አሸብር (ከጀርመን)

“እርስ በርሳችሁ ስትተራመሱ የወያኔን አንድ ዝንብ እንኳን ‘እሽ‘ ሳትሉ ዕድሜአችሁን ገፋችሁ“ ከታዛቢ

በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጀቶች ስለሕብረት ጉዳይ ሲወያዩ፤ አልፎ - አልፎ የሚያነሱት ጉዳይ ካለፉት ትብብሮች ምን መማር እንዳለባቸው ነው። ስለሆነም ካለፉ ትብብሮች ሊገኝ ስለሚችል ትምህርት አጋጣሚ ያስገኘልኝን ግንዛቤ ባካፍል በጥቂቱም ቢሆን አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብዬ ስለገመትኩ የምትከተለዋን ለማለት ሞክሬአለሁ። በቅድሚያ ግን አንባቢዎችን ማሳሰብ የምሻው፤ የጽሑፌ ዓላማ በየጊዜው የተቋቋሙ ሕብረቶች ውስጥ በእኔ ዕይታ ለጋራ ትግሉ እንቅፋቶች ነበሩ ያልኳቸውን ድርጊቶች ለማሳየትና ለወደፊት ትምህርት የሚቀሰምባቸው ይሆናሉ በሚል ብቻ እንጂ፤ ባለፉት ለተፈጸሙ ልማቶችም ሆኑ ጥፋቶች ማንንም ተጠያቂ አድርጎ ለማቅረብ የታሰበ እንዳልሆነ ነው። ስለዚህም በጽሑፌ ውስት በክፉም ሆነ በደግ የማንንም ግለሰብ ሆነ ድርጅት ስም አላነሳሁም።

 

መነሻ የማደርገው ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ስለተፈጠሩ ሕብረቶች ሲሆን፤ ለዚህም፦

 

1. የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ኢዲኃቅ)

በ1983 ዓ.ም. በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲዊ ኃይሎች ቅንጅት (ኢዲኃቅ)“ የሚል ሕብረት አቋቋሙ። በዚህ ድርጅት ውስጥ ተሳታፊ ስለነበሩት አካላት እነማን ናቸው ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ማን ቀረ? ብሎ መጠየቁ ይቀል ነበር። የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ማኅበራዊ ስብስቦች፤ ታዋቂ የተባሉ ግለሰቦች ሳይቀሩ ተሳትፈውበታል።

 

ታዲያ የዚህን ስብስብ መፈጠር ምክንያት በማድረግ ሳላነሳው የማላልፈው ነገር፤ ስብስቡ በጊዜው በነበረው ፀረ-ደርግ ትግል አቅጣጫ የጋራ አቋም ይዞ መነሳቱ ብቻ ሳይሆን፤ እንደትልቅ ግኝት ታይቶ የነበረው የኢህአፓ እና የመኢሶን በጋራ አብሮ መሥራት መቻል ነበር። ትዝ ከሚለኝ አንድ ነገር ጠቀስ አድርጌ ልለፍ። ቅንጅቱ እንደተመሰረተ በያካባቢው የቅንጅቱን ዓላማ ማስተዋወቅና ባጋጣሚውም ለድርጅቱ እርዳታ ማሰባሰበ ተጀምሮ ስለነበር፤ ባንድ አካባቢ በተደረገ ስብስባ ላይ አንዲት ሴት ከሁሉም በላይ ደስ ያሰኛቸው ነገር በዚህ ድርጅት ውስጥ የመኢሶንና የኢህአፓ ተስማምቶ መሥራት ስለነበር፤ ለቅንጅት መርጃ የሚሆን ያንገት ወርቅ ሃብሌን ሰጥቻለሁ ሲሉ ሰምቼ ነበር። ሴቲቱ ያሉትን ሃሳብ ብዙዎች የማይጋሩት ሃሳብ አልነበረም። ሆኖም የሴቲቱ ንግግር ደግሞ፤ ይህን ያሉበትን ምክንያት እንዳመላክት አደረገኝ።

 

