አለቃ ተክሌ-ከካናዳ (ክፍል አንድ)

ትንሽ ወደኋላ፡ ሌላ ዙር ቅስቀሳ

ቅስቀሳ እወዳለሁ። “ይሄ ቅስቀሳ አይደለም ቁስቆሳ ነው። ለነገሩ አብላጫው ዝምተኛ፡ ያንተን ቅስቀሳ የሚያነብ አይደለም፡ ዝም ብለህ ነው የምትደክመው” የሚል ቀስቃሽና ቀዥቃዥ አስተያየት ደርሶኝ ነበር፡ ሰሞኑን። ስለዚህ በግንቦት ሰባት የዳላስ ስብሰባ ላይ ያቀረብኩትን አንድ የቁስቆሳ ጽሁፍ እንደምለጥፍላችሁ የገባሁትን ቃል አጥፌ፡ ትንሽ ቆየሁ። ግን ሰው መቀስቀስ ባልችል ለምን ራሴን አልቀሰቅስም የሚል ቅስቀሳ ቀሰቀሰኝና፡ ይኸው ጽሁፌን፡ እናንተን ለመቀስቀስ ሳይሆን ራሴን ለመቀስቀስ ሰድጄዋለሁ።

 

ስለዚህ ይሄ ቅስቀሳ ለራሴ ነው። ለኔና ለመሰሎቼ። ንግግሬን የጀመርኩት በተስፋዬና በታዬ ነው። በመስከረም መጀመሪያ ገደማ፡ 2009 ዓ.ም.፡ በአቶ ኦባንግና ወዳጆቹ ፊታውራሪነት በዋሽንግተን ዲሲ የሚደረገው ሰልፍ ለምን የሁላችንም ሰልፍ መሆን እንዳለበት ለማሳየት፡ የዛሬ አራት ዓመት ከሶስት ወር ግድም፡ በ2005 ምርጫ ማግስት የተከሰተን ክስተት አትቼ ነበር። የዛሬ አራት ዓመት ከአራት ወር አካባቢ፡ ተስፋዬ አዳነ የሚታየው ከምኔው ፓርላማ ገብቶ፡ ከምኔው ተመርቆና ድግሪውን ተቀብሎ አገሩን እንደሚያገለግል፡ ከምኔው ለአገሩም ለሱም ቀን ወጥቶላቸው ከድህነትና ከአምባገነናት እንደሚገላገሉ ነበር። የኢትዮጵያ ህልም ባፍጢሙ በተደፋበት በምርጫ 97 ማግስት ግን፡ የተስፋዬም ህልም መከነ።


ባንድ እሁድ ከሰዓት፡ ሁለት የጠገቡ የትልልቆቹ አምባገነናት ተላላኪዎች፡ የታጠቁ ትንንሾቹ የኦህዴድ አምባገነናት “ህግ ይፈልግሃል” ብለው ተስፋዬን ከመንገድ ወሰዱት። “ሕግ ለምንድነው የሚፈልገኝ? ምን ወንጀል ሰራሁ?” ብሎ ብቻ ነው የጠየቃቸው። ተስፋዬን በመሳሪያ ነደሉት። ሰው የሚታደንበት፡ ሰው ግዳይ የሚጣልበት አገር። ለአርሲ ነጌሌ ኦብኮን ወክሎ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመርጦ የነበረው ተስፋዬ አዳነ፡ ጓደኞቼ ከተማሩበት እሱም ካደገበት ት/ቤት በታች ተገደለ። አስከሬኑም ተጣለ። ገዳዮቹ ለጊዜው ለማስመሰል ያህል ታሰሩ፤ በታሰሩበት ግን የአበባ ምንጣፍና ጫት ክትፎና ሴትም ጭምር ገባላቸው፤ እነሆ እነዚህ ተስፋዬን የገደሉ ፖሊሶች፡ ወደሌላ ከተማ በሹመት ተሻግረው ህይወታቸውን ይገፋሉ፤ የተስፋዬ ደም ደመ ከልብ ሆኖ ይቀራልን ብዬ ጠይቄም አትቼም ነበር። “ለጊዜው ሰይፍና ሰደፍ ያለው ከጠላታችን እጅ ነው፤ እኛ ግን ቢያንስ ሰልፍ አለን እንሰልፍ አለኩ፡ ያንግዜ።”
ደግሞ ቀጠልኩ።

