የ2002 ምርጫና ቻቻታው (ኩችዬ)
ኩችዬ http://www.kuchiye.blogspot.com/
ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ ጋር በተያያዘ ፊት-ለፊትና በሠያፍ የሚወረወሩት ትችቶች ብዛታቸውም ግለታቸውም እየጨመረ መሄዱ በመሃላችን የሰፈነውን የመረበሽና የጥርጣሬ ስሜት ያመለክታል። ስጋቱ ማንንም ከማን የለየ አይደለምና ትንሽ ልተችበት ፈለግሁ።
በኢህአዲግ ልጀምር ...
“ነገሮች በቁጥጥሬ ሥር ናቸው!” የሚል ገጽታ ማስተጋባት የሚፈልገው ኢህአዲግ ውስጣዊ ጭንቀት እንዳለበት የፖለቲካን አቡጊዳ ለዘለቀ ሁሉ ስውር አይደለም። በ1997 ምርጫ ያደረሰው ጥፋት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማዳከም የሚያካሂደው ቅጥ ያጣ ዘመቻ፤ ህዝብ የማስተባበር ችሎታ ያላቸውን መሪዎች ማሠሩና ማሳደዱ፤ ነጻውን ፕሬስ ማዳከሙ፤ ፍትሀዊ የምርጫ ሜዳ የለም ብለው ተቃዋሚዎች ባይካፈሉ የሚደርስበት ኪሣራ፤ ብቻውን ሮጦ አሸነፍኩ ቢል የውጭ መንግሥታት የገንዘብም የዲፕሎማሲም ድጋፍ ለመስጠት የመቆጠባቸው ጣጣ፤ የተዛባ ምርጫን ተከትሎ ሊመጣ የሚችል ቀውስ፤ … እነዚህ ሁሉ ኢህአዲግን ማስጨነቃቸው እርግጥ ነው።
የጠቀስኳቸው ዝርዝሮች በቂ አይደሉም የምትሉ ከሆነ ደግሞ ጥቂት ላክልበት እችላለሁ። በአሜሪካው ፀረ-ሽብር ዘመቻ ውስጥ ኢህአዲግ የነበረው ተፈላጊነት መመንመኑ፤ በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ “ንብረትና ዕዳ” ሚዛን መዝገብ ላይ ኢህአዲግ በዕዳው ዘርፍ መፈረጁ፤ ሀገሪቱን እያጥለቀለቀ ያለው የኢኮኖሚና የረሃብ ግሽበት፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዓለም መሪዎች መድረክ ላይ ቀዝቃዛ ትከሻ እያገኙ መሄዳቸው፤ … እነዚህ ሁሉ ኢህአዲግን እንቅልፍ መንሳታቸው ከቶውንም አያጠራጥር። ቁንጮ ላይ ያሉት ባለሥልጣኖች ደፍኖባቸው ቢሆን እንኳ አንዳንድ አስሊ ፖለቲከኞቻቸው ይህን አይስቱትም።
ወገኖቼ! ከላይ የተዘረዘሩት ጭንቀቶች ናቸው ኢህአዲግን ከተቃዋሚዎች ጋር እንዲደራደር ያስገደዱት። ተቃዋሚዎችም ወደ ድርድሩ ያመሩት የመንግሥቱን አጣብቂኞች ከግምት አስገብተው፤ የፖለቲካ ኮንሴሽኖች እንደሚኖሩ አምነው፤ አጋጣሚው የነርሱን ራዕይ ልዑዋላዊነትና የኢህአዲግን ፕሮግራም ክስረት ለማሳየት ያመቻል ብለው ነው። በየትኛውም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሚዛን ላይ ብናስቀምጠው ተቃዋሚዎቹ ማለፊያ ስሌት አድርገዋል።
ስለ ስሌት ካነሳን ዘንድ የኢህአዲግ አመራር ፍፁም ወጥ የሆነ አመለካከት አለው ብሎ መደምደም ስህተት እንደሆነ ሳላመላክት አላፍም። መንግሥት ከህዝብ ጋር እየተራራቀ መሄዱና ባጠቃላይ ሀገሪቱ ያለችበት አሳዛኝ ሁኔታ የሚያሳስባቸውና ለውጥ ማየት የሚሹ ግለሰቦች/ቡድኖች መኖራቸው ሊያከራክር አይገባም። ጥያቄው ቁጥራቸውና የኃይል ሚዛናቸው ተፈላጊውን ለውጥ ማምጣት ከሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል - አልደረሰም? ከሚለው ላይ ብቻ ነው። ኢህአዲግ በጥቅል ሲታይ ጫካውን ከዛፉ ለይቶ ማየት የተሳነው፤ የፍልስፍና ችኮነትና የ“ስኬታማነት” እብሪት ጠላቶቹ የሆኑት መንግሥት ይመስለኛል። እነዚህ ሁለቱ ደግሞ የብዙ መንግሥታት መጥፊያ (ወተርሉ) ለመሆናቸው የኛም የዓለምም ታሪክ ይመሰክራሉና፤ ኢህአዲግን ከእንቅልፉ የሚያነቃው “ደብል-ኤስፕሬሶ” ያስፈልገዋል እላለሁ።
ወደ ተቃዋሚው ልሸጋገር?
