ከዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም

Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2000 ዓ.ም. March 14,2008) የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29፣ ግለሰቦችም ሆኑ ፕሬስ ወይንም ሌሎች መገናኛ ብዙኀን ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽ ተፈጥሮአዊ መብት ያረጋግጥላቸዋል። የአሜሪካ ሕገ መንግሥት እነዚህን መብቶች ከማረጋገጥ አልፎ እንዲያውም ኮንግሬስ ይህንን መብት ለመገደብ ሕግ ሊያወጣ እንደማይችል ይደነግጋል። ይህ የንግግርና የጽሁፍ ነፃነት ይህን ያህል ዋጋ የሚሰጠው ያለ ፕሬስ ነፃነት ዲሞክራሲና የተመጣጠነ ክብር ያለው ኑሮ ለመኖር የሚያስችል ልማት ፈጽሞ የማይታሰብ በመሆኑ ነው። የፕሬስ ነፃነት መዳበር ወይንም መቀጨጭ አንድ አገር በሥልጣኔ ምን ያህል ወደፊት እንደመጠቀ ወይንም ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረ የሚጠቁም ነው።

 

ማንኛውም መብት ግዴታን እንደሚያስከትል ሁሉ የሌላውን መብት ለማስከበርና ለመጠበቅ ሲባል በፕሬስ ነፃነት ላይ በሕግ በተደነገገው መሠረት ገደብ ሊጣልበት ይችላል። ሕግ ለፕሬስ ነፃነት ይህን ያህል ጥበቃ የሚያደርግለት፣ የንግግርና የጽሑፍ ነፃነት ተፈጥሮአዊ መብት ከመሆን አልፎ ሕዝብን ስለሚያስተምር፣ ስለሚያሳውቅና ስለሚያዝናና ነው። ከእነዚህ የተቀደሱ ተግባራት ወጥቶ የሰውን መልካም ስም በሃሰት በሚያጠፋበት ጊዜ ወይንም ሕብረተሰቡን የሚጎዱ ተግባራት ለምሳሌ በብሔረሰቦች መሃከል ጥላቻ እንዲፈጠር በሚያነሳሳበት ጊዜ ወይንም ጦርነትን በሚቀሰቅሱ ተግባራት በተሰማራ ጊዜ ከድርጊቶቹ እንዲታቀብ ከዚያም ሲያልፍም በወንጀል ተከስሶ ሊቀጣ ይችላል።

 

በሃገራችን በአሁኑ ወቅት ጋዜጦች የተለየ ሃገራዊ ኃላፊነት አለባቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ጋዜጦች እስኪንዱት ድረስ በጋዜጣ የወጣ ማንኛውም ዜና ፍጹም ተዓማኒነት ነበረው። አገራችን በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ አመለካከትና ወገንተኛነት፣ በአይዲኦሎጂ፣ በመደብና በዘር ክፉኛ የተከፋፈለች አገር ስትሆን እርስ በርስ መጠራጠር፣ መናናቅ በተለያዩ ምክንያቶች ላይ የተንጠላጠሉ ጥላቻዎች እየተስፋፉ ነው። ስለዚህ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ሕዝብን የማግባባት እና በፖሊስ ላይ ብቻ ያተኰረ የሰለጠነና ሠላማዊ ፍልሚያና ፉክክር እንዲያደርጉ ማበረታታት፣ ጥላቻ ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ሌላውን ወገን ካለማወቅ ስለሆነ ህዝቡን ማስተዋወቅ፣ ገበሬውና ሠራተኛው ለሥራ ማነሳሳት፣ የመንግሥት አካላት በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት በደል ቆፍሮ አውጥቶ ማጋለጥ የመሳሰሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኰር ይኖርባቸዋል። ለጹሁፌ መነሻ ወደሆነኝ ጉዳይ ልመልሳችሁ በዚህ ሰሞን መውጣት የጀመረ አንድ ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው በተከታታይ ሁለት እትሞቹ በእኔ በአንድ ተራ ዜጋ ላይ ከባድና ሃሰተኛ ወንጀል ማዥጎድጎዱን ተያይዞታል። 60 ከሚጠጉት ከቀድሞው ቅንጅት የአመራር አባላት እኔን መርጦ ከባድ የሃሰት ወንጀል ሊለድፍብኝ መነሳሳቱ ከማስገረም በስተቀር አላስደነገጠኝም። ነገር ግን ምንም ያልጠበቅሁትና ያላለምኩት ሌባ ዝናብ ሆነብኝ።

