ ኢትዮጵያ የህዝብ መዝሙር ሊቆጠር የሚገባውን ዜማ እያዜሙ ነበር የምርጫ ዘጠና ሰባት መሰረቅ ላይ ያተኮረውን ተቃውሟቸውን የገለጹት።
የዜማው መልዕክት ግልጽና ቀጥተኛ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ያደላት፣ ከሌሎች ሀገሮች በምንም የማትተናነስ እንደሆነች፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የደኸየነውና የቆረቆዝነው ፍቅር በማጣታችንና ይቅር መባባል ባለመቻላችን ብቻ እንደሆነ ነው ቴዲ አፍሮ ደስ በሚያሰኝ ቃና የገለጸልን።
እርስ በርስ መገዳደል፣ እርስ በርስ መባላት አይበቃንም ወይ? ነው ያለን። እጅ ለእጃችን ከተያያዝን፣ አንድ ከሆንን፣ በዘር በኃይማኖት ካልተከፋፈልን፣ ከግል ጥቅማችን አልፈን ለወገናችን ካሰብን የኢትዮጵያ ትንሳዔ ቅርብ እንደሚሆንና እግዚአብሔር አምላክም እንደሚታረቀን ነው ያስተማረን። በዚህ ዜማ ኢትዮጵያዊነትን አይቻለሁ። ፍቅርንና መተባበርን አሽትቻለሁ።
ይህ ብቻ አይደለም። ወደ አሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ አንድ ወዳጄ ቤት እራት ተጋበዝኩ። በርካታ ሰዎች ነበሩ። ለካ ሌላ ተመሳሳይ ዘፈን ቴዲ አፍሮ ከዚህ በፊት አውጥቶ ኖሯል፤ ቀልቤን የሳበ በቪዲዮ የተቀነባበረ ዜማ ለማዳመጥ ቻልኩ። በአቴንስ ግሪክ ኦሎምፒክ ወቅት ወገኖቻችን ያሳዩት አኩሪ ውጤት ላይ ያተኮረና በምሳሌያዊነት የመያያዝንና የመደጋገፍን ጥቅም ለማሳየት የሞከረበት የዜማ ቅንብር ነበር። አንጋፋው ኃይሌ ገብረሥላሴ እግሩን በመታመሙ ወደ ኋላ ሲቀር፤ ቀነኒሳ እና ስለሺ ወደ ኋላ እርሱን ሲመለከቱ ነው ቪዲዮው የሚያሳየው። ወንድማቸው ወደ ኋላ በመቅረቱ ውስጣቸው አዝኖ እግራቸው ወደፊት እየሮጠ ዓይናቸው ወደ ኋላ ይመለከት ነበር።
ኃይሌ ገብረሥስላሴ፦
“… መርቆ ሸኝቶን ሀገር፣ አሲዞን ሰንድቅ ዓላማ
መርዶ ነው ለወገናችን፣ ማሸነፍ ካቃተንማ
ብሰለፍ ሕመሜን ችዬ፣ እሮጬ ላሯሩጣችሁ
ትልቁን እምነት በናንተ፣ ጥለናል እንግዲህ አይዟችሁ …” ሲላቸው፤
ስለሺ እና ቀነኒሳ ደግሞ በተራቸው፦
“… እዮሃ ከባንዲራው ነው፣ እዮሃ ቃልኪዳናችን
እዮሃ አታፍርም በኛ፣ እዮሃ ኃይሌ አባታችን …”
እያሉ ኢትዮጵያን፤ እንዲሁም “አባታቸው” ኃይሌን ሲያኮሩ እናያለን። አንዱ ሲደክም ሌላው እያገዘ፣ አንዱ ሲወድቅ ሌላው እየተነሳ፣ በሕብረት፣ በወንድማማችነት፣ እርስ በርስ በመተያየትና በመያያዝ ሀገራችንን ከውርደት ማንሳት እንደሚቻል ነው የምንማረው። የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ከሌሎች ሀገራት ባንዲራዎች ከፍ ብላ እንድትውለበለብ ማድረግ እንደሚቻል ነው ቴዲ አፍሮ ለማሳየት የሞከረው። ምሳሌው ሩጫ ሆነ እንጂ በሁሉም መስክ ፍቅርና አንድነት ካለን ቀዳሚ የማንሆንበት ምክንያት የለም። ከላይ የተጠቀሱት ዜማዎች ብቻ አልነበሩም።
“… ስማ ስጠራህ በዚህ ማሲንቆ፣
ይጥራ ዘመኑ ሁሉም ሰው ታርቆ
እንኳን አደርሰን ለአዲስ ዘመን፣
ዘመን ጀንበር ነው ይውጣልን
ለዓለም ለዓለም፣
እንዳይለያየን ዘለዓለም …”
ሲል ነበር ቴዎድሮስ አፍሮ በአበባየዎሽ ዜማ፣ ኢትዮጵያውያን ከ1999 ወደ 2000 ዓ.ም. በምንሸጋገርበት ጊዜ በፍቅር፣ በእርቅና በአንድነት እንድንሻገር መልካም ምኞቱን የገለጸው።
“… ሆ በል ማሲንቆ ሆ በል ክራር
ዝፈን ላገር፣
ሆ በል ዋሽንት ሆ በል ማሲኦንቆ
ስታይ ሰው ታርቆ …”
ብሎ እያቀነነቀ ነበር፣ በሀገር ውስጥ፣ ከሀገር ውጭ፣ በአራት ኪሎ የምኒልክ ቤት መንግሥት፣ በእሥር ቤት፣ በከተማ፣ በገጠርን በሚታወቅ አድራሻ ለሚኖሩ፣ በየበረሃውና በየጫካው ነፍጥ አንስተው ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ ቴዲ አፍሮ መልዕክቱን ያስተላለፈው።
“ሰው ገጭተሃል” በሚል ክስ፣ ቴዲ አፍሮ ወደ እሥር ቤት ከመወረዱ በፊት ደግሞ የሰማነው ዜማ፣ ኢትዮጵያውያን ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር እንድንመልስ የሚያስተምርና የሚገስጽ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ በቀራንዩ መስቀል ላይ ስለኛ የከፈለውን የፍቅር መስዋዕትነት የሚያስታወስ መንፈሣዊ ዜማ ነበር።
“… ኣርነት አወጣኝ ቀራንዩ ላይ፣