ተቃዋሚው ወገን በሁለት ጎራ ሊከፈል የሚችል ይመስለኛል። ጎራ-አንድ “ኢህአዲግ ከመሣሪያ ትግል ውጭ አይሞከርም፤ የሠላማዊ ትግሉ ምዕራፍ አክትሟል፤ ገዥው መንግሥት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሂዳል ማለት ዘበት ነው” የሚለው ነው። የሳይበር ደጋፊዎቹ ቻቻታ አስተማማኝ መለኪያ ይሆናል ብንል ይህ ጎራ “ሠላማዊ ትግል” ብሎ ሀገር ውስጥ ለሚንቀሳቀሰው ወገን ብዙም አድናቆት ያለው አይመስልም። በጎራ-አንድ ደግፊዎች ዕይታ ያገር ውስጦቹ ፓርቲዎች ወይ ባንዳዎች ናቸው፤ ወይንም ደግሞ ባንዳ ለመሆን የተሰለፉ ናቸው። እንዴ! ይሄ ፍረጃ የሚባለው ነገር ጊዜው ያለፈበት ርካሽ የግራ ፖለቲካ ቅሪት መስሎኝ? ያሁኑን ዘመን ፖለቲካ እኮ በነጭና በጥቁር ብቻ ፈርጀው የሚያዩት አይደለም። “እኔ ትክክል፤ አንተ ስህተተኛ” የሚባልበትም አይደለም። እመሃል ላይ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መስክ መፍጠር ነው አሸናፊ ፖለቲካ የሚባለው። ስለዚህ ተቃዋሚው ወገን ዓይን ላይን መተያየትን ሊለምድ ይገባል፤ ሊከባበር ያስፈልጋል፤ አንዱ የሌላውን ስብራት ለማከም በጎ ፍቃድ ማሳየት አለበት። እዚህ ላይ የመሪዎቹ ቀደምት ምሳሌ መሆን እስከታች የሚዘልቅ መልዕክት ያስተላልፋልና አንድኛቸው የመጀመሪያውን እርምጃ ሲወስዱ ማየት እንፈልጋለን። “ሁሉም ዜሮ ዜሮ”ማ ያብቃ!
ጎራ-ሁለት ደግሞ “ሠላማዊ እንጂ ትጥቅ ትግል ለማካሄድ አመች ሀገራዊና ዓለም-አቀፋዊ ሁኔታ የለም” ባይ ነው። በተጨማሪም ኢህአዲግን መግጠም በሠለጠነበትና በተካነበት የመሣሪያ ትግል ሳይሆን ፍጥጥ ብሎ የሚታየውን ደካማ ጎኑን ዕለት ተለት በማጋለጥ፤ ደንጊያ እንደምትሰብረዋ የዝናብ ጠብታ ያልታከተ የፖለቲካ ሥራ በመሥራት ነው ይላል። በሁለቱ ተቃራኒ አቋሞች ላይ ብዙ ስለተጻፈ በዝርዝር አላሰለቻችሁም። ስለ ግል አመለካከቴ “ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ - እንካስላንቲያዎቹ” በሚል ርዕስ የጻፍኩትን ማንበብ ትችላላችሁ።
የጎራ-ሁለት ደካማ ጎን አምስት ዓመት እንኳ ዕድሜ ያላስቆጠረ ብላቴና መሆኑ ነው። ስለሆነም የልምድ ማነስ ቢታይበት ልንበረግግ አይገባም። የዚህ ዓይነቱ ትግል አራማጆች ፈተና ብዙና ውስብስብ ነው። የሚመሩባቸውን ሰነዶች የማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ግልጽ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ደጋፊያቸው በሰቀቀን ኑሮ ውስጥ የሚገኝ ነውና ዛሬውኑ ውጤት ውለዱ ይላቸዋል። ሥራቸው ፊትለፊት ነውና ለነቀፋ፤ ለሴራና ለወከባ የተጋለጡ ናቸው። የሚጋፉት ካዝናውንም ወታደሩንም ሚዲያውንም ፍርድ ቤቱንም የግሉ ካደረገ መንግሥት ጋር ነው። በየድርጅቶቻቸው ውስጥ ሊመሠርቱ የሚሞክሩት የዲሞክራሲ ባህል ለብዙዎች ባይተዋር ስለሆነ የግጭትና አንዳንዴም የመሰንጠቅ ጣጣ ያመጣባቸዋል። ከሥራው ጠባይ ጋር አብሮ የሚጓዝ መሰናክል ስለሆነ እንዴት እንደሚዘሉት ብቻ ነው ማሰብ የሚችሉት። ሊያስወግዱት ግን አይሆንላቸውም። እንዲህ ዓይነቱን የኃላፊነት ፈተና ለመቀበል የቆረጡ ወገኖቻችንን መደገፍ ባንችል እንዴት ልናከብራቸው ያስቸግረናል?
