አለቃ ተክሌ-ከካናዳ (ክፍል ሁለት)


ምን ላይ ነር ያቆምኩት? የትግራይ ጉዳይ ላይ። ከዚያ በፊት ግን፡ ማለትም የጀመርኩትን የሚኮሰኩስም የሚለሰልስም፤ ወደድንም ጠላንም ግን ልናመልጠው የማንችለውን ርእስ ከመቋጨቴ በፊት ትንሽ እንቀልዳለን። (በነገራችን ላይ፡ ከዳላስ ወደ ሲያትል በሚጓዘው የአሜሪካን አየርመስመር (አ.አ.) ላይ ሆኜ ነው ይሄንን ጽሁፍ የማስተካክልላችሁ።

 

አየር መንገድ ነው አየር መስመር? ሁለቱስ ምን ለውጥ አለው? ምንም። የት እንደሆንኩ መጥቀሴ ለምን አስፈለገ? በቃ አሰኘኛ። ለነገሩ ስላሰኘኝም ብቻ አይደለም። አየር ላይ ተንጠልጥሎ መጻፍ ትንሽ ብርቄም ስለሆነ ነው። አየር መስመር ነው መሆን ያለበት አየር መንገድ ስል አንድ የስደት ትርጉሜ ትዝ አለኝ። ኬንያ፡ ካኩማ የስደተኞች ካምፕ።

አንዲት የምወዳትም ባይሆን የማስባት ኬኒያዊት የተባበሩት መንግስታት የስደት ኮሚሽን ሰራተኛ ቡና ልናፈላላት ጋብዘናት ከተጠለልንበት ቦታ መጣች። ቡና ቁርስ ቀረበ። እኔና ጓደኞቼ ስለኢትዮጵያ ቡና ስርአት ማብራራት ጀመርን። ቡና ቁርስን በእንግሊዘኛ ምን እንበለው? እንደወረደ ተረጎምኩት። “ኮፊ በሬክፋስት” ከከከከከከከከከከከከከ። ለረጅም ጊዜ ረስቼው ነበር ይሄንን ገጠመኝ። አንዲት በወቅቱ የነበረች ተንኮለኛ ሴት ነች ከስንት ግዜ በኋላ እዚህ ካናዳ ስንገናኝ ያስታወሰችኝ።


ሳቅ ይበቃናል። ወደ ቁምነገር። ወደ ምሬት። ሳቅ ስለናፈቀው ህዝብ ስንናገር፡ እኛ ከትከት ብለን ብንስቅ አያምርብንም። በዚህ ሰዓት አስራ ሶስት ጉዳዮች ያሳስቡኛል። አንዳንዶቹ የግል ናቸው። የሶስተኛ ዓመት ትምህርት የአንደናው አጋማሽ መርሀ ግብርን በድል ስለማጠናቀቅና በጥናት መሸፈን ስለሚገባኝ ጉዳዮች። ሁለተኛው ስለእናቴ ነው። እሱም በቀጥታ አይመለከታችሁም። ሶስተኛው ያው ስለኛ ነው። ስለትግራይና ስለኛ። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ፡ ልክ እንደአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ፡ ከመረጃ ውጭ ነው ወይም ከወያኔ የሚሰጠው የተሳሳተ መረጃ ነው ያለው። ባለፈው ሰሞን ያየሁት ዜና “አረና ትግርኛ ተናጋሪ ቅንጅት ነው” የሚል የተቃውሞ ሰልፍ በማይጨው ተካሄደ ይላል። ከዚያ ቀደምም፡ መቀሌ ላይ አረና ስብሰባ ሲጠራ እንዲሁ፡ አንዳንድ ሰዎች አረናዎችን ከቅንጅት ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ሲከሱ ነበር። ሌላ ምሳሌ ልጨምር። አቶ ስዬ አብርሀም እንዲሁ አንዴ ቃለምልልስ ላይ እኔን “ከትግራይ ህዝብ ጋራ ለማጣላት የቅንጅት አባል ሆኗል እያሉ ያወራሉ” ብለው ተናግረዋል። ስለዚህ ቅንጅትን በትግራይ ህዝብ ላይ የተነሳ ጠላት አድርጎ የማየት አዝማሚያ አለ ማለት ነው በትግራይ ህዝብ ዘንድ። እኛም እነሱን እነደበዳይ፡ እነሱም እኛን በጥላቻ ልናጠፋቸው እንደተነሳንባቸው የማየት አዝማሚያ አለ ማለት ነው። ስለዚህ ትግሉ የተቀረውን ህዝብ ስለማንቃትና ስለመድረስም ነው። ለዚህ ነው የመገናና ብዙሀን ነገር ሁልግዜም የሚያሳስበኝ። ሎተሪ መቁረጥ የጀመርኩት ለመገናኛ ብዙሀን ስል ነው። ከብዙ መንግስታት ጋር ሳንጣላ፡ ልንገነባው የምንችለው ግን በጣም አስፈላጊ ሚሳይላችን ሬድዮና ቴሌቪዥን ነው።


