ስሜነህ ታምራት (ከስዊድን)

"... ገዢው መንግሥት ሥልጣን ሲለቅ ተቀናቃኝ የነበሩ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱማ ማንም የሚያውቀውና ባለፉት ሁለት መንግሥታት መለዋወጥም አይተነዋል። አሳሪውን መንግሥት በምርጫ ከሥልጣን ስናስወግደው ያኔ የብርቱካን ነፃነትም ይከበራል ብሎ መናገር ወያኔ እስከሚወርድ ድረስ ብርቱካን በእስር የመቆየቷን ጉዳይ አምኖ እንደመቀበልም ይቆጠራል። ከዚህም ባሻገር የዕድሜ ልክ እስራቱንም ቢሆን እንደመቀበል ይመስላል። ይህ መግለጫ በተለይ ከራሷ ፓርቲ አንደበት መውጣቱ በእጅጉ ያሳፍራል። ..."

 

መሪውን ያላስፈታ ፓርቲ አዝማች እንደሌለው ጦር ይቆጠራል

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የቅንጅት ዓላማ ወራሽ ሆኖ ብሔራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለው የአንድነት ፓርቲ ፈለግን የተከተሉ በርካታዎች ነበሩ። በዚህ የተነሳም ደጋፊው ከፓርቲው ምስረታ ጀምሮ ሁለንተና ድጋፉንና አብሮነቱን በተግባር አሳይቷል። በሀገር ቤት የክልል ጽ/ቤቶችን ሲከፍትና ህዝባዊ ውይይቶችን ሲያካሂድ በየቦታው እየተገኘ “አይዞህ! በርታ! ከጎንህ ነን” በማለት አዎንታዊ ድጋፉን ለግሶታል።

 

ፓርቲው በውጭ ሀገር ለሥራ ጉብኝት ሲንቀሳቀስም ተመሳሳይ ህዝባዊ ድጋፍ አልተለየውም ነበር። ህዝቡ በየጊዜው ድጋፉን የገለፀበት አንድ መሰረታዊ ምክንያት ነበረው። ይህም አንድነት በትክክል የቅንጅትን ዓላማ ይዞና ከድክመቶቹ ተምሮ የኢትዮጵያን ህዝብ ላቅ ወዳለ ዲሞክራሲያዊ እርከን ያሸጋግራል የሚል ተስፋ ጨብጦ በመነሳቱ ነው።

 

ይሁን እንጂ አንድነት ሊቀመንበሩን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ከመምረጡ በፊት ይታይ የነበረው ስውር ሽኩቻ አሁን አሁን ዓይኑን አፍጥጦና ጥርሱን አግጥጦ በይፋ መታየት ጀምሯል። በመጀመሪያ በፓርቲው ምስረታ ወቅት ብርቱካን እንድትመረጥ ይፈልጉ የነበሩ ግለሰቦችን በሰበብ አስባቡ ፊት በመንሳትና በማግለል ሥልጣንን በእነሱ ደጋፊዎች ብቻ ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት በግልፅ ይታያል። የፓርቲው ሊቀመንበር ከታሰረች በኋላም እስሩ የግል ጉዳይ ነው፣ ጉዳዩን በሕግ እየተከታተልነው ነው፣ ኮሚቴ አቋቁመን በኮሚቴ እየታየ ነው፣ … ወዘተ እየተባለ የመሸንገያ መግለጫዎች ሲሰጡ ተደምጠዋል።

 

ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚደግፈውን ፓርቲ ውስጠ ገላ ቀርቶ የመንግሥትን አድራጎት አሳምሮ ስለሚያውቅ ከእውነታው ውጪ በምርጥ ቃላትና በለስላሳ አንደበት እውነትን መሸፋፈን የቀረ አካሄድ ነው። አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ የአንድነት ደጋፊዎች ከፓርቲው የሚጠብቁት በርካታ ብሔራዊ ተግባራት አሉ። ነገር ግን ከሚጠብቃቸው ብሔራዊ ኃላፊነት አንፃር ግምት ውስጥ የማይገባ ልዩነታቸውን በውስጥ መፍታት ተስኗቸው አደባባይ መሳለቂያ መሆኑ በደጋፊው ላይ የፈጠረው ኀዘንና የሞራል ውድቀት በቀላሉ አይታይም።

