እኛና ጠላት፣ ሰልፍና ሰይፍ፤ ሰይፍ አልመዘዝንም እስኪ ሰልፍ እንውጣ፤ ሴፕቴምበር 13፣ 2009
አለቃ ተክሌ - ቫንኩቨር ካናዳ
ይሄ ፅሁፍ የቅስቀሳ ነው፤ ከጋሽ ከቤ ልጀምር
ቅስቀሳ የማይወድ ከዚህ ሳይዘልቅ ያቁም። ብዙ አይልፋ። እነሆ ቅስቀሳ። አሁን ጥቅምት ሲመጣ 56ኛ ዓመቱን ይይዛል። ያሳዝነኛል። አንዳንደዬ ቢያናድደኝም፤ ሁልግዜ ግን ያስደስተኛል። ከቫንኩቨር ሲያትል ከሲያትል ዲሲ፡ ከዲሲ ቶሮንቶ ከቶሮንቶ ደግሞ መልሶ ካልግሪ ሲንከራተት፡ ጽናቱ ይገርመኛል። ፅድቅን ፍለጋ አይደለም። ሰማያዊ ድህነትን ሽቶም አይደለም። ዝናና ክብርም አይደለም ረሀቡ። የኢትዮጵያ ጉዳይ እያንገበገበው እንጂ።
አሁንም የኦባንግን ድምጽ ሰምቶ ወደ ዲሲ ሊያመራ ሻንጣውን ሲሸክፍ አገኘሁት። ብዙ ሰልፎችን ተሰልፌያለሁ። ብዙ ስብሰባዎችንም ተካፍያለሁ። በነዚህ ሁሉ ስብሰባዎችና ሰልፎች ብዙ ሰዎችን አይቻለሁ። አንዳንዱ ሰው ጥግ ይዞ መፈክር ለማለት ወይም ለማንሳት ይልመጠመጣል። አንዳንዱ ሰው ደግሞ አስተያየት ያበዛል። አንዳንዱ እውቀቱ ብዙ ነው። ብዙ ያውቃል። አንዳንዱ ደግሞ ይጀነናል። አንዳንዱ ይተቻል። አንዳንዱ አቃቂር ያወጣል። ጋሽ ከቤ ግን ከነዚህ ሀሉ ውስጥ የለበትም። ቀድሞ መፈክር ይሸከማል። ሰው አይጠብቅም። ሰልፍ ካለ ልብሱ የብርቱካን ፎቶ ነው። ካባው የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የራሱ የሆኑ ችግሮች ይኖሩበታል። ግን ያ መቼም እንቅፋት ሆኖ አያውቅም። እንደ ልጅ ይላላካል። ጋሽ ከቤ ማስታወቂያ ለጥፍልኝ። “አንጣው !!”። ጋሽ ከቤ ለዚህ ቀን ሰልፍ ባንድራና መፈክሮች አዘጋጅ፡ “እሺ ምን ችግር አለ።” ከቤ። ሰው ሞተ፡ ቀባሪው ከቤ ነው። ሰው ታመመ፡ ጠያቂው ጎብኚ ነው። ከቤ እድር ነው። ከቤ አገር ነው። ከተጣላም እንደዚያው ነው። ያመራል። ጥሉን እንተወው። ቁምነገሩን እንያዝ።
ዛሬ ብዙዎቻችን በልጅና በስራ፡ በትምህርትና በሰበብ አስባብ ተጠምደን ከብሄራዊ ግዴታችን ስናፈገፍግ፡ ጋሽ ከቤ ግን ምንም አያመነታም። ጋሽ ከቤና የኢትዮጵያ ባንድራ አይለያዩም። የመኪናው ኋላ ሲከፈት፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ባንድራችን ቦግ ይላል። መቀበሪያዬ ነው ይላል። ወደ ዲሲ ሊጓዝ ሲሰናዳ አገኘሁት። ኦባንግን ፍለጋ።