ኢዲኃቅ በተቋቋመ ጊዜ ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ደርግ፤ የሠርቶ አደሩን/የላብአደሩን ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት የማሰፍነው እኔ ነኝ፤ እኔ ነኝ፤ የኔ መንገድ ነው ትክክሉ በማለት እርስ በርስ ባደረጉት ትንቅንቅ ደርግ ከሌሎቹ የነቃም ባይሆን በተሻለ የታጠቀና የተደራጀ ስለነበረ፤ ከትንቅንቁ በአሸናፊነት ሲወጣ፤ ሁለቱ በሀገሪቱ ውስጥ ከተዘረጋው የፖለቲካ መስክ ከተሰናበቱና ውጭ ውጭውን ማለት ከጀመሩ ወደ 12 ዓመት ሆኖአቸዋል። በዚህ ዘመን ውስጥም ሁለቱም ድርጅቶች በሁለት ግንባር፤ ማለትም ባንድ በኩል በየግላቸው እናውቅበታለን በሚሉት መንገድ ፀረ-ደርግ ትግል፤ በሌላው ወገን ደግሞ እርስ በርሳቸው የመወነጃጀል ጦርነት ያካሂዱ ነበር። የኒያ ሴት አነጋገርም የሚያመለክተው ይህ በ2ኛ ግንባር የተከፈተው ጦርነት ያከተመ መሆኑ አስደስቷቸው እንደሆነ መጠራጠር አይቻልም። ሴትዮይቱ ባሉት ቆዩና የሚከተለውን ተከታተሉ፤

 

ኢዲኃቅ በሚያዝያ 1983 ዓ.ም. ተቋቁሞ በዚያው ዓመት ግንቦት ወያኔ ኢትዮጵያን ይቆጣጠራል። ወዲያው ሁለት የኢዲኃቅ አባል ድርጅቶች ከኢዲኃቅ ከድተው ወያኔ ጉያ ይሸጎጣሉ። ታወቂ የተባሉ ግለሰብ የኢዲኃቅ አባላትም አፈንግጠው በመውጣት የራሳቸውን ድርጅት ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ፀረ-ኢዲኃቅ ሆኑ። እነዚህ ሁኔታዎች ለኢዲኃቅ መዳከም አስተዋጽዖ እንዳላቸው ባያጠራጥርም ወሳኝነት ግን አልነበራቸውም። ከዚህ ይልቅ የሚከተሉት ሁኔታዎች በወሳኝነት የሚጤኑ ናቸው።

 

ከኢዲኃቅ መቋቋም ጋር እስከዚያ ጊዜ ድረስ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አንድ ክስተት ይፈጠራል። ይኸውም ለኢዲኃቅ ደጋፊ ኮሚቲዎችን ማቋቋም የሚለው ሲሆን፤ የዚህ የድጋፍ ኮሚቴ ዓላማ የነበረው በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሳይሆኑ፤ ነገር ግን በጋራ የተተለመውን የኢዲኃቅን ዓላማ የሚደግፉ ግለሰቦች እየተሰባሰቡ በመረጡት መንገድ ድጋፍና እርዳታ እንዲያደርጉ ለማስቻል ነበር። ታዲያ የድጋፍ ኮሚቴው የወርቅ ማዕድ መስሎ የታየ መሰለና ወዲያውኑ ከኢዲኃቅ አባል ድርጅቶች ውስጥ አንዳንዶቹ የራሳችውን የድጋፍ ኮሚቴ ማቋቋም ይጀምራሉ። ምናልባት “መልክ ስጠኝ እንጂ፤ ሙያ ከጎረቤቴ ...“ እንዳለችው ድርጅቶቹ ከኢዲኃቅ ተማሩ ክፋት የለውም ማለት ቢቻልም፤ የዚህን የጎን ድጋፍ ኮሚቴ መቋቋም ክፉ መልክ እንዲይዝ የሚያደርገው፤ ለኢዲኃቅ ተብሎ የተዘጋጀውን የድጋፍ ስብስብ ለኔ ሁኑ በማለት ንጥቂያም ጭምር መፈጸሙ ነበር።

 

ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፤ የየድርጅቱ አባላት እራሳቸው መልሰው የድጋፍ ደርጅት ነን እያሉ ብቅ ማለት፤ ኢዲኃቅን ወክለው በየቦታው በተለያዩ ጉባዔዎቸ ላይ እየተገኙ መግለጫዎችን እንዲሰጡና ውይይት እንዲያደርጉ የሚላኩ ግለሰቦች ስለኢዲኃቅ ሳይሆን፤ ስለራሳቸው ድርጅት ሚናና አቋም ማነብንብ፤ በየቦታው የሚገኙ ከኢዲኃቅ አባል ድርጅቶች ግለ-ሰብ አባላት የኢዲኃቅን ዓላማ በማስረዳትም ሆነ ለድርጅቱ አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን ለማሰባሰብ ኃላፊነትን እየወሰዱ እንዲሠሩ በሚደረግበት ጊዜ፤ ያንደኛው ድርጀት አባል ባለበት አካባቢ የሌላው አባል ከሌለ ያንዱ ድርጅት አባል ብቻውን የቅንጅቱን (ኢዲኃቅን) ሥራ እንዲሠራ ማድረግ የማይሞከር መሆኑን፤ ... የመሳሰሉት ሁሉ ይታዩ ነበር። ይህን ሁኔታ የሚያይ አንባቢ የርስ-በርስ መደነቃቀፍ መኖሩን ማጤኑ ብቻ ሳይሆን “ምክንያቱ ምንድነው?“ የሚል ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር ስለሆነ፤ በቀጣዮቹም ስብስቦች አካባቢ ያለው ሁኔታ ከተገመገመ በኋላ ጥያቄው ባንድ ላይ ዘግይቶ ይመለሳል።

 

2. ያማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት፤

በ1986 ዓ.ም. የአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት ከመቋቋሙ ቀደም ሲል በ1985 ዓ.ም. ፓሪስ አንድ የሚባለው ጉባዔ በፈረንሣይ ሀገር ፓሪስ ከተማ ይጠራል። በዚህ ጉባዔ ላይ በሀገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ድርጅቶች ባከሄዱት ውይይትና በደረሱበት ስምምነት መሰረት እነሱንና ወያኔ/ኢህአዲግንም ያካተተ አንድ የሠላምና ዕርቅ ጉባዔ በሀገር ቤት እንዲደረግ ስምምነት ይደረሳል። በዚህም ስምምነት መሰረት፤ ወያኔ/ኢህአዲግ በወግ በማዕረግ ስላልተጣላን ለዕርቅ እንድቀመጥ የሚያደርግ ጉዳይ የለኝም በማለት አሻፈረኝ ሲልና፤ ውጭ ያሉት ድርጅቶችም ወደሀገር ገብተው እንዳይሳተፉ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር እንዳይካፈሉ ቢያደርግም፤ ጉባዔው ሀገር ቤት በሚገኙት ተቃዋሚ ደርጅቶች አማካይነት ተካሂዶ የዚሁ ጉባዔ ውጤት የሆነው የአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት ተቋቋመ።

 

ከዚህ በኋላ በሀገር ቤትና በውጭ ያሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች ግንኙነት እውጭ ያለው ኃይል ያማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት አባል ነው አይደለም፤ ይሆናል አይሆንም በሚለው ጥያቄ ተወጠረ። ይሁንና ተወጥሮም ቢሆን ጥያቄው እስከመጨረሻው መፍትሔ ሳያገኝ ቢቆይም፤ ትርምሱ እንዳለ ሆኖ የጋራ እንቀስቃሴዎች እየተደረጉ ሰነበተ።

 

3. የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት (ኢተፖድሕ)