የተሸነፍነው በመገናኛ ብዙሀን እጦት ነው፡ የምናሸንፈውም


ለኔ የኢትዮጵያን ትግል በሁለት ቃል ጭመቀው ብባል፡ የመገናኛ ብዙሀን ትግል ነው የምለው። ያንን፡ መገናኛ ብዙሀንን ካገኘን ድላችን ይፋጠናል። ያለበለዚያ ያው እነሱም እኛም ባለንበት እንቀጥላለን። ከምንም በላይ ደግሞ የተሸነፍነው በመገናኛ ብዙሀን እጦት ነው። የኢህአዴግን፡ “ተራ፡” ግን አጥፊ ፕሮፓጋንዳ መስበር አለብን። ኢህአዴግ የረባ ፕሮፓጋንዳ የለውም። ግን ቢያንስ የኛ ፕሮፓጋንዳ ህዝብ ዘንድ እንዳይደርስ በሚገባ አድርጓል። ኢህአዴግን የምናሸንፈው ጦር ሰራዊቱን የመታን እለት አይደለም። የመገናኛ ብዙሀን አከርካሪውን በሌላ መገናኛ ብዙሀን መምታት የቻልን እለት ነው። እነሆ ምሳሌ፡ በሚያዚያ 2001 ዓ.ም. በመቶዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች፡ የአ.አ.ዩ. ስድስት ኪሎ ግቢ ሰብረው ገቡና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ደበደቡ። አቆሰሉም። የአግአዚ ጦር አጥፊ የከተማ ጽንስ የተፈጠረው ከዚያ በኋላ ይመስለኛል። እኔ ያኔ የአራተኛ ዓመት ተማሪ መሆኔ ነው። የትምህርት ሚኒስትራቸው፡ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ መጡ። ፖሊሶቹን ገሰጿቸው። ትንሽ ተረጋጋን። ወደ ፍሬሽማን ህንጻ፡ 505 ወሰዷቸው። የኢ.ቴ. ጋዜጠኞች ነበሩ የዚያን ግዜ። ጋዜጠኞቹም ካሜራ አንሺዎቻቸውም እባካችሁ ካልቀረጽን አሉ። ኢቲቪዎችን፡ ተማሪዎች ያኔም አንወዳቸውም። በፍጹም ይውጡ ተብሎ፡ በመጨረሻ አግባቡ እግራችን ላይ ወደቁና ቀረጹት።

ማንም፡ እንኩዋንስ እንዳለ፡ ቆራርጠውም ያስተላልፉታል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ማታ ግን አስተላለፉት።
ረቡእ ሚያዚያ ዘጠኝ ቀን፡ በሰሙነ ሕማማት፡ በማታው ዜና ላይ ደምና የተሰባበሩ ቆመጦች፤ የተፈነካከቱና የቆሰሉ ተማሪዎች፡ እንዲሁም መፈክር የምናሰማ ሌሎች ተማሪዎች ምስል በቴሌቪዥን ታየ። በስህተት፡ ወይንም በተሳሳተ ስሌት፡ ነገሩ በሌላ ዜና ከሚወጣና ህዝብ ከሚያውክ ብለው መሰለኝ ቀድመው ያወጡት። የተመጠነ ዜናም ቢሆን የዚአን እለት የኢትዮጵያ ቴ/ቪ ሳያውቀው ታሪክ ሰራ። ወይም ነገር አበላሸ። ለነሱ። በነጋታው በያቅጣጫው ተቃውሞ በረከተ። መቀሌም አልቀረም። በኋላ የትግራይ ተወላጆች ሱቆችና ወርቅ ቤቶች ተዘረፉ፡ ተማሪዎቹም “ትግሬ ላይ ነው የተነሱት” ሲባል በየቤተክርስቲያኑና ሆቴሎች ተማሪዎች አስጠግተው የነበሩ የመቀሌ ሰዎች ተማሪዎቹን ማባረር ጀመሩ። አሉ። እዚአ አልነበርኩም። ያቺ አንተን ሊበሉህ ነው አንተን ሊያጠፉህ ነው እያሉ ትግሬን ማስፈራራት ለመጀመሪያ ግዜ የተሞከረችው ያኔ ነው። ከዚህ የከፋ ኑክሌር ደማሚት የለም። ቦምብ ደማሚት ከሆነ ብዬ ነው። ግን ፈንጅ ነው መሰል ደማሚት። ስለዚህ ቦምብን ደማማይ እንበለዋ።