መቼም ብዙዎቻችን፡ ይሄንን ኬዝ ሰርተንበት ነው እዚህ የምንኖረው። አሁን ያለም ዙሪያ ተሾመን እናት፡ “ተዉ ባሌን አትውሰዱ” ብለው በጮሁ በጥይት በጠራራ ጸሀይ በጥይት የተገደሉትን፡ ወ/ሮ እቴነሽን እንዘነጋለን? ከዚህ በላይ ምን ይምጣ? እነሆ እዳን የመክፈል ቀን ዛሬ ነው። አሁን። እንሰለፋ ብዬ ቀሰቀስኩ። ያው ግልጽ እንነጋገር፡ የትሁት ተቺዬ ትንቢት እውነት ሆኖ “አብላጫው ዝምተኛ” ሰልፍ አልወጣም። “ጽንፈኛው ጥቂት” እንጂ። ግን፡ “ታሪክ ሰሪወ ሰፊው ህዝብ ነው” መፈክር ብቻ ነው። ስለዘሂ ይሄም ሌላ ለኔና መሰሎቼ የተዘጋጀ የዚያ ቀጣይ ቅስቀሳ አካል ነው።


የኔ መድረክ ላይ መሰቀልና ስለናንተ የወሰድኳቸው ግምቶቼም እዚህ መድረክ ላይ ልናገር ስሰቀል፡ (በአይነ ሕሊናችሁ ሳሉ፡ እዚያ ዳላስ መሆኑ ነው፡ አንድ ጸጉሩ አለቅጥ ያደገ፡ እሱ አጭር፡ ያደረገው የተውሶ ሱፍ ኮት ግን የሰፋው ሰው፡ እኔን ማለቴ ነው)፡ ስለናንት ስለአድማጮቼና ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ግምቶችን ገምቼ፡ ባንዳንድ ጉዳዮች ላይ ቅድመ ድምዳሜ አድርጌ ነው። ለምሳሌ፡ ሁላችሁም ወይም አብላጫዎቻችሁ፡ የሕወሀት/ኢህአዴግ አስተዳደር በማናቸውም መንገድ ወመገድ ያለበት መጥፎ ስርአት ነው ብላችሁ አምናችኋል የሚለው ግምቴ ማለቂያ ከሌላቸው ግምቶቼ አንደኛው ነው። በሌላ አነጋገር፡ ስለሕወሀት መወገድ አስፈላጊነትና ምክንያት፡ ከኔ ማብራሪያ ያስፈልጋችኋል ብዬ አልገምትም። እንደዚያ አይነት ሰዎች ካለን፡ ምንም አይደል፤ ግን በዚህ ርእስ ላይ ሌላ “የልጆች ክፍለጊዜ” አይነት ነገር ያስፈልገናል ማለት ነው።

ስለዚህ እዚህ የተሰበሰባችሁ በሙሉ ወይንም ባብዛኞቻችሁ ያንን “ኮርስ” ኖራችሁታል ወይም ወስዳችሁታል፡ ብየ ገምቼ፡ ከዚያ መለስ ባሉ ነገሮች ላይ ነው የምንነጋገረው።


እንጂ፡ ሕወሀት ይሄንን አደረገ፡ ይሄንንም ሰራ ብዬ የግፍና አረመኔነት ብዛት ስደረድር አልከርምም። አንዳንዱ ልጻፍህም ቢሉት ይሰቀጥጣል። ባለፈው ዲ.ቪ. ደርሶት ከኢትዮጵያ የመጣ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ሲያጫውተኝ፡ አንዱ በቅርቡ በኤድስ በሽታ የሞተ ያደግንባት ከተማ የኦህዴድ ባለስልጣን፡ ከጥጋቡ መብዛት የተነሳ፡ ይህቺን ሴት አወጣለሁ፡ ይህቺንም እደግማለሁ እያለ በውስኪና በምናምን ይወራረድና ይፎክር ያደርገውም ነበር። መቼም መርሳት ቀላል ነው፡ በተለይ በራስ ላይ ካልደረሰ እንጂ፡ ባንድ ምላጭ እየላጩ፡ ባንድ በርሜል ያሳጥቧቸው የነበሩትን በዘዋይና በሸዋ ሮቢት የታሰሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች አንረሳም። አንድ ልመርቅላችሁ። የታዬ ነገር መጣብኝ። (ይሄ አንድ በቅርቡ በትህትና ብዙ ባልደክም መልካም እንደሆነ አስተያየት የሰጠኝን ሰው ሀሳብም ለመዳሰስ ያግዘናልና ዳላስ ላይ ካልኩት በተጨማሪ ማብራሪያም አክልበታለሁ)።


