አለቃ ተክሌ (ለዓመቱ ታላቅ ሰው ሽልማት ሥነሥርዓት ላይ ቀረበ)

የብርቱ ካህን ፈተናና የብርቱ ካህን የሕይወት ጥሪ

ደሳሳ ጎጆ። ፍቅር። በእበት የተለቀለቀ ወለል። አርበጠባብ አልጋዎች። የልጅ እናት። ብርቱካን፡ ቀድሞውንም፡ በልጅነቷ ካህን እንድትሆን የተጠራች መሆኗና መናገር ይቻላል። የታመሙትን ለማጥናናት፡ የተበደሉትን ለመካስ፡ የተጠቁትን ለመከላከል፡ ተስፋ ያጡትን ተስፋ ለመመገብ፡ ፍትህ ያጡትን ደግሞ ፍትህ ለማደል፡ የተጠራች ካህን። የዛሬ ሶስት ሳምንት አካባባ፡ ዋሽንግተን ዲ.ሲ. ያገኘሁት ሳምሶን ጋዜጠኛ ነው። ወይም ነበር። እኔና ሳምሶን፡ የኬንያን ስደት ለሶስት ዓመታት ባንድ ላይ አርሰነዋል። ገፍተነዋል።

 

ጋዜጠኛው ሳምሶን በ1991 ዓ.ም. ታስሮና ተከሶ ከብርቱካን ፊት ቀረበ። ለምን ታሰረ? ሟቹ የሮማው ካቶሊክ ቤ/ክ ፖፕ፡ ዮሀንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በካሜሩን ጉብኝት ወቅት፡ ነጠላና ጋቢ ላልለበሱ የካሜሩን ምእመናን ራሳቸውን ካልተፈለገ እርግዝና ይሁን ከበሽታ የሚከላከሉበት ኮንዶም አደሉ የሚል ዜና ያያል። አይቶ ዝም ቢልስ? ዝም አላለም። የኛው ሰውዬ አባ ጳውሎስ፡ ወይም አባ ገ/መድህን፡ እንደው ለወንዱ ኮንዶም ለሴቱ ደግሞ ፒልስ ቢያድሉስ ወይም አደሉ የሚመስል ዜና ጎህ ጋዜጣ ላይ ያወጣል። በነጋታው የአባ ጳውሎስ ዘመዶች ሳምሶንን እያክለበለቡ እስር ቤት ወሰዱት። ዳኛ ብርቱካን ጋር ቀረበ። “አንድ፡ እንደው ትዝ ይለኛል፡ እተተተተ የሚል አማራ መሳይ ነገረ ፈጅ፡ የአባ ጳውሎስ ጠበቃ ሆኖ ቀረበ” አለኝ ሳሚ። እኔ ብርቱካን የስዬንና የሀያላንን ብቻ የምትመለከት መስሎኝ ነበር። ለካስ ምስኪኖችንም ታይ ኖሯል። የጋዜጠኛው ሳምሶን የዋስ መብት እንዲጠበቅለት ብላ አዘዘች። በስዬና በሳሚ የደረሰ ይመሳሰላል። ሳሚ በዋስ መብት ከአራዳ ፍ/ቤት እንደወጣ፡ ከዚያው ከጊዮርጊስ ከፍ ሳይል ወደ ማእከላዊ አስገቡት። ይሄ የዋስ መብት መስጠትና ማስከበር ድፍረት አይደለም ስለብርቱካን የሳበኝ። ይሄም አይደለም የገረመኝ። ይሄም አይደለም ያስደነቀኝ። የሚለጥቀው እንጂ። ከደሳሳ ጎጆ የወጣው ተራራ ድፍረት እንጂ።

 