የሆነ ሆነና፡ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ። የአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ተ/ቤቶች ተማሪዎች ጆሮዋቸውን አቀኑ። በቀጣዮቹ ቀናት ከኛ ብሰው ቁጭ አሉ። አዲስ አበባ ለሳምንት ቀውጢ ሆነች። ባንድ ሌሊት በስህተት ባይሆንም በሌላ ዓላማ የተላለፈ ዜና አገሩን ሁሉ ደረሰው። ከዚያ በኋላ ማናቸውም ዜና አመጹን አላቆመውም። አመጽ ፈነዳ። ሌሎች የሚሉትን እንጃ። እኔ ግን፡ እኔ ያኔ ጥግ ይዤ እታዘብ የነበርኩት ሰው የምለው፡ ያ የተማሪዎች አመጽ የደረሰበት ደረጃ ላይ የደረሰው በራሱ በወያኔ የተሳሳተ ስሌት በተሰራ የመገናኛ ብዙሀን ስራ ነው። ያኔ በመጀመሪያ ምሽት በአ.አ.ዩ. የፈሰሰው ደም በቴሌቪዥን ባይታይ፡ በሬድዮ ባይሰማ፡ ምን በወቅቱ የነበሩት የግል ፕሬስ ውጤቶች የሚችሉትን ሁሉ ቢያደርጉ አመጹ ከአዲስ አበባ አይወጣም ነበር።

 
ከኬንያ እስከ ዙምባቤ፡ ከሆንዱራስ እስከ ኡክሬይን፡ ከምድር እስከ ማርስ ሂዱ፡ ያለ መገናና ብዙሀን ድል የለም። በዚህ ዘመን፡ ጽድቅና ኩነኔ ራሱ በመገናኛ ብዙሀን ነው ባይ ነኝ። እኔ ኢህአዴግ፡ ይቅርታ “ኢህአዴግ የሚባል ነገር የለም ሕወሀት ብቻ ነው” ብሎናል የቀድሞ ልጃቸው ገብረመድህን፡ ህወሀት በመገናኛ ብዙሀን እንጂ በምንም አላሸነፈንም ባይ ነኝ። ሰው ገድሏል። ሰውም አስሯል። ሰውም አሰድዷል። ሰውም አስፈራርቷል። ሰው አካለ ስንኩል አድርጓል። ከምንም በላይ ግን ያሸነፈን፡ ከመገናኛ ብዙሀን ስለለየን ነው። ስለዚህም በልሳንም ብንነጋገር አንግባባም። ብርሀኑ የሚለውን ሀይሉ አይሰማም። አንዳንድ ጊዜ፡ ብርሀኑ የሚለውን ራሱ የብርሀኑ ተከታዮች አይሰሙትም። የግንቦት ሰባትን መወለድ የሰሙ ምን ያህል ሰዎች እንዳሉ አላውቅም። ጠንካራና አስተማማኝ መገናኛ ብዙሀን ማግኘት የትግሉ ማእከል ነው ባይ ነኝ።

ጠንካራ መገናኛ ብዙሀን ማግኘት ትግሉን በግማሽ ይቀንስልናል ባይ ነኝ። ሰላማዊም በሉት ሰላማዊ ያልሆነው፡ ህዝባዊም በሉት የአመጽ ትግል ሁሉም የተሳኩ እንዲሆኑ የሚጋሩትና የሚያስፈልጋቸው አንድ ነገር፡ መገናኛ ብዙሀን ነው። አስራ ስምንት አመት ህወሀት ምንም ፍንክች ያላለበትና ለማስመሰልም በግል እንዲያዝ ያላፈቀደው መስክ መገናኛ ብዙሀን ነው። ዶ/ር ብርሀኑ ይሄንን ትንሽ ይሄድበታል፡ በ2005 ምርጫ ላይ ወያኔ ቲቪና ሬዲዮ ባይፈቅድ ያንን ያስመዘገቡትን ውጤት ያስገኙ ነበር ወይ? ለእኔ አይመስለኝም። እንደውም የ2005 ምርጫ ዋናው ስራ መገናኛ ብዙሀን ይመስለኛል። (አሁንም እዚያው ዳላስ ክራሥን ፕላዛ፡ መድረክ ላይ ነኝ። ይሄንን ዶ/ር ብርሀኑ ይሂድበት አይሂድበት አላውቅም)።