የ“አንድነት” እና የ “መድረክ” ጉዳይስ?
“ቻተር” ይሉታል ፈረንጆቹ። የተሻለ ትርጉም የሚነግረኝ እስኪመጣ ድረስ “ቻቻታ” ብየዋለሁ። የሳይበሩ ኅብረተሰብ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚያደርገው ቻቻታ ከተጧጧፈ ያ ጉዳይ አሳስቦታል ማለት ነው። ያሳሳቢነቱ ደረጃ የሚለካው ደግሞ የተወሰኑ ቃላት ድግግሞሽ ሲበዛ ነው። የሐበሻውን ድረ-ገጽ ላንዳፍታ ብትቃኙት “አንድነት” “መድረክ” እና “ምርጫ” የሚሏቸው ቃላት ድግግሞሽ ጣራ ነክተዋል። ለምን? ማለት ጥሩ ነው። እስቲ “ምርጫና አንድነትን” እንዲሁም “አንድነትና መድረክን” ላንዳፍታ እንመርምራቸው።
ምርጫና አንድነት
አንድነት ከመነሻው ሠላማዊ ትግል አካሂዳለሁ ብሎ ያወጀ ድርጅት ነውና ስለ2002 ዓ.ም. ምርጫ ቢያወራ፤ መግለጫ ቢሰጥ፤ ከመንግሥትና ከመንግሥታት ጋር ቢደራደር፤ ስትራቴጅያዊና ታክቲካዊ ጥቅም ባየበት ቦታ ከሌሎች ጋር ቢሻረክ ፍፁም መብቱ ነው። የሚጠበቅበትም ነው። ከነዚህ ተግባሮች ሊታቀብ የሚችለው ሥርዓትን በተከተለ መልክ በአባሎቹ በሚደረግ ውሳኔ ብቻ ነው። የሠለጠነው ሀገር አሠራርም የዲሞክራሲ ወግም ከዚህ የተለየ አይደለም። በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥና ዙሪያ የተሰባሰቡ ግለሰቦች በአንድነት የፖለቲካ ምርጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ የማድረግ ሕጋዊም ሞራላዊም ሥልጣን እንደሌላቸው ቢረዱ ጥሩ ይመስለኛል። እነዚህ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው የራሳቸውን ቤት የማጠናከርና የማሳመር ብርቱ ኃላፊነት እያለባቸው ስለሌላው ቤት ለምን እንደሚጨነቁ ግራ የምጋባበት ጉዳይ ነው።
አንድነትና መድረክ
ተሳስቼ ከሆነ እታረማለሁ እንጅ በመድረክ መቋቋም ፀጉራቸውን ሲነጩ የማየው በሠላማዊው ትግል ዙሪያ ያሉ ፖለቲከኞች አይደሉም። “አንድነት ፓርቲ የብሔር ቅኝት ካላቸው ድርጅቶች ጋር ትብብር መፍጠሩ የስህተትም ስህተት ነው” እያሉ የሚደሰኩሩትም ከጥቂቶቹ በስተቀር የፓርቲው አባል ያልሆኑ፤ በደጋፊነት ደረጃ ተመዝግበው እንኳ የገንዘብም የሃሳብም አስተዋጽዖ የማያደርጉ ናቸው። ራስህን ዋቢ አደረግህ አትበሉኝ እንጂ በዚህ ርዕስ ላይም የጻፍኩትን http://kuchiye.blogspot.com/2009_07_01_archive.html ማየት ትችላላችሁ። ዘርዘር አድርጌ እንዳልተች በራሴ ላይ የጣልኩት የገጽ ገደብ አይፈቅድልኝም። ወደፊት ግን እመለስበታለሁ።
አንድ ነገር አስተውላችኋል? ልብ ብሎ ለተመለከታቸው ጥያቄዎች ብዙውን ጊዜ መልሳቸውንም አዝለው ነው የሚጓዙት። እስኪ በተረፉኝ መስመሮቼ ጥቂት ጥያቄዎች አንስቼ ልሰናበታችሁ።
1. በቅርብ ዘመን ታሪካችን ድርጅቶችና ፓርቲዎች “ሕብረት፤ ጥምረት፤ መድረክ” መፍጠራቸው ትዝ ይለናል። የውጤታማነታቸውን ነገር ለጊዜው ወደጎን ብንተወው በመተባበራቸው ምክንያት ደም ፈሶ አይታችኋል?
2. መተባበር ቀርቶ መነጋገርን አሻፈረን ያሉ ድርጅቶችና መንግሥታቶች ጦር በመማዘዛቸው አንድ ትውልድ እንዳለቀ ረስተነው ይሆን?
3. የመድረክ መቋቋም የተራራቁ አቋሞችን ለማቀራረብ፤ የጥርጣሬ ቀዳዳዎችን ለመዝጋት፤ የርስበርስ መተማመንን ለማዳበር ከመርዳት ሌላ ምን የሚያስከትለው ጥፋት አለ?
ኩችዬ - ኦክቶበር 29፣ 2009 This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