አንድ ግዜ እንዲህ ሆነ። እሱ፡ ጋዤጠኛው ሳሚና፡ ሌላ ኬንያ የሚገኝ ጋዜጠኛ ጓደኛው፡ ብርቱካን ለ1992 ምርጫ ልትወዳደር፡ ደፋ ቀና ስትል በቅስቀሳ ሊያግዟት፡ ብርቱካን ቤት ተገኙ። ያኔ ብርቱካን በተከራየችው ላዳ ታክሲ ላይ በእጅ የሚያዝ ትንሽዬ ሜጋፎን ይዘው ህዝቡ እንዲመርጣት ሲቀሰቅሱ ባይኑ መጣበት። ሳሚ ስለነ ብርቱካን ቤት ሲናገር እንዲህ አለኝ። “እንደው ትዝ ይለኛል፡ ወለሉ በእበት የተለቀለቀ፡ ደሳሳ ጎጆ አይነት ቤት አይኔ ላይ ይመጣል።” ፊቱን በመገረም እየቀያየረ ቀጠለ ሳሚ “አሁን ቁጭ ብዬ ሳስበው ከዚያ በእበት ከተለቀለቀና፡” አሁን እንደሚያስበው ትዝ እንደሚለውም “ታጣፊ የሚመስሉ፡ አርበ ጠባብ አልጋዎች ጎንና ጎን ከተዘረጉባት ያረጁ ጎጆዎች፡ ያረጁ የአፈር ቤት፡” አንዲት አባቷ በልጅነቷ ሞተው ምስኪን እናቷ ያሳደጓት፡ ምስኪን ሴት እንዲህ እላይ ትወጣለች ብዬ፡ ፈጽሞም አላሰብኩም ነበር አለኝ። እጅግ ይገርመው ነበር ሳሚ። በዚያ ደሳሳ ጎጆ፡ ለምርጫ ስትወዳደር የነበራት እምነትና ጥንካሬ አስገርሞን ነበር። ብርቱካን። ደሳሳ ጎጆ። ደሀ። ምስኪን። እናት።

 

የኢትዮጵያ ታላቅ ሰው፡ ታላቅም ሴት፡ ታላቅ እስረኛ

ስለብርቱካን ሳስብ በጣም የሚያስደንቀኝና ሁልግዜም የሚመስጠኝ፡ ይላል አንድ በቅርቡ ሀሳቡን በድረ-ገጾች አስተያየት መስጫ ላይ የጠቀሰ ሰው፡ መድረክ ላይ ስትወጣ “በጣም ለምወዳችሁና ለማከብራችሁ ውድ ያገሬ ልጆች!” የምትለው ነገር። ቃል በቃል እንዲህ ሲል ጨመረ አስተያየት ሰጪው፡ በእንግሊዘኛ፡ “It is this sort of words of humbleness, honesty, decency etc that she feeds to the audience that always rings to me the moment I remember about her። ይሄ ትህትና አላዋቂነት፡ ይሄ ትህትና ፈሪነት ይሄም ትህትና ታናሽነት ሊመስል ይችላል። ይምሰላ። ቢመስልስ? እነሆ ይህቺ ወጣት፡ ትሁት፡ አስተዋይ፡ የልጅ እናት የአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችን ከደሳሳ ጎጆ፡ ከአፈር ወለል ቤት የወጣን ኢትዮጵያዊያን መሪ ብርቱካን ከታሰረች፡ ዛሬ 250 ቀን ሆናት። ብርቱካን ታሰረችም ታፈነችም የኢትዮጵያ ታላቅ ሴት ሆና ትኖራለች። ከዚህ ቀደምም ብለናል። ያልታሰረ ማንዴላ፡ ያልተሰቃየ ጋንዲ፡ ያልተጎሳቆለ ማርቲን ሉተር ኪንግ ስናስብ፡ በእውኑ ከተራው ሰው የተለዩ የሚያደርጋቸው ምን ነገር እናገኛለን። ሰውን ታሰር ወይም ሙት ወይም ተሰዋ ብሎ መምከር ይከብዳል። ስለመብታቸው የሚታሰሩና የሚሰዉ ሁሉ ግን ያለምንም ማመንታት ታላላቆች ናቸው። እንደውም በማሰር አፍናታለሁ፡ አሸማቅቃታለሁ እንዲሁም አንበረክካታለሁ ብሎ ያሰባው አሳሪ ካሰበው በተቃራኒ፡ የብርቱካን መታሰሪ በብዙዎቻችን ውስጥ ስለብርቱካን ያለንን ክብር ጨመረው፡ ያለንን ጥርጣሬ ደመሰሰው። እነሆ ወያኔ በብርቱካን ላይ ጀግነንትን አበዛልን።

 