 
ደግሞ ድርጅት፡ ከዚያ ድርጅት


መገናኛ ብዙሀን አየር ላይ አይቆምም። ይሄ የግንቦት ሰባት መድረክ ነው (የዳላሱን ስብሰባ ማለቴ ነው)። ግን ግንቦት ሰባት ብቸኛ አዳኝ ድርጅታዊ መሲህ ነው ብዬ አላምንም። ግንቦት ሰባትም አያምንም። ምንም ይሁን፤ ብቻ ድርጅት ያስፈልገናል። በዚህ 10 12 ዓመት ውስጥ በጣም የምጠላውና የሚሸክከኝ እምነትና አቋም ይሄ “እስኪ ትንሽ እንየውና” እንደባለቃለን የሚል ነገር ነው። ያ ብቻም አይደለም፡ የመሞከርና ሪስክ የመውሰድ እልሃችን መክኗል። እዚህ ጋር ቀጥተኛ ቅስቀሳ ላስገባ፡ “ጎበዝ፡ ሕይወት ሙከራ ነው። እየሞከርን ነው መሞት ያለብን። ምንኩስና ሙከራ ነው። ሰው ይመነኩሳል። ይሞክራል። በመጨረሻ እንደመነኮሰ ሲሞት ነው ምንኩስናው የተሳካ መሆኑን የምናውቀው። ሰው ለምሳሌ ይደቁናል። ወይ እንደደቆነና ህግ እንደ ጠበቀ ይቀራል። ወይም እንደኔ መንገድ ላይ ያፈርሳል። ትግልም ድርጅትም ሙከራ ነው። ሰው ሕይወት አልተሳካልኝም ብሎ መኖር አያበቃም። አይሰቀልም። ያንን የሚያደርጉ ይኖራሉ።

ግን ኤክሰፕሽንስ ናቸው እነዚያ። ኦብኮ አላዋጣንም፡ መልካም፡ ኦፌዲንን እንሞክረው። ኢህአፓ አላዋጣንም። ኦኬ፡ ቅንጅትን መሞከር። አማራጭ ሀየሎችና ማየት። ግንቦት ሰባትን ማየት። ቅንጅት ስል በነገራችን ላይ አገርቤት እንጂ የሚያሻማው እዚህ አያሻማም ብዬ ነው ማንን ለማለት እንደፈለግኩ። ቅንጅት አንድነት ነው። ከከተማ ከተማ፡ ካገር አገር ትንሽ ዞሬያለሁ። ሁላችንም የምንጋራው ስንፍናና ድክመት ይሄ በፖለቲካና ማህበራዊ ድርጅቶች ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ እግራችንን የምንጎትተው ነገር ነው። ያም ብቻ አይደለም የምንሰጣቸው ምክንያቶች አጥጋቢ አይደሉም። በሌሎች ማሳበብን እንወዳለን። ርስ በርሳቸው በማይግባቡ መሪዎቹ። ግን ለኔ የኢትዮጵያ ጉዳይ የቤተሰብ ጉዳይ ያህል ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ የሕይወት ጉዳይ ያህል ነው። ልጄ አበሳጨኝ ብዬ ልጄን ልጅነቱን አልክድም። ቀድሞውንም የአገርን ጉዳይ የልጆቻችንንና የቤተሰባቸንን ያህል ቦታ አልሰጠነው እንደሁ እንጂ፡ ምን የፖለቲካ መሪዎቻችን ቢያበሳጩን የትዮጵያ ጉዳይ በነሱ ተበሳጭተን ገሸሽ የምናደርገው አይደለም። ሰበብ አሳዳጆች አንሁን። ኢህአዴግም እንሁን፤ ግን እንደራጅ። 

     
ሀይማኖትና ፖለቲካ


ባለፈው ሰሞን ጽፌ ነበር። ስለሀይማኖት ተቋማትና ፖለቲካ። ስለዴሞክራሲና ቤ/ክርስቲአን። የእስልምና እምነት በፖለቲካ ላይ ያለውን አቋም ጠንቅቄ አላውቅም። ከክርስትናው የሚርቅ አይመስለኝም። እንደውም ዓለም ሁሉ የአላህ ነው ስለዚህ ዓለም በአላህ ትእዛዝና ህግጋት መገዛት አለባት የሚል ይመስለኛል። እነዚህ ስልጣን ይዘው ሰው የሚገድሉ፡ ሰው የሚያስሩና ሰው የሚያንገላቱ ሁሉ ደግሞ የአላሃን ትእዛዝ የሚተላለፉ ናቸው ማለት ነው። ስለዚህ እስልምናም ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝብ ገዢዎችን እንድንፋለማቸው ያዘናል። (ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በዳላሱ ስብሰባ ላይ ስለሀይማኖትና ፖለቲካ፡ በተለይም ስለክርስቶስ ለሰው ልጆች መብት መሞትና መጎሳቆል በሰፊው ተናግሯል)። እኔም አልኩ። በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ገብተን የሀይማኖት ተከታዮችን ማሰለፍ ካልቻልን ማንን ልናሰልፍ ነው? ያንን ከሲያትል በሶስት አውቶብሶችና በግል መኪናዎች ተጭኖ ወደ ቫንኩቨር የመጣ ሕዝብ ታስታውሳላችሁ? እንደውም አማኞች ዋና ተከታዮች ይመስሉኛል።