 

«ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ» በሚሉት ዓይነት ዘመድ ለመጠየቅ ዓይኔን ለመታከም አሜሪካ በዘለቅሁበት ጊዜ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሌላ በአካልም ሆነ በሌላ መልኩ ፍጹም ያልተገናኘኋቸው ሰዎችንም ሆነ ድርጅቶች አግኝቼ ከእነርሱ ጋር ተሰብስቤ አገራችንን በጦርነት ለማናወጥ ተስማምቼ ለዚህ ተግባር በእነዚሁ አካላትና ግለሰቦች ተወክዬ ወደ አገሬ መመለሴን ጽፎአል። ጋዜጣው ጥረቱ ለእኔ ፍጹም በማይገባኝ ምክንያት በአገር ክህደት ወንጀል ተከስሼ የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶብኝ ስለነበረ፤ አሁንም ይህንኑ የአገር ክህደት ወንጀል የለጠፈብኝ ቀደም ሲል በተከሰሰበት ወንጀል ተሰማርቶአል በማለት ይቅርታው ተሰርዞ ወህኒ ቤት እንድወርድ ለመገፋፋት ነው የሚል ሃሳብ አጫረብኝ። ከዚህ መለስ ካለም በውንጀላው ተደናግጬ አገር ለቅቄ እንድሰደድ ይሆን ስልም አሰብኩ። በዚህ መሠረት ቢስ ውንጀላ ዘብጥያ ብወርድ ለመከላከል የማደርገው ነገር የለም። አገሬን ለቅቄ የትም እንደማልሄድና በአገሬ ዴሞክራሲ ሰፍኖ የሕግ ልዕልና ተከብሮ ሕዝባችን ለሰው ልጅ ተገቢ የሆነ ክብር ያለው ኑሮ እንዲኖር የአቅሜ አስተዋጽኦ ለማድረግ የገባሁት ቃል መቼም አላጥፈውምና የትም አልሄድም። ጠንካራ ተቃዋሚ መኖር ዘለቄታነት ላለው ዴሞክራሲና ለልማት እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆናቸው ፓርቲያችንን ለማጠናከር ከመሥራት አሁንም አልቦዝንም። እቅጩም ይኸው ነው።

 

አንድን ሰላማዊ ዜጋ በእንደዚህ ዓይነቱ መሠረተ ቢስ ክስ መወንጀል አንድም «ጌታዋን የተማመነች በግ ጅራቷን ውጭ ታሳድራለች» ከሚለው የመነጨ ወይንም ደግሞ አንድ ሊቅ እንዳለው «ምሁራን ስለረቂቅ ሃሳቦች ሲጽፍ «ሌሎች» ደግሞ ስለሰው ሃሜታ መጻፍ ይወዳሉ» የሚለው ብቻ ይሆናል። በዚህ ጽሁፍ በተሰነዘረብኝ ሃሰትና ከባድ ወንጀል በምርመራ ተጣርቶ ክስ እንዲመሠረትልኝ መጠየቅ እችል ነበር። ውጤቱ ከወዲሁ ግልጽ ስለሆነ ስለ ነፃ ፕሬስ አስፈላጊነት ባለኝ ጽኑ እምነት ምክንያት ጋዜጦች ተከስሰው በሚጽፉት እንዲሸማቀቁ አስተዋጽኦ ማድረግ አልፈልግም።

 

ሌላው ክስ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማስተባበር ዶ/ር ነጋሶን፣ ፕሮፌሠር በየነን፣ ዶ/ር መራራንና አቶ ቡልቻን በተለያዩ ወቅት አነጋግሮአል የሚል ነው። እነዚህን ግለሰቦች ሁሉንም ስለማውቃቸው አንዳንዴ ለመዝናናት አንዳንዴም በአገራችን ጉዳይ ለማውራት በተለያዩ ጊዜዎች አግኝቼአቸዋለሁ። እነርሱን ለማስተባበር አቅሙም ሆነ ኃላፊነቱ የለብኝም እንጂ ባስተባብራቸው ወንጀልም ባልሆነ ነበር።

 