ታዬ ደንደኣ አረዶ፡ ምስኪን ኦሮሞ፡ ምስኪን ኢትዮጵያዊ


ታዬ ደንዳአ አረዶ። ታዬ ግለሰብ ነው። ግን የብሄርተኝነት አደጋ ላይ፡ በተለይም በኦሮሞ ብሄርተኝነት ጉዳይና አደጋው እኛም እንዴት ብናስተናግደው መልካም እንደሆነ ትንሽ ወረድ ብዬ ስለምሄድበት ታዬን ባነሳው ፍኖተ-ውይይታችንን ያቀልንላል። ደግሞም ታዬ ደንደአ አረዳ ከኛ እንዳንዱ ነው። ታዬ ተክሌ ነው። ታዬ ብርሀኑ ነጋ በልጅነቱ ነው። ታዬ ብርቱካንንም ነው። ታዬ የአ.አ.ዩ. ተማሪ እያለ ከ2003 እስከ 2006 ታሰረ። ከዚያ ተፈታ። አ.አ.ዩ. የሕግ ትምህርቱን ቀጠለና ሊመረቅ ሶስት ቀን ሲቀረው ባለፈው ሀምሌ ወር፡ 2009/2001 ዓ.ም. እንደገና ታሰረ። ታዬ ኦሮሞ ነው። ስለዚህ ታዬ ኢትዮጵያዊ ነው።


ታዬ ባንድ በኩል እድለኛ ነው። በ2003 ከሱ ጋር ከታሰሩት አንዱ አለማየሁ ገርባ በጥይት ተመቶ በሳምንቱ ሞቷል። ኦክቶበር 2006/1998። ሌላኛው ጓደኛው ጋዲሳ ሂርጳሳ በድብደባና ስቃይ ብዛት እስር ቤት ሞቷዋል። ምናልባት ያኔ ታዬ እድለኛ ነበር። አሁን ካልሞተ። ታዬ የምስኪን ልጅ ነው። ልክ እንደኔ። እኔ ሳልሻል አልቀርም። ገብረ ጉራቻን ታውቋታላችሁ? እዚያ ነው የተወለደው። ጠላ ለሚሸጡ ሰዎች ውሀ እየቀዳ እየሸጠ፡ በመልሱም እነሱ እያጎረሱት ነው ትምህርቱን የጨረሰው። በጣም ብሩህ አእምሮ ስላለው፡ በሰቃይነት ትምህርቱን ጨረሰ። አ.አ.ዩ. በመምህርነት ቀጥሮ አስቀረው። የመመረቂያ ጽሁፉ ኤ ፕላስ አስገኝቶለታል። “ፎልስ ኮንቪክሽን በኢትዮጵያ” ይላል ጽሁፉ። ታዬ ራሱ የሀሰት ፍርድ ሰለባ ስለሆነ ይሄንን ርእስ አሳምሮ ያውቀዋል። አሳምሮ ጻፈው። ግን ታሰረበት።


ታዬ ላሳደገው ህ/ሰብ ተቆርቋሪ ነው። ወዳደገበተ ገብረ ጉራቻ እየተመላለሰ ሴቶችን እየሰበሰበ ያስተምራል። ሴቶች ለምንድነው በትምህርት ቤት ከወንዶች ደረጃ እኩል ነጥብ የማያመጡት? ይሄ ችግር የህብለ በራሂ ነው ወይንስ ሰው ሰራሽ? ብሎ በእልህ ሴቶችን ያስጠናል። ከሀምሳ በላይ ቀድሞ በእረኝነት ሙያ የተሰማሩ ታዳጊዎች፡ ዛሬ በታዬ ገፋፊነት ከእረኝነት ወጥተው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ታየን ያመሰግናሉ። እነሆ ታዬ ታሰረ። ለምን? በመመረቂያ ጽሁፉ ሽብር ፈጠረ። ሰው ቀሰቀሰ። ማእከላዊ ታሰረ። እስካሁን ይኑር ይሙት የሚያውቅ የለም። ቤተሰብ ከታሰረ ጀምሮ አላየውም። አሳሪዎቹ ዝም ብለው፡ ስንቅ ብቻ አንጡ እያሉ ይቀበላሉ። ይድረሰው አይድረሰው አይታወቅም። ከዚህ ቀደም ከሱ ጋር የታሰሩ ሰዎች እንደገለጹት፡ በቃ ይደበድቡትና ፊቱም ምኑም ሲያብጥ እስኪያገግም ድረስ፡ ሰው አንዳያው ወደ ውጭ አያወጡትም አሉ፡ በሕወሀት የእስር ባህል። ታዬ ሊታሰር ትንሽ ቀን ሲቀረው አባቱ ሞተዋል። እናቱና ወንድሞቹ ግን አሉ።


