ከሳጥን ውጭ ማሰብ አይከፋም (ኩችዬ)
(ስለ ኃይሉ፣ ኢህአዴግ፣ ፈረንጆቹና ብርቱካን)
ኩችዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ብርድ ልብስ ውስጥ እንደተጀበንኩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መፍታት ሲሳነኝ የቡና ተርቲበኛ ወዳጄን “ካሪቡ” እንደምቀጥረው አምና አካባቢ ያጫወትኳችሁ መሰለኝ። እጣኑ ይጐድል እንደሁ እንጅ የካሪቡ ቡናና የቤቱ ጌጥ (ፌንክ-ሹዌ ይሉታል ቻይናዎች) ከራማ ያስታርቃል። ታዲያ ይሄ ወዳጄ አንገቱን ከብርድ ልብስ ውስጥ ብቅ አርጎ መወያየትን አይፈራም። ጥልቅ አሳቢነቱን ብቻ ሳይሆን ወዛም ጨዋታውንም እናፍቀዋለሁ። እንዲህ ያለ ወዳጅ አያሳጣችሁ አቦ!
“እናም ኃይሉ ሻውል በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ውስጥ ለመግባት መወሰኑ ከምን መጣ? በእሥር የተንገላታበት የቅንጅት ባለ ስምንት ነጥብ ቅድመ ሁኔታስ ምን ጅብ በላው? ከትናንት በስቲያ የብርቱካን መፈታት ቅድመ ሁኔታ ነው አላለም ነበር ወይ? በርግጥ ሀብቱንና ንብረቱን ካደጋ ለመጠበቅ ሲል ያደረገው ሰጥቶ-መቀበል ነው? በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ያሳዘናቸውን ደጋፊዎቹን እንደገና ማሰባሰብ እችላለሁ ቢል የለየለት እብደት አይደለም ወይ?” እነዚህንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ወዳጄ ላይ ያራገፍሁት እንደመትረየስ ነበር።
በንዲህ ያለ ስሜታዊነት ጨዋታ በጀመርኩ ቁጥር ምንጊዜም ዓይኑ ወደጣራው፣ እጁ ወደ ቡናው ስኒ ነው የሚያመራው። በርጋታ ፉት ብሎ እስኪያጣጥም ድረስ የኔ ስሜት ሳይወድ-በግዱ እንደሚበርድ ያውቃል። ሰው የዚህን ያህል ውስጣችሁን ሲያነብ እህ! አትሉም? … ቀጥልኩ ደግሞ ስለምርጫው - “የኢህአዲግ ስሌት ምን ይመስልሃል? ምን ያህል ያገር ውስጥና የውጭ መንግሥታት ተጽዕኖ አለበት? ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ያለው አቅምስ? የኦባማስ አዲስ ፖሊሲ? ኢዩስ (የአውሮፓ ሕብረትስ)? የብርቱካንስ ጉዳይ? መድረክ ምርጫው ውስጥ የሚሳተፍ ይመስልሃል? …” ትንፋሼ መቆራረጥ ሲጀምር ራሴን ታዝብሁና እኔም እጄን ወደቡናው ስኒ ላክሁ።
ጥቂት ሴኮንዶች በፀጥታ ካለፉ በኋላ ጨዋታችን በተረጋጋ ሁኔታ መቀጣጠል ጀመረ። ሰው የሚያዘወትረውን ጎዳና ትተን በማይጓዝበት መስመር ማሰብና መመርመርን ቀጠልን። ጨዋታችንን ከነሙሉ ለዛው የማቅረብ ክህሎት ቢኖረኝ ምንኛ ደስ ባለኝ። ለዛሬው ግን ፈረንጆቹ እንደሚሉት ከሣጥኑ ወጣ ብለን (እኔ ከብርድ ልብሱ ያልኩት መሆኑ ነው) ለማሰብ ያደረግነውን ሙከራ አቃምሳችኋለሁ። “ይሄን መቼ አጣነው?” ለምትሉ አዋቂዎች ይቅርታ፣ የሚጥማችሁ ከተገኛችሁ ደግሞ መልካም።
የኃይሉ ሻውል ጉዳይ
