ይንበርበሩ ደምሴ

ሰባተኛው በአውሮፓ የስፖርትና የባሀል ፌስቲቫል ዝግጅትን በተመለከተ 3 የተለያዩ ፀሐፊዎች (2 ከስዊዘርላንድ፣ አንድ ከሆላንድ) የጻፉትን አስተያየት ካነበብኩ በኋላ፤ በዓሉ ላይ የታዘብኩትንና ሦስቱ የተለያዩ ፀሐፊዎች እንደዋዛ የረሱትን የባንዲራውን ምስጢር ለመጻፍ ወሰንኩ።

 

በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርት በዓል ላይ ከ2000 ዓ.ም. (በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት የዘመን አቆጣጠሮች በሙሉ እ.ኤ.አ. ናቸው) የፍራንክፈርቱ ውድድር በስተቀር በሁሉም ላይ ተገኝቻለሁኝ። ለዚህ በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርት በዓል ውድድር መሰባሰብ በር የከፈቱልን የጀርመኑ አዲስ ፍራንክፈርት ቡድን ሲሆን፤ የሆላንድን የስዊድን እና የፈረንሣይን ቡድኖች ሀገራቸው ላይ በመጋበዝ እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበው፤ የስዊድን ቡድን ሳይገኝ በ3ቱ ሀገራት ተከናወነ።

 

በ2001 ውድድሩን ለምን በሆላንድ ሀገር አናደርገውም ተባብለው በደንሀግ ከተማ ላይ በርካታ ቡድኖች ተሳትፈውበት በጥሩ ሁኔታ ተጠናቀቀ። የ2002ቱ ዝግጅትም በፓሪስ ይከናወን ተባለና በርካታ ህዝብና ቡድኖች ተካፈሉበት። ታዲያ በዚህ ውድድር ላይ የወያኔ ኤምባሲ ተወካይ የሆነችዋ ግለሰብ በሸላሚነት በመገኘትዋ በቡድኖችና በህዝቡ መካከል ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ። ከውድድሩ በፊትም የወያኔ ባለኮከቡ ባንዲራ ተሰቅሎ እንደነበርና ገና በጠዋቱ ግለሰቦች እንዳወረዱት ተሰምቷል።

 

የዚህ ዓይነት ሁኔታ መከሰት ፌዴሬሽኑ በቅጡ ስላልተደራጀና መተዳደሪያ ደንብ የሌለው ስለሆነ ፌዴሬሽን ይመስረት ተብሎ በኦክቶበር 2002 በሆላንድ ሮተርዳም ከተማ ላይ ከ10 ሀገሮች በላይ ተካፋይ በሆኑበት ስብሰባ አመራሮችን በመምረጥና መተዳደሪያ ደንብ በማውጣት በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርት ፌዴሬሽን ተመሰረተ።

 

በ2003 ዓ.ም. የጀርመኑ ሽቱትጋርት የመጀመሪያውን በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች በዓል አዘጋጁ። በፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሠረት የፌዴሬሽኑ አንደኛ ዓመት ተብሎ የሚቆጠረው ከፌዴሬሽኑ ምስረታ በኋላ ከተከናወነው የ2003ቱ የሽቱትጋርቱ ውደድር ጀምሮ ነው። የአውሮፓን ውድድር ከ2000 ዓ.ም. የፍራንክፈርቱ ውድድር ጀምሮ ከቆጠርን 10 ጊዜ ያህል ተከናውኗል።

 

ለአጠቃላይ ግንዛቤ ይህን ካልኩ ወደ ፓሪሱ የስፖርት በዓል የበኩሌን ልበል። በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን ዝግጅት እንዲካሄድና ተበታትኖ የነበረው ኅብረተሰብ በአንድ ጥላ ስር ላሰባሰቡት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በነፃ እየሰዉ ላሉት በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርት ፌዴሬሽን አባላት ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

 