 

ይህ ህሊና የሚያቆስል አፍራሽ አድራጎት በመልካም ተግባር ሳይጠገን፤ የመሪዎቹ መከፋፈልና አንዱ አባራሪ፣ ሌላው ተባራሪ የመሆኑ ፈሊጥም በእጅጉ አሳዛኝ ጥፋት ነው። በጉዳዩ ግራ የገባቸውና የተደናገጡ ደጋፊዎች ችግሩ በሽምግልና እንዲፈታ ጥረት የማድረጋቸው ፋይዳም በፓርቲው ውስጥ ከመሪዎቹና ከተመሪዎቹ ቅራኔን በአግባቡ በመፍታት ማን ልቆ እንደሚገኝ በግልፅ አሳይቷል።

 

ውድ አንባብያን! ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ መስከረም 24 ቀን 2002 ዓ.ም. ስዊድን የሚገኘው የኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ ከፓርቲው ዋና ፀሐፊ ከአቶ አስራታ ጣሴ ጋር ያደረገው ቃለምልለስ ነው። ዋና ፀሐፊው አቶ አስራት ጣሴ መድረክ ከገዥው ፓርቲ ጋር ስለጀመረው ድርድር ሰፊ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ “የብርቱካንን መፈታት እንደቅድመ ሁኔታ ታቀርቡታላችሁ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ በእኔ አስተያየት፤ “የብርቱካን ትፈታ!” ትግልን የሚያቀዘቅዝ ሆኖ ስላገኘሁት ግላዊ አስተያየቴን ቀጥሎ አቀርባለሁ።

 

አቶ አስራት ጣሴ በንግግራቸው፤ “እኛ ወ/ት ብርቱካንን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞችን የተመለከተ ጥያቄ አቅርበናል። በድርድሩ አጀንዳ ውስጥ ወ/ት ብርቱካንን ጠቅሶ መጠየቁ ግን ጠቃሚነቱ ጎልቶ አይታይምና ይህን አላደረግንም” ብለዋል። በማያያዝም የብርቱካን የዕድሜ ልክ እስራት የኢህአዲግ ዕድሜ ሲያልቅ አብሮ ስለሚያልቅ፤ ይህን መንግሥት በምርጫ በመጣል የእርሷን ነፃነት ማስከበር እንደሚቻል አብራርተዋል። እዚህ ላይ ያልጠበቅኩት ንግግር ስለሆነ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንዳነሳ ስሜቴ አነሳሳኝ።

 

መንደርደሪያ

ራሱን መከላከል ያልቻለ ፓርቲ እንዴት ነው ሌላውን ማዳን የሚቻለው? ብርቱካን የገጠማት ዕጣ ፈንታስ ነገ በእነአቶ አስራት እና በሌሎቹ ላይ ላለመደገሙ ዋስትናው ምንድን ነው? የዲሞክራሲ መሠረታዊ ጥያቄስ የሰዎች ነፃነት ወይስ የምርጫ አካሄድ (procedure)? አሳሪ መንግሥት ከሥልጣን ሲወርድ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው ዛሬ በአንድ ፓርቲ መሪ የሚነገር መግለጨ ወይስ የታወቀ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር እውነት? ለጥያቄዎቹ በዝርዝር መልስ መሰል አስያየት መስጠት አንባቢን ማሰልቸት ስለሚሆን አንኳር አንኳር የሚመስሉኝን መሠረተ ሃሳቦች ግን በሚከተለው ሁኔታ አቀርባቸዋለሁ።

 