በባዶ እግሩ ተምሮ እዚህ የደረሰው ታዬ እሱንና ወገኖቹን ከአማሮች አገዛዝ ነጻ ሊያወጣ በመጣ ነጻ ያልወጣ ነጻ አውጪ ታስሯል። ዶ/ር ቡልቻ ደመቅሳ፡ ስለታዬ መታሰር ሲጠይቋቸው፡ “የሱን ነገር አታንሱብኝ ብለው ያለቅስሉ” ብሎኛል አንድ ጓደኛዬ። ዶ/ር መረራም እንደዚያው። እንባቸው ይመጣል። ስለዚህ ስለሰዎች መታሰር ስለሰዎች መገደል ስለሰዎች መሰደድ ስለሰዎች መታፈን ለመናገር አልተዘጋጀሁም። ምክንያቱም እሱን እኩል እናውቀዋለንና። ይህቺን ያህል መጥቀሴም አንድም ወረድ ብዬ ለማብራራው ነገር ያግዘን ዘንድ በተጨማሪም ሕወሀት/ኢህአዴግ የትዮጵአን ህዝብ አብዛኛውን ጥያቄ የመለሰ ጥሩ መንግስት ነው ብለው በቅንም በጠማማም ለሚከራከሩ ተከራካሪዎች ምስል ለመፍጠር ነው። ስለዚህ፡ ስለ ሕወሀት/ኢህአዴግ መጥፎነት ትተን ወደሚያከራክሩንና ወደሚያወያዩን ነገሮች እንዝለቅ።
  
እድለኞች ናቸው፡ እኛም እድለ ቢሶች

እኔ፡ “እነዚህ ሰዎች እኮ አልቆላቸዋል፡ ትንሽ ቢገፏቸው ይወድቃሉ፡ ውስጣቸው ባዶ ነው” የሚለውን ጠላትን ዝቅ አድርጎ የመገመት ባህል አቀንቃኝ አይደለሁም። እነዚህ ሰዎች የማይበገሩ፡ የማይሸነፉ ናቸው አልልም። በይቻላል አምናለሁ። ግን እነዚህ ሰዎች፡ አደገኞች፡ ብልጦች፡ የሚሰሩትን ጠንቅቀው የሚያውቁ፡ ስልጣናቸውን ለመጠበቅ ጥፋት ቢኖረውም ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ፡ ኑክሌር ቦምብ ቢኖራቸው አገዛዛቸውን ለመቀጠልም ባይሆን፡ ጠፍቶ ለመጥፋት፡ በመጨረሻው ቀን ያንን ከመጠቀም ወደኋላ የማይሉ ሰዎች ናቸው። የብሄሮችን ጉዳይ ማራገብና አንዱን ብሄር በሌላው ላይ ማነሳሳትን እንደ ትንሽ ቦምብ ልንወሰደው እንችላለን። የሀይማኖትን ጉዳይ እንደ ሌላ አቶም ብምብ እያበለጸጉት ነው። እንደ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ ሀይ ባይ አጥተው እንጂ፡ እነዚህ ሰዎች ቦምበኞች ናቸው። የብሄርን ቅራኔ ማጋጋል ወይንም የሀይማኖትን ልዩነት ለጥፋት መጠቀም ኑክሌር ቦምብ ያለው አላባውያን ሁሉ አሉት ማለት ባይቻልም፡ እነዚህ ሁለቱንም ፈንጂዎች፡ እነዚህ ሰዎች እነዚህን ልዩነቶች እንደ አጥፊ የፖለቲካ ደማሚት ሊጠቀሙባቸው ወደኋላ አይሉም።

እነዚህ ሰዎች ጊዜና እድል ከነሱ ጋር ነች። ልብ በሉ ደርግም አጼ ሀይለስላሴም አድርጎት በማያውቀው ልክ ሰማኒያ ሚሊዮን ህዝብ ይቀርጣሉ። በየዓመቱ አንዳንዴም በየመንፈቁ የውጭ ምኒዛሪያቸው ተንጠፍጥፎ አለቀ ሲባል የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ምንዛሬ ይዘረግፍላቸዋል። ይጎመዝዛል፡ ግን እውነት ነው። ሰውዬው ጭራሽ አፍሪካን ወክሎ በተለያዩ መድረኮች ይላካል። ዓለም ሁልግዜም አሸናፊዎችን ትቀበላለች። ምሳሌ፡ መጥፎ ናቸው ብዬ ባልሟገትም፤ ያ የአገራቸው ህዝብ ጉዳይ ነውና፤ እነ ሙጋቤን ተመልከቱ፡ ጋዳፊን ተመልከቱ፡ አህመዲናጃድን ተመልከቱ፡ እንደ አምባገነን ወይም አላግባባ ስልጣን የያዙ አድርገን የተመለከትናቸውን ሁሉ የሚቀበልና የሚያስተናግድ አለምአቀፍ ስብስብ ነው ያለው። አሸናፊ እስከሆኑ ድረስ ዓለም እነሱን ይሰማል።