በዘንድሮው የፓሪስ ዝገጅት ከሆላንድና ከስዊድኑ ውድድር የበለጠ ተመልካች የተገኘ ሲሆን፤ የመክፈቻውም ሆነ የመዝጊያው ሥነሥርዓት ካለፉት ዓመታት የደከመ ነበር። በሆላንድም ሆነ በስዊድኑ ውድድር የባህል ሙዚቃ ቡድን ልዩ ልዩ ትርዒቶችን በስቴዲየሙ በማቅረብ ተመልካቹን ሲያዝናኑ ነበር። በፈረንሣዩ ዝግጅት ግን በሜዳው ላይ ይህንን ለማየት አልታደልኩም። የምግብና የመጠጥ ሽያጭን በተመለከተ ከሌሎች ሀገር ውድድሮች የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም። ውድድሮቹን በተመለከተ ተጨዋቾቹ ፕሮፌሽናል ባለመሆናቸው ጎል ቢበዛም ሊያስገርም አይገባም። በዛው አንፃር ደግሞ ጠንካራ ቡድኖችም እንደነበሩ መካድ አይቻልም።

 

የድንኳን ንግድም ዓይን በሚስብ መልኩ በመዘጋጀቱ ሊመሰገኑ ይገባል። ነገር ግን ግለሰቦች በፖለቲካ አመለካከታቸው ቦታ ሲከለከሉ በማየቴና በማረጋገጤ አዝኛለሁ። አርቲስት ሻምበል በላይነሀን ካነጋገሩት ግለሰቦች አንዱ ነበርኩ። “ፖለቲካ ስለምትዘፍን ድንኳን አንሰጥህም” መባሉ በእውነት በጣም ያሳፍራል። ልብ በሉ የፌዴሬሽኑ ሙሉ ስም በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርትና የባህል ምክር ቤት ነው። አርቲስቶቻችን ደግሞ የባህላችን አካል ናቸው። የወያኔ ኤምባሲ በሰጠው ትዕዛዝ መከልከሉ የበለጠ አናደደኝ።

 

እኔ እስከሚገባኝ የአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርትና የባህል ምክር ቤት ሕገ-ማኅበር የሚለው በስፖርት ሜዳው ውስጥ የኃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ድንኳን ይዘው መቀስቀስም ሆነ መስበክ አይችሉም ነው የሚለው! ታዲያ ግለሰቡ ለግንቦት 7 የሙዚቃ ዝግጅት ይጫወታል ስለተባለ ፖለቲከኛ ያሰኘዋል? እንደዚያማ ከሆነ የወያኔ መንግሥት እያዘዛቸው ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚዘፍኑት አርቲስቶች በሙሉ ወያኔዎች ናችሁ ተብለው ሊከለከሉ ነው።

 

ወገኖቼ ብዙ ጊዜ ለምንፈልገው ነገር ሲሆን ፖለቲካና ስፖርት አይገናኙም። ለማንፈልገው ነገር ሲሆን ደግሞ ፖለቲካና ስፖርት ይገናኛሉ የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ። ይህንን ለማለት ያነሳሳኝ “ግምገማው ሲገመገም” በሚል ርዕስ አቶ ሚስጥረ የፖለቲካ ድርጅቶችን በባዶ ሜዳ በሰው ድግስ ካላዘዝኩኝ ብሎ ቡራ ከረዩ ያስተዛዝባል የሚል አስተያየት መስጠታቸው አሳዝኖኝ ነው። ግለሰቡ ይህን አይነት አቋም ካላቸው በኮለን ከተማ በተካሄደው በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች በዓል ላይ በምርጫ 97 በወያኔ ለተገደሉ ዜጎቻችን የህሊና ፀሎት ፌዴሬሽኑ አላስደርግም በማለቱ ፌዴሬሽኑ ላይ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ሲያሳድሙ አልነበረም? መልስዎት አይደለም ከሆነ የኢትዮ-ስዊዝ ቡድን ተወካይ ነኝ ብለው አድማው ወረቀት ላይ የፈረሙበት በፌዴሬሽኑ እጅ ይገኛል።

 