በ1992 ዓ.ም. ፓሪስ 2 የሚባለው ጉባዔ ይጠራና ሀገር ቤትና ውጭ ያለው ተቃዋሚ ኃይል ፓሪስ ከተማ ተሰባስቦ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት (ኢተፖድሕ) የሚባል ተፈጠረ። በዚህ ጉባዔ ላይ አዲስ የነበሩ ነገሮች፤ አንደኛ፦ ከተሰብሳቢዎቹ መሃል የጦር ትግልን እናራምዳለን የሚሉትን የተመለከተና፤ ሁለተኛ፦ የተፈጠረው የጋራ ስብስብ አመራሩ ሀገር ቤት መሆን አለበት የሚሉት ሲሆኑ፤ ሌሎቹ አጀንዳዎች ያሉና ቀደም ሲል የነበሩ ሃሳቦች ነበሩ። ብሎም የጦረኞች ጉዳይ በራሳቸው በጎ ፈቃደኝነት ጦረኝነትን ከጨዋታ ውጭ አድርገው ለሠላማዊ ትግል ብቻ የቆሙ መሆናቸውን ስላረጋገጡ አቋራጭ መፍትሔ ሲያገኝ፤ የአመራሩ ወዳገር ቤት መግባት ጉዳይ ግን ብዙ ካከራከረ በኋላ በዚህም በዚያ ተብሎ ዕድሉ ሆነና አመራሩ በስደት እንዲቆይ ተደረጎ ጉባዔው ተጠናቀቀ።

 

ከዚያም ውሎ ሳያድር፤ ኃላፊነቱ በተሰጠው አካል ላይ በመጀመሪያ ከውጭ የስብስቡ አካላት አንደኛው “አመራሩ ውስጥ የኔ ሰው የለበትም“ በሚል ኃላፊነቱን በያዘው ሰው ላይ ተቃውሞ ያነሳል። ከሀገር ውስጥ ደግሞ አንዱ ድርጅት፣ “የውጭውን አመራር የያዘው ሰው ለውጭ ኃይሎች የሚመች አይደለምና ቀፈፈኝ፤ ከኢተፖድህም ወጥቻለሁ አለ። በሁለቱም ወገን ተቃውሞ የቀረበበት ኃይል በጉባዔው በነዚሁ ተቃዋሚዎች ተባባሪነት በልመና ጭምር ኃላፊነቱ የተሰጠው ነው። አንባቢዎች ትንሽ ግር ይላችሁ ይሆናል፤ የሆነ ነገር ስለሆነ ያዙት።

 

4. “የኢትዮጵያ ዲሞከራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዲኃሕ)

በ1995 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ አሁንም ሀገር ቤት ያለውና እውጭ ያለው ተቃዋሚ ድርጅት በዋሽንግተን ተሰባሰበና “የኢትዮጵያ ዲሞከራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት“ን (ኢዲኃሕ)ን ፈጠረ። ይህ ሕብረት ችግር የገጠመው ገና ተሰብሳቢዎቹ ሕብረቱን ከቋጠሩበት ከአሜሪካ ሀገር ወደየመጡበት ጣቢያ ከመመለሳቸው በፊት እዚያው እንዳሉ ነበር። የጀመሩትን አተኻሮ እንደያዙ ያገር ቤቶቹም ወዳገር ቤት ገቡ፤ የውጭም እንደልማዱ ባለበት ተከበረ። ወደ ሀገር ተመላሾች ውስጥ ግማሹ ተገንጥሎ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የሚለውን ድርጅት ፈጠረ። የተቀረው ያገር ቤቱ ሕብረት እውጭ የቀሩትን አባላቱን “ሀገር ገብታችሁ ተመዝገቡ፤ ሕጋዊ ካልሆናችሁ በሕብረት አካልነት ተቆጥራችሁ በምርጫ ተጠቃሚ አትሆኑም“ ሲል መልዕክት አስተላለፈ። የውጭ አካላት ደግሞ “ለኛ የሚሆን ልዩ ዋስትና ካላገኘን አንገባም“ አሉ። ነገሩ የዋስትና ጉዳይ ሳይሆን የየራሳቸው የውስጥ ጉዳዮች ነበሯቸው የሚለው አስተሳሰብ ሚዛን የሚደፋ ነበር።

 