ስለኔ ብዙ አየ ስቃይ
እዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና፣
ያከበረህ አምላክ ይድርስህ ምስጋና
ውዳሴ ለስሙ ላዳነኝ ጌታ፣
በምን ልመልሰው የርሱን ውለታ
ሃሌ ሃሌሉያ ለታረደው ጌታ፣
በምን ልመልሰው እኔ የርሱን ውለታ
ሰማያዊ ጸጋ የማርያም ልጅ፣
በመስቀሉ ዘጋ የሲዖል ደጅ
ባንተ ቦታ ያድርጉኝ ይስቀሉኝ ጌታዬ፣
ስቃይህን ልካፈል ባለውለታዬ …”
እያለ የመላዕክት ቋንቋ በሆነው በሙዚቃ አምላኩንና አምላካችንን አከበረ። “… ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ አብ እግዚአብሔር ሃሌሉያ። ሠላም አማን አርጋት ሀገራችንን …” ሲል ምድርና ሰማይን የፈጠረ አምላካ የምህረት እጁን ለሀገራችን እንዲዘረጋ፣ በምድራችን የእርቅ፣ የሠላም፣ የመዋደድ መንፈሥ እንዲሰፍንም ፀለየ።
ሕግ እናስከብራለን የሚሉ ባለሥልጣናት መረጃ አለን ይላሉ። “ሰው ገጭቷል” የሚል ክስ አቅርበው 484 ቀናት ቴዲ አፍሮ እንዲታሰር ተደረገ። የዚህ ወጣት መታሰር ብዙዎቻችንን አሳዘነ። አስቆጣም።
የስድስት ዓመት የእሥራት ውሳኔ ወደ ሁለት እንዲቀየር ተደርጎ በእግዚብሔር ቸርነት ቴዲ አፍሮ የማታ ማታ ተፈታ። እኛም ተደሰትን። ቴዲ አፍሮን፣ የቴዲ አፍሮ ቤተሰቦችና ወዳጆች ሁሉ በዚህ አጋጣሚ “እንኳን ደስ ያላችሁ! እንኳን ደስ ያለን!” እላለሁ።
ገዢው ፓርቲም ለህዝባዊ ጥያቄና ጥሪ አዎንታዊ መልስ በመስጠት፣ ብዙዎቻችን ከነበሩን በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የነበረው የቴዲ አፍሮ መፈታት ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረጉ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ። የቴዲ አፍሮ መፈታትንም አንድ ብለናል።
ነገር ግን መቀጠል ያለበት ነገር አለ። ሌላዋ የኢትዮጵያ አንድነት፣ የፍትህ፣ የሠላምና የፍቅር ሐዋርያ የሆነችው በአሥር ሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የምትወደድ፣ ለምታምንበትና ለመርኅዎቿ የቆመች፣ ከርሷ ምቾትና ድሎት ይልቅ የሀገርን ጥቅም ያስቀደመች፣ አንዲት እህታችን አሁንም ኢፍትሃዊና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ በቃሊቲ እሥር ቤት ትገኛለች። ይችንም ሴት ገዢው ፓርቲ በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ ከሌሎች በሚሊዮን የሚቆጥሩ ወገኖቼ ጋር በመሆን ሀገራዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ይህች ሴት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት። ኢህአዲግ በምርጫና ሠላማዊ በሆነ እንቅስቃሴ የሚያምን ከሆነ፣ በሌሎች ዜጎች ላይ ጥይት ተኩሳ ያልገለደችን፣ የሀገሪቱን ሕገመንግሥት አክብራ የምትንቀሳቀስን፣ እንዳንዶች “ወያኔ ጠላት ነው። መጥፋት አለበት” በሚሉበት ጊዜ “አይደለም። ወያኔም ሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ የማንም ሌላ ኢትዮጵያዊ ጠላት አይደለም። በፍቅር በይቅር መባባል ሀገራችንን በጋራና በሠላም ነው መገንባት ያለብን” ብላ ያስተማረችን፣ የአምስት ዓመት ሕፃን እናትና የሰባ አራት ዓመት አሮጊት እናት ጧሪን የሆነችዋን፣ ብርቱካን ሚደቅሳን መፍታት ይኖርበታል። ከሁለት ዓመት በፊት የነበረን ያረጀንና ያከሰመን ክስ በመምዘዝ፣ ገዢው ፓርቲ እየተጫወተው ያለውን ጨዋታ አቁሞ፤ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅምን፣ በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር የሚረዳን ሥራ ይሥራ እላለሁ። ብርቱካን ሚደቅሳ አሁን ትፈታ!!!!
(ስለብርቱካን ሚደቅሳ የበለጠ ለማወቅና ይህችንም ሴት ለማስፈታት የሚደረገውን የተቀደሰ ጥረት ለማገዝ ወደ http://wwww.freebirtukan.org ድረ ገጽ በመሄድ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል)
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ነሐሴ 18 ቀን 2001 ዓ.ም.