ይሄንን ማንሳቴ እነዚህን ሰዎች ለማግነን ሳይሆን፡ ይህንን ሁኔታ አውቀን እንድንገባበት ለማለት ነው።  ትግላችንን በዚህ ልክ እንድንሰፋ ነው። ትግላችንን በዚህ ልክ እንድንቀድ ነው። ጠላትን አግዝፎ ማየት “አይቻልም” እንድንል ያደርገን ይሆናል። ጠላትን አግዝፎ ማየት ደግሞ እንደዚሁ በዚያ ልክ እንድንዘጋጅ ወይንም አውቀነው እንድንጓዝ ያደርጋል ለማለት ነው። አድበስብሰንና አቅለን አሳንሰንን አኩስሰን መቅረቡ ትግሉ ሁሉ ቶሎ ቅልጥፍ ብሎ የሚያልቅ እንዲመስለንና፡ አልሳካ ሲለን ደግሞ ቶሎ ተስፋ ቆርጠን እንድሄድ ያደርጋል። ስለዚህ በዚያ ልክ እንዘጋጅበት እነዚህ ሰዎች በትንሹ መገፋት የማይወድቁ አደገኞች ናቸው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተገፍተው ቢወድቁም እንኩዋን፡ እነሱ ያበላሹት ቀሪ የቤት ስራ እንዲህ የዋዛ አይደለም። ሕወሀት ከወጣበት ብሄር አንስቶ በተቀሩት ብሄሮች መካከል የፈጠረውናና እየፈጠረ ያለው ጥርጣሬና ጥላቻ ዘወተር ያሳስበኛል። (የሚቀጥለውን ንኡስ ርእስ ዳላስ ላይ ይዤው ሄዤ፡ ግን አላነሳሁትም። ቀነስኩት።)

ስለብሄርና ስለትግሬነት፡ ሌሎችስ ምን ይልላሉ?

የብሄር ብሄረሰብ ጉዳይ፡ የብሄር ብሄረሰቦች መብትና ማንነት ታሪክና ቋንቋ ቢከበር ሆዴን የሚቆርጠኝ ሰው አይደለሁም። የብሄሮች መብትና ፍላጎት እንዲከበር አጥብቄ የምደግፍ ከመሆኔ የተነሳ፡ እንዲያውም ሕወሀትን ብንጥለው እንኳን፡ አንዳንድ ሕሀወት ለክፋትም ይሁን ለብልሀት ያመጣቸውን ነገሮች መንካት የለብንም እላለሁ። እንደውም ሌሎች በዚህ ስርአት ተጠቀምን የሚሉ ብሄሮች ካሉ፡ የኛ ስልጣን መያዝ እነሱ ያገኙትን ጥቅም የሚነጥቅ እንደማይሆን ማሳየትና ዋስትና መስጠት አለብን ብዬ አምናለሁ። ያ ብቻ አይደለም። ምናልባት እነዚህ ሰዎች ይሄ ብሄርን መሰረት ያደረገ አካሄድ ኢትዮጵያን ይጠቅማል ብለው ይሆን እንዴ በቅን ልቡና እየተገበሩት ያሉት፤ ብዬ አስባለሁ አንዳንድ ግዜ። ግን የህወሀት ትልቁ ችግር፡ ሰው የምር ትግሬ እንዲሆን ብቻ ነው የተፈቀደለት። ሕወሀት ከመጠነው ውጪ፡ የምር አማራና፡ የምር ኦሮሞ መሆን ጠባብ ትምክህተኛ ነውጠኛና ጸረ ሰላም ያሰኛል።