ለጊዜው ከዚህ በላይ አልቆይበትም። ባጭሩ ከላይ የጠቀሰኳቸውን ስብስቦች እያንዳንዳቸውን በተመለከተ ያቀረብኩት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከዚህ በታች ያሉትን ሕብረቶቹ በጋራ የሚጋሩዋቸውን ጠባዮች ልጠቁምና ወደማጠቃለያዬ ላቅና።

 

ድርጅቶቹ፦

1. ስብስቡን ለመፍጠር ከመገናኘታቸው በፊት እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

2. ተወካዮቻቸው ከራሳቸው ሌላ የሚወክሉት አባል ይኑራቸው አይኑራቸው ጥያቄ ውስጥ አይገባም፤

3. በተጨባች ምን እየሠሩ እንደሆነም ለማወቅ የሚደረግ ጥረት የለም፤

4. በጉባዔ በሚያስተላልፉት ሰነድ ላይ የመሪዎችን ፈርማና ማኅተም ማኖር ታስቦም አይታወቅ።

5. ለፈጠሩት ድርጅት/ስብስብ ሥራ መንቀሳቀሻ የሚሆን መዋጮ/ክፍያ መወሰን የሚባል ጉዳይ ባዕድ ዘር ነው፤

6. አንዱን ስብስበ/ድርጅት ትተው ሌላ ሲመሠርቱ ያለፈውን ገምግመው፣ ጥፋትና ልማቱ ታውቆ፣ በይፋም ከዚህ ጊዜ አንስቶ ይህ ድርጅት/ስብስብ ፈርሷል ብለው የገለጹበት ጊዜ ተሰምቶም አይታወቅ። እነዚህ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።

 

ማጠቃለያ

ስለመጀመሪያው ስብስብ (ኢዲኃቅ) ያቀረብኩትን ሃሳብ ስደመድም፤ አንባቢ በውስጥ የርስ-በርስ መደነቃቀፍ መኖሩን ማጤኑ ብቻ ሳይሆን፤ ምክንያቱ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር መሆኑን ጠቁሜ፤ በቀጣዮቹም ስብስቦች አካባቢ ያለው ሁኔታ ከተገመገመ በኋላ ጥያቄው ባንድ ላይ ዘግይቶ ይመለሳል በሚል ካቆየሁት ሃሳብ በመነሳት፤ የሚከተለውን ልበል፦

 

ባቀረብኳቸው ስብስቦች ውስጥ ለታዩት ትርምሶች የመሰረት ድንጋይ አለመተማመን ነው። ላለመተማመኑ ምክንያቶቹ ስፍር ቁጥር የላቸውም። ለናሙና ያህልም የሚከተሉትን ልወርውር፤

 

1. ያልተቀረፈ በድርጅቶች መካከል ያለ ቂም በቀል፤ - በሁሉም አባላት መካከል ቂም በቀል አለ ማለት ባይቻልም፤ ሁለትም ሆኑ ሦስት በሆዳቸው ቂም ቋጥረው የተቀላቀሉ መኖራቸው፤ በጋራ ጉዳዩ ላይ ከማተኮር ይልቅ አንዱ የሌላውን እንቀስቃሴ መከታተል ላይ ማተኮር፤

2. እርስ በርስ በሁለትዮሸም ሆነ በሌላ መልክ የሚደረግ ቅድመ ትውውቅ በድርጅቶች መካከል አለመኖር፤

3. የሀገር ቤቱ ድርጅትና የውጨው ደርጅት መቀላቀል ያስከተለው ቸግር፤ በዚህ 3ኛው ነጥብ ላይ የሚከተለውን ማለት አስፈላጊ ይመስለኛል። በተለይ የሥራ ድርሻን መከፋፈል በሚመለከት፤ ያገር ቤቱ ኃይል ኃላፊነት ሲቀበል ያንን ኃላፊነት በሀገሪቱ ሁኔታ ሊፈጽመው እንደማይችል ቢያውቅም፤ ከውጭው ኃይል የሚደረግለትን የገንዘብ ድጋፍ ላለማጣት በማሰብ ኃላፊነቱን እንደሚፈጽም ቃል ገብቶ፤ እጅ ነስቶ ይቀበልና ይሄዳል። ከዚያ ሰነባብቶ ሥራ እንዴት ነው ሲባል፤ እናንተ እኮ ሀገር ቤት ያለውን ሁኔታ አታውቁትም፤ መከራ ውስጥ ስላለን ያንና ይሄንን መሥራት አልተቻለም ይላል።