የብርቱካን ጉዳይ የሀገርና የህዝብ ጉዳይ በመሆኑ የትፈታ ትግሉም ብሔራዊ ሊሆን ይገባዋል

ብርቱካን በቅንጅት ውስጥ የተፈጠረው የአካሄድ ልዩነት አድጎና ጎልት ድርጅቱን እንዳያናጋና ህዝባዊ ትግሉ እንዳይቦረቦር ገና ከመጀመሪያው ጀምራ መሪዎቹን እንደአባት አክብራ ለአንድነት የተማፀነች የአንድነት መሠረት ናት። በሰው ልጆች እኩልነት፣ በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በሕግ የበላይነትና በሠላማዊ ፖለቲካዊ ፉክክር መንግሥታዊ ሽግግር ሊመጣ እንደሚችል የምታምንና ለዚህ ህዝባዊ ዓላማም ማናቸውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጣ የተነሳች የዲሞክራሲ ጠበቃነቷን በተግባር አሳይታለች።

 

ማናቸውም መንግሥታዊ ማስፈራሪያና ዛቻ ድፍረቷንና በራስ መተማመኗን ያልበገራት፣ ለህዝባዊ ጥያቄና ለሕግ የበላይነት ራሷን ለመስዋዕትነት በማቅረቧ በአርኣያነቷ መላው ደጋፊ የሚኮራባት መንፈሠ ጠንካራ የፓርቲው መሪ መሆኗን ማንም ደጋፊ ይገነዘበዋል።

 

ዛሬ የወያኔ በህዝብ መጠላት ጣራ መድረሱ በአንድ በኩል፤ የብርቱካን ፓርቲ የማደራጀት እንቅስቃሴና ህዝባዊ ተቀባይነት ማግኘት በሌላ በኩል ተዳምረው የወያኔን የሥልጣን ዕድሜ አደጋ ውስጥ ጥለውታል። እንግዲህ ብርቱካንን ብቻ ለይቶ በድጋሚ የማሰር አባዜም ዋና ምክንያቱ ይኸው ነው። የብርቱካን የማይናወፅ ጽኑ ሰብዕናዋም ወያኔን ክፉኛ አበሳጭቷል። ከታሰረች በኋላ እየተፈፀመባት ያለው ሁለንተና ግፍ ሁሉ የዚሁ የወያኔ የመበሳጨት ስሜት የፈጠረው እኩይ ተግባር ነው።

 

እዚህ ላይ በውል መጤን ያለበት አንድ መሠረታዊ ጉዳይ አለ። የብርቱካን ሠላማዊ ተጋድሎና የብርቱካን ልፋት የግል ሥልጣን ጉዳይ አይደለም። ይህ ቢሆንማ ኖሮ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ የፈለጉትን ከመፍረድ በላይ ሥልጣን ምን ያደርግላት ነበር? የእሷ ጥያቄና የእሷ ትግል ሀገር የማዳንና ትውልድን ከጥቃት የመከላከል ብሔራዊ ተግባር ነው። ትግሏ የሀገርና የህዝብ እንደመሆኑ መጠን የብርቱካን የመፈታት ጥያቄም ብሔራዊ ደረጃ ሊሰጠው ይገባል እንጂ፤ አቶ አስራት እንደሚሉት የእሷ የነፃነት ጥያቄ ከወያኔ ሥልጣን ማክተም ጋር መያያዝና መቆራኘት በጭራሽ አይገባውም።

 

ገዢው መንግሥት ሥልጣን ሲለቅ ተቀናቃኝ የነበሩ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱማ ማንም የሚያውቀውና ባለፉት ሁለት መንግሥታት መለዋወጥም አይተነዋል። አሳሪውን መንግሥት በምርጫ ከሥልጣን ስናስወግደው ያኔ የብርቱካን ነፃነትም ይከበራል ብሎ መናገር ወያኔ እስከሚወርድ ድረስ ብርቱካን በእስር የመቆየቷን ጉዳይ አምኖ እንደመቀበልም ይቆጠራል። ከዚህም ባሻገር የዕድሜ ልክ እስራቱንም ቢሆን እንደመቀበል ይመስላል። ይህ መግለጫ በተለይ ከራሷ ፓርቲ አንደበት መውጣቱ በእጅጉ ያሳፍራል።

 

የፖለቲካ እስረኞችን መፈታት ያላስቀደመ ፖለቲከኛ እሱ ራሱ ነገ ላለመታሰሩ ዋስትናው ምንድን ነው?

