ብርቱካን በቃሊቲ - አቶ ኃይሉና አቶ መለስ ተጨባበጡ
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ትዝ ይለኛል ከሁለት ዓመታት በፊት ከአንድ ኢህአዲግን ከሚደግፍ ወዳጄ ጋር የተነጋገርኩት። የቅንጅት መሪዎች ከእሥር ቤት ተፈተዋል። ወደ ሁለተኛው ሚሊንየም ለመሸጋገር እየተዘጋጀን ነው። አቶ መለስ ዜናዊ፣ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ አቶ ስዩም መስፍን … ሁሉም በአንድ ላይ ጎን ለጎን ቆመው፣ እንደ ወንድማማቾች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሠላም፣ የፍቅር፣ የእርቅና የአንድነት መልዕክት በቴሌቭዥን ቢያሰሙን በጣም ጥሩ ይሆን እንደነበረ ለዚሁ ወዳጄ ገልጬለት ነበር።
በነሐሴ 2000 ዓ.ም. “እኔም ሕልም አለኝ“ በሚለውና አውራምባ ታይምስ ላይ በታተመው ጽሑፌ “እኔም ሕልም አለኝ፣ አቶ መለስ ዜናዊ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ አቶ ቡልቻ ደምቅሳ፣ አቶ ኃይሉ ሻውል፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ … እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ መሪዎች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው፣ እንደ አንድ ሀገር ልጆች፣ እንደ አንድ ቤተሰብ እንደሚነጋገሩና ካለንበት የፖለቲካ እሽክርክሪት ቀውስ እንደምንላቀቅ” በማለት የፖለቲካ መሪዎቻችን መቀራረብና መከባበር በሀገራችን ትልቅ ምዕራፍ እንደሚከፍት ለማሳየትም ሞክሬ ነበር።
ጥቅምት 20 ቀን 2002 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሼራተን ሆቴል በአቶ መለስ ዜናዊና በአቶ ኃይሉ ሻውል መካከል የተደረገው መጨባበጥ “በኢህአዲግና በተቃዋሚዎች መካከል መቀራረብ መኖር አለበት። መነጋገር ያስፈልጋል” ብለን እንከራከር ለነበርነው ዜጎች ትልቅ ደስታ ሊፈጥር እንደሚችል መቼም አንዳንዶች የላይ ላዩን በማየት ሊገምቱ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።
ነገር ግን እየሆነ ያለውን በጥልቀት ለሚከታተል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ የዚህን እንደ ትልቅ ታሪካዊና ጠቃሚ ክስተት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባው የነበረውን የሼራተኑን ዜና፣ የሸፈነ አንድ ትልቅ ጋሬጣ እንዳለ መረዳቱ አይቀርም። ይህንን ጋሬጣ አቶ ኃይሉ ሻውልም ሆኑ አቶ መለስ ዜናዊ ብዙ ቦታ የሰጡት አይመስለኝም።
“ጠጅ በብርሌ፣ ነገር በምሳሌ” እንደሚባል ምሳሌ በማቅረብ ሃሳቤን የበለጠ ለማብራራትና ለማስፋት እንደሚከተለው እሞክራለሁ።
አንድ ሰው የዶሮ ወጥ በጣም ይወዳል። በአንድ ምግብ ቤት በኩል ሲያልፍ የቀይ ወጥ ሽታ አፍንጫውን አወደው። በቀጥታ ወደ ምግብ ቤቱ ገባ። “አንድ እንጀራ በዶሮ ወጥ ከአንድ ጣሳ ውሃ ጋር አቅርቢልኝ የኔ እህት” ብሎ አስተናጋጇን በትህትና አዘዘ። ምራቁን እየዋጠ ነው። ትንሽ እንደቆየ ሰፋ ባለ ትሪ ምን የመሰለ ዶሮ ወጥ ከአንድ እንቁላልና ከአንድ ፈረሰኛ ጋር ቀረበለት። ከመቀመጫው ብድግ ብሎ ተነሳ። ወደ ሽንት ቤት ሄዶ እጁን ታጠበ። እንደተመለሰም “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ” ብሎ ምግቡን ባረከ። አንድ ሁለት ጉርሻ እንደጎረሰ ቀና ብሎ ዓይኑን አፈጠጠ። ሁለት ዓይን የሚያክሉ ዝንቦች በወጡ ውስጥ ቁጭ ብለዋል። ሊያስመልሰው ሆነ። እጁን ወደ ታጠበበት ሽንት ቤት እየቸኮለ ሄደ። የጎረሰውን እንዳለ አስወጣው። አስመለሰው።