ኃይሉ ሻውል ሰንበት ያለ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን የተዋጣለት ነጋዴም ነውና ችሎታውን አኮስሶ ማየት የተዛባ ድምዳሜ ላይ ይጥላል ብለን እንሰጋለን። በቃለ-ምልልስ ወቅት አንገት ከሚያስደፋው ኃይሉ ሻውል በስተጀርባ ሌላ ኃይሉ መኖሩን ታሳቢ ማድረግ በፖለቲካ ሣይንስ ሕግም የተደገፈ ነውና በዚህኛው ወገን መሳሳትን መረጥን። ይህን መነሻ አድርገን ነው የኃይሉን ድርጊት በለሆሳሱ የመረመርነው።
ኃይሉ እንደማንኛውም ፖለቲከኛ ለሥልጣን የተሰለፈ ሰው ነው። ችግሩ ግን ዕድሜው የገፋው ኃይሉና የዕድሜ ወስን የማታውቀዋ ሥልጣን በተለያየ ፍጥነት መሮጣቸው ላይ ሆነ። “ከህልፈቴ በፊት ታሪክ ገበታ ላይ ስሜን መቅረጽ አለብኝ” ብሎ ከተነሳ ማን ሊያቆመው ይችላል? ጥያቄው ታሪኩ የሚጻፍበት ርዕስና በየትኛው ገጽ ላይ ይሆናል የሚለው ብቻ ይሆናል። ኃይሉ የፖለቲካ ካርታዎች እንዳሉትም አንዘንጋ። የኃይሉ ስም ከመላ አማራ፣ መላ ኢትዮጵያና ከቅንጅት ጋር በተያያዥነት ሲነሳ ኖሯል። የስም ታዋቂነት ደግሞ በፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ንብረት ነውና በተለይ በገጠሩ የአማራ ክልል ድጋፍ ሊያገኝ የሚችል ይመስለናል። አንዳንዶች እንደሚሉት ስሙ ጎድፎ ቢሆን እንኳ በባለሙያ የህዝብ ግንኙነት ዘመቻና በገንዘብ ኃይል ሊታደስ የሚችል ነው። “የህዝብ ማስታወስ ችሎታ አፍታዊ ነው፣ ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ፣ ስለትናንቱ አትንገረኝ ዛሬ ምን አደርግክህልኝ?” የሚሏቸውን የፖለቲካ ብሂሎች ታውቁ የለም?! ከዚህም ሌላ የኃይሉ ፓርቲ ባንዳንድ ክልሎች ውስጥ ማልዶ ሥራ መጀመሩ በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የወደፊት ይዞታ ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም ማለትም አይቻልም።
ከሳጥን ውጭ ማሰባችን ካልቀረ ዘንድ በኃይሉ ጭንቅላት ውስጥ ሊመላለሱ የሚችሉ ሃሳቦችንም ቃኝተናል። “ኢህአዲግ ለተወሰኑ ዓመታታ ሥልጣን ላይ መቆየቱ የማይቀር ከሆነ ሜዳውን ወለል አርገን መልቀቅ የበለጠ ጥፋት እንዲያደርስ የመፍቀድ ያህል ነው፤ ባለው የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥም ኢህአዲግን ማጋለጥ ምኅዳሩንም እንዲሰፋ መግፋት ይቻላል፤ በፖለቲካ ጠርዝ ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየት መረሳትን ያመጣል ከበሬታንም እየቀነሰ ይሄዳል፤ … ወዘተ” ብሎ አስቦም ሊሆን እንደሚችል ገመትን። ከ1997 ምርጫ ወዲህ ተቃዋሚው ወገን በፖለቲካ ጠርዝ ላይ አልሰፈረም ማለት ይቻላል።