ትግራይና ሕወሀትን አንድም ቀን ደባልቄ አላውቅም። ልንደባልቅም አንችልም። ያንን የማላደርገው ሁለቱ አንድ ስላልሆኑ ብቻ አይደለም። ያ አይነቱ አካሄድ ራስ ላይ መልሶ እንደመተኮስ ስለሆነ ነው። “ባክፋየር” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል መተርጎሜ ነው። ትግራይና ሕወሀትን ወይንም የትግራይ ህዝብንና ሕወሀትን አንድ አካል አንድ አምሳል አድርጎ ማየት፡ እነ አጼ ሀይለስላሴንና እነ አጼ ምኒሊክን አማራና ስርአታቸውም የአማራን የበላይነት ያመጣ ነው ብሎ ለሚነሳው ክርክር ጉልበት የመስጠት ያህል ነው። ካንድ ብሄር የወጡ ገዢዎች አንድን ብሄር በሙሉ ተጠያቂና ተሳታፊ አያደርጉትም። ባጠቃላይ የትግራይን ህዝብ በሁለት እንክፈለው። አንደኛ፡ ማንም ሰው ሊያደርግ በሚችለው መልኩ ሕወሀትን የሚደግፍና፡ ሁለተኛ ሆን ብሎ የህወሀትን አጥፊ ተልእኮ እያወቀ በጥቅማ ጥቅም ተደልሎ ሕወሀትን የሚደግፍ እንዲያውም የህወሀትን አጥፊ ተልእኮ የሚያሳካ ትግሬ ብለን። እነዚህኛዎቹን ነው እንግዲህ የምንዋጋው። ይሄ አከፋፈል በኛ ላያምር ይችላል። አቶ ገብረመድህ አርአያም ግን ያለውም ይሄንኑ ነው። ከባለቤቱ ያወቀ ባዳ ወይም ቡዳ ነውና። በኔ አስተያየት ከዚህ ከትግራይ ጋር በተያያዘ በብዙዎቹ ወገን ያለው አመለካከት የተሳሳተ ነው እላለሁ። የተሻለና እኔ የምጋራው አመለካከት በከፊል በአቶ ገብረመድህን አርአያ የጠጠቀሰው ነው። ችግሩ ግን ፖለቲካ ዛሬ ትክክል ነው ብለን ያመንበት፡ ነገ ስህተት ይሆናል። ስለዚህ የኔንም እንደተለዋጭና አማራጭ አስተያየት እዩት። እንጂ ቋሚ አይደለም። እኔም ትናንት ያመንኩበትና የሰበኩበት ጉዳይ ሀሰት ሆኖ ሲገለጥ አይቻለሁና። 
  
ስለትግራይ ሲነሳ፡ ስለትግራይ ሲወሳ

ወያኔ/ሕወሀት የትግራይን ብሄርተኝነት አሰፈነ፡ በኢትዮጵያም ላይ የትግራይ ብሄረሰብ ብቻ እንዲበለጽግ አደረገ ማለት የትግራይ ህዝብ በዚህ በሚሆነው ነገር ሁሉ ተጠያቂ ነው ማለት አይደለም። ወይንም የትግራይ ህዝብ የወያኔ አገዛዝ ደጋፊ ሆነ ማለት፡ የትግራይ ህዝብ ሁሉ በትብብሩ ወይንም በድጋፉ በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ወንጀል ፈጽሟል አያሰኘውም። የትግራይ ህዝብ ሕወሀትን ቢደግፍ ምክንያታዊ ነው። ያስኬዳል። የትግራይ ህዝብ በደርግና ከዚያ በቀደሙት መንግስታት ተበድሎ ከነበረ፡ የህወሀት ያንን በደል እንዲቆም ማድረግ፡ እንዲያውም ያ የጦርነት አውድማ የነበረና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብዙም ይሄ ነው የሚባል የጎላ አስተዋጽኦ ያልነበረው ክልል፡ የልማትና የእድገት ክልል እንዲሆን ማድረጉ ማንም የዚያን ክልል ተወላጅ ወያኔ/ህወሀትን እንዲደግፍ ሊያደርግ ይችላል። ያ ሎጂካል ነው። ተጠቀሙ፤ ደገፉ። በንጽጽር ነው ጥቅሙ። የስራ እድል ተፈጠረ። ግንባታዎች ተካሄዱ። የትምህርት ቤቶችና ክሊኒኮች ተገነቡ።
 
ከተሞችና ተቋማት ታነጹ። ከዚህ ቀደም ባልተደረገ መልኩ የትግራይ ተወላጆች በመንግስት መስሪያ ቤቶች በንግድ ድርጅቶችና በውጭ አገራት በከፍተኛ እድል የሰራ እድል ተፈጠረላቸው። ማንም ህሊና ያለው ህዝብ ያንን ይደግፋል። ጎንደርም ቢደረግ ወለጋ፡ አርሲም ይደረግ ወሎ፡ የዚያ አካባቢ ህዝብ ያንን መሰረት አድርጎ ያንን ስርአት መደገፉ ያስኬዳል። ያ ህዝብ ይሄንን ትርፍ ተከለትሎ ያንን ድጋፍ መስጠቱ ሎጂካልና ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለው ከሆነ ያንን ህዝብ በምንም ሕወሀትን በመደገፉ ልንከሰው አንችልም። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ሌላ ነው። ምንድር ነው?