የቆሙለትን ነገር እንደግፋለን አንደግፍም ሌላ ጉዳይ ነው። ግን በዚህ ሰዓት እንኩዋን፡ ከነጻነት ታጋዮች ይልቅ የሀይማኖት ታጋዮች ወይንም በሀይማኖት ስም የሚታገሉ ሰዎች መስዋእትነትና ተጋድሎ እጅግ ሰፊ ነው። ራሳቸውን አፈንድተው ጠላታቸውንም ለማፈንዳት ስለሚወስኑና ስለሚያደርጉ ሰዎች አስቡ። ቁርጠኝነታቸው አይገርማችሁም? በምንም መልኩ ግን ያንን መደገፌ አይደለም። የሀይማኖት መልእክተኞች ካመኑበት ዋና ተከታዮችም ናቸው ለማለት ነው። ከዚያ መለስ ግን ከዚሁ ሳልወጣ ሌላው በጣም የሚያበሳጨኝና የሚያናድደኝ ነገር ይሄ ባንድ በኩል የፖለቲካ ስደተኞች ነን፡ ወያኔ አባቴን አሰረው፡ ወያኔ እኔን ደበደበኝ፡ ወያኔ ቤታችንን አቃጠለው ኢትዮጵያ ውስጥ በነጻነት መኖር አልቻልንም፡ ተጨቆንን እያሉ የአገሪቱን መከራ ኬዝ አሳምረው ተሰደውበት፡ በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ ሲመጡ ፖለቲካን አይንህን ላፈር የሚሉት ነገር ነው። ከፈለጉ ኢህአዴግን መርዳትም ይሁን። ከፖለቲካ ግን መራቅም መውጣትም አይቻለንም። ፖለቲካዊ ምንኩስ የሚባል ነገር የለም። በፖለቲካ መመንኮስ እንጂ። ወይንም ከፖለቲካ መጾም የሚሉት ነገር አይታየንም። መጾም ያለብን ከፖለቲካ መሸሽን ራሱን ነው። ፖለቲካ አገር ሀይማኖት የተደበላለቁ ነገሮች ናቸው። ግን ሚዛኑን ጠብቀን በነዚህ ተቋማት ውስጥ መሳተፍና ማሳተፍ አለብን ሌሎችንም።


ስለለውጥ፡ ስለትግል፡ ስለግንቦት ሰባት


እዚያው ዳላስ ነኝ አሁንም። ከዚያ ስለለውጥ ቀጠልኩ። ለውጥ ግርግርና የደመ ነፍስ መሆን የለበትም። ድል ባለቤትና አቀናጅ ይፈልጋል። አለበለዚያ ለውጥ ነውጥ ይሆናል። እኔ የምመኘው ለውጥ፡ በራሳቸው በሕወሀቶች ቀዳሚነትና ፍላጎት የሚመጣውን፡ እኛም እነሱም አሸናፊ የምንሆንበትን ሰላማዊ ለውጥ ነበር። ቢሆን ቢሆን ደስ የሚለው ለኢትዮጵያም ዘላቂ ሰላም ይበጃል የምለው፡ አንዱ ተሸናፊ ሌላው አንዱ አሸናፊና ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድበት ስርአት ሳይሆን፡ ሁላችንም የምናሸንፈበት ቢሆን ነበር። ምክንያቱም፡ ለውጡ በኛ አሸናፊነትና በነሱ፡ ማለትም በሕወሀት ተሸናፊነት በሀይል ከመጣ፡ ነገሮችን በቁጥጥር ስር እስኪውሉ ድረስ ከፍተኛ ጥፋት መድረሱ አይቀርም። በሁለታችንም አሸናፊነት ካልተጠናቀቀ በስተቀር፡ ትናንት ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሲተካ ምንም ያልነበረውና ዛሬ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ጠብመንጃ ታጥቆ የአገሪቱን ሀብት የሚመዘብረውን፡ የኢትዮጵያን ወጣት እንደ ሽንኩርት የሚቀረድደውን ሕወሀትና ደጋፊዎቹን ሕዝቡ ታቅፎ ዝም ብሎ ምንም እንዳልተፈጠረ ይኖራል ለማለት ይከብዳል። ስለዚህ ድሉ የጋራ መሆን አለበት፡ የኛም የሕወሀትም። የኛም የኦነግም። የኛም የጎረቤቶቻችንም።


ይሄንን የተደላደለ ድል ለማምጣት ደግሞ አገር ውስጥም ካገር ውጪም ያለው ታጋይ፡ ሰላማዊውም አመጸኛውም ታጋይ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። አሁን ባለው ሁኔታ፡ ሕወሀት አሸናፊ ነው። አሸናፊ ብቻም አይደለም፡ ለወደፊቱም አንሸነፍም የሚል እምነትና መንፈስ የሞላው ድርጅት ነው። በዚህ ሁኔታ ሰላማዊ ታጋዮችን መድረክ ሰጥቶ ተፎካክረው ወይንም ተደራድረው እንዲያሸንፉት የሚያስገድደው ምንም ሞራላዊም፡ ቁሳዊም፡ ኢኮኖሚያዊም አለማቀፋዊም ግፊትና ጫና የለም። ስለዚህ ሕወሀትን ወዲዚህ ድርድር የሚያስገድድ ነገር መፍጠር አለብን ማለት ነው። እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ ድርጅቶች ናቸው ያንን አስገዳጅ ርእዮት ወይንም ሀይለ ወይንም ሚንስ መፍጠር ያለባቸው። ያለብን ማለት ነው።