4. የስብስቡ አባላት በሚጠሉትና በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ያላቸው አቋም ቁርጥ ያለና ግልጽ አይሆንም። አንዳንዱ ጠቡ ከወያኔ ወይም ከሥርዓቱ ጋር ሳይሆን ጠቡ ከመለስ ጋር ብቻ ይሆናል፤ ሌላው ወያኔን ማስወገዱ ላይ እንጂ ከዚያ ባሻገር ያለውን ጉዳይ ከጎን ጎኑ አያገላብጠውም። የሚጠላውንና የሚፈልገውን ያወቀው ደግሞ ፀረ-ዲሞክራቱን ሥርዓት አስወግዶ ዲሞክራሲያውን ሥርዓት ለማምጣት ነው የምፈልገው ቢልም፤ ወደዚያ በሚያደርሰው መንገድ ላይ ግን ችግር አለበት። የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚለካው የነፃና ፍትሃዊ ምርጫ መካሄድ ሲቻል ስለሆነ፤ የምርጫ ጉዳይ ሎቶሪ ነውና በጋራ የሚራመደው ትግል ከወዲሁ የሱን ሥልጣን ለማስያዝ ዋስትና የማይሰጠው መስሎ ሲታየው፤ የሚጠበቅበትን ከማደረግ ወደኋላ መጎተት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ መሰናክል ወደመፍጠር ይሸጋገራል።

 

አንባቢዎች እነዚህ 4 ምክንያቶች ከብዙ በጥቂቱ ቢሆኑም ዋና-ዋናዎቹ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ በርግጥም የሆኑና የነበሩ መሆናቸውም የሚያጠራጥር አልነበረም። ለመገንዘብ ግን የግድ በቅርብ ሆኖ መከታተልን ይጠይቃል። የዚህን ክፍል በዚህ ልግታውና አንባቢዎች ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ድርጅት እየተሰባሰበ በተለያየ ስም የጋራ ድርጅት በማቋቋም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ እለውጣለሁ ባለው የትግል አቅጣጫ ምን የፈየደው ነገር አለው? የሚል ጥያቄ እንደምታነሱና ማንሳትም እንደሚገባ ስለማምን ያለኝን መልስ ጀባ ብየ ልሰናበት።

 

ከጽሑፌ መጀመሪያ አናት ላይ ወዳስቀመጥኩዋት ትንሽ ጥቅስ ልመልሳችሁና ያንን አነጋገር የተናገሩት አንዲት የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ ሴት ሲሆኑ፣ እነዚህንም ከላይ የዘረዘርኳቸውን ስብስቦች በተመለከተ ልንታግልለት ቆመናል ላሉት ዓላማ የሚያደርጉትን ጥረት እርስ በርሳቸው ከሚያደርጉት ሽኩቻና ትርምስ ጋር ካነጻጸሩ በኋላ የደረሱበት ድምዳሜ ነው።

 

ቸር ወሬ ያሰማን!

ከዚህ በላይ በየመልኩ በዘበዘብኩት ምክንያት አንዱም ስብስብ አንዲት ዝንብ እንኩዋን ከወያኔ ፊት ላይ እሽ ሳይል ዛሬ ላይ ደርሷል። የወደፊት ሕብረት ፈጣሪዎች ከዚህ ጽሑፍ ትምህርት የሚሆን ነገር ታገኙበታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

 

በማንኛውም ደረጃና ምክንያት በጋራ ለሚሠራ ጉዳይ የሚጠይቀው የመጀመሪያውና የጉዳዩ የጀርባ አጥንት ጥያቄ በጋራ በተወሰነው ጉዳይ ያለምንም ማቅማማት ማመንና ለጉዳዩ እዳር መድረስ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ቅድሚያ በቁርጠኝነት መሥራት ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!