የትግራይ ህዝብ የተጠቀመው ወይንም ከላይ የጠቀስኳቸውን ብልጫዎች እየተደረገለት ያለው በተቀረው ህዝብ ኪሳራ መሆኑን ያውቃል ወይ ነው ጥያቄው? ሕወሀት ማነው? ሕወሀትና የትግራይ ህዝብስ አንድነታቸውና ልዩነታቸው የት ላይ ነው? እዚህ ጋር ነው አቶ ገብረመድህን ጥሩ መልስ የሚሰጠን። አቶ ገብረመድህን ከኔም ከብዙዎችም በተሻለ መልኩ ይሄንን ጥያቄ በደንብ አድርጎ የዳሰሰና የመለሰ ሰው ነው። ገብረመድህን አርአያ “ያለው ህወሀት ብቻ ነው። ኢህአዴግ የሚባል ነገር የለም።” ይለናል ሲጀምር ገና። የአግአዚ አባላት፡ የወያኔ ደጋፊዎችና አባላት፡ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ከማንም በላይ የዚህ ስርአት ደጋፊዎችና ጋሻ ጃግሬዎች ናቸው ይለናል። ገብረመድህን፡ በደርግም ይሁን በሀይለስላሴ መንግስት፡ ከፍተኛ የአማካሪነት ስልጣን የያዙና በብሄራቸው ያልተበደሉ ሰዎች የትግራይ ሰዎች ናቸው። እንዲህ አሁን በተለይ ከትግራይ የወጣው አክራሪ ብሄርተኛ አገዛዝ ያሰፈነው አይነት ዘረኝነትና ጭቆና አልነበረም ይለናል። ወያኔ ጸረ ሕዝብ ነው፤ በትግራይ ውስጥ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የታጠቁ ሰራዊት አሉት። የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ አልተሳካለትም እንጂ ጸረ-ወያኔ ነው፤ ይሁን እንጂ፡ ወያኔን ያቆመና ሀይል የሰጠውም ትግሪኛ ተናጋሪውና ከትግራይ የወጣው ሰው ነው ይለናል። ገብረመድህን ሲናገር ምንም ጥርጣሬ አያሳይም። ስለዚህ የተቀረው የትግራይ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆም ጥሪውን አቀረበ፡ ያንን ተከትሎ። ገብሬ። ያለበለዚያ በገብሬ አማርኛ፡ “ትነጠላለህ፡ ይነጥሉሀል” ብሏል።

መቼም መሬት ወረድ ብለን ናሙና የምንወስድበት መንገድ የለም። ከምንሰማውና ከምናነበው ነው ድምዳሜ የምንወሰደው። ያ የምንሰማውና የምናየው የሚጠቁመው ከሞላ ጎደል ሁሉም ወይንም ፍጹም አብላጫው የትግራይ ህዝብ ሕወሀትን እንደሚደግፍ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት ያ መሆኑ ሎጂካል ነው ባይ ነኝ። ለትግራይ ህዝብ ከዚህ የተሻለ ጠቃሚ ስርአት ነበር ወደፊትም ይኖራል ብሎ ማለት ይከብዳል። ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ሕወሀትን የሚቃወምበት መሰረታዊ ነገር አይታየኝም። የትግራይ ህዝብ የሚያሰራውንና የስራ እድል የፈጠረለትን መንግስት ሊቃወም የሚነሳበት ምክንያት አይታየኝም። አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያዊነቱና የሕወሀት ጸረ ኢትዮጵያዊነት የትግራይ ህዝብ ሕወሀትን እንዲቃወም ሊያደርገው ይችላል ብለው ሊከራከሩ ይችላሉ። ግን ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ እየተሸረሸረ እተለወጠ መጥቶ በትግሬነት በኦሮሞነት በሶማሊነት ወይንም በብሄርተኝነት እየተተካ መጥቷል። በዚህ አስራ ስምንት ዓመት ሕወሀት እየተከለ ያለው ኢትዮጵያዊነት የትግራይ ህዝብ ሊቃወመው የሚችለው ኢትዮጵያዊነት ነው ብለን እንዳንከራከር የትግራይ ህዝብ ያንን ያሳየበት አጋጣሚና ወቅት አይታየኝም። የትግራይ ሕዝብ ምንም አልተጠቀመም፡ እንዲያውም በዚህ ስርአት ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ርእዮት ደስተኛ አይደለም፡ ስለዚህም ይሄንን ስርአት አይደግፍም የምንል ከሆነ ግን ያንን በምን ማወቅ እንችላለን ነው ሌላው ጥያቄ። ያ ማለት ግን፡ የትግራይ ህዝብ ተቃውሞውን አልገለጸምና የትግራይ ህዝብ በተዘዋዋሪ ነው ደጋፊነቱን ያሳየው ለማለት አይደለም።