ብርቱካንና እናቷ፡ ልምጭ ለሚገባው እድሜ ይፍታህ

የዓለም ሁሉ እናቶች አንድ ሊሆኑ ይችላሉ። የኢትዮጵያ እናቶች ግን በጣም አንድ ናቸው። የኢትዮጵያ እናቶች ከወለዱ በኋላ የራሳቸው ሕይወት የላቸውም። የሚኖሩት ለልጆቻቸው ነው። ለኢትዮጵያ እናቶች፡ ልጆቻቸው፡ አግብተውም ወልደውም ለነሱ ያው ህጻን ናቸው። ምስኪን። ስለዚህም ወ/ሮ አልማዝ ያቺ ሽንት ጨርቅ ቀይረው፡ ቆንጥጠው ያሳደጓት የድሮዋ ሚጡ፡ የአሁኗ ወ/ት ልጃቸው እንኩዋንስ በእድሜ ልክ እስራት ልትቀጣ፡ ቁንጥጫም እንደማይገባት ልባቸው ጠንቅቆ ስለሚያውቀው፡ ልጃቸው ለእድሜ ልክ እስራት ወደ ቃሊቲ ስትወርድ እውነት አልመሰላቸውም። ድምጻቸውና ንግግራቸው አሁንም ድረስ አይኔም ጆሮዬም ላይ አለ። “እሷ፡ ትንሽ ልጅ ነች። ምንም አታውቅ። ልጅ ቢያጠፋ እንኩዋን በልምጭ ይቀጣል እንጂ እንደምን፡ እንደዋዛ እድሜ ይፍታህ ይታሰራል?” ወ/ሮ አልማዝ እንባቸው መጣ። የብርቱካን የእድሜ ይፍታህ እስራት እውነት አይመስልም። እውነትም እውነት አይመስልም። ይህ ስርአት ግን ገገማ ነው። አስራ ስምንት ዓመት ወይ የማይሟሽ ወይ የማይሟሽሽ ገገማ መንግስት። ሕወሀት/ኢህአዴግ የገገማዎች ስብስብ፡ የቂሎች ጥርቅም ይሆንብኛል አንዳንዴ።

 

ብርቱካን በምን ተከሰሰች? መጀመሪያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነበር። ብርቱካንና ጓደኞቿ የትግራይ ብሄረሰብ ተወላጆችን ሊያጠፉ። አረ፡ ስለእመብርሀን ይህን የማይመስል ነገር ተዉ ብሎ ፕሮፌሰር ሌቪን መሰለኝ መከራቸው አሉ ፕሮፌሰር መስፍን። ስለዚህ የዘር ማጥፋት ሙከራ አደረጉት። ህገ መንግስታዊ ስርአትን በሀይል ለመጣል ተጨመረበት። ብርቱካን ሚደቅሳ፡ ታንክና ሚግ፡ መትረየስና ፈንጂ፡ እ፡ ሚሳይልና ገጀራ ታጥቃ የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል ተነሳች። ሌላ የማይመስል ነገር። ስለዚህም ነው እነዚህ ሰዎች የቂሎች ጥርቅም ይመስላሉ ያልኩት። እንጂ መሳደብ ነውር ነው። ብርቱካን አትደግፈውም። እሷ ጠላቶቿን እንኩዋን ለመሳደብ የሚከብዳት ትሁት ሴት ነች።

 

ከትቢያ ላይ ተነስታ፡ ከደሳሳ ጎጆ ወጥታ

ለሕወሀት፡ ሴት ማሰር ማዋረድ ነው። ሰው ማሰር ማንበርከክ ነው። ሴት ማሰር ማሸነፍ ነው። ሰው ማሰር መሰልጠን ነው። ሴት ማሰር ማስደንገጥ ነው። ሰው ማሰር አመጽንና ተቃውሞን ማቆም ነው። ሴት ማሰር የእባብን ልጅ በእንጭጩ የማለት ያህል ነው። ሸፍቶ እዚህ ለደረሰው ሕወሀት፡ ሰው ታስሮም ሸፍቶም እዚህ እነሱ የደረሰበት ይደርሳል ብለው አያስቡም። ለሕወሀት የታሰረ የሞተ፡ የሞተ ደግሞ መና የቀረ ያህል ነው። ሰው ታስሮም እንደሚያድግ ታስሮም እንደሚታገል ይዘነጋል። ሕወሀት ሲያስር ሰውን ሽባ ያደረገ ያህል ይሰማዋል። በእውኑ የሰው ልጅ የእጁና የእግሩ መታሰር ግን፡ የጭንቅላቱ መታሰር እንዳልሆነ፡ ይልቅስ እስራት ጽናትን፡ ጽናትም ማንዴላን እንደወለደ፡ ጽናት የሆነው ማንዴላም ደቡብ አፍሪካን እንደተቤዠ ማየት እንደምን ተሳናቸው? ብርቱካን ጽናት ነች።