ማናቸውም ለሥልጣን የሚታገል የፖለቲካ ፓርቲ ከሁሉ በፊት ማለትም በምርጫ ወደሥልጣን ለመውጣት ከመነሳቱ በፊት የፓርቲው ቁልፍ አንቀሳቃሽ ካድሬዎቹ የሚገኙበትን የደህንነት ሁኔታ በአስተማማኝ ደረጃ ለማስከበር የሚያደርገው ስምምነት የፉክክሩን ዲሞክራሲያዊነት ከወዲሁ አመላካች መሆኑን መረዳት ይኖርበታል። በአንፃሩም ለህዝብ ቅርብ የሆኑ አደራጅና ቀስቃሽ ሠራተኞቹ እንዲሁም የፓርቲው ዋና መዘውር ማለትም የፓርቲውን መሪ በእስር እያንገላታበት የሚገኘው ገዥ ፓርቲ ሥልጣኑን በቀላሉ ለማስረከብ የተዘጋጀ መንግሥት ነው ብሎ በምርጫ ላይ ብቻ ማተኮር ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደመጠበቅ ይቆጠራል።

 

ዛሬ በእስር ላይ ለሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ያልተሟገተ ፓርቲ፤ ነገ ሳይሆን ዛሬ ምሽት በራሱ ላይ የሚደርስበት አደጋ ምን እንደሚሆን እንኳን ለማወቅ ይሳነዋል። እንዲህ ባለ የደመነፍስ እንቅስቃሴ ህዝብን መርቶ ለሥልጣን ማብቃት የሚጠይቀው ጊዜ ደግሞ እጅግ ረጅምና ውስብስብም ነው። የዲሞክራዊያዊ ምርጫ መገለጫ ባህርያት በርካታ ዘርፎች ቢኖሩትም አንዱና ዋናው ግን፤ የፓርቲ ሰዎች በነፃነት መንቀሳቀስና በህዝብ መካከል ተገኝተው የምረጡኝ ዘመቻ የሚያካሂዱበት ሁኔታን ማረጋገጥ መሆኑ ይታመናል። ዳሩ ግን የፖለቲካ ሰዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ቀርቶ ከእስር ቤት ሳይለቀቁ ፓርቲው በምርጫ ተወዳድሬና አሸንፌ ሥልጣን ስይዝ አስፈታቸዋለሁ የሚል ከሆነ፤ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም ብቻ ሳይሆን፤ ህዝብንም በህልም እንጀራ እንደማጥገብ ይቆጠራል። ስለሆነም የዛሬ ተቃዋሚዎች በሚያደርጉት ድርድር ለሌሎች ብለው ሳይሆን ለራሳቸውም በነፃነት መሥራት ሲሉ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጥያቄ የግንባር ቀደም ጥያቄ ሊያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በላይ መሪውን ሳያስፈታ ወደምርጫ የሚሄድ ፓርቲ፤ ያለጦር አዝማች ጦርነት እንደከፈተ ኃይል ይቆጠራል። ውጤቱና ባለድሉም በቅድሚያ ይታወቃል።

 

ይህ ሳይሆን ቢቀርና ወያኔን ከማስጨነቅና ሁኔታዎችን እንዲለውጥ ከማስገደድ ይልቅ አብሮ በመሳተፍ ህዝባዊ ድል ይመጣል ብሎ ማመን እራስንም ሆነ ሌላውን አደጋ ላይ መጣል መሆኑ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። ከእንግዲህ ወዲህ ጥንቃቄ በጎደለው አካሄድ እየተጓዙ መሪዎቹ ነገም ሌላ አደጋ ቢደርስባቸው የዲሞክራሲያዊ ግንባታው በ“መሪዎች ይፈቱ!” ጥያቄ ተለውጦ የድላችንን ዘመን ማራዘም አይጠበቅብንም።