ስለትግራይ ከተነሳ፡ እነሱ፡ አንድ ብሄር መሆናቸው አንድ ቋንቋ መናገራቸው፡ አንድ ባህልና አንድ ክልል ማደጋቸው ረድቷቸዋል። አሁን ያንን በማንሳቴ እንደክፋት እንዳታዩብኝ። ግን ያኔ እናዳሁኑ ክፋትን በማላውቅበት የልጅነት ዘመኔም እነዚህ ሰዎች ሲጋቡ ርስ በርሳቸው ነው፤ ከብሄራቸው ወጥተው የመጋባት ባህላቸው ልል የሆነው ለምንድር ነው ብዬ እጠይቅ ነበር። ያ መጥፎ ነው ለማለት አይደለም። ያንን መረዳት ለአሰላለፍ ስለሚረዳን ነው። የሌሎችን አሰላለፍ ማወቅ የራሳችንን አሰላለፍ ለማሳመር ወይንም ለማስተካከል ይረዳናል። እኛ አስር አማራ፡ አስራአምስት ኦሮሞ፡ ሰባት ጉራጌ፡ ስድስት ከምባታ፡ ሶስት ጋሞ፡ አምስት ሸዋ፡ ሁለት ወሎ፡ ዘጠኝ እስላም፡ አስራ አንድ ክርስቲያሰኖች ነን። የሰጠሁት ቁጥር የታሰበበት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የብሄርን ወይንም የሀይማኖትን ያህል ሊያስተሳስረን አልቻለም። በድርጅቶች መካከል የምናየው ርስ በርስ መባላት በተወሰነ መልኩ ከዚያ የመነጨ ነው ባይ ነኝ። ወይ ከላላ ኢትዮጵያዊነት፡ ወይ ከግለኝነት ወይ ከግዴለሽነት። እነሱ ስዬንም ይብሉት ገብሩን፡ ከዚያ በኋላ ግን አንድ ላይ ይቀጥላሉ። (አንድ በቅርቡ በሌላ አገባብ አስተያየት የላከልኝ ሰው የኛ ተቃዋሚዎች ርስ በርስ ይባላሉ፡ እነሱ ግን፡ እነ ሕወሀትን ማለቱ ነው፡ ያለአንዳች ርህራሄ ማስወገድ ያለባቸውን አስወግደው፡ በልተው ወደፊት ይጓዛሉ። ያም ነው የሚያኖራቸው። የራሳቸውንም ሰው በልተው ቢሆን ወደፊት መጓዛቸው። አስፈላጊ የሆነ ቀን፡ እሱም ሌሎችን በልቶ እዚህ እንደደረሰው፡ መለስንም ሊበሉት ይችላሉ እንደማለት ነው።)

እነሱ ሰማኒያ ስምንት ክርስቲያን፡ አስራ ሁለት ሙስሊም ናቸው። ይሄንን እኔ አላልኩም፡ የራሳቸው ሰው አቶ ገብረ መድህን አርአያ ነው ያለው። ኢህአዴግ ምናምን ብሎ ነገር የለም። ያለው ከትግራይ በሚወለዱ በትግርኛ ተናጋሪዎች የተሞላ ሕወሀት የሚባል ድርጅት ብቻ ነው። የተቀረው አጃቢ ነው። ይሄንን እንደ እውነት እንወቀው ለማለት ነው እንጂ ይሄ ትግሬ ወይንም ትግሪኛ ተናጋሪ በሙሉ ጠላት ነው ወይንም ወያኔ ነው ወደሚል መደምደሚያ አያደርሰንም።  ይሄ የትግራይና ትግሪኛ ተናጋሪዎች ጉዳይ በግልጽና ሳናድበሰብስ ካልተወያየንበት ውስጥ ውስጡን እየበላን ይጨርሰናል። እንደውም ያጠፋናል። እንደውም እነሱም፡ ከላይ ያሉት፡ የሚነግዱበትና የሚያስፈራሩበት መሳሪያ ይሄው ነው። እነሱ ያንን ከማለታቸውም በፊት ግን ያ ስጋት ቀድሞውንም አለ። ግን እኛ የነሱን ስሜት እነሱም የኛን ስሜት በምን ያውቁታል? በምንስ ይደርሱታል? ከዚያ ባሻገር መገናኛ ብዙሀን የለንም። ለነገሩ፡ ... እቀጥላለሁ። (ጽሁፍህ ተንቀወለለ የሚል አስተያየትም ደርሶኛልና ነው እዚህ የቆረጥኩት። ብልጠት መሆኑ ነው። መቼም እውቀቴን አልልም፡ ጊዜየንና ጉልበቴን አንጠፍጥፌ የተየብኩትን ጽሁፍ ቆርጦ የመጣል ጭካኔ የለኝም። የተመቸው ይቀጥላል። ያልተመቸውም ይደበርበታል።) ይቀጥላል . . .

ቢትወደድ ተክሌ፡ ተጻፈ፡ መስከረም በገባ በሃያኛዎቹ ቀናት። 2002። ተሻሻለ፡ በጥቅምት። ታተመ፡ አሁን።
 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