ለኢትዮጵያ ጉዳይ ብሩን መንዝሮ ቢጨርስ፡ ሰማይ ደርሶ ማርስ ተሻግሮ ቢመጣ የት ሄድክ፡ የት ዋልክ ብላ የማትነዘንዝ ቀኝ የሆነች ሚስት አለችው። ጋሽ ከቤ አካባቢውን ለማስተባበር፡ ሰዉን አንድ ለማድረግ ሰንጋ ጥሎ ቀቅይ ቢላት የማትሰለች ወርቅ ሚስት አለችው። ግርም ይለኛል። ዓመት በዓል መጣ፡ ኤርትራዊ የለም ሱዳናዊ፡ ኢትዮጵያዊ የለም ኬንያዊ፡ ነጭ የለም ጥቁር፡ ትንሽ የለም ትልቅ፡ ሁሉም ጋሽ ከቤ ቤት ይመሽጋል። ቅራሬው ሳይደፋ አንወጣም አይነት ነገር። እሱም ለቤቱ ይሞታል። ቤቱን ያከብራል። ቆይ ይሄንን ሁሉ ማተቴ ለምንድነው? ያው ነገር ይገባችኋል ብዬ ነው። ጋሽ ከቤ የራሱን ወጪ ሸፍኖ፡ የራሱን ግዜ ገድሎ፡ የራሱን ስራ በድሎ፡ የሚያሰናክለው ነገር ካልተገኘ በስተቀር፡ እነሆ ለሴፕቴምበር 13 ሰልፍ፡ ወደ ዲሲ ሊያመራ ይዘጋጃል። ጋሽ ከቤ።
የመዳን መድረክ፡ የቅድስና ጥሪ። “It is fun”
ጋሽ ከቤ የቫንኩቨር ኦባንግ ነው። ኦባንግ በአኝዋክኛ የማይደክመው ማለት ይመስለኛል። ኦባንግ ትክክል ነኝ?። የማይደክመው የማይሰለቸው። የሌሎችን ስራ የሚሰራ የሌሎችን መስቀል የሚሸከም፡ የማይደክመው ሰው። ኦባንግ ሰልፍና ስብሰባ በጠራ ቁጥር ለቅድስና የጠራኝ ያህል ይሰማኛል። ለጽድቅ። ለመዳን እድል የፈጠረልኝ ያህል እወደዋለሁ። ኦብንግ ግን ሰው ነው። የሰው ባህርይ አያጣውም። ኦባንግ የኛን ስራ እየሰራ መድረክ ፈጠረልን። ሰበብና ምክንያት፡ ድክመትና ጉድለት አሳዳጅ አይጠፋም። አንዳንዶች አሉ፡ እነሱ ያልባረኩት ሰልፍ፡ እነሱ ያላጸደቁት ጉባኤ፡ እነሱ ያልጸለዩበት ስብሰባ፡ አገራዊና ኢትዮጵያዊ የማይመስላቸው። አንዳንዶች ደግሞ አሉ፡ የሰበብ ፋብሪካዎች። ሰበባችንንና ምክንያታችንን ወደጎን አድርገን፡ ይሄንን መድረክ እንዴት እንጠቀምበት ነው ጥያቄው። በየቤታችን መብከንከናችን፡ በየቤታችን መቃጠላችን ካልቀረ፡ ኦብንግ እኛ ማድረግ የተሳነንን ስራ ነው ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የፈጠረው። ኦባንግ እድለ ሰጠን። እድሉን መጠቀም የና ፋንታ ነው።
የኦባንግ አይደለም የኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊያንም ጥሪ ከባድ አይደለም። ለነቢያት የቀረበ አይነት ልጅህን ሰዋልኝ፡ ወይም ለሀዋሪያት የቀረበ አሳ የማሰገር እንጀራህን ትተህ ተከተለኝ አይነት ጥያቄ አይደለም። ሚስቶቻችሁንና ልጆቻችሁን፡ ባሎቻችሁንና እንጀራችሁን ትታችሁ ተከተሉኝ አይደለም የኦባንግ ጥሪ። ዛሬ፡ በዚህ ሰዓት፡ በዚህ ቀን፡ በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብና ቸነፈር ይረግፋሉ። ያም አልበቃ ብሎ፡ በአምባገነኖችና በዘር አጥፊዎች ይታመሳሉ። ስለዚህ ይሄንን አዲስ ዓመት ስናከብር አብረን እናስባቸው አብረን እናክብር፡ ጥቂት ቅጽበቶችን ከህይወታችን ሰርቀን እንሰለፍ ነው። ፈረንጆቹ “It is fun።” ይላሉ። መሰለፍም ፈን ነው። ተሰልፎ መዘመር። ተሰልፎ መፎከር። ተሰልፎ መላቀስ። ተሰልፎ መነጋገር። አሁን ተስፋዬን እንረሳዋለን? ተስፋዬ አዳነ ጋራን? ምን የኛ ነገር እኮ ከንቱ ነው ብዙ ጊዜ። ለነጻነታችን የሞቱትን ለህልውናችን የተሰዉትን ለኛ ደህንነት የታሰሩትን ቶሎ እንዘነጋለን።
ተስፋዬን አልረሳውም፡ ወ/ሮ እቴነሽንም፡ የአምባገነኖች ሰለባ
የዛሬ አራት ዓመት ከሶስት ወር አካባቢ፡ ተስፋዬ አዳነ የሚታየው ከምኔው ፓርላማ ገብቶ፡ ከምኔው ተመርቆና ድግሪውን ተቀብሎ አገሩን እንደሚያገለግል ከምኔው ለአገሩም ለሱም ቀን ወጥቶላቸው ከድህነትና ከአምባገነናት እንደሚገላገሉ ነበር። ከምርጫ 97 በኋላ ግን፡ ባንድ እሁድ ከሰዓት ግን ሁለት የጠገቡ የትልልቆቹ አምባገነናት ጠባቂዎች፡ የታጠቁ ትንንሾቹ የኦህዴድ አምባገነናት ህግ ይፈልግሃል ብለው ከቤቱ ወሰዱት። ነጌሌ ያደግኩበት ከተማ ነው። ሕግ ለምንድነው የሚፈልገኝ? ምን ወንጀል ሰራሁ? ብሎ ብቻ ነው የጠየቃቸው። በመሳሪያ እንዳልነበር አደረጉት። ለአርሲ ነጌሌ ኦብኮን ወክሎ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመርጦ የነበረው ተስፋዬ አዳነ፡ ጓደኞቼ ከተማሩበት እሱም ካደገበት ት/ቤት በታች ተገደለ። ተጣለም። የገዳዩ ስም አንዱ ታምሩ ነው፡ ሌላኛው ስሙን ዘነጋሁት። ለጊዜው ለማስመሰል ያህል ታሰሩ። በታሰሩበት ግን የአበባ ምንጣፍና ጫት ክትፎና ሴትም ጭምር ገባላቸው። እነሆ ከአራት ዓመት በኋላም ወደሌላ ከተማ በሹመት ተሻግረው ህይወታቸውን ይገፋሉ። የተስፋዬ ደም ደመ ከልብ ሆኖ ይቀራልን? ለጊዜው ሰይፍና ሰደፍ ያለው ከጠላታችን እጅ ነው። እኛ ግን ቢያንስ ሰልፍ አለን። መቼም ብዙዎቻችን፡ ይሄንን ኬዝ ሰርተንበት ነው እዚህ የምንኖረው። አሁን ያለም ዙሪያን እናት፡ ተዉ ባሌን አትውሰዱ ብለው በጮሁ በጥይት በጠራራ ጸሀይ የተገደሉትን፡ ወ/ሮ እቴነሽን እንዘነጋለን? ከዚህ በላይ ምን ይምጣ? እነሆ እዳን የመክፈል ቀን ዛሬ ነው። አሁን። እንሰለፋ።