ሌላም ከበድ ያለ ነገር አይጠፋ። ኢህአዲግ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት፤ “መኢአድ”ን እሹሩሩ ሲሉ ለመክረማቸው አያሌ ማስረጃዎች አሉ። ኃይሉ በድርድሩ ውስጥ መቆየቱ መድረክ አባላት ላይ ሥነ-ልቦናዊ ጫና ነበረው። መንግሥትና አምባሣደሮቹ ኃይሉን በኪሳቸው አርገው ነው መድረክን ሲጫኑ የከረሙት። በመጨረሻም ኃይሉ ፊርማውን በነጠብጣቡ መሥመር ላይ ባስቀመጠ ዕለት ተጨማሪ ተጽዕኖ ተፈጥሯል ባይ ነን። ያቶ መለስና የበረከት ስምዖን ደስታ ከዚያ የመነጨ ይመስለናል።
ታዲያ ኃይሉ ይህንን ሁሉ ውለታ የዋለው በነፃ ይመስላችኋል? ፈጽሞ! ከኢህአዲግም ከፈረንጆቹም ተገቢውን ካሣ ለማግኘቱ አንጠራጠርም። አለያማ ርባና ያለው ፖለቲከኛም ጥሩ ነጋዴም አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ ጥሩ የሚዲያ ጊዜ፣ የተመቻቸ የመንቀሳቀሻ ምኅዳርና የገንዘብ ዳረጎት ያገኛል። የመልካም ተቃዋሚ ምሣሌ ለማድረግ ሲሉም በፓርላማና በያደባባዩ የክብር ቦታ ይሰጡታል። በውጭው ዓለም ደግሞ አሜሪካና አውሮፓ ለታላላቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ዲፕሎማቲክ ኢሚውኒቲና የክብር አቀባበል ቃል ገብተውለት ይሆናል። እነዚህ ነገሮች የትኛውንም ፖለቲከኛና የፖለቲካ ድርጅት ሲጎዱ አይተን አናውቅም። የዘረዘርናቸው ታሳቢዎች እውነት ከሆኑ ኃይሉ የፖለቲካ “ሃርድ-ቦል” ተጫውቷል ማለት እንችላለን።
ኢህአዲግን በሚመለከት …
ከእውነተኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሃከል ዳጎስ-ዳጎስ ያሉት በ2002 ምርጫ ካልተሳተፉ ለኢህአዲግ ኪሣራ ነው። ባገር ውስጥም በውጭው ዓለምም መሳለቂያ እንደሚሆን ያውቀዋል። አዲሱ የኦባማ መንግሥት ደግሞ የዲሞክራሲ ምኅዳሩን ለቀቅ እንዲያደርግ አምባሣደር ባለመሰየምና ከፍተኛ ባላሥልጣኖቹን በመላክ ጫና እያሳደረበት ነው። አውሮፓውያን ለኢህአዲግ ጥፋቶች ይቅርታ ማፈላለግ ሰልችቷቸዋል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትና የዲሞክራሲ እምባ-ጠባቂ ድርጅቶች ይህን መንግሥት አሁን ከሚገኝበት ጭራ ደረጃ ወዴት ዝቅ እንደሚያደርጉት ግራ ሳይጋቡ አልቀሩም።
ከላይ የተዘረዘሩትና ሌሎችም ችግሮች ናቸው ኢህአዲግን ወደ ድርድር ያመጡት። የኃይሉ ሻውል ፊርማ ምርጫው በፅኑ የሚፈልገውን “ሌጂቲመሲ” (ሕጋዊ እውቅና) ባይሰጠውም ላፍሪካ ብዙ ትዕግሥት በሌላቸው ምዕራባውያን ዘንድ “የሚያበረታታ ጅምር” ተብሎ የሚታለፍ ዓይነት ሆኖ ይታየናል። ይሁን እንጅ ምርጫው እርባና ያለው ሌጅቲመሲ የሚያገኘው የቅንጅት ወራሽ የሆነው አንድነት ፓርቲ ወይንም በቅርቡ የተመሠረተው መድረክ ሲሳተፉ ብቻ እንደሆነ አይስቱትም። በዚህም የተነሳ ከአንድነትና ከመድረክ ጋር ውይይት አላቋረጡም የሚል ስሜት አድሮብናል።
በዚህ በ2002 ምርጫ ድርድርና ቻቻታ ውስጥ የተደበቀውንም የኢህአዲግ ግኝት አንርሳ። “መኢአድ” በሙሉ ኃይል መንቀሳቀስ የሚጀምረው በ“ብአዲን” ኪሣራ ነው። ለዚህ ነው መለስ ሰፊ የህዝብ መሠረት ያለውንና የሚፈራውን ያማራውን ክልል ለሁለት በመሰንጠቁ ደስተኛ ሊሆን የሚችለው። ምስኪን ብአዲን!