ይህ በነአቶ ኃይሉ ሻውልና በነአቶ መለስ ዜናዊ መካከል የታየው መጨባበጥና መፈራረም በጣም መልካም ነገር ነበር። ከላይ እንደጠቀስኩት ሁላችንም የምንመኘውና የምንደግፈው፣ ከዚህ በፊት መሆን የነበረበት፣ ለሀገር የሚበጅና የሠለጠነ ጥቅም ያለው ነበር። ሰውዬው የዶሮ ወጡን ለመብላት እንዳስቸኮለውና እንደተመኘው ሁሉ፣ ያየነው መጨባበጥና መቀራረብ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊን ሊያስደስትና ሊያስፈነጥዝ የሚገባው ክስተት ነበር። በርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ ትልቅ አዎንታዊ እርምጃ ሊወሰድ የሚገባው ነበር።
ነገር ግን “ነበር” ብቻ ሆነ ቀረ። መሆን እንደነበረበት ሊሆን አልቻለም። አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይሉ ሻውል ያቀረቡልን መዓድ ምንም እንኳን ሽታው የሚያውድና የሚጥም ቢመስልም፣ ዝምቦች ያሉበትና የሚያስታወከን መዓድ ሆኖ ተገኘ። ልንመገበው አልቻልንም። ቦታም አንሰጠውም። አልተደነቅንበትም። መጨባበጡን መፈራረሙ የተደረገበትን ቀን እንደ ታሪካዊ ቀንም አናየውም።
አስቡት ከአራት ዓመታት በፊት “እነ አቶ ኃይሉ ሻውል” በሚል ፋይል የተከሰሱ የቅንጅት መሪዎች በሙሉ፣ የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸው ነበር። እንደ አቶ መለስ ዜናዊ አባባል፣ የታሰሩት የቀድሞ ቅንጅት መሪዎች “ወንጀል” ፈጽመዋል። (ወንጀል የሚለውን ቃል ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያደረኩት እንደ እውነቱ ከሆነ የቅንጅት መሪዎች አንዳች ወንጀል ፈጽመዋል ብዬ ስለማላምን ነው) የነዚህ የቅንጅት አመራር አባላት ሊቀመንበር ደግሞ አቶ ኃይሉ ሻውል ነበሩ።
አቶ መለስ ዜናዊ የ“ወንጀለኞች” መሪ ከነበሩት ከአቶ ኃይሉ ሻውል ጋር በአንድ በኩል ሲጨባበጡና ሲሞጋገሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአቶ ኃይሉ ሻውል ምክትል የነበረችዋን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ የአቶ ኃይሉ ሻውል ምክትል ሆና በነበረበት ጊዜ ተሠራ በተባለ፣ አቶ ኃይሉ ሻውልም እራሳችው እንዲፈረድባቸው ባደረገው “ወንጀል” ምክንያት፣ በግፍ ቃሊት እሥር ቤት እንድትታሰር አድርገዋል። ታዲያ ይህን የታዘበ ሰው፣ በእውኑ የተደረገው ስምምነት ቅንነት ያለው ስምምነት ነው ብሎ ሊያስበውና ትልቅ ግምት ሊሰጠው ይችላልን? ጆክና ቀልድ ነው ብሎ ቢያጣጥለው ያስደንቃልን?
የቅንጅት መሪዎች ይቅርታ ጠይቀው እንደተፈቱ በሰፊው ተዘግቧል። ይቅርታ የጠየቁትም ተገደው በኃይል (under duress) እንደሆነ አቶ ኃይሉ ሻውል በራዲዮ አንድ ወቅት ተናግረውም እንደነበረ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው። ሌሎች በቃሊቲ እስር ቤት ታስረው የተፈቱ የቀድሞ እሥረኞችም በሽምግልና ወግና ሥርዓት መሰረት ይቅርታ ጠይቀው እንደተፈቱ በግልጽ አስታወቀዋል።
እንግዲህ አቶ ኃይሉ ሻውልም ሆኑ ሌሎች የቅንጅት መሪዎች ከተናገሩት የባሰ ወይንም የተለየ ነገር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ምን ብትናገር ነው ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር አቶ ኃይሉ ሻውል የ“ወርቅ መቀመጫ” ላይ እንዲቀመጡ ሲደረግ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በቃሊቲ ከቱሃንና ከቁንጫ ጋር ሌትና ቀን የምትማቅቀው?