ይሄ ቅስቀሳ አይደለም። ልቀጥል? ቅስቀሳም ከሆነ፡ ቅስቀሳዬ ግን እውነት ቀመስ ነው። ጭፍን አይደለም። እንደዋሽንግተን ዲሲ ያለ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ይኖርበታል የሚባል አካባቢ፡ መቶ ሰልፈኞች አጥቶ የጠላት ማላገጫ ቢሆን ያሳቅቃል። ሰበብ የለንም። ወይ ግዴለንም። ወይ ወሬኞች ነን። ብንሰለፍ ኦባንግ ይደሰት ይሆናል። ባንሰለፍ ግን ኢትዮጵያ ትጎዳለች። ግን ትኖራለች። ኦባንግና ኦባንግ ግን ሕይወቱን ይቀጥላል። መሰለፍ ለአገራችን ልናደርግ የምንችለው ትንሹ ነገር ነው። አሁን እኛ አንድነት አንድነት እንላለን እንጂ፤ መቼ ነው አንድ ሆነን የምናውቀው? አንዳንድ ሰዎች አይዋጥላቸውም። አንድነት መፈለግና አንድ መሆን ይለያያሉ። አንድ ነበርን፡ ግን አንድም አልነበርንም። አሁን ደግሞ እድሜ ለህወሀት/ኢህአዴግ አንድ አለመሆናችን እየባሰበት ሄዷል። በርእዮተ ዓለም ደረጃ ልዩነትንና መለያየትን የህልውናው መሰረት ያደረገ ስርአት አገሪቱን እያንገላታታ ባለበት ሰዓት፡ እንደ ኦባንግ ያሉ በኢትዩኦጵያዊነትና ሰብአዊ ብሄርተኝነት የሚያምኑ ሰዎች የሚያዘጋጁትን ሰልፍ ማድመቅ አለብን።
የአንድነት ናሙና፡ ኢትዮጵያዊነቱ የሚያመው፡ ኢትዮጵያዊነቱ የሚቆጨው ካለ እናክመው
ይሄ ሰልፍ የአንድነት ናሙና ነው። ኢትዮጵያዊ መሆኑ እንደጎዳው የሚያምን ኦሮሞ ካለ፡ ኢትዮጵያዊ መሆኑ የሚያመው ኦጋዴን ካለ፡ ኢትዮጵያዊ መሆኑ የሚቆጨው ሲዳማ ካለ፡ እነሆ ብድግ ብለን ሊቆጭ ሊያመው ሊከፋው እነደማይገባ የምናሳይበት አጋጣሚ እንዲህ ያለው ነው። ቀድሞውንም ነገር እኮ፡ የምንገናኝባቸው መድረኮች ኢምንት ናቸው። ካሉም፡ አብዛኞቹ የምንለያይባቸው መድረኮች ይበዛሉ። ወይ እንደ ክርስቲያንነና እንደ እስላም እንደ ትግሬና እንደ ጎንደሬ እንደ ኦሮሞና እና ሶማሌ የምንሰበሰብብት መድረክ ይሆናል። እንደ ክርስቲያን ራሱ ስንት ፈርጅ አለን። እንደ ፖለቲከኞችም የተለያየየን ነን። አንዳንዶቻችን የኢንጂነር፡ አንዳንዶቻችን የፕሮፌሰር፡ አንዳንዶቻችን የኢህአፓ ዲ አንዳንዶቻችን የኢህአፓ አ፡ አንዳንዶቻችን የግንቦት ሰባት አንዳንዶቻችን የአንድነት። እንደ ኦባንግ ያሉ ሰዎች ሁለመናቸውን ሰውተው ሁላችንንንም ሊያሰባስብ የሚችል መድረክ ሲፈጥሩ ግን ልንገኝ ይገባል። ለኦባንግ ብለን አይደለም። ለራሳችን ብለን። እስከዚህ ስላነበባችሁኝ፡ እነሆ እስከዚህ በትእግስት ባታነቡ የማታገኙትን ምስጋናዬን ውሰዱ።
አለቃ ተክሌ - ቫንኩቨር ካናዳ (ሴፕቴምበር 10/2009)