በየትኛውም ወገን እያገላበጥን ብናየው ከሰሞኑ ሆያሆዬ እንደ ኢህአዲግ የተጠቀመ የለም። ስለሆነም በምርጫው ሰሞን ሚዲያውን ከፈት፣ ወከባውን ቀነስ፣ እሥረኛውን ለቀቅ፣ ... በማድረግ ጥሩ ልጅ መስሎ ቢታይ ልንገረም አይገባም። ያን ካደረገ የርዳታውም የምኑም ቧንቧ እንደማይዘጋበት ያውቃል።
አሜሪካንና አውሮፓ ሕብረትን ደግሞ እንዳስ
የኦባማ መንግሥት የውጭ ፖሊሲ ያገሩን ብሔራዊ ጥቅም ተከትሎ እንደሚሄድና ከቀድሞው ብዙም ሊለይ እንደማይችል ባለፈው የተስማማን ይመስለኛል። ይህን በሚመለከት “በርግጥ ኢትዮጵያ ላይ ሴራ አለ?” በሚል አምና አካባቢ ያቀለምኳትን እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ። (ጽሑፉን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
ዘመዶች! ፈረንጆቹ ያፍሪካ ቀንድ የውጭ ፖሊሲያቸውን የሚያጠነጥኑት ሁለት እንዝርቶች ላይ መሆኑን አትዘንጉ። እርግጥ ዘይት መሳይ ቢኖረን ሦስተኛ እንዝርታቸውን ከማውጣት ወደኋላ አይሉም። አንደኛው እንዝርት ባፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ውስጥ እልቂት የሚያስከትል የፖለቲካ ቀውስ አለመኖሩን የሚያረጋገጥ ሲሆን፤ ሁለተኛው እንዝርት ደግሞ ሽብርተኞች ባካባቢው አስቀያሚ ድራቸውን እንዳያደሩ የሚከላከል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ሁነኛ አማራጭ ኃይል እስካላገኙ ድረስ መለስ ላይ የሚቻላቸውን ያህል ተጽዕኖ እያደረጉና የሚያገኙትን ያህል የፖለቲካ እንጎቻ እየተቀበሉ ከመኖር የተሻለ አማራጭ የላቸውም። መለስ በሁለት ያማራ ድርጅቶች ቅልልቦሽ ለመጫወት እንደታደለው ሁሉ እነርሱም በኢህአዲግና በሌላ አማራጭ ፓርቲ ቅልልቦሽ መጫወትን ይፈልጋሉ። ይሄ ነዋ የፖለቲካ ሣይንሱ።
የብርቱካን ጉዳይ
ከወዳጄ ጋር የምናደርገው ወግ ከሳጥን ውጭ በማሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እያወቅን እንኳ፤ የብርቱካን ተራ ሲደርስ ስሜታችን እንደመጋል አለ። ብርቱካን የምን ተምሳሌት እንደሆነች እንኳንስ ያበሻ ሰው ተክሉና አራዊቱም ያውቃልና በዝርዝር ትችት አናሰለቻችሁም። መንግሥታት ሳይቀሩ የዚችን ሠላማዊ ትግል አራማጅ መሃረብ ማውለብለብ ጀምረዋል።