እርግጥ ነው የእኔን አቋም ቢጠይቁኝ እንደ 3ኛው ፀሐፊ እንደ አቶ አንዱአለም ለፖለቲካ ድርጅቶች ስፖርቱን በማይበጠብጥ ሁኔታ ለየት ያለ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ለኅብረተሰቡ መረጃ ቢሰጡ ማንንም አይጎዳም ባይ ነኝ። ወደድንም ጠላንም ሁኔታዎች ስፖርትን ከፖለቲካ ጋር እንድናገናኘው ያስገድደናል። ለዚህም ምሳሌ አሜሪካ ሀገር በሚተላለፈው የአማርኛ ቴሌቪዝን አርቲስት ታማኝ ከሁለት የስዊድን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰዎች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ አንደኛው ግለሰብ የሰጠው መልስ ለሁላችንም ትምህርት ይሆናል። ግለሰቡ ፖለቲካና ስፖርት እንዴት ሊገናኙ እንደሚችሉ ሲገልፁ፤

 

  • ደቡብ አፍሪቃ ለረጅም ዓመታቶች ከአፍሪቃ ዋንጫ የተገለለችው ትከተል በነበረው ዘረኛ ፖሊሲ ነበር።
  • እስራኤል በእስያ ምድብ ግብታ በመጫወት ፋንታ በአውሮፓ ምድብ ገብታ የምትጫወተው ከዐረቦች ጋር እንዳትጫረስ ነው።
  • አሜሪካ የሞስኮን ኦሎምፒክ ቦይኮት ያደረገችው በፖለቲካ ነው።
  • ኢትዮጵያ የሎስ አንጀለስንና የሲኦልን ኦሎምፒክን ቦይኮት ያደረገችው በፖለቲካ ነው።
  • ወደ አውሮፓም የመጣን እንደሆን በ1992 በስዊድን በተካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር የዩጎዝላቪያ ቡድን ለውድድሩ አልፎ ስዊድን ከገባ በኋላ ሚሎሶቪች ያካሂድ በነበረው ጦርነት ምክንያት የዩጎዝላቪያን ቡድን ከስዊድን አባረው በምትኩ የዴንማርክ ቡድን ገብቶ ዴንማርክ ጀርመንን በፍፃሜው ውድድር 2 ለባዶ አሸንፋ ያልታሰበ ሲሳይ ገጥሟታል።

 

ወገኖቼ በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርት በዓል የሚለው ሊቆይ የሚችለው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ስትኖር ነው። በዚህ የሀገራችን ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት ስለሀገር ችግርና ብሶት በስፖርት ሜዳ ላይ መነጋገር መስማትና መቀስቀስ ወንጀል መሆን የለበትም።

 

በመጨረሻም በስቴዲየሙ የባንዲራ መስቀያ ላይ የኢትዮጵያዊ ባንዲራ አልነበረም። የተወሰኑ ግለሰቦች ከፈረንሣይ የስፖርት ኮሚቴ አመራሮች ጋር ለምን እንዳልተሰቀለ ሲከራከሩ ጆሮዬን ጣል አደረኩ። ሊቀመንበሩ “እኔን አያገባኝም ስለባንዲራ ጉዳይ የሚመልስ ሌላ የኮሚቴ አባል አለ” ሲል አስገረመኝ። በኋላ ነገሩን ስሰማ ውድድሩ የተዘጋጀበት የፈረንሣይ ከተማ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ከምትገኘው ደብረብርሃን ከተማ ጋር የእህትማማች ከተማ (Sister City) ተብሎ ስለተሰየመ ባንዲራ መስቀያው ላይ ባንዲራ መሰቀል ያለበት ባለ ኮከቡ ነው የሚል ትዕዛዝ ከኤምባሲው ስለመጣባቸው ያንን ቢሰቅሉ ደግሞ ከኅብረተሰቡ ከፍተኛ ብጥብጥ እንደሚያስነሳ ስላወቁ፤ የትኛውንም ባንዲራ ላለመስቀል ተስማምተው በስቴዲየሙ ባንዲራ መስቀያው ላይ ባንዲራችን ሳትሰቀል ቀርታለች። ይህንን አሳፋሪ ድርጊት በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያኖች የስፖርትና የባህል ምክር ቤት ችላ ሊለው አይገባም እላለሁ።

 

በተረፈ ለቀጣዩ አዘጋጅ ከተማ አምስተርዳም በጎና ደካማ ጎኖችን ገምግማችሁ መልካም ዝግጅት በ2010 እንድታዘጋጁ መልካም ምኞቴን እገልፃለሁኝ።


 

ይንበርበሩ ደምሴ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