ያንን እንዴት ያመጡታል? ያንን ለነሱ እንተወው። ሀሳብ መስጠት መልካም ነው። ግን ጊዜና ዴፈረንስ መስጠት አለብን። መጀመሪያ ማመን አለብን። መሞከር። ይችላሉ። ያደርጋሉ። የሚሰሩትን ያውቃሉ ብለን ማመን አለብን። ያውቃሉም ብቻ አይደለም፡ ለማወቅም ከኛ የተሻለ ቦታና ጊዜ ውስጥ ነበሩም ናቸውም። በነዚህ ሰዎች ካመንባቸው፡ ይችላሉ ያደርጉታል፡ ካልን፡ ለግንቦት ሰባት ሰዎች ስለምንሰጠው ዴፈረንስ፡ በመርህ ደረጃ ከተስማማን፡ የተቀረውን አመራር ለነሱ መተው ነው። ለምሳሌ ደ/ር ብርሀኑ ብድግ ብሎ ኤርትራ ቢገባና ከአቶ ኢሳይያስ ጋር አብሮ የመስራት ስምምነት ቢፈራረም፡ በዶ/ር ብርሀኑና ድርጅቱ እስከተማመንን ድረስ፡ ደ/ር ብርሀኑ እኛ የምናስበውን ያህል እንዲያውም በተሻለ ሁኔታ ከኤርትራ ጋር መስራት ያለውን አደጋና ጥቅም ማሰላሰልና ማሰብ ይችላል ብለን ካመንንና በሱና በድርጅቱ ላይ እምነት ካለን፡ የሚሰራውን ያውቃል ብለን እድል መስጠት አለብን። እንደግፍ አይደለም። ግን እንዲሞክር እድል እንስጠው። ለነገሩ ብንሰጠውም ባንሰጠውም የኛን መቀበል የሚወስነው ውጤቱ፡ ማሸነፉ ነው። ካሸነፈ እንደግፈዋለን። ከተሸነፈና ካልተሳካለት እንረግመዋለን። የኛም የዓለምም ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለመው። አሸናፊዎች ይወደሳሉ። ተሸናፊዎች ይወገዛሉ። እስከዚያው ግን ጠላትም እንደዚያ ነበር። ዛሬ ይረሳዋል እንጂ። ከትቢያ ላይ ተነስቶ ነው የረታን። ጠላትም እኛን ድል ለማድረግ ከጠላት ወይም ከጠላት መሰል ሀይላት ጋር ተባብሯል። ጠላት የሚለውን ይበል። የሚጠቅመንን የሚያስኬደንን የምናውቀው ግን እኛ ነን። አማረ አረጋዊ አይደለም።


የኤርትራ ነገር ሲነሳ ያብረከርካቸዋል


የረጅም ግዜ የህወሀት አባልና የሪፖርተር ባለቤት፡ አቶ አማረ አረጋዊ በፓልቶክ ቃለ ምልልስ ይደረግ ነበር። ያኔ በፌሮ ከደበደቡት በኋላ። “ሰው እንዴት የፈለገ ኢህአዴግን ቢጠላ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ከሻእቢያና ከሶማሌ ጋር ያብራል?” አይነት ጥያቄ እያነሳ ያንን ከኤርትራ ጋር እንስራ ሀሳብ የሚያነሱትን ያወግዛል። ሰው እንዴት የት እንደነበረ እንዲህ በትንሹ ይረሳል? አስራ ስምንት አመት ብቻ፡ እንደውም ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ከዚያ ያነሰ ነው ያለፈው። ከኤርትራም ከሶማሌም ጋር አብረው እነሱ ደርግን ስለጠሉ ብቻ ኢትዮጵያን ሲወጉ አልነበር እንዴ? ስለዚህ እኔ ሳደርገው ትክክል ነው። ሌሎች ሲያደርጉት ግን ስህተት ነው አይነት ነገር መሆኑ ነው። ጥያቄው የኤርትራ መንገድ እዚያ እምንፈልግበት ከነአን ያደርሰናል ወይ ነው።ካደረሰን ወይንም ያደርሰናል ብለው የሚያምኑ ካሉ እንሞክረው ይሞክሩትም። እናነትም ሞካሪዎቹም ሞክሩት። አትሽኮርመሙ።

ስለዚህ ባለፈው አቶ አንዳርጋቸው አስመራ ታየ የሚለውን ዜና ኤልያስ ክፍሌ ሲለጥፈው፡ የግንቦት ሰባት ሰዎች የጮሁት ጩኸት አልተመቸኝም። ድርጅት ህዝቡን ቀድሞ መምራት አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የኤርትራን መንገድ ሊያጸድቅ አይችልም። መንገዱን ቀዶ መሞከርና ሄዶ ማሳየት የድርጅቶች ፈንታ ነው። ስለዚህ የሚደግፍ ይደግፋል። የሚቃወምም ይቃወማል። ግንቦት ሰባት ግን የኤርትራን መንገድ ማፈርም መፍራትም የለበትም።

 
አንዳንድ ሰው ያለቀለት፡ ከዲሲ ተነስቶ አራት ኪሎ የሚያደርስ የትግል ቀመር ተስሎ ማየት ይፈልጋል። እኔ ራእይ ነው የማየው። ግንቦት ሰባት ሀሳብ ነው። ከቀንም ቀን አለ። አንዳንዱ ቀን ከቀንም በላይ ነው። ግንቦት ሰባት ቀን ነው። ግንቦት ሰባት ግን ራእይም ነው። ግንቦት ሰባት ክስተትም ነው። ግንቦት ሰባት ወኪል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግንቦት ሰባት 2005 ዓ.ም. ተናገረ። ያ መልእክቱ ግን ከሸፈ። ያንን ከግብ ሊያደርስ የተነሳ ድርጅት ነው። ቅልብጭ ያለ ራእይና ጥርት አለ ተለእኮ ናቸው። “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ የተከበረበት፡ የኢኮኖሚ ብልጽግናና ማህበራዊ ፍትህ የሚያገኝበት፡ የዜጎች ህይወት ደህንነትና ጥቅም የተከበረበት ሀገር እንዲኖረው ማድረግ ነው።

የመንግስትና የፖለቲካ ስልጣን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበትና የሀገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለጽበትን ብሄራዊ ፖለቲካዊ ስርአትን እንዲገነባ ማገዝ።” የግንቦት ሰባትን የህዝብ ውሳኔ ለመመለስም ባይሆን፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱን በራሱ የሚመርጥበት ስርአት ለመገንባት የሚታገለው ግንቦት ሰባት፡ እስካሁን በተጓዘው ጉዞ አካሄዱ ሁሉ ይበል የሚያሰኝ ነው። በተለይ የሌሎችን ቁስ ለማከም የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ኢትዮጵያዊነት ለማስፈን ሕወሀትን ከጣልንም በኋላ የማይተዉን የግድ መነሳት ያለባቸው ሕወሀት በስልጣን ዘመኑ የባሰ ያመረቀዛቸው ቁስሎች አሉ። ግንቦት ሰባት ያንን ሲሆን ሲሆን ለማከም፡ ያለበለዚያም ለመረዳት የተዘጋጀ ይመስላል።


ኢትዮጵያዊነቱ የሚያመው፡ ኢትዮጵያዊነቱ የሚቆጨው ካለ እናክመው


ባለፈው ሰሞን አቶ ኦባንግና ጓደኞቹ የሚያዘጋጁትን ሰልፍ ደግፌ ስጽፍ እንዲህ ብዬ ነበር። “ይሄ ሰልፍ የአንድነት ናሙና ነው። ኢትዮጵያዊ መሆኑ እንደጎዳው የሚያምን ኦሮሞ ካለ፡ ኢትዮጵያዊ መሆኑ የሚያመው ኦጋዴን ካለ፡ ኢትዮጵያዊ መሆኑ የሚቆጨው ሲዳማ ካለ፡ እነሆ ብድግ ብለን ሊቆጭ ሊያመው ሊከፋው እነደማይገባ የምናሳይበት አጋጣሚ እንዲህ ያለው ነው” ብዬ ነበር። እኛ ላይመስለን፡ እኛ ላናምንበት እንችላለን፡ ግን አንዳንዶች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተበድለናል፡ ተገፍተናል፡ ሙሉ ኢትዮጵያዊ አልነበርንም የሚሉ አሉ። ይሄ እውነት ነው ይሄ ሀሰት ነው የሚል ክርክር ውስጥ አንግባ። ጊዜውም የለንም። ይሄንን ደግሞ ጥሩ አድርጎ ሕወሀት አስፍቶታል። አባብሶታል። ፖለቲካ ደግሞ ፉክክርም ነው። ሕወሀትን ተሽለን መገኘት አለብን። ከሕወሀት የተሻለ ኦፈር ማድረግ አለብን። ከዚህ አንጻር አንዳንዶቹን ወደኋላ መቀልበስ አንችልም።

ከዚህ ቀደም ዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ ስብሰባ ላይም እንዲሁ ተናግሬያለሁ፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሕወሀት ለስልትም ብሎ ይሁን የምሩን የሰጣቸው ጥቅማጥቅሞች ካሉ በነሱ ላይ የምንጨምር እንጂ እነሱን የምንቀማ መስለንም ሆነንም መታየት የለብንም። ለምሳሌ፡ ሀብታቸውን በዘረፋና በሙስና ያገኙ ሰዎችን ወይንም ቡድኖችን ልንታገስ አንችል አይገባምም ይሆናል። ግን በኦሮምኛ ቋንቋ፡ መናገርና መዳኘት በምንም መልኩ ልንነጥቀው የምንችለው መብት አይደለም። ከዚህ ቀደምም እንዳልኩት፡ እንደውም ሕወሀት ኦሮምኛ ያንድ ክልል ቋንቋ ነው ያደረገው እኛ የኢትዮጵያ እናደርገዋለን ነው ማለት ያለብን።


ከዚህ አንጻር የግንቦት ሰባትን አቋም ባላውቀውም፡ ግንቦት ሰባት ያንን ለማድረግ የሚሳሳ አይመስልም። ግንቦት ሰባት ሁሉንም ብሄሮችና በኢትዮጵያ ውስጥ ባንድም በሌላም መልኩ ሚና አላቸው ከሚላቸው ሀይሎች ጋር የሚያደርገው ውይይት መቀጠል አለበት።  እንግዲህ የቀረው የኤርትራ መንገድ ነው። ታሪክ ተለዋዋጭ ነው። በነበረበት የሚኖር ምንም ነገር የለም። እኔና እናንተም የዛሬ አስር ዓመት እዚህ አልነበርንም። ዛሬ እዚህ ነን። እነዚህ ሰዎች ላይ የተገኘውን ነገር ሁሉ ነው መወርወር ያለብን። መሳሪያና መንገድ ረዳትና ተባባሪ መምረጥ የለብንም። እዬዬም ሲዳላ ነው። ደግሞም እነ አቶ ኢሳይያስም ትንሽ መቀየር እያሳዩ ነው። የሚፈልጉትን ነጻነት አግኝተዋል። ከዚህ በኋላ የሁለታችንም ሕልውና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳሰረ ነው። ቢመረንም ቢቆጨንም ኤርትራ አገር ሆናለች። ለምናደርገው ትግል የጎረቤት አገር እገዛ ካስፈለገን ኤርትራን እንደምርጫ ማሰብ የግድ ነው። አሰብን እንደ ወደብ አምጡ ሳይሆን ኤርትራን እንደ ጎረቤት ወይንም እንደአገር ወይንም እንደ ፌደራል ግዛት ማሰብ ነው የሚበጀው። ፕሮፌሰር መሳይም ይሄንኑ ነው ያለው በቅርቡ በጻፈው ጽሁፍ ላይ እንዳስታወሰን።


እነሆ ወደ ቫንኩቨር ተመለስኩ


ግዜ አጠረኝ እንጂ፡ በዚህ ርእስ ላይም ብናገር ደስ ይለኝ ነበር፡ የሙሉ ጊዜ ጠላትን በትርፍ ግዜ ትግል ስለመግጠም። እኛ በትርፍ ጊዜ ነው የምንንቀሳቀሰው። በትርፍ ጊዜም አይደለም፡ በትርፍራፊ ጊዜ እንጂ። እነሱ በሙሉ ጊዜ ነው የሚሰሩት። በሙሉ ጊዜም ብቻ አይደለም፡ ከወደፊቱና ከመጪው ዘማናችንም ሰርቀው እንጂ። ትግላችን የሙሉ ጊዜ ሰራተኛ ያስፈልገዋል። ከመደበኛ ስራው እየቆነጠረ እንዳደረሰው የሚንቀሳቀስ ሳይሆን፡ ቀንና ሌሊት ይሄንን ጉዳዩ ያደረገ ታጋይ እንጂ። እነሱም እንደዚያ ነው አዲስ አበባ የገቡት። ሁላችንም ደግሞ በቀጥታ የሙሉ ጊዜ ታጋይ ልንሆን አይቻለንም። ግን የሙሉ ጊዜ ደጋፊዎች የሙሉ ጊዜ አታጋዮች የሙሉ ጊዜ ደጀኖች ልንሆን እንችላለን። ገንዘብ። ነጻ ምሳ የለም ነው ያለው የስነ-ምጣኔ ሀብት ጠበብቱ። ነጻ ድል የለም። እንግዲህ ሁሉም እየለየለት ነው። ሁሉም ያመነበትን የመሰለውን ያድርግ። እነ አቶ ሀይሉንም አናውግዛቸው። የመሰላቸውን የሚያዋጣቸውን መርጠዋል። የነሱን መንገድ ማውግዝ ለኛ መንገድ አይወልድልንም። የራሳችንን መንገድ ከመገንባትም ጋር አይገናኝም። እነሱም በምርጫ ያሸንፉት፤ ሕወሀትን። እኛም በጡጫ። ወይ በርግጫ። ወይ በሙቀጫ። ለምን ግንቦት ሰባትን አንሞክረውም?


ቢትወደድ ተክሌ፤ ተጻፈ፡ መስከረም በገባ በሃአኛዎቹ ቀናት። 2002። ተሻሻለ፡ በጥቅምት። ታተመ፡ አሁን።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