አቶ መለስ ዜናዊ “የሕግ ጉዳይ ነው። ይቅርታ አልጠየኩም ብላለች” ይላሉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን የሽምግልና ሥርዓትና ወግን መሰረት ያደረገ ይቅርታ እንደጠየቀች በጋዜጣ ላይ ለህዝብ ይፋ አድርጋለች። ታዲያ በይፋ ይቅርታ የጠየቀችን እህት ይቅርታ አልጠየቀችም ብሎ ማሰቃየት ምን ይባላል? ሐቁና እውነቱ ይህ ሆኖ እያለ፣ አንዱ “ወንጀለኛ” እንደ ወዳጅ የሚታይበት፣ ሌላው “ወንጀለኛ” ደግሞ እሥር ቤት የሚማቅቅበትስ ምክንያቱ ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንዳየነው በአቶ ኃይሉ ሻውልና በአቶ መለስ ዜናዊ መካከል የነበረው መቀራረብ በመርኅ ደረጃ አልቃወመውም። ከላይ እንደገለጽኩት መቼም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን በኃይልና በጥይት ከመፍታት ይልቅ ቁጭ ብለን በንግግር ብንፈታ የሚመረጥ መንገድ ነው።
ነገር ግን ምንም ጥፋት ያላጠፋች፣ የሀገሪቱን ሕግና ሥርዓት ጠብቃ ትንቀሳቀስ የነበረች፣ “ወያኔ ጠላት አይደለም” ብላ የነአቶ መለስ ዜናዊ ጠበቃ ሆና በአደባባይ የተከራከረች፣ እንደ አብዛኞቻችን በባዕድ ሀገር ኑሮዋን አድርጋ በኢኮኖሚ የተመቻቸ ኑሮ መኖር ስትችል ሀገሬንና ህዝቤን አገለግላለሁ ብላ ሠላማዊና ሕጋዊ ትግል ለማድረግ የቆረጠች፣ በሀገር ባህል ወግ መሰረት በሽምግልና ይቅርታ እንደጠየቅች በግልጽ በማስቀመጥ እውነቱን ያልካደች፣ ለኢትዮጵያ አንድነትን ሉዓላዊነት ጠንካራ አቋም ያላት፣ የሠላምና የፍትህ ደቀ መዝሙርና የመጀመሪያዋ የሴት የፖለቲካ ፓርቲ መሪ የሆነችው ብርቱካን ሚደቅሳ ከሦስት መቶ ሰባት ቀናት በላይ በአሰቃቂው በቃሊቲ እሥር ቤት በግፍ እየተሰቃየች ባለችበት ሁኔታ ነው የሼራተኑ ስምምነት ምንም ግፍ እንዳልተደረገና ሁሉ ነገር ሠላም እንደሆነ ተደባብሶ ዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት እንዳለ የተዘገበልን። በሀገራችን የብዙኀን ፓርቲ ዲሞክራሲ አንድ እርምጃ ወደፊት እየሄደ እንደሆነ ነው የተሰበከልን።
ይህንን ልንቀበለው የማንችለውና የማይዋጥልን ነገር ነው። የተደከመበትን ያህል ዶሮ ወጡን ብንመገበው ደስ ይለን ነበር። ይቅርታ ያደርጉልንና ወጡ ውስጥ ግን ዝንብ ገብቶበታል።
አቶ ኃይሉ ሻውል ሊመጣባቸው የሚችለውን ትልቅ ተቃውሞ እያወቁም ደፍረው ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ለመጨባበጥ መድፈራቸው በአንድ በኩል የሚያስደንቅ ነው። በምንም አይነት መልኩ አቶ ኃይሉ ሻውል ከአቶ መለስ ጋር መጨባበጣቸው ሊያስወቅሳቸውና ሊያስነቅፋቸው አይገባም። በዚህም ምክንያት እርሳቸውን በዚህ ጽሑፍ ላይ ልዘልፍ አልፈልግም። አይገባምም።
ነገር ግን የርሳቸው ምክትል ሊቀመንበር የነበረችዋን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በቃሊቲ እሥር ቤት በስቃይ እንዳለች እያወቁ፣ የርሷን ጉዳይ ወደ ጎን ማድረጋቸውና እርሷን መርሳታቸው አሳዝኖኛል። ከአንድ ትልቅ አባት በጭራሽ አይጠበቅም ባይ ነኝ።
እንግዲህ የተሠራው ተሠርቷል። የሆነው ሆኗል። ትችቱንና ተቃውሞውን እዚህ ላይ ላቁምና ከአሁን በኋላ ምን እናድርግ ወደሚለው ልሂድ።
አሁንም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢህአዲግ ጋር አብረው በጋራ የሀገራችን ኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም ይህ የአቶ ኃይሉ ሻውልና የአቶ መለስ ዜናዊ መቀራራብና ተፈረመ የተባለውም ሰነድ፣ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ቦታ ባንሰጠውም፣ ከአሁን በኋላ ባለው ጉዞ ለሁላችንም በሚበጅ መልኩ፣ ከተቃና ትልቅ ጥቅም ሊያመጣ ይችላል ባይ ነኝ።