ታዲያ የጥያቄዎችም ጥያቄ የሆነብን “ይሄ ኢህአዲግ ብርቱካንን በማሠር ምን የፖለቲካ ትርፍ አገኘ?” የሚለው ሆነ። ብርቱካንን የዲሞክራሲ ትግሉ ሰንደቅና ማዕከል ነው ያደረጋት። ብርቱካንን ባልረባ ሰበብ ማሠሩ ኢህአዲግን “በቀለኛና እብሪተኛ መንግሥት” የሚል ስም ነው ያከናነበው። መቀራረብ ተስኖት የነበረውን የተቃዋሚው ጎራ ነው እንዲሰባሰብ ምክንያት የሆነው። ባጭሩ ትልቅ የፖለቲካ ቡቡ ነው የሠራው።
ታዲያ የ2002 ምርጫን አስመልክቶ የብርቱካን መፈታት ለሁሉም ነገር ቅድመ ሁኔታ ሆኖ መቅረቡ ማንንም ሊያስደንቅ አይገባ። ህዝቡም፣ ፖለቲካ ፓርቲዎቹም፣ የውጭ መንግሥታትም ብርቱካን እንድትፈታ ይፈልጋሉ። ጥቂት የማይባሉ የኢህአዲግ ደጋፊዎች እንኳ የብርቱካን መታሠር የፖለቲካ ፋይዳ እንደሌለው ከመነሻው ጀምሮ ይከራከሩ እንደነበር እናውቃለን። በዚህ ሁሉ የተነሳ ነው ዲፕሎማቲክ ኅብረተሰቡ የብርቱንን ጉዳይ እኋለኛው ምድጃ ላይ ሊጥድ ያልቻለው። ለዚህም ነው መድረክ፣ ኢህአዲግና የውጭ መንግሥታት ተወካዮች ባደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ሁሉ ዓብይ መነጋገሪያ የሆነችው።
ኢህአዲግ ብርቱካንን ይፈታል። ሰንብቶም ቢሆን የተጫወተው ቁማር እርሱን እንዳልጠቀመው ገብቶታል። የምትፈታበትን አጋጣሚ ግን ቸርና ይቅርታ አድራጊ መስሎ የሚታይበት ያደርገዋል። ኃይሉ ሻውልና ዲፕሎማቶቹም የኛ ልፋት ፍሬ ሰጠ ለማለት ይሽቀዳደማሉ፣ አንዱ የሌላውን ጀርባ ቸብ-ቸብ የሚያደርግበት ዘመንም ይሆናል።
ከምርጫው በፊት ብርቱካንን ለመፍታት ኢህአዲግ ወኔው ይኑረው አይኑረው የሚታይ ነገር ይሆናል።
ማሳሰቢያ
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “የተከበሩ፣ አቶ፣ ወይዘሮ፣ ኢንጂንየር፣ ... ወዘተ” የሚሉትን ቅጽሎች ያልተጠቀምሁት ለሰዎቹ ከበሬታ ሳይኖረኝ ቀርቶ አይደለም። በፖለቲካ ሥነጽሑፍ የተለመደ አሠራር ስለሆነ ነው። “ኢንጂንየር እከሌ” የሚሉት መጠሪያ ካለ “አካውንታንት እከሌ”፣ “ኢኮኖሚስት እከሌ”፣ … ስንል ልንኖር ነውና፤ እባካችሁ ይህን አጉል ባህል እንተው። ከየት እንደመጣ የሚያስረዳኝ አለ?
“Thinking out of the box”
The case of Hailu, EPRDF, the Ferenjies and Bertukan
ኩችዬ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.