 

ወ/ት ብርቱካን ለሰላማዊ ትግል ያላትን ታማኝነት በየግዜው ብትገልጽምና ብታሳይም፡ ቀደም ሲል በቅንጅት ም/ሊ/መት በነበረችበት ግዜ ምርጫ 2005ን ተከትሎ በሕወሀት ታስራ በቃሊቲ ከ18 ወራት በላይ መስዋእትነት ከፍላለች። ቃላቸውን ባልጠበቁ ሽማግሌዎች ሸፋፋ ሽምግልና አማክኝነት ወ/ት ብርቱካንና የእስርም የትግልም አጋሮቿ፡ ከእስር ቢፈቱም፡ በየጊዜው የሚደርስባትን ወከባና አፈና ተቋቁማ በአገዛዙ እርምጃ የፈረሰውን ቅንጅትን እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረግ ባዲስ መልኩ አዋቅራ፡ የአንድነት ፓርቲን በተሳካ ሁኔታ መስርታ በሊቀ መንበርነት ተመርጣ ነበር። ይሁን እንጂ የብርቱካንን ጽናትና እየገነነ መምጣት የተመለከተው አገዛዝ በተለያየ ግዜ ቅስሟን ለመስበር ያጠመደው ወጥመድ አልሳካ ቢለው፡ ወ/ት ብርቱካን በድጋሜ ወደ እስር ተወርውራ በቃሊቲ መኖር ከጀመረች እነሆ 250 ቀናት አለፏት። በነጻነት ትንቀሳቀስ በነበረበት ወቅት ሁሉ ብርቱካን ሰላምን አጥብቃ የምትሰብክ፡ ከበቀልና ጥላቻ የራቀች የፍቅር ሰው ነበረች። በእስር ባለችበት ሰዓትም ብርቱካን የጽናትና የኢትዮጵያዊነት ምሳሌ ነች።

 

የቅርብ አጋራቸው፡ ገብረመድህን አርአያ በቅርቡ፡ ከዚህ የሽልማት ስነ ስርአት አንዱ አዘጋጅ ጋር በሰጠው ቃለምልልስ እንደገለጸው፡ “የስጋ ልደቶቻቸውን በቀላጤ ማህተም ረግጠው እያስረሸኑ እየረሸኑ እዚህ የደረሱት የአመጻ ልጆች” እንደ ብርቱካን ያለችውን ምስኪን ለማስር ምንም እንደማይመልሳቸው አላጣችውም። ብርቱካን። ነገር ግን በራሷ ቃል እንደገለጸችው፡ ብርቱካን፡ የህግ የበላይነት፡ አንዳንዴም የምትታሰርለት እንዲሁም የምትሞትለት እንደሆነ ገልጻለች። ብርቱካን የኣልጋ ባልጋ ትግል አልጠበቀችም። እነሆ ተናገረች የተናገረችውንም ፈጸመች። ስለዚህም፡ ከተለያዩ የካናዳ ከተሞች የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን ያሉበት ኮሚቴ፡ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የዓመቱ ታላቅ ሰው ብሎ ሲመርጣት፡ ስለሚገባት ነው። እድሉን አግኝተው ኢትዮጵአዊያን ድምጽ ቢሰጡ ይሄንን ታላቅ ሰውነት አይነፍጓትም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ ዲግሪ ከተመረቀችበት ግዜ አንስቶ ከአምስት ዓመታት በላይ በአንደኛና ከፍተኛ ፍ/ት ደረጃ በሰራችበት ጊዜ ሁሉ የቀድሞውን የሕወሀት መከላከያ ሚኒስቴር ጨምሮ ሌሎች ያለአግባብ የታሰሩና ህገ መንግስታዊ መብታቸው የተጣሰ ሰዎችን መብት በማስከበር ረገድ ላሳየችው ሐቀንኝነት፤ እንዲሁም ከዳኝነት ሙያዋ ስትነሳም፡ ወደ ፖለቲካው መስክ ገብታ በኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ እየከፈለች ላለቸው መስዋእትነት ለዚህ ሽልማት በቅታለች።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