 

ስለሆነም የፓርቲ መሪዎች የሚሠሩትን አውቀውና የሚናገሩትን መጥነው ኃይልን አጠናካሪና አሰባሳቢ የሆነ ተግባር በማከናወን የሚሠሩትን ቅደም ተከተል አውጣተው ብሔራዊ ቅራኔዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በዓላማቸው ፀንተው በቆራጥነት ሊራመዱ ይገባል። “እኔ በመንፈሥም በራዕይም ፅኑ ነኝ። እናንተስ?” በማለት የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ላቀረበችው የማረጋገጫ ጥያቄ ሁላችንም መልሳችንን እናዘጋጅ በማለት የብርቱካን ሚደቅሳ የትፈታ ጥያቄ አንድነት ከገዥው ፓርቲ ጋር ከሚያደርጋቸው ድርድሮች ውስጥ የግንባር ቀደም ጥያቄው ሆኖ ሊቀርብ ይገባል ብዬ በግሌ አምናለሁ።

 

ማጠቃለያ

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የመሪው የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የመፈታት ጥያቄ የምርጫ ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ሊያቀርብ ይገባል። የፓርቲው አደራጅ፣ መሥራችና መሪ ያለተጨባጭ ምክንያት መታሰር ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በሚዘገንን ሰብዓዊ መብት አያያዝ እየተሰቃየች ትገኛለች። መሪዋ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ላይ እያለች ፓርቲው መሪውን ሳያስፈታ ወደ ምርጫ መግባት ያለአዝማች እንደመዝመት ይቆጠራል።

 

በእርግጥ ዛሬ አንድነት ፓርቲ የመድረክ አባል ነው። የፓርቲው ፕሮግራም እንደተጠበቀ ቢሆንም በመድረክ አባልነቱ በግል የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች በጋር ተወስነው በመድረኩ በኩል የሚቀርቡ መሆናቸው ይታወቃል። ይሄ አካሄድ ዲሞክራሲያዊ መንገድ ነው ቢባል እንኳ፤ አንድነት በራሱ ግን የብርቱካንን መፈታት የቅድመ ሁኔታ ጥያቄ አድርጎ ለመድረክ ማቅረብ የሰብዓዊነትም ሆነ የሞራል ግዴታ ነበረበት። ከዚያ በኋላ በጋራ በሚወሰነው አካሄድ ቢጓዝ እንኳ አግባብነት ያለው መንገድ ይመስላል። ዳሩ ግን ይህ ሳይሆን፣ ገና ከጅምሩ ፓርቲው እራሱ የብርቱካንን የመፈታት ጥያቄ የምርጫ ቅድመ ሁኔታ አድርጌ አላቀርብም የሚል ከሆነ በእርግጥ ትግሉ የዲሞክራሲያዊ ግንባታ ሳይሆን የሥልጣን ግንባታ ይመስላልና ጥንቃቄ ቢደረግበት ይበጃል በማለት አሳቤን አጠቃልላለሁ።

 

ውድ አንባብያን!

ግላዊ አስተያየቴ የብርቱካንን ከእስር የመፈታት ጥያቄ ለአንድነት ፓርቲ ቀዳሚ ጥያቄውና ቀዳሚ ተግባሩም ሊሆን ይገባል ከሚል መሠረታዊ ሃሳብ ተነስቼ እንጂ፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ትግል ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ከመሰዋት አልፈው ብዙ እስርና እንግልት የደረሳባቸውን ወገኖች ሞራልና ስሜት ለመንካት አለመሆኑ እንዲታወቅልኝ እሻለሁ። አንዳንዴ ታላላቆቹ ከታናናሾቹ ሊማሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ ብዬም አምናለሁ። ከዚህ እውነታ ወጥቼ ባልሆነ መልኩ ገልጫቸው ከሆነ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ።


ስሜነህ ታምራት (ከስዊድን) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