ከቅንጅት አንኳር መርሆዎች አንዱ ለዴሞክራሲ፣ ለነፃነትና ለፍትሕ ታግሎ በነፃና በሰላማዊ ውድድር በሕዝብ ነፃ ውሳኔ ሥልጣንን መያዝ ወይንም ከሌሎች ፓርቲ/ፓርቲዎች ጋር ሥልጣንን መጋራት ነው።

 

የቅንጅት አመራሮች በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ብቅ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ በተገኙት መድረኮችና አጋጣሚዎች ሁሉ ሳይታክቱ አገራችን ከጦርነትና እርስ በእርስ ከመጠፋፋት አዙሪት መውጣት እንዳለባት ሲሰብኩና ሲያስተምሩ ኖረዋል። በአገራችን፣ ሥልጣን በኃይል መነጣጠቅ ምን ያህል እንደጎዳ እና በልማት ወደኋላ ለመቅረታችን ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ መሆኑ በሕዝብና በመሪዎቹ አእምሮ እንዲቀረጽ ቅንጅት ብዙ ጥሮአል።

 

በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት አንድ ኢትዮጵያዊ ሌላውን፣ ወንድሙን፣ እህቱን የሚገድልበት ምክንያት የለም። ሁለት ኢትዮጵያውያን በግልም ይሁን በቡድን በመግባባት በውይይት ሊፈቱት የማይችሉት ምንም የፖለቲካ ልዩነት ሊኖር አይችልም ወይንም ሊኖር አይገባም። ጠመንጃና ጥይት አገርን ለሚወር ብቻ መዋል አለበት። የትጥቅ ትግል መንግሥትን ለመለወጥ ቢያስችል ወይንም የትጥቅ ትግል ቢሳካ እንኳን ብዙ ጊዜ ፈጅቶ፣ ብዙ ንብረት ወድሞእና ብዙ ሰው በተለይ ወጣቱ አልቆ በተፋላሚ ወገኖች ላይ ዘላለማዊ ጠላትነት ተክሎ ነው የሚሆነው ከዚህ ቀደም እንደታየው በትጥቅ ትግል የተገኘ ድል አንድን መንግሥት ከመገልበጥ ውጭ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የወለደበት ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም። ሆ ቺ ሚንና ማኦ ዜ ዱንግ አገራቸውን ከኢምፔሪያሊስቶች ክራንቻ ሊያላቅቁ ቢችሉም ዘላቂና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመሠርቱ ግን አልቻሉም። የሙሴቬኒ፣ የካጋሜ፣ የመለስ፣ የኢሣያስ የትጥቅ ትግል ድሎችም ከዚህ የተለዩ ውጤት አላሳዩም። ደቡብ አፍሪቃውያን ነፃ ወጥተው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመሠረቱት ትግላቸው በመሳሪያ ኃይል ቢታገዝም ዋነኛው የትግል ስልታቸው ግን ሰላማዊ ነበር። ስለዚህ የትጥቅ ትግል ለዘለቄታዊ ዴሞክራሲ ሊያበቃ የሚችለውን ሰላማዊውን ትግል ስለሚያዘናጋ እና ስለሚያቀጭጭ በአገራችን የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱ ሁሉ ወደ ሰላማዊው ትግል ቢገቡ ይበጃል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

 

ከኢሕአዴግና ከደጋፊዎቹ ጋር አንዳንድ የፖለቲካ ልዩነት ያለውን ሰው ወይንም ድርጅቶች በጠላትነት ፈርጀ ማስፈራራት ሲያልፍም ማጥፋት ጊዜያዊ እፎይታ ይሸምት እንደሆነ እንጂ ዘላቂነት የለውም። ከመጠፋፋት፣ ከመጠላላት፣ ከመናቆር የተሻሉ መነጋገር፣ መግባባት፣ ሰጥቶ መቀበል የመሳሰሉ ጥሩ አማራጮች አሉ። ጋዜጦችም ቢሆኑ የአንዳንዶችን ቀልብ ለመሳብና የግል ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሞያዊ ግዴታቸውን ወደ ጎን ትተው በግለሰቦች ላይ የሃሰት ውንጀላ ከማናፈስ ይልቅ ለህብረተሰቡ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊያስገኙ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ትኩረት ሊሰጡ ይበጃል እላለሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!