አቶ ኃይሉ ሻውል፣ ይህ ከነአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ያደረጉትን ስምምነት ህዝብ እንዲቀበለውና ለህዝብ መሸጥ ከፈለጉ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንድትፈታ አቶ መለስ ዜናዊን በግልጽ እንዲያነጋገሩና እንዲያሳምኑ ያስፈልጋል። (አሁን ጓደኛሞች ስለሆኑ)
አቶ መለስ ዜናዊም ቢሆኑ በሼራተን እንደተናገሩት፣ በሀገራችን የሚደረገው የ2002 ምርጫ ነጻ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ከፈለጉ፣ በርግጥ ድርጅታቸው ለዚህ ቁርጠኝነት ካለው በሥራ በተግባር ያሳዩን ዘንድ ይገባል። ከአቶ ኃይሉ ሻውልና ከሌሎች ጋር የተደረገው ስምምነት የበለጠ ዳብሮ ጠቃሚ ሊሆን የሚችል ስምምነት እንዲሆንና በህዝብ የበለጠ ተቀባይነት አግኝቶም ውጤት እንዲያመጣ፣ ተጨባጭ ሥራዎች በኢህአዲግ መሠራት አለባቸው። ኢህአዲግንም ተቃዋሚዎችንም ሁሉ የሚጠቅም ስምምነት እንዳይኖር ጋሬጣ የሆነውን ነገር መግፈፍ ያስፈልጋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአስቸኳይ መፈታት አለባት።
በርካታ የሕግ ምሁራን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የውጭ ዲፕሎማቶች፣ የኢህአዲግን አቋም በማንጸባረቅ የሚጽፉ የኢህአዲግ ደጋፊዎችም ሁሉ ሳይቀር (እነ አቶ ኃይማኖት ላቀው፣ አቶ ጌታቸው መኳንንት፣ አቶ ተስፋዬ ሃቢስ፣ የሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል ኃላፊው አቶ አባ መላ፣ …) የብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት ቁልፍና አስፈላጊ እንደሆነ ከመምከር አልፈው እንድትፈታ ግፊት እያደረጉ ናቸው። ፕሮፌሠር ዶናልድ ሌቪን ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችበት የሕግ መከራከሪያ አጨቃጫቂና ግልጽነት የጎደለው አወዛጋቢ እንደሆነ በመጠቆም፣ ሰብዓዊነትን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በአስቸኳይ ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ትኩረት ሰጥተው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በአስቸኳይ የምትፈታበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በታሰረችበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ፈረንጆች ሊቀበሉት ቢችሉም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን አይቀበለውም። ኢትዮጵያውያንም ይህንን ምርጫ አክብረው ይሳተፉበታል ብዬ አልጠብቅም።
የሼራተኑን ስብሰባ የፈረሙ ተቃዋሚዎች የተባሉትም በምንም መልኩ ህዝብን እንደማይወክሉ መቼም አቶ መለስ ዜናዊ በሚገባ የሚያወቁት ይመስለኛል። የህዝብ ድጋፍና ልብ ያለው ቃሊቲ በመሆኑ ከህዝብ ጋር መታረቅ ከተፈለገ፣ ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ቁርጠኝነት ካለ ሥራው የሚጀምረው ብርቱካን ሚደቅሳን አሁን በመፍታት ነው።
እግዚአብሔር ልቦና ለሁላችንም ይስጠን! አቶ መለስ ዜናዊ ከአቶ ኃይሉ ሻውል ጋር እንደተጨባበጡትም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ቁጭ ብለው የሚወያዩበትንና የሚጨባበጡበትን ቀን ያሳየን!
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ጥቅምት 21 ቀን 2002 ዓ